Saturday, 22 November 2014 12:42

ጨዋው ሀበሻ እና ፖስት ሞደርኒዝም

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“ፒካሶ የሚባለው ዋና የጥፋት ዲያቆን ነው፡፡ ከስዕል ጥበብ ውስጥ ምክንያታዊነትን ሙሉ ለሙሉ አውጥቶ አብስትራክት አርት ፈጠርኩ አለ፡፡ ደግሞም ፈጥሯል፡፡ በድህረ-ዘመናዊነት ማፍረስ መፍጠር በመሆኑ ማለት ነው፡፡ ባለ ሦስት አውታሩን ስዕል ወደ ሁለት አውታር፣ ሲሻው ደግሞ አውታር አልባ አድርጐ አቀረበ፡፡”


ስለ ምን ላውራ? ስለ ምንም ነገር ባወራ ከዘመኑ መንፈስ ውጭ አይሆንም አይደል? አንድ ወዳጄ ዘመኑ “ድህረ ዘመናዊነት” (Post modernism) ነው ብሎኛል፤ እኔም አምኜዋለሁ፡፡ አምኜም ለአማኝ አውርቼ አሳምኛለሁ፡፡ እንግዲህ ይህ የሀሳብ ወዳጅ እንደነገረኝ ከሆነ፣ መጀመሪያ የአዳም እና የሄዋንን ታሪክ ከስር መሰረቱ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የአዳም እና የሄዋን ታሪክ በጣም አጭር ነው፡፡ አንድ መስመር ነው እንዲያውም፡፡ ሄዋን አንገት ናት፤ አዳም ደግሞ እራስ ነው፡፡ ይሄ አጭር ታሪክ ጥንታዊ ነው፡፡ ጥንታዊ እና ሃይማኖታዊ፡፡
ዘመናዊው የሰው ልጅ ታሪክም እንደ ጥንታዊው በጣም አጭር ነው፡፡ ጥንታዊው አዳም እራስ፣ ሄዋን አንገት ነበረች ብያለሁ፡፡ ዘመናዊው ላይ ምንም አዲስ ነገር አልተከሰተም፡፡ ጥንታዊው አዳም ዘመናዊ ሲሆን ጭንቅላቱን መጠቀም ጀመረ፡፡ ጭንቅላቱን መጠቀም ሲጀምር ልቡን መጠቀም ያቆማል፡፡ ልቡን መጠቀም ሲጀምር ደግሞ ተገላቢጦሽ፡፡ የዘመናዊነት አስተሳሰብ በአዳም ጭንቅላት መስራት እና አለመስራት ሁልጊዜ ብቅ የሚል እና ተመልሶ እልም የሚል ነገር ነው፡፡ ልክ እንደ ሀገራችን የመብራት አቅርቦት ብዬ መመሰል አይጠበቅብኝም፡፡ በግሪኮቹ ዘመን ጭንቅላቱን መጠቀም ጀምሮ ነበር ይባላል አዳም፡፡ በኋላ የክርስትና አብዮት ሲቀጣጠል ጭንቅላቱ ተመልሶ ጠፋበት፡፡ ጠፍቶበት ቆይቶ ወደ አስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ መልሶ መብራት መጣለት፡፡ ጭንቅላቱን እና እጁን አጣምሮ ሳይንስን አዋለደ፡፡ ማሽን ሰራ፣ በጭንቅላቱ ውስጥ ብቻ የማይቀር መብራት በጐጆው አበራ፡፡ ፋብሪካው፣ መድሃኒቱ፣ መንገዱ፣ ባቡሩ…የዚህ ፈጠራው ማስታወሻ ናቸው፡፡
ይሄ ከላይ የጻፍኩት ሁሉ ወዳጄ ያወራልኝን መሆኑ አይዘንጋ!
