Saturday, 20 December 2014 13:16

የፊደል ላይ ዘመቻው አይበጀንም

Written by  ጌታቸው አበበ አየለ
Rate this item
(1 Vote)

    የሰው ልጅ አለኝታውና ማዕረጉ፣ ሞገሱና ኩራቱ ታሪኩ ነው፡፡ ታሪክ ደግሞ ታሪክነቱን ሊያገኝ የሚችለው የሰው ልጅ ራሱ ከትውልድ ወደ ትውልድ ጠብቆ በሚያስተላልፋቸው ወጐቹ፣ ቋንቋዎቹ፣ አፍአዊ ኪነቃሎቹ፣ ፊደልና ሥነ ጽሑፎቹ አማካኝነተ መኾኑ አያከራክርም፡፡ ታሪኩን በራሱ ፊደል መዝግቦ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያስተላልፍ አገር ደግሞ በእጅጉ የታደለ ነው፡፡ በዓለም ላይ ከሚገኙ አያሌ አገራት መካከል የራሳቸውን ፊደል ቀርጸው የሚጠቀሙት ግን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም አንዷ በራስ ፊደል ተጠቃሚ ኢትዮጵያ መኾኗ ለሕዝቦቿ ታላቅ ኩራት ነው፡፡ ለዚህ ታሪካዊ ዕድል ያበቋት የጥንት አባቶቻችን ተጋድሎ በዚህ ትውልድ ያለነውንና ቀጣዩንም ጭምር በእጅጉ ያኮራል፡፡ ይህ ታሪካዊ ኩራት ዘለቄታዊነቱን ሊያገኝ የሚችለው ግን ይህ ትውልድ የተረከበውን ታሪካዊ ቅርስ በሚገባ ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ሲችል ብቻ መኾኑን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡፡
እስከአሁንም ድረስ ኢትዮጵያ ወጐቿን፣ ቋንቋዎቿን፣ ባሕሎቿን ኪነ ቃሎቿንና የመሳሰሉትን በራሷ ፊደል ቀርፃ (ታሪኳን መዝግባ) ከትውልድ ትውልድ አሸጋግራለች፡፡
 ወደፊትም ታሸጋግራለች የሚለው ግን ጥያቄ ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ምክንያቱንም በፊደሎቿ ላይ የተደጋገሙ ዘመቻዎች መካሔዳቸውና እየተካሄዱም በመገኘታቸው በሚል ዐጭር መልስ ከመዝጋት ይልቅ በመጠኑም ቢሆን መዘርዘሩ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
የአገሪቱ የቋንቋ ምሁራን ለሁለት ጐራ ተከፍለው ፊደሎቻችን በዝተዋልና ይቀነሱ በሚሉና ፊደሎቹ ህፀፅ የለባቸውም በሚሉ ሐሳቦች መፋጨት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፤ ማለትም ዘመናትን አስቆጥረዋል፡፡
ይህ የፊደሎች ይቀነሱ ጉዳይ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች በቃል ሲወሳና በጽሑፍም ሲዘገብ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ እንደምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ፊደሎች ይቀነሱ ብለው ከተነሡት ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡
አቶ በእምነት ገብረ አምላክ፤ “የአንድ ቋንቋ ዕድገት ወይም አማርኛ እንደተስፋፋ ፲፱፻፵፯ ዓ.ም” መጽሐፋቸው “አማርኛን ማሻሻል ያስፈልጋል” ከሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ያሠፈሩት እንዲህ ይነበባል፡-
