Saturday, 29 November 2014 11:42

ፍቅርተና የፍቅር ዲዛይኗ

Written by 
Rate this item
(17 votes)

በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪና ስነ አእምሮ ያጠናችው ፍቅርተ አዲስ፣ በአልባሳት ጥበብ (ፋሽን ዲዛይን) የተዋጣላት ባለሙያ ናት፡፡ ከአራት ሺ ብር ገደማ አንስቶ እስከ 20 ሺ ብር የሚያወጡ የሰርግ ልብሶችን ለበርካታ ደንበኞች ማዘጋጀት፣ በተለይም በሰርግ ወራት ፋታ እንደሚያሳጣ የምትናገረው ፍቅርተ፤ የአልባሳት ጥበብን ኑሮና መተዳደሪያዋ አድርጋዋለች፡፡ ከሞሮኮ እስከ ጃማይካ፣ ከፓሪስ እስከ ኒውዮርክ በርካታ ትርኢቶችን አቅርባም እውቅናና ሽልማት አትርፋበታለች፡፡ ነገር ግን የስነ አእምሮ ትምህርቷ ባክኖ አልቀረም፡፡ የስራዋና የህይወቷ አካል ሆኗል፡፡ ቢቻል ሁሉም ሰው፣ በተወሰነ ደረጃ የስነ አእምሮና የፍልስፍና እውቀት ቢኖረው ይመረጣል ብላ ስትናገር ለወጉ ያህል አይደለም፡፡ ከአለባበስና ከአረማመድ ጀምሮ፣ የጨርቅ ቀለም ምርጫና የልብስ ዲዛይን ፈጠራ፤ የሰርግ ውድ ልብስና የትምህርት ቤት ዩኒፎርም ሳይቀር ከስነ አእምሮ ጋር ይገናኛል፡፡ የስራ ባልደረቦች ግንኙነትና የቤተሰብ ሁኔታ፣ የደንበኞች ፍላጎትና መስተንግዶም እንዲሁ፡፡ የአገር ገፅታና የዓለም ገበያ፣ የፆታ ጥቃትና የልጆች አስተዳደግ ከስነ አእምሮና ከፍልስፍና ጋር የተያያዘ ነው ለፍቅርተ፡፡ ተወልዳ ባደገችበት አዲስ አበባ “የፍቅር ዲዛይን” የተሰኘ ቢዝነስ የከፈተችው ፍቅርተ፤ ስለ ልብስ ምርጫ እንዲህ ትላለች - ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ፡፡

ብዙ ሰው፤ ፋሽን ነው ተብሎ የሚመጣውን ነገር ሁሉ መልበስ ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ይስማማዋል ማለት አይደለም፤ የራስን የሰውነት ቅርፅና ቁመና መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በዚያ ላይ ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ የግል ማንነት አለው፡፡ ፕሮፌሽናል ዲዛይነር እነዚህን ነገሮች ያገናዘበ ምክርና አገልግሎት ለደንበኞቹ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ሙያዬ ስለሆነ ደንበኞችን በደንብ አስተናግዳለሁ፡፡ ደንበኞች ሲመጡ፣ ለሰውነታቸው ቅርፅና ቁመት፣ ለሚፈልጉት ፕሮግራምና ዝግጅት፣ ለሚለብሱበት ሰአትና ለማንነታቸው  የሚስማማ ልብስ  እሰራለሁ፡፡ አንዳንድ ሰዎች በጣም ጎበዞች ናቸው፣ የሚያምርባቸውን ያውቃሉ፡፡ ከነሱ ጋር የማይሄድ ነገር የሚመርጡትንም ሰዎች ማስተናገድና በሙያዊ ምክር ማስተማር በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ለምሳሌ ጋቢ ወይ ቡፍ የሚል ቀሚስ፣ ወፈር ላለ ሰው አይመከርም፡፡ ይህን የሚመርጡ ሲመጡ፣ ቁጭ ብዬ ጊዜ ሰጥቼ በተለያዩ ጨርቆች የተሰሩ ልብሶችን እየሞከሩ እንዲያዩ እና እንዲመርጡ እረዳቸዋለሁ፡፡  እኔ በጣም የሚያረካኝ አንድ ልብስ ጀምሬ ስጨርስና  የሰራሁላቸው ሰዎች በጣም ሲደሰቱ ሳይ ነው፡፡

