Saturday, 22 November 2014 12:15

ፊታውራሪ እርጅና

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለ ጋሻ ጀግሬው ሰልፍ የሚያምርለት፣
አጀቡ አስፈሪ ጦር የበዛለት፣
ሠራዊተ ብዙ ፊታውራሪ እርጅና፣
ረጋ ብሎ ይመጣል ሞት ያስከትልና፡፡
    ስሜት ሲደበዝዝ፣
አካል ሲቀዘቅዝ፣
ዕይታ ሲደክም፣
አእምሮ ሲያዘግም፣
አደብ ይገዛሉ ህዋሳት በመላ፣
ሰውነት ይበርዳል ላይሞቅም ላይፈላ፡፡
ሆድ ጠግቦ ላይበላ ጉረሮ እህል ላይውጥ፣
ጉልበት ላይሆንለት ጦርን ሮጣ ማምለጥ፣
ነገርን አስታውሶ ለመናገር ፈጥኖ፣
እንደ ቀድሞ አይሆንም ጠፍቷልና ተንኖ፡፡
ዕቅድና ዓላማ እርግፍ አርጐ ትቶ፣
በትዝታ መኖር ምሃት፣ ተስፋ ጠፍቶ፡፡
እንስት ተባዕትን፣ ተባዕት እንስትን፣
ላይፈቃቀዱ ያሰንፋል ስሜትን፡፡
ጣፋጩ መራር ነው የሞቀው ቀዝቃዛ፣
በስተርጅና ሁሉም ይሆናል ጐምዛዛ፡፡
        ተው እርጅና፣
        ብቻህን ና!
ይህ ሁሉ ሳያንስህ ስኳሩን፣ ግፊቱን፣
ሪሁን፣ ራስ ምታቱን፣ ውጋት፣ ቁርጥማቱን፣
ነጭናጫ መሆኑን መነዝነዝ ዕለቱን፣
በትንሽ ትልቁ ፈጥኖ መከፋቱን፣
አንጋግተህ ያመጣህ ጨካኝ ነህ እርጅና፣
በስንት ጣዕሙ ሞት ይገባው ምስጋና፡፡
ኧረ ተው እርጀና አንተ ጅራታም፣
ምነው ጓዝህ በዛ (ሆንክና/ሆንክብኝ?) ኮተታም!
    ተው እርጅና፣
    ብቻህን ና!
ጥሩ ስም የሰጠህ ንገረን ማነው?
እርጅና እያሉ የጠሩህ ምነው?
እስቲ ከሞት ጋራ ተነጋገሩና፣
ከነ ተከታይህ በአንድ ላይ ሁኑና፣
እናንት? ሁለታችሁ ስብሰባ ግቡና፣
ስምህን ለውጡ ተመካከሩና፡፡
ሌላ ስም ይውጣልህ ከሞት ያላነሰ፣
ሥራህ ቢበዛ እንጂ መች ከእሱ ቀነሰ?
እናም…. ይኸው ወቀስኩህ ላትሰማኝ ነገር፣
 (ከእለታት ቀን ቆጥረህ መከሰትህ ሳይቀር?)
በሥራ በስፖርቱ አካሌን አጥብቄ፣
እጠብቅሃለሁ (አልቀርም) ወድቄ፡፡
ጦሬን ይዤ መጣሁ ደረስሁ ብትለኝም፣
እኔ አለሁ፣ አንተም ና ሥጋት አይገባኝም፡፡
በል እንግዲህ እርጅና - በቸር ያገናኘን
እስከዚያው ድረስ፣
አንተም አርጅተህ ሙት
- ወደ ልጅነቴ እኔም ልመለስ፡፡
*    *    *
ከአምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ
ኅዳር 2007 ዓ.ም

Read 1319 times