“…የአማርኛ ፊደሎች ብዛት ከመጠን ያለፈ ብዙ ስለሆነ መቀነስ አለበት፡፡…ብዙው ዓለም በ፳፮ የላቲን ፊደሎች የሚጠቀም ሲሆን አማርኛ ግን በ፻፪፴፯ ፊደሎች ይጻፋል…” በማለት የፊደሎቹ መብዛት ያስከተሏቸውን ችግሮች “ለጽሕፈት ያሳስታሉ፣ የእጅ ጽሕፈት መኪና እንዳይሠራ እንቅፋት ሆነዋል፣ ከመብዛታቸው የተነሣ ለጥናት ያስቸግራሉ፡፡ በእዚህም ምክንያት የፊደል በረከቱ ሳይደርሳቸው የሚቀሩ ብዙዎች ናቸው፡፡”
 በማለት ፊደሎቹ እንዲቀነሱ አስተያየታቸውን ዘርዝረዋል፡፡ ከበእምነት በፊትም ሆነ ከእሳቸው በኋላ በፊደላት ይቀነሱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ግለሰቦችና ቡድኖች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህም የመሰላቸውን መንገድ በመከተል የፈረዱባቸውን ሆሄያት እያስወገዱ መዝገበ ቃላትን ያህል ትልቅ ሥራ ለሕዝብ እያሠራጩ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ይባስ ብለው የፊደል ገበታው ሙሉ በሙሉ እንዲለወጡ የራሳቸውን ጥናት እስከማቅረብ ደርሰዋል፡፡ አማርኛ ቋንቋ የሚጠቀምባቸውን ፊደላት እርግፍ አድርገን ትተን በላቲን ፊደሎች ሙሉ በሙሉ እንጠቀም ያሉም አሉ፡፡ እስቲ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ሊሆኑ ይችላሉ ያልኳቸውን ሁለቱን ብቻ በምሳሌነት ለመጥቀስ ልሞክር፡፡
የመጀመሪያው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር በየካቲት ፲፱፻፺፫ ዓ.ም አዘጋጅቶ ያቀረበው “የአማርኛ መዝገበ ቃላት” የሚለው ነው፡፡ የመዝገበ ቃላቱ አዘገጃጀት በአዲስ የፊደል ገበታ መሠረት የቀረበ ሲሆን የፊደሎቹ ብዛት ሃያ ስምንት ናቸው፡፡ ይህም ከነባሩ የፊደል ገበታ አምስቱ ፊደላት ማለትም (ሐ፣ ሠ፣ ኅ፣ ዐ፣ ፀ) የተባሉትን ከጨዋታ ውጪ አድርጎ መሆኑ ነው፡፡
የቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከሉ ሆሄያቱን በመቀነስ ብቻ አልቆመም፡፡ “አንድ ፊደል መወከል ያለበት አንድን ድምፅ ነው፡፡” በሚል የሥነ ልሳን መርኅ ሰበብ የፊደል ማሻሻያ በማድረግ “ሀ” በራብዕ ድምፅ “ሃ” እየተባለ መጠራቱ ቀርቶ በግእዙ ድምፅ “ኸ” እየተባለ እንዲጠራ፤ ለምሳሌ - በቀድሞው አባባል (አጻጻፍ) “ይኸው” ተብሎ በሚጻፈው ምትክ “ይሀው” ተብሎ እንዲጻፍና “ሀ” በ “ኸ” ድምፅ እየተተካ እንዲነበብ፡፡
በተመሳሳይም ሁኔታ “አ” በራብዕ “ኣ” እየተባለ መጠራቱ ቀርቶ በ “ኧ” ድምፅ እንዲጠራና የ “ኧ”ን ቦታ እየተካ እንዲነበብ፤ (ለምሳሌ፡-“ኧረ!” በሚለው ምትክ “አረ!” ተብሎ እንዲጻፍና “አ” በ “ኧ” ድምጽ እንዲጠራ ወይም እንዲነበብ) ተደርጓል፡፡…” በማለት በመዝገበ ቃላቱ መግቢያ ላይ ዐውጇል፡፡ በዚህም መሠረት ፡- ፀሐይ ለማለት ፀሐይ መባሉም ቀረና “ፀኸይ” ሆነ፡፡ ሀገር ለማለት ኸገር፤ ሀብት ለማለት ኸብት፣ እያልን ልንጽፍ ወይም ልንናገር ነው፡፡ ታድያ ይኸ ለፊደሎቻችን ዕድገት ነው ወይስ ውድቀት?