የስነ አእምሮ ትምህርት - የአልባሳት ጥበብ
የመጀመሪያ ዲግሪዬን በኤዱኬሽናል ሳይኮሎጂ፣ የሁለተኛ ዲግሪዬን ደግሞ በዴቨሎፕመንታል ሳይኮሎጂ አግኝቻለሁ፡፡ የስነ አእምሮ ትምህርት በዚያው መስክ ላይ ለመቀጠር ሳይሆን በአጠቃላይ ለህይወቴ ጠቅሞኛል፡፡ እንዲያውም ገና ተምሬው አልጠገብኩም፤ ወደ ላይ እቀጥላለሁ፡፡ በእርግጥ ትምህርቱ ከስራ እና ከቤተሰብ ሀላፊነት ጋር በጣም ይከብዳል ግን በየእለቱ ሀያ አራት ሰአት አለሽ፡፡ የኛ የሰዎች ፋንታ፣ ቅድሚያ ለምትሰጪው ነገር ሰዓት መስጠት ነው፡፡  ትምህርት ከጨረስኩ በኋላ አፕሪፍስ በተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ተቀጥሬ፤ ጥቃት ለደረሰባቸውና በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ለተጎዱ አማካሪ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ ህፃናቱ ከቤተሰቦቻቸው እና ከማህበረሰቡ ጋር ከመቀላቀላቸው በፊት የስነልቦና ምክር በመስጠት እንዲዘጋጁ እረዳቸዋለሁ ማለት ነው፡፡ በዚህ ስራ ትልቁ የተማርኩት ነገር ምን መሰለሽ? ለነዚህ ልጆች የቱንም ያህል የስነልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ ብትሰጫቸው ኢኮኖሚው ላይ እሰካልተሰራ ድረስ ምንም ለውጥ አይመጣም፡፡

የዲዛይን ህይወትስ ከወዴት መጣ?
ዲዛይን ከልጅነቴ ጀምሮ ቀልቤን የምሰጠው ነገር ነው፡፡ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ነው የንድፍ ስዕል መስራት የጀመርኩት፡፡ እናቴና አክስቴ ልብስ ስፌት ይማሩ ነበር፡፡ ሁለቱም እየረዱኝ፣ ቤት ውስጥ በእናቴ የልብስ መስፊያ ማሽን በመቀስና በስፌት ማሽን ተለማመድኩ፡፡ የራሴን ልብሶች መለማመጃ አደረኳቸው፡፡ ልብሶቼን በተለያየ መንገድ እየቀያየርኩ፣ ገና የልብስ ስፌት ትምህርት ቤት ከመግባቴ በፊት ልብስ መስፋት እችል ነበር፡፡ ለራሴ ለጓደኞቼ እና ለቤተሰቦቼ ስሰራ፣ ከዚያ እነሱ የሚያውቋቸው ሰዎች ሲያዩ፣ በሰው በሰው ስራ እየመጣልኝ … ለካ ሳላውቀው ስራው ውስጥ ገብቼያለሁ፡፡ ሰዎች በአጋጣሚ አግኝተው ለሰርግ ልብስ ሰርተሽልን ነበር ሲሉኝ እደነግጥ ነበር፡፡ ከዛሬ አምስት አመት በፊት ነው ሙሉ ለሙሉ ወደዚህ ሙያ ጠቅልዬ የገባሁት፡፡ የስነ ልቦና ስራዬንና የዲዛይን ሙያዬን ደርቤ መስራት አልፈልግም፡፡ ከልጆቼ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ስላለብኝም ጊዜዬን በራሴ መንገድ ለመጠቀም ወስኜ፤ ይኸው እስከአሁን እየሰራሁ ነው፡፡