ድህረ - ዘመናዊነትስ? አልኩት፡፡
ድህረ - ዘመናዊነት ልብንም ሆነ ጭንቅላትን በአንድ ላይ ለማጣት የሚያደርገው ሙከራ ነው አለኝ፡፡ ምሳሌ እንዲሰጠኝ ጠየቅሁት፡፡
ምሳሌውን ከፈላስፎቹ ነው የጀመረልኝ…ሳይንስ በተወለደበት ግርግም ውስጥ ሰበአ ሰገሎቹ ስጦታ ይዘው ለሰው ልጅ መጡ፡፡ ይዘው የመጡት እጅ መንሻ ግን ከርቤ፣ ወርቅ እና እጣን አልነበረም፤ አለኝ፡፡
የሰበአ ሰገሎቹ ስም ሰረን ኪርከርጋርድ፣ ማርቲን ሀይደርጋር እና ፍሬድሪክ ኒቼ ናቸው፡፡ ይዘው የመጡት ስጦታ…ሳይንስ ወይም የልጅነት ልምሻን የሚከላከል ክትባት አልነበረም፡፡ አቀጭጮ የሚገድለውን መጽሐፍ ነው ያበረከቱለት፡፡ ሳይንስ ቀጭጮም አልሞተም፤በልጅነት ልምሻ ተጠቅቶ በዱላ እየተደገፈ በህይወት መኖረ ቀጠለ፡፡
ከሳይንስ ጋር የጓደኛዬ ትረካም ቀጥሏል፡፡
ሳይንስ የሚኖረው ምክንያታዊነት እስካለ ድረስ ነው፡፡ ምክንያታዊነት በጭንቅላት ነው የሚሰራው፡፡ ምክንያታዊነት በሃይማኖት ወይንም በልብ ወይንም በስሜት አይሰራም፡፡ ድህረ - ዘመናዊነት በማይሰራው እንዲሰራ፣ በሚሰራው እንዳይሰራ የማድረጊያ ፍልስፍና ነው፡፡ አንገትን ጭንቅላት፣ ጭንቅላትን አንገት ሲደረጉ ነው ወይ የማይሰራው እንዲሰራ የሚሆነው፡፡ አልኩት፡፡ እኔ የሴቶችን ከጓዳ ወደ መስክ መውጣት ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
ሴት እና ወንድ ሁለቱም ጭንቅላት፣ ሁለቱም አንገት አላቸው፤ልዩነታቸው በአንገት እና በጭንቅላት ሊመሰል አይችልም፡፡ ሴቶች የወንዶችን የቀድሞ ሃላፊነት መጋራታቸው እንዲያውም ምክንያታዊ-- ሳይንሳዊ ነው፡፡ እኔ የምልህ ሌላ ነው፡፡ እኔ የምልህ በደንብ እንዲገባህ ወደ ጥበባቱ ብናተኩር ይሻላል፡፡
ቅድም የጠቀስኳቸው ሰብዓ ሰገሎች፣ ፈላስፎች ወይንም ጠንቋዮች ምክንያታዊነትን የሚያጣጥል ፍልስፍና በምክንያታዊ መሳይ አቀራረብ፣በተወለደው ልጅ ደም ውስጥ ረጭተው ዞር አሉ፡፡ የተረጨው መርዝ መስራት የጀመረው…እንደ ሁልጊዜውም መጀመሪያ በተጨባጭ የታየው ጥበበኞቹ ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የድህረ-ዘመናዊነት ምረዛ ሰለባዎች፣ በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው ወደ አለም መድረክ የመጡት፡፡ ስማቸውን ታውቃቸዋለህ? እነ ፒካሶ፣ እነ ገርትሩድ እስታይን፣ እነ ጄምስ ጆይስ…ምናምን ናቸው፡፡ ይዘን መጣን የሚሉት የጥበብ ዘይቤ…ኪውቢዝም፣ ዳይዝም…ስትሪም ኦፍ ኮንሸስነስ…ጂኒ ቁልቋል…ጂኒ ጃንካ… ፒካሶ የሚባለው ዋና የጥፋት ዲያቆን ነው፡፡ ከስዕል ጥበብ ውስጥ ምክንያታዊነትን ሙሉ ለሙሉ አውጥቶ አብስትራክት አርት ፈጠርኩ አለ፡፡ ደግሞም ፈጥሯል፡፡ በድህረ-ዘመናዊነት ማፍረስ መፍጠር በመሆኑ ማለት ነው፡፡ ባለ ሦስት አውታሩን ስዕል ወደ ሁለት አውታር፣ ሲሻው ደግሞ አውታር አልባ አድርጐ አቀረበ፡፡
