Monday, 03 November 2014 08:11

የአዳም ረታ ሃሳቦች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ስለስኬታማ ደራሲነት

         ስኬታማ ደራሲ ላልከው አንፃራዊነት ለሚንከባከቡ፣ ከጥናትም ይሁን ከግል ስሜትና ፍላጎት ተነስተው ለሚፈርዱ ወይም ለሚያደሉ ቦታውን ብለቅ ይሻላል፡፡ ስኬታማ የሚለውን ቃል ሙሉ ፍቺ አይናአፋር የተጠየቅ ቅንፍ ውስጥ ልክተተው፡፡
ስኬታማነት ተነቃናቂ ኢላማ ነው፡፡ ማታ ላይ አጠናቅቄ በሰራሁት ድርሰት ረካሁ ብዬ ብተኛም፣ ሲነጋ ቅር የሚሉኝ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከአመታት በፊት በፃፍኩት ዛሬ ላልደሰት እችላለሁ፡፡ የስኬታማነት መለኪያዎች አስራ አስር ናቸው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው አገሩ ውስጥ መኖሩን ወይም አለመኖሩን የስነ-ፅሁፍ ስኬታማነት መገምገሚያ ማድረግ ምስፋርን/ስፍራን (place) ብቻ የብቃት መለኪያ ማድረግ ነው፡፡ ይሄ ነጠላ ብቆታ በአብዛኛው ከውጤቱ ወይም ከድርሰቱ ውጭ ያለ ነው፡፡ የተለያዩ የስፍራ መደቦች አሉ፡፡ የግል ስፍራ አለ (Personal space)፣ የቤትህ፣ የቀበሌህ ስፍራ፣ ወዘተ … አለ፡፡ በተጨማሪም ደራሲው በኢምንትነቱ የሙሉኩሌው ወይም የወተትማው መንገድ አባል ነው፡፡ ግንባሩ በሶላር ፍሌርስ ይግላል፣ በበጋ በሚመጣ ዝናብ የሚከረስስ ቆዳ አለው፡፡ በምድር የመግነጢስ መረብ ይረግባል፣ ይወጠራል፡፡
አንድ ደራሲ ዋናው መሳሪያው ምናቡ ነው፡፡ ግን ነባር ልዩ ቦታህ በነበርክ ጊዜ በስርነቀል ልምድ ውስጥ እንድታልፍ ደንብ መሰለኝ (ይሄ ልምድ ፖለቲካ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ብዙ ጊዜ አንድ የልምድ ዝርያ ላይ ብቻ በማተኮርና ለዛም የማይገባውን ክብደት ብቻ በመስጠት በልምድ የመብሰል መለኪያ ሊደረግ ይሞክራል፡፡ ይሄ አድልኦ ነው፡፡)
ትተኸው (በእርግጥ ትተኀዋል ወይ?) የሄድከው ህብረተሰብ ውስጡ ምን ይመስል እንደነበር በመጠኑም ቢሆን መረዳት አለብህ፡፡ የትኛው ክስተትና ዕውነታ ነው ውዝፍ? (constant) የትኛው ነው ተለዋዋጩ? የቱ ነው ፈዞ/ተለውጦ የሚጠብቅህ? አለዋወጡ የሚገዙት የግንጵሊት ንጥረ ነገሮቹ (elements of metamorphosis) ምንድናቸው? ወዘተ…
ብዙ ብሑት (innovators) የሚባሉ የባዕድ ደራሲዎች ትልልቅ ድርሰቶቻቸውን የፃፉት ከትውልድ አገራቸው ውጭ ሆነው ነው፡፡ እንደውም አንዳንዴ ስለ ራሳቸው አገር በጠለላቸው አገር ቋንቋም ይፅፋሉ፡፡ ወሳኙ ያሳለፍከው የልምድ ስፋትና ጥልቀት፣ ለዚያም ያለህ ግንዛቤና በንቁነት ወይም በኢ-ንቁነት የምታነሳቸው ንፅፅሮች ናቸው እንጂ አካላዊ ዕርቀትና ቅርበት መለኪያ አይደለም፡፡
