Monday, 08 December 2014 14:12

መድረክ ለመጪው እሁድ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ

Written by  ማህሌት ሰለሞን
Rate this item
(2 votes)

በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ነፃና ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒነት ያለው እንዲሁም የምርጫ ሜዳው ለሁሉም እኩል የተመቻቸ እንዲሆን በተደጋጋሚ ለቀረበው ጥያቄ ኢህአዴግ የአሻፈረኝ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን የጠቆመው የኢትዮጵያዊ ፌደራላዊና ዲሞክራሲያዊ አንድነት (መድረክ)፤ በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ እስራትና ወከባ እየተካሄደ እንደሆነ በመጥቀስ ይሄን ለመቃወም በመጪው ሳምንት እሁድ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያካሂድ ገለፀ፡፡ባለፈው ረቡዕ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ደብዳቤ አስገብተው “ይፈቀድላችኋል፣ እናንተ ዝግጅታችሁን ቀጥሉ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው የጠቆሙት የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ ይሁን እንጂ እስካሁን መፈቀዱ በደብዳቤ አልተገለፀልንም ብለዋል፡፡
“በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ኢህአዴግ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመወያየትና በመደራደር ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ እንዲሆን እንዲሁም የታሰሩ የፓርቲው አባላት (የፖለቲካ እስረኞች) እንዲፈቱና በአባላቶችና ደጋፊዎች ላይ የሚደረገው ጫናም እንዲቆም እንጠይቃለን” ብለዋል፤ ሊቀመንበሩ፡፡
ሰላማዊ ሰልፉ በመጪው ሳምንት እሁድ ከጠዋቱ 3፡00 እስከ ቀኑ 7፡00 እንደሚካሄድ የተገለፀ ሲሆን፤ ከግንፍሌ ወንዝ ድልድይ በመነሳት፣ በቀበና ወንዝ ድልድይና በባልደራስ በኩል አድርጎ ወረዳ 8 ኳስ ሜዳ ድረስ እንደሚዘልቅ ፓርቲው በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
አ “የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በመሳተፍ ለሰላማዊ ትግሉ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ከታላቅ አክብሮት ጋር ጥሪውን ያስተላልፋል- ብሏል መድረክ፡፡

Read 2682 times