ለስነጽሑፉ ደግሞ ጄምስ ጆይስ አለልህ፡፡ የሰውን የውስጥ የሃሳብ አፈሳሰስ አሳያለሁ ብሎ በእውን ህልም የሚያዩ ገፀ ባህሪዎች ቀረፀ፡፡ መጽሐፉን እስካሁን በቅጡ የሚረዱት ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ በኋላ የመጨረሻ ስራውን አወጣ፡፡ Finnigans wake ይባላል፡፡ በዓለም ላይ የመጨረሻው ከባድ የልብ ወለድ ድርሰት መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ከባድ የተባለው ከደራሲው በስተቀር ለማንም በግልፅ ስለማይገባ ነው፡፡ የራሱን አዲስ ቃላት እየፈጠረ፣ አንድ አረፍተ ነገር የሚያክሉ ቃላትን ያለ ክፍተት አንድ ላይ እያጠባበቀ … መግለፅ ሳይሆን መደበቅን ለአንባቢ አበረከተ፡፡ … ይኸው አበርክቶቱ የድርሰት ቁንጮ መሆኑ ይሰበካል … የድርሰትን ምክኒያታዊነት ሙሉ በሙሉ ኢ - ምክኒያታዊ ማድረግ ነው ግቡ፡፡ ግቡ ተሳክቶለታል፡፡
 ቅድም ልብን በጭንቅላት ስለ መቀየር አንስቼብሀለሁ፡፡ ድህረ ዘመናዊነት ልብም ጭንቅላትም አይደለም፡፡ ሁለቱንም አፈራርሶ፣ ከፍርስራሹ ከሁለቱም ውጭ የሆነ ነገር መፍጠር ነው፡፡ ልብን እምነት፣ ጭንቅላትን እውነታ ልንላቸው እንችላለን፡፡ ድህረ-ዘመናዊነት ጭንቅላትን እና ልብን እንደ መሳሪያ ተጠቅሞ .. መሳሪያውን መልሶ ለማፍረስ የሚደረግ የትዕቢት እንቅስቃሴ ነው … አለኝ እና ከንዴቱ መለስ አለ፡፡ እናም ቀጠለ፡፡
ወደ ሀገራችን ስትመጣም ጥበቡ በዚሁ ደዌ የተመታ ነው፡፡ ግን ደዌው ምክንያታዊነትን አይገድለውም፡፡ ምክንያቱም አበሻ ምክንያታዊነት በጭንቅላቱ ውስጥ ወይንም በልቡ ውስጥ የሚገኝ ባለመሆኑ ነው፡፡  የአበሻ ምክንያታዊነት የሚገኘው በባህሉ ውስጥ ነው፡፡ ባህል ደግሞ መቼ እንደተሰቀለ የማይታወቅ  ርቆ ያለ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ማስጠንቀቂያው የፈለገ ርቆ ቢሰቀልም … ግልፅ ሆኖ ባይነበብም… መስራቱ ግን አይቀርም፡፡ ማስጠንቀቂያውን “የአበሻ ጨዋነት” ብለን ብንጠራው የራቀ ስያሜ አይመስለኝም፡፡ ማስጠንቀቂያው ከላይ “የአበሻ ጨዋነት” … ዝቅ ሲል ደግሞ በደቃቅ ፅሁፍ “የአበሻ ነብራዊ ዥንጉርጉርነት” ነው፡፡
ዥንጉርጉርነቱን በምሳሌ ላሳይህ፡-
በአንድ ቀለሙ ድህነትን የሚያከብር ህዝብ ነው… በሌላ በኩል ባለፀጋነትንም ይመኛል፡፡ በአንድ በኩል ክርስቲያን ነው-- በሌላ በኩል አዶ ከብሬ አለበት፡፡ ክታብ እና መስቀሉን አቻችሎ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ ሰም እና ወርቅ አለው፡፡ በጨዋነት ሰምና ወርቁን እየደበቀ እና እየገለፀ አንድ ላይ ያስተናግዳል፡፡ ቋንቋው  ራሱ የሰም እና የወርቅን ባህርይ በውስጡ ያቀፈ ነው፡፡ ስለዚህ የአበሻ ምክንያታዊነት የፈረንጆቹን አይደለም፡፡ የአበሻ ሃይማኖት የአውሮፓዊያኖቹን አይመስልም፡፡ ከውጭ መስሎ ቢገኝ እንኳን ከውስጥ ግን እነሱን አይደለም፡፡ አበሻ የራሱ አንገት እና የራሱ ጭንቅላት ባለቤት ነው፡፡ በአንገቱ አዟዙሮ ቢያይም በጭንቅላቱ አዟዙሮ ቢያስብም … ከዥንጉርጉርነቱ እና ከጨዋነቱ አያፈነግጥም፡፡
እና ምን እያልከኝ ነው? አልኩት፡፡