በራስህ ከምትገነዘበው፣ ተገንዝበህ የምታሰላስለው፣ አሰላስለህ መደምደሚያ የምትወስድበት፣ አንድ ተራ የመሰለ ድርጊት/ገጠመኝ ሰዎችን በግል ብቻ ሳይሆን ስርአት ውስጥ ያላቸውን ባህርይ እንድትረዳ ሰፊም ይሁን ጠባብ መንገድ ይከፍትልሃል፡፡ በስደት ስኖር በእርግጥ አዲስ የረቀቀ የስነፅሁፍ መሰረተልማት (Infrastructure) ውስጥ እገባለሁ፡፡ እነዚያ መኖራቸውን ታያለህ ግን ለእኔ ስራ መመጠናቸውን ማመዛዘን አለብኝ፡፡ ንፅፅር ያልኩት ይሄንን ነው፡፡
ባዕድ አገር ሆኜ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለ የቄስ ትምህርት ቤት ዘመን ብፅፍ በግል ተዘክሮዬ ይዤው የመጣሁት የመረጃ ወይም የዕውነታ አንኳር አለ፡፡ ዝርዝሩ ምናብ ነው፡፡ ጥቂት የሚታወሱ ነጥቦች አንስተህ እነዚያን ሚዛን በመጠበቅ የማያያዝና ጊዜ - ዘላይ ጭብጥ የማስነከስ ነው፡፡ ከልጅነቴ አርባ አመታት እርቄአለሁ በሚል ስለ ልጅነት ልብወለድ የመፃፍ መብቴን አላነሳም፡፡ የተወለድኩት አዋሳ ነው፣ አዲስ አባ መጥቼ ለምን ስለ አዋሳ እፅፋለሁ? ብዬ በቦታ መሸጋሸግን ወሳኝ አላደርግም (በአገር ውስጥ ስደት)፡፡ ይሄን መሰረታዊ ነጥብ ሃያሲው ከሳተ የቀረበው ትችት ሳይሆን ስህተት ፍለጋ ነው፡፡ የልጅነታችን ቦታዎችና ጊዜዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንኩዋን ብንሆን ሁሉንም ትተናቸው ሄደናል፡፡ ሁሉም ደራሲ ላለፈው ዘመንም ይሁን ቦታ/ስፍራ በሆነ ደረጃና መልክ ባዕድ ነው፡፡ ቦታዎችም እንደ ሰው ይለወጣሉ፡፡ እንደ ደራሲው እንደ ራሱ እና እንደ ገፀባህርያት፡፡ ልበወለድ ዶክመንታሪ አይደለም፡፡

ስለግንዛቤውና አፃፃፉ
የተወሳሰቡ ልምዶች አሳልፌአለሁ፡፡ በእኔ የተፈጠሩ ወይም በሌሎች ተየሰጡኝ፡፡ (ምርቃትም ይሁን እርግማን) አስከፊም ይሁን ደስ የሚሉ፡፡ እነዚህን ልዘረዘርልህ አልችልም፡፡ ብዙም ናቸው፤ ጥቂትም ናቸው፡፡
በባህርዬ በደንብ አያለሁ፡፡ አድልዖ አላደርግም፡፡ ይሄ ሁኔታዎች በነፃነት ለእኔ እንዲከሰቱ ያደርጋል፡፡ በጣም የሚሞቅ ፀሐያማ ቀን ባልወድም ፀሐይ ውስጥ እቆማለሁ፣ አለመውደዴን አጠናለሁ፡፡ እሱንም አወጣና አወርደዋለሁ፡፡ የሆነ የዜን ዝንባሌ (zen attitude) እይዛለሁ፡፡ ያለ ይሉኝታ (ምን መሆኔ ነው? ሰዎች ምን ይሉኛል?) ሳልል ለማየው ህያው ወይም ጎፍ (physical) አለም ራሴን በመስጠት ነው፡፡
ቅን መሆን አለብህ፡፡ ይሄን ደሞ አስበህ አታመጣውም (የሚያደርጉትይኖራሉ፡፡) ጥንቁቅ አይደለሁም፡፡ ዕቅድ የለህም፡፡ መረጃዎችን ብቻቸውን ሳይ (መገንዘገብ) ከፍፁም ግንኙነት አርቃቸዋለሁ ማለትም አይደለም፡፡ ያኔውኑ በፍጥነት ሊከሰትባቸው የሚችሉ አውታሮችን አስባለሁ፣ ወይም በትካቴ ይመጣሉ፡፡ በቀለ የተባለ ረዥም ልጅ ስልክ እንጨት ሊያስታውሰኝ ይችላል፡፡ ስልክ እንጨቱን ሳይ በቀለ ትዝ ሊለኝ ይችላል፡፡ አልማዝን ሳይ ቄጤማ ትዝ ሊለኝ ይችላል፡፡ የትርሲትን ድምፅ ስሰማ ሚጥሚጣ፣ ቁሶቹን ሳይ ደሞ አልማዝና ትርሲት፡፡ ዝርው የመሰለው ነገር በተለዋጭና በንፅፅር ስርአት ውስጥ ይገባል፡፡ ነጠላነትና ውህድነት በአያዎነት ይተገበራሉ፡፡ የመገንዘብ አድልኦ (Cognitive bias) ብዙ ነገር የመፃፍ ግላዊ ነፃነትህን ሊጋፋ ይችላል፡፡ በእኛ አገር ያልተነገረለት ሳንሱር ይሄ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወሳኝም ይሆናል፡፡