ትልቁ ፈተና - ፋታ የሚያሳጣ ሙያ
 ሌሎች ዲዛይነሮችም የሚጋሩት ይመስለኛል፡፡ በጣም ፈታኙ ነገር ስራን እና የቤተሰብ ህይወትን አንድ ላይ አጣጥሞ የማስኬድ ፈተና ነው፡፡ የዲዛይን ሙያ በጣም ጊዜ ይፈልጋል፡፡ በተለይ የሰርግ ወቅቶች ሲመጡ ትንፋሽ ያሳጣል፡፡ ከዚያ ውጭ ተስማምቶና  ተከባብሮ፣ ሙያውን ከልብ አፍቅሮ የመስራት ጉዳይ ነው፡፡
“የፍቅር ዲዛይን” የራሱ መርህ አለው፡፡ የአገር ውስጥ ምርቶችን እንጠቀማለን፡፡ አማራጭ ሲጠፋ ብቻ፣ የተወሰኑ የውጪ ጨርቆች ብንጠቀምም፤ ልብሶቻችን ከዘጠና በመቶ በላይ ከጥጥ የተሰሩ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ የተማርኩት ሳይኮሎጂ ስለሆነ፣ በህፃናት የጉልበት ብዝበዛ ላይ ብዙ ነገር አውቃለሁ፡፡ በአለም ላይ የህፃናት የጉልበት ብዝበዛ እጅግ ከተንሰራፋባቸው ዘርፎች ቀዳሚው የሽመና ዘርፍ ነው፡፡  የጨርቅ ምርት የሚያቀርቡልኝ ባለሙያዎች ከህፃናት ብዝበዛ የፀዱ ናቸው፡፡ ማህበራቸው “በህብረት እናምልጥ” ይባላል፡፡  ቦታ ተሰጥቷቸው ህጋዊ ሆነው የሚሰሩ በሙያው እጅግ የተካኑ ጎበዝ ሰራተኞች ናቸው፡፡ ከሁሉም ጋር ያለኝ ግንኙነት በመከባበርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እነሱም ይፈልጉኛል፤ እኔም እፈልጋቸዋለሁ፡፡ ራሴን የራሴ አለቃ ሳደርግ ያገኘሁትን ነፃነት ሌሎችም እንዲያገኙ እፈልጋለሁ፡፡ አንድ ሰው ከኔ ጋር አስር አመት ሰርቶ ጡረታ ይዞ ከሚወጣ፤ የራሱን ድርጅት ከፍቶ፣ እሱም በተራው ለሌሎች ሰዎች እድል ሲያመቻች ማየት ያስደስታል፡፡ የስራና የምርት አቅርቦት ሰንሰለት ይፈጠራል፤ ሰዎችም ያድጋሉ፡፡ ይሄ የዘወትር ህልሜ ነው፡፡ ጥልፍ እና ኪሮሽ ከሚሰሩ ሴቶች ጋር እንሰራለን፡፡ ከሴቶች ጋር መስራት እንፈልጋለን፡፡ ግን ሴቶች ማለት እናቶች መሆናቸውንም መርሳት የለብንም፡፡ በስራ ራሳችንን ጠምደን ልጆቻችን እንዴት ሊጠፉ እንደሚችሉ ሳስበው ያስጨንቀኛል፡፡ የየቀኑ ፈተናዬ ነው፡፡ ልጆች ትምህርት ቤት የተማሩትንና፣ የቤትስራ ይዘው የመጡትን፣ መከታተል የአባትና የእናት ሀላፊነት ነው፡፡  ያ ሳይሆን ሲቀር ነው፣ የተዛባ ባህርይ እየተስፋፋ አገር የሚያጠፋው፡፡ ስለዚህ እናቶች ከልጆቻቸው ሳይርቁ ቤታቸው ሰርተው በቀጠሮ ቀን እንዲያመጡ አደርጋለሁ፡፡ ለአንድ የጥልፍ ስራ እስከ 6 ሺ ብር ድረስ እከፍላለሁ፡፡