አበሻ ዘንድ ሞደርኒዝምም ሆነ ፖስት ሞደርኒዝም አይገባም፡፡ ሳይንስን በግርግሙ ስላላዋለደ … ሳይንስን አይነጠቅም፡፡ ድሮውኑ ያልነበረ ነገር አይጠፋም፡፡ ሳይንስን ያዋለዱት ሳይንስን ሲያከብሩ አብሮ ያከብራል፡፡ የሳይንስን ምክንያታዊነት ሲያዋርዱ ያዋርዳል፤ ግን የሚያዋርደው እነሱን ለማገዝ እንጂ ራሱን ለማርከስ አይደለም፡፡ የሚያከብረውም ሆነ የሚያደንቀው በሰም ደረጃ ያለውን ነው፡፡ ወርቁን ግን አያስነካም፡፡ አበሻ ዥንጉርጉርነት እና ጨዋነት ባህሉ ነው፡፡ ሳይንስም ሃይማኖትም ለሱ እነዚህ ናቸው፡፡
ስለዚህ … ሰለሞን ደሬሳ ቅርፃዊነት ብሎ ሲነሳ .. ወይንም አንቶኔ ኢንስታሌሽን አርት ብሎ ብቅ ሲል … ከራሱ ጥፋት ወይንም ልማት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው … በደመነብሱም ቢሆን አውቆ ነው፡፡
የአበሻ ጨዋነት እና ዥንጉርጉርነት በድህረ-ዘመናዊነት አይነካም፡፡ አበሻ ሞደርን ከመሆኑ አስቀድሞ post modern ሊሆን ይችላል፡፡ አለም የያዘውን ፋሽን ይይዛል፡፡ ስለ ማንነት ቀውስ ሲነሳ፣ የቀውሱን መገለጫዎች ተላብሶ ወየው! ይላል፡፡ የጨዋነቱ አካል ነው ይኼም፡፡
አበሻ እንደ ፒካሶ ሙሉ ለሙሉ ሊያምፅ አይችልም፡፡ ምክንያታዊነት ላይ ለማመፅ መጀመሪያ ሳይንሳዊ ማንነት ያስፈልጋል፡፡ ሳይንሳዊ ማንነት ያላቸው፣ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች ሲልኩለት ይቀበላል፡፡ ሳይንሳዊ ማንነትን ለማጥፋት የሚቀሰቅሱትንም ይተባበራል፡፡ ዘመናዊ ልብወለድን እና ዘመናዊ ትያትርን ይመለከታል፡፡ እነሱ በሰሩት መልክ ይሰራል፡፡ ባፈረሱት መንገድ ያፈርሳል፡፡ ወርቁን ግን አያስነካም፡፡ ዘመናዊ ልብወለዱን እያጻፈ፣ ባህላዊውን ተረቱን በዥንጉርጉር ልቡ የወርቅ ማህደር ውስጥ ይዞ ይቀጥላል፡፡ ባህላዊው ተረትና ምሳሌ በዘመናዊነት ውስጥ አልተፈጠረም፡፡ በድህረ-ዘመናዊነት ውስጥም አይለወጥም፡፡ ባህላዊው አበሻ ከፍልስፍና ውስጥ የተፈጠረም አይደለም፡፡ የፈረንጆቹ ምክንያታዊነት በጥቂት ፈላስፎች የተፈጠረ ነው፡፡ በመሆኑም በጥቂት ኢ-ምክኒያታዊ ፈላስፎች ተመልሶ ሊናድ ይችላል፡
ከአበሻ ጨዋነት ጋር የሚጋጭ ፍልስፍና ይዞ የሚመጣ ወዮለት፡፡ በአበሻ ዥንጉርጉርነት ጉራማይሌ ባህሉ ውስጥ የሚጋጨው ፍልስፍና፣ ከነብሩ ዥንጉርጉሮች መሀል አንዱ ይሆናል፡፡ የአበሻ ጨዋነት አንድ ኢላማ ስላልሆነ አንድ ተኳሽ አይመታውም፡፡ በነብር ቆዳ ላይ ያሉትን ነጠብጣቦች በአንድ ተኩስ መምታት አይቻልም፡፡ የነብሩ ህልውና ያለው በነጠብጣቦቹ ላይ ነው፡፡
ስለዚህ---አንተ ምክንያታዊነትን ነው የምትደግፈው ወይንስ ፖስት ሞደርኒዝምን? ቁርጡን ጠየቅሁት፡፡ የምደግፈው አበሻነቴን ነው፡፡ በአበሻነቴ ውስጥ ሁለቱም የሉም፡፡ ግን እንደ ፋሽን ፖስት ሞደርኒዝም ወደ እብደት ያጋደለ ሲመስለኝ ወደ ምክንያታዊነት እመለሳለሁ፡፡ ምክንያታዊነት አላፈናፍን ብሎ ችክ ሲልብኝ ደግሞ ወደ ሀይደርጋር ወይንም ወደ ኤግዚዝቴንሻሊዝም እመለሳለሁ፡፡ ኤግዚዝቴንሻሊዝም ራሱ ፖስት ሞደርኒዝም የገራው ኮሚኒዝም መሆኑን አትዘንጋ---፡፡ ብሎ ንግግሩን ቋጨልኝ፡፡ ግን የነገረኝ ሁሉ ራሴ መስማት የምፈልገውን በመሆኑ፣ ከሱ ወርጄ ንግግሩን የራሴ አደረግኋቸው፡፡  

Read 4106 times