እነዚህ በእንግሊዘኛው ተሳፋሪነት (bandwagon effect) ፣ የጥማድ ህልዮ (group think) የጂም ባህርይ (herd behavior) ፣ ምናምን የሚባሉ ናቸው፡፡
ይሄ ወደ ስሜት ህዋስ አድልዖ (observational bias) ወይም የፅንሰ ሃሳብ አድልዖ (Conceptual bias) ይወስዳል፡፡ ብዙ ሰው ስለሚያደርገው ላድርገው ብዬ ማድረግ፣ ያለ ዝርዝር ብቆታ መርጬ ማየት፣ እኔ ነገሩ ገብቶኛል ብዬ ከመጀመሪያው የማየውን ነገርና የምሰማውን ወስኜ በራሴም ይሁን በሌሎች ትርጓሜ መጥኜ ማስቀመጥና የግል/የቡድን እሴቴን ወይም ሕልዮዬን የማየው/የምገነዘበው/ ጉዳይና ነገር ላይ በጫና ማሸጋገር ከእውነታው ስለሚያሸሹኝ አልጠለልባቸውም፡፡
ሁሉ ነገር ለደራሲ መረጃ ነው፡፡ መረጃ ስል በተጨባጭ የማየው (በራሴ የስሜት ህዋሶች)፣ ከሰው የምሰማው፣ የማነበው፣ በህልሜ የማየው፣ የምቃዠው ሊሆን ይችላል፡፡ ለእኔ ክብደትና መራሂነት ያለው የመጀመሪያው ነው፡፡ አንዳንድ የመረጃ አንኩዋሮች ጥቅጥቅ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እሴታቸው ቸኩሎ ላይከሰት ይችላል፡፡ ዛሬ ያነጫነጨኝ ልምድ ነገ ሊያስቀኝ ይችላል፡፡ ትናንት አደገኛ ያልመሰለህ ልምድ ቆይቶ አደገኛነቱ ይከሰታል፡፡ ዛሬ አደገኛ የመሰለ ልምድ ነገ ምቹ ሊሆን ይችላል፡፡ የአንዳንዱ ተራ የመሰለ ተፅዕኖ ወደ ድንጋግ የለሽ (ዳርቻ የለሽ) መረጃ ሊፈነዳ ይችላል፡፡ የማደርገው ከፈነዳ በሁዋላ የተበታተኑ የኩነት ፍንጣሪዎችን ወይም ዛላዎችን በማያያዝ መስራት ነው፡፡ …

ቅርፅና ይዘትን በተመለከተ
ዘመናዊ ደራሲዎች በየትም አገር በተለያየ መልክ የአገራቸውን የጥንት ተረቶች ለድርሰቶቻቸው ቅርፅና ይዘት መስሪያ ተጠቅመውባቸዋል፡፡ ይሄ መሸጋገር (translation) ብዙ ጊዜ ግን ከትረካ ወደ ትረካ ነው፡፡ ከድርሳን ወደ ድርሳን ነው፡፡ ከተረት ወደ ተረት ነው፡፡
“ግራጫ ቃጭሎች” የተባለው የመጀመሪያ ልብወለድ እዚህ ይመጣል፡፡ ይሄ መጽሐፍ ዋናውን ታሪክ በሚያጅቡ ንዑስ ታሪኮች በህዳግ ማስታወሻዎች፣ በቁርጥራጭ መረጃዎች፣ በአንዳንድ  የቁዘማ ውጤቶች አጀብ የተሰራ ነው፡፡ ይሄ ቅርፅን ለማደን መጣር አይደለም፡፡ ሁልጊዜ በደቡላወዊ (dualistic) ስልት ስለምናስብ እንጂ፣ ቅርፅና ይዘት የተናጠል ቦታ የላቸውም፡፡ እዚያና እዚህ አይደሉም፡፡
አንድ ላይ የሚተገበሩ ናቸው፡፡ በፍልስፍናም ይሁን ሃይማኖቶቻችን በምድራሶቻቸው (hermeneutics) ሁልጊዜ ባለቤትና ተሳቢ (Subject – object) ክፍፍል ላይ ስለሚያተኩሩ ከዚያ የተበደርነው ይሆናል፡ እንጀራ ጠንካራ የልዋጭነት እሴት አለው (metaphorical value)፡፡ ለመፃፊያ ሞዴልነት ለመጠቀም ይመቻል፡፡