ሽልማቶች እና እድሎች
እንደጀመርኩኝ ብዙ ሾዎች ነበሩ፡፡ በዚያው አመት አሊያንስ በተዘጋጀ ውድድር ሁለተኛ ወጣሁ፡፡ ያን አጣጥሜ ሳልጨርስ፤ ሞሪሺየስ ላይ ከ12 የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ዲዛይነሮች የተሳተፉበት “ኦሪጅን አፍሪካ” በተባለ ውድድር ላይ አንደኛ ወጣሁ፡፡ በ2011 ኒውዮርክ የሚካሄደውን “አፍሪካ ፋሽን ዊክ” ተመርጬ አዘጋጀሁ፡፡ በ2012 እዚያው ኒውዮርክ  ውድድሩን ዲዛይነሯ ማፊ በማሸነፏ እኔ ደግሞ እንዳዘጋጅ እንደገና ተመርጬ አዘጋጀን፡፡ አሁንም ለማሳየት እየተዘጋጀን ነው፡፡ ሌላው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም፣ አጎዋ ላይ ተሳትፈናል፡፡ ፕራግ፣ ፓሪስ፣ ጃማይካ እና ሌሎች ቦታዎችም አሳይቻለሁ፡፡ ሁልጊዜ የኢትዮጵያ ስም ሲነሳ በውጭው ዓለም የተቀረፀው መጥፎ ገፅታ ጎልቶ ይታያል፡፡ አንዳንዶቹ መጥፎ ገፅታዎች የእውነትም የሉም ማለት አይደለም፡፡ ለመለወጥ ብዙ መስራት አለብን፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በጎ ገፅታዎችን ሳታጣ፣ መጥፎው ብቻ መጋነኑ ሚዛናዊ ስላልሆነ ያበሳጫል፡፡ በውጭ አገራት ትዕይንት ስናቀርብም የተጠቀምነውን የጨርቅ ምርትና ዲዛይኑን አይተው ሲደነቁ እጅግ ያስደስተኛል፡፡
ከሁሉም የሚበልጠው ሽልማት በስራው እውቅና ማግኘት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉንን ባህላዊ እሴቶች መማር ለኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ጨንቻ ሄጄ በተፈጥሮአዊ መንገድ ልብስ ሲያቀልሙ አይቻለሁ፡፡ ውጪ አገር ለተፈጥሮ ማቅለሚያ የሚከፈለው ገንዘብ ከአርቲፊሻሉ ይበልጣል፡፡ እነዚህን ጥበቦች መማሬ ያስደስተኛል፡፡
ገበያው ምን ይመስላል
የአገር ልብስ ተፈላጊነት እየጨመረ ነው፡፡ በፊት በጣም ጎበዝ ልጆች የነበሩ ቢሆንም ሁኔታዎች ምቹ አልነበሩም፡፡ በፊት ለመልስ ይፈለግ የነበረው የአበሻ  ልብስ፣ አሁን ለሰርግ የሚፈለግ ሆኗል፡፡ ዋጋው ከ3800 እስከ 20ሺህ ይደርሳል፡፡ አንድ ልብስ ስትሰሪ ለዛች ሴት ብቻ ነው የምትሰሪው፡፡ ለምሳሌ አስር ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው ጥልፍ፤ አንድ ጠላፊ ለወር ቁጭ ብሎ የሚሰራው ስራ ነው ለአንድ ወር ጊዜ ተሰጥቶ የተሰራው ስራ ዋጋው ከፍ እንዲል ያደርገዋል፡፡ ከሰርግ ውጪ የሚለበሱት ደግሞ 400፣ 500 ይሸጣሉ፡፡ ዋጋዬ ትንሽ ወደድ ይላል፡፡ ግን የስራው እና የጨርቁ ጥራት ነው፡፡ ማሰብ ያለብን የአገር ውስተር ገበያ ብቻ አይደለም፡፡ የአልባሳት ስራ በደንብ ከሰራንበት በአለም ገበያ ተፈላጊነቱ እንደሚጨምር እርግጠኛ ነኝ፡፡

የትምህርት ቤት ዩኒፎርም  ለምን ግራጫ ይሆናል?
የመጀመሪያው ነገር ምቾት ነው፡፡ የሴት  ተማሪዎች ቀሚስ ከጉልበት በታች ሲረዝም ምቾት አይሰጣቸውም፡፡ ምቾት እና ውበትን፣ አላማንና ስብዕናን አንድ ላይ ማምጣት ይቻላል፡፡ ልጆቼን ሁልጊዜ “ቆንጆ ንፁህ ሰው ሁኑ” እላቸዋለሁ፡፡ ዝርዝሩን እድሜያቸው በጨመረ ቁጥር ያውቁታል፡፡ ነገር ግን በንፅህና ስብእና ይቃኛል፡፡ “የመታጠብ ንፅህና የልብ ንፅህና” እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ደማቅ ከለሮች ደስ ይላሉ፡፡
ልጆች ይወዳሉ፡፡ ታዲያ ለተማሪዎች ዩኒፎርም ለምን ደማቅ ቀለማት አይመረጡም ልትይ ትችያለሽ፡፡ ነገር ግን የትምህርት ቤት ዩኒፎርም ምንን እንደሚወክል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ዲሲፕሊን ወይም በስርዓት የመማር አላማን የሚያሳይ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህም ነው የትምህርት ቤት የደንብ ልብሶች በአብዛኛው በግራጫ ወይም በደብዛዛ ሰማያዊ ጨርቆች ተሰርተው የሚቀርቡት፡፡ አላማቸውን ያሳኩ ቀለሞች ናቸው፡፡ ደግሞም ያምራሉ፣ ከጥጥ የተሰሩ ቢሆኑ ግን  ደስ ይለኛል፡፡