ሁለተኛው በምሳሌነት የምጠቅሰው ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ማለትም በ2001 ዓ.ም “ብቸኛው አፍሪካዊ ፊደል (The Sole African Alphabet)” በሚል ርዕስ ዶ/ር ፍቅሬ ዮሴፍ “ተሻሽሎ የቀረበ አዲስ የኢትዮጵያ ሥርዓተ - ፊደል ገበታና የንባብ መለማመጃ” መጽሐፍ አዘጋጅተው ያሠራጩት ነው፡፡ በዶ/ር ፍቅሬ ዮሴፍ የጥናት ውጤት መሠረት፤ ነባሩ የፊደል ገበታ በቁጥር መብዛት ብቻ ሳይሆን በቅርጽም ጭምር ሙሉ ለሙሉ ተለውጠው እናገኛለን፡፡ ከግእዝ (የመጀመሪያ) ፊደላት በስተቀር ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ፊደል እንዲሻሻል ባቀረቡት አዲስ የፊደል ገበታ መሠረት በመጽሐፋቸው ገጽ 68 ያሠፈሩትን ተመልከቱት፡-
“የኢትዮጵያ ስርአተ ፊደሉ ገበታ” “የኢትዮጵያውያኑ ህብረ ብሔራዊ ሩሕየ” ይላል፡፡ መቼም ቃላቱ የተለመዱ በመሆናቸው እንደምንም ተመራምራችሁ በግምትም ቢሆን አንብባችሁት ከሆነ ትደነቃላችሁ፡፡ ጐበዝ በዚህ ዓይነትማ እስከ አሁን ተምሬአለሁ ያለው ሁሉ እንደገና ፊደል ቆጠራ መግባቱ እኮ ነው፡፡ ታድያ! እንዲህ ዓይነቱ በፊደል ላይ የሚካሄደው ዘመቻ ለዕድገት ነው? ወይስ ለውድቀት? ያሰኛል፡፡
የሚገርመው ይህንን ያህል ጥናት አድርገው የደከሙበትን የፊደል ገበታ ማሻሻል ሥራ እሳቸው ራሳቸው አልተጠቀሙበትም፡፡ በመጽሐፋቸው የተላለፈው መልእክት የተተየበባቸው ፊደላት በሙሉ ማለት ይቻላል፣ በነባሩ የፊደል ገበታ መሠረት ነው፡፡ መቀነስ አለባቸው ያሏቸውን ፊደሎች ሳይቀር እንደ አገባባቸው ተጠቅመውባቸዋል፡፡ ከመጽሐፉ ሽፋን ጀምሮ ብንመለከት ስርኣተ - ፊደል ብለው አላበላሹትም፤ በአግባቡ “ሥርዓተ - ፊደል” በማለት ጽፈውታል፡፡ ወደ ውስጥ ገፆቹም ዘልቀን ስናይ ሦስቱ “ሀ” ዎች (ሀ፣ ሐ፣ ኅ) ፣ ሁለቱ “ሰ”ዎች (ሰ፣ሠ)፣ ሁለቱ “አ”ዎች (አ፣ ዐ) እና ሁለቱ “ፀ”ዎች (ፀ፣ጸ) እንደየአገባባቸው ጥቅም ላይ ውለው እናገኛቸዋለን፡፡ ይህን በማድረጋቸው አደንቃቸዋለሁ፡፡
የ “ብቸኛው አፍሪካዊ ፊደል (The Sole African Alphabet) መጽሐፍ አቅራቢ በኢትዮጵያ ፊደል ላይ ጥልቅ ግንዛቤ እንዳላቸውና ከፍተኛ ጥናት እንዳካሄሔዱም መጽሐፋቸው ይመሠክርላቸዋል፡፡ እንዲያውም በመጽሐፋቸው ገጽ 9 ላይ የውጪ አገር ዜጐች የሆኑ ወዳጆችና የሥራ ጓደኞች እንደነበሯቸውና የኢትዮጵያን ፊደል ሊያስተምሯቸው ሲሞክሩ የፊደሉን ብዛት በማየት ብቻ እየተሳለቁባቸውና ተስፋ በመቁረጥም የማይሞከር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ታድያ! በቁጭት ተነሣሥተው “Oh la! la! L’ alphabet ethiopien C’ est trop complique” (ኦ!ላ!ላ የኢትዮጵያ ፊደል በጣም ውስብስብ ነው) ያሏቸውን የፈረንሳይ አምባሳደር አባባል ለማክሸፍ ደረጉትን ጥረት እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፡-