ሞዴል ሲደረግ ከእንጀራነት ይላቀቅና ንፁህ ጂኦሜትሪ ይሆናል፡ ብዙ ጊዜ ሞዴሎች ከሚያጠኑት ጉዳይ የበለጠ ወይም የሚስተካከል ውስብስብነት ይኖራቸውና ራሳቸው መልሰው ችግር ይሆናሉ፡፡ እንጀራ እንደ ሞዴል የቀላልነቱ ምክንያቶች እነዚህ ናቸው፡፡
1/እንጀራ የተሟላ አይነት ውክልና አለው፡፡ ይታያል (እንደ ስዕል)፣ ይነካል፣ ይቀመሳል፣ እናም ይበላል፡፡ የመጨረሻው ፀባዩ የተለየ ያደርገዋል፡፡ እንደ ብዙ ቁሳቁስ በሩቅ የሚታይ አይደለም፡፡ ከሳብጀክቱ (የሰው ልጅ) ጋር ይዋሃዳል (embodied)፡፡
2/ የትውስታም ሰሌዳ ነው፡፡ አርኪዮሎጂስቶች በጥንት ጊዜ የተሰራ ቁስ አግኝተው በመሳሪያቸው መርምረው የእነዚህን ቁሶች ምንነታቸውን ያነባሉ፡፡ ተፎካካሪ ወይም የሚጋጭ ትርጉም ቢሰጣቸውም መረጃ ይሆናሉ፡፡ አፄ ሰንደቅአላማ የፈጠረው ጤፍ ተፎካካሪዎች የሚሻሙበት ጽላት (Icon) ነው፡፡ እንጀራ በሆነ መልክ ወገናዊነትን ያመልጣል፡፡ ተፎካካሪዎች ሁለቱም ይሽቱታል፡፡ በልቶ የማያድር የለም፡፡ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ሲጠፉ፣ ሲቃጠሉ፣ ሲዘረፉ፣ ከቦታ ቦታ ተላልፈው ሲጠፉ፣ እንጀራን ማንም ሊያሸሸው ባለመቻሉ እዚህ ደርሷል፡፡ ብዙ ዘመን የኖረው ሰንደቅአላማ መቃብር ላይ መገኘቱ ረዥም ዕድሜ ከእሱ መዋሱ ምሳሌ ይሆን?
በአሁኑ ወቅት ለምሰራው ስራ መረጃ ስለምፈልግ ብዙ ጊዜ ኢንተርኔት ላይ ነበርኩ፡፡ የግጥም ባሕር፣ የመጣጥፍ ሃይቅ በዛ አለ፡፡ ፌስ ቡክ በመጠቀም ብቸኛ ደራሲ መሆኔን አንተ ነህ የነገርከኝ፡፡ “ፍሬንዶች” ለሚያቀርቡልኝ አንዳንድ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ግን ብዙ ጊዜ አረፍዳለሁ፡፡ ከእኔ ይልቅ የአገራችንን ስነፅሁፍ ወደ መርበትብተ - ኤሌክትሮኒክ ያመጡት ወጣቶች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ የእነሱ የድርጊት ሕልውና ስለሚቀድም ልፋታቸው የገነነ ነው፡፡ ስለ ራሴም እንዳውቅ ገፋፍተውኛል፡፡ ልክ እንደ ጠንቋይ፣ ደራሲ ስለራሱ አያውቅም፡፡
ምናልባት ወጣቶቹ የበዙት ደራሲያን ማንሳት ይገባቸዋል የሚሏቸውን እስከ ዛሬ የተሳቱ ጉዳዮች ስላነሳሁ ይሆናል፤ ወይም ገና ወጣትነቴ አልከሰመምና (እስከ አሁን ድረስ ከምኑም ከምኑም እየተላተመ መጥቶ ከተረፈ፣ በተአብነት ይመዘገባል) እኔን የሚመዘምዘኝ ጉዳይ እነሱንም ይመዘምዝ ይሆናል፡፡ እነዚህ ግምቶቼ ናቸው፡፡ በግምት ደግሞ እርቀት አይኬድም፡፡

ስለአስገራሚ ገጠመኙ
በብዙ ነገር ተገርሜ የጨረስኩ ይመስለኛል፡፡ ድሮ የገረሙኝ ነገሮችን ዛሬ ሳስባቸው ለዛሬ አስገራሚ ሆነው አይታዩኝም፡፡ የሚያስቅ? ሎል (lol) ከመጣች ጀምሮ መንተክተክ ሳይቀንስ አልቀረም? (ለማሾፍ ይፈቀድልኛል?)  

Read 2070 times