ዲዛይን እና ሳይኮሎጂ  
ማንም ሰው ቢችል በተወሰነ ደረጃ ታሪክን፣ ፍልስፍናንና ሳይኮሎጂን ቢያውቅ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ሳይኮሎጂ የሰውን ባህርይ የሚያጠና ስለሆነ፣ የማይገባበት ነገር የለም፣ እሱን አወቅሽ ማለት፣ ህይወትን አንዴት እንደምትመሪ ቤተሰብ፣ ልጆች እንደምታሳድጊና በስራ ቦታ ባልደረቦችንና ደንበኞችን እንዴት እንደምታስተናግጂ አወቅሽ ማለት ነው፡፡ ከተፈጥሮዬም ጋር የሳይኮሎጂ ትምህርቴ ተጨምሮበት የደንበኞቼን አይን፣ የአካል እንቅስቃሴያቸውን አይቼ ስሜታቸውን ለመረዳት፣ እንዴት ልረዳቸው እንደምችል ለማሰብና መላ ለመፍጠር ትልቅ እድል ሰጥቶኛል፡፡
የኢትዮጵያውያን የልብስ ቀለም ምርጫ ከብዙ የአፍሪካ አገራት የደማቅ ቀለም ምርጫ የተለያየው ለምን ይሆን? ባህላዊና ዘመናዊ ልብሶች የተለያየ የቀለም ዝንባሌ እንዳላቸው ፍቅርተ ትናገራለች፡፡
ባህላዊ ልብሶቻችን በቀለማት የተሞሉና የደመቁ ናቸው፡፡ ዘመናዊ ልብሶች ቀለም በአመዛኙ ነው ደብዘዝ ይላል፡፡ ያ ደግሞ ከውጪው ዓለም ተፅዕኖ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የዘመናዊ ልብሶች ብዙ ጊዜ ከሁለት ወይም ከሶስት ቀለሞች በላይ አይሄዱም፡፡ ጥቁር፣ ነጭ እና ዝም ያለ ቀለም ነው ይበዛባቸዋል፡፡ የባህል ልብሳችን፡፡ ደግሞ ተመልከቺ፡፡ ጥለት ውስጥ ስንት ቀለም እንዳለ አስቢ፡፡
በየዓመቱ ለማቀርባቸው አዳዲስ የአልባሳት ፈጠራዎች ለመዘጋጀት ወደ ሀረር ሄጄ ነበር፡፡ የሀረሪን፣ የሶማሌን እና የአፋርን የአለባበስ ዘይቤ ያካተተ ፈጠራ  ለመስራት ነው የፈለግኩት፡፡ ሃረር ስትደርሺ ቀለሞች ይቀበሉሻል፡፡ ግንቡ፣ ቀይ ፒንክ ነው፡፡
ጀጎል ስትገቢ ቀለሞቹ ሙቀት ይሰጡሻል፡፡ ዲዛይን እራስን የመግለጫ መንገድ ነው፡፡ አለባበስ ማንነትን አጉልቶ መናገር ይቻላል፡፡
የሀና ጉዳይ
የሚያስከፋ ነገር ነው፡፡ የማህበረሰብ ጤንነት ማጣትን ያሳያል፡፡ ኮሌክቲቭ ኮንፈርሚቲ የሚባል ነገር አለ፡፡ አንድ ላይ ስትሆኚ የምታመጪው ባህርይ ልክ ነው ብሎ ማሰቡ ራሱ በስራዬ አውቃለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ያልተነካ በጣም ጥቂት ነው፡፡
 ወንዶች ይደፈራሉ፡፡ የስነልቦና ጤንነት እንደሌለ ያሳያል፡፡ ስለማይወራ ዝም የተባሉ ብዙ ተመሳሳይ ኬዞች አሉ፡፡ ልጆቻችንን ስንቶቻችን እናስተምራለን? ስንቶቻችን መረጃ እንሰጣለን? ጥቃት ምን እንደሆነ ምን ምን ነገሮች ሲያጋጥማቸው ለቤተሰብ ማሳወቅ እንደሚገባቸው እናደርጋቸዋለን? ጥፋት ፈፃሚዎቹ እኮ የሆኑ ሰዎች ልጆች ናቸው፡፡ እንዴት ነው ያሳደግናቸው? ምን ያህል ጥበቃ ያደርጋል? መንገድ ላይ ትንኮሳ ሲያጋጥም እንዴት ይታለፋል? የማህበረሰብ የጤንነት ደረጃን ያሳያል፡፡ ከቅጣት በፊት መከላከል ይቀድማል ሁሉም በየቤቱ ልጆቹን ጥሩ እሴት ይዘው እንዲያድጉ ማድረግ አለበት፡፡   እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ የሚለውን ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ጊዜ ላይ ነን፡፡  ሁላችንም ራሳችንን ሀና ቦታ ላይ እናስቀምጥ፡፡
ያለፈችባቸውን ስቃዮች እናስባቸው፡፡ ለቤተሰቦቿ መፅናናትን እመኛለሁ፡፡

Read 10888 times