“…እኔም ቀድሞውኑ ከፍተኛ ቁጭት ስለበነበረብኝ ከመቅጽበት ዶ/ር ሞሪስ የሚባለውን የፈረንሣይ ዜጋ ጓደኛዬን “ተወራረዳቸውና በ15 ቀናት ውስጥ አሰልጥኜህ አማርኛ እንድታነብ አደርግሃለሁ፣” በማለት በገባሁለት ቃል መሰረት ጓደኛዬ አማርኛን በ15 ቀናት ውስጥ አቀላጥፎ ማንበብ እንደቻለ አስታውሳለሁ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማን በተሽከርካሪ በምናቆራርጥበት  ወቅት “ኮካ ኮላ - ሜታ ቢራ - ፊሊፕስ፣ …” የሚሉትን ማስታወቂያዎቸ ጓደኛዬ እያነበበ ችሎታውን ሲያረጋግጥልኝ በማየቴ ምንኛ እረካ ነበር፡፡ …” ብለው አስፍረዋል፡፡ ይህም አባባላቸው “አስተማሪው ካለ የፊደላችን ቁጥር መብዛት ለጥናት አያስቸግርም፡፡” የሚል ዓይነት መልእክት የሚያስተላልፍ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፣ በዚሁ ከላይ በተገለጸው መጽሐፋቸው እስከ ገጽ 10 ድረስ የኢትዮጵያ ፊደል ከ3000 ዓመታት የማያንስ ዕድሜ ያለውና በዓለም ላይ በቀደምትነት ከተፈለሰፉት ፊደላት መሐከል መሆኑን በመጥቀስ ያሞካሹታል፡፡ ታድያ! ይህን ያህል ያደነቁትንና ከኢትዮጵያም አልፈው አፍሪካዊ ፊደል ብለው ክብር የሰጡትን ፊደል በማሻሻል ስም እንዴት እንዳልነበረ ለማድረግ ቻሉ? ያሰኛል፡፡ በበኩሌ ከመጽሐፉ እንደተረዳሁት ከመንፈሳዊና ፖለቲካዊ አመላከት በመነጨ ሁኔታ በመነሳት ነባሩ ፊደል እንዲለወጥ ፈልገዋል፡፡ ምክንያቱም፤
1ኛ/ በቄስ ት/ቤቶች ፊደልን ለማስተማር በፊደል ገበታው ላይ ከተቀመጡ 8 ሰሌዳዎች መካከል በተለይ የመደበኛው ሆሄያትና የመልእክተ ዮሐንስ ሰሌዳዎች ስሜታቸውን እንደነኩት ነው፡፡ ይህንንም በመጽሐፋቸው ገፅ 24 ላይ “… በተረፈ የቀሩት 2 ሰሌዳዎች ገበታውን ከማጣበብ በስተቀር ለኢትዮጵያዊነት መገለጫ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የላቸውም…” በማለት መግለጻቸው
2ኛ/ ፊደሉ ሙሉ ለሙሉ መለወጥ እንዳለበት ምክንያታቸውን ሲያቀርቡ “… በአሁኑ ወቅት የአማርኛ ቋንቋ ከግእዝኛ እየራቀና ከፍተኛ ዕድገትም እያሳየ በመሔዱ፣ እንዲሁም ደግሞ በአገራችን በርካታ የብሔር ብሄረሰቦች ቋንቋዎች የሚገኙ በመኾኑ፣ ፊደሉ አሁን በሚገኝበት ደረጃ አዲስ የተከሰቱትን ሁኔታዎች አሟልቶ፣ የወቅቱን አማርኛና ብሔረሰቦችን ቋንቋዎች አጥጋቢ በሆነ መልክ ለመጻፍ የሚያስችል ሆኖ አይታይም፡፡ …” (ገጽ 19) ብለው የገለጹትን በማንበቤ ነው፡፡
 ዶ/ር ፍቅሬ ለፊደሉ ካላቸው ከበሬታ የተነሳ ከኢትዮጵያ አሳልፈው ለአፍሪካ እንዲሂበን ያልተመኙትን ያህል በማሻሻል ሰበብ ጭራሽ ሁሉም እንዲለወጡ ያደረጉት ሙከራ ትክክል አይደለም፡፡
 የኢትዮጵያ ፊደል ያልነው ግዕዝ ወይም ተረካቢው አማርኛ ለአንድ ብሔረሰብ መገልገያ እንዲሆን የተፈለሰፈ አይደለም፡፡ ምናልባትም የግዕዝ ነው፡፡  ያም የራሱ የኾነ ምክንያት ስለነበረው ዛሬ ላይ ሆነን የምናነሳው ሊሆን የሚችል አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ዶ/ር ፍቅሬ ያተኮሩበት አማርኛ ቋንቋ ዕድገት የፊደል ገበታውን ሙሉ በሙሉ ቀርቶ አንዷን ቅንጣት ሆሄም የሚያስቀይር አይደለም፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ሁሉም “የፊደል መሻሻል ወይም መለወጥ” ጥያቄ ሐሳብ አቅራቢዎች አማርኛ በሚለው ላይ ለምን ትኩረት እንዳደረጉ ከሚሰነዝሯቸው ምክንያቶች መረዳት ይቻላል፡፡
ለመኾኑ! አማርኛ የራሱ የሆነ ብቸኛ የፊደል ገበታ አለውን? “የይሻሻል ወይም የይለወጥ” ሐሳብ መቅረብ የሚገባውም ይህ ጥያቄ መልስ ሲያገኝ ብቻ ይመስለኛል፡፡ እናም በሚቀጥለው ሳምንት ይህን የተመለከተ ፅሁፌን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡   

Read 2456 times