Monday, 05 January 2015 08:17

አሸናፊው “ነቄዎቹ የስድስት ኪሎ ልጆች” ድርሰት ወይ አለማወቅ ደጉ! (Ignorance Is Blessed!)

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በዚህ “አሸናፊ” በተባለው ድርሰት መጨረሻ አካባቢ በተካተተው “የሞኝ አንግስ” ቤቶች ወሬ እኔንና አያሌ የጓደኞቼን ቤተሰቦች  እጅግ አሳዝኗል። ዕውነታን መሠረት ባደረገም ይሁን በልብ ወለድ ትረካ ውስጥ ለሚጠቀስ የግለሰብ ስም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ የግድ ነበር፣ ምክንያቱም ስሙ የጎደፈበት ግለሰብ ራሱን ይከላከል ዘንድ በሕይወት ስለማይኖር።

     ታህሳስ 4 ቀን 2007 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ “ነቄዎቹ የስድስት ኪሎ ልጆች” በሚል ርዕስ የተጻፈውን ድርሰት አነበብኩ። ይህ ድርሰት በድረ ገጽ በተደረገ ውድድር ያሸነፈና የአዳም ረታን “መረቅ” መጽሐፍ መሸለሙን አዲስ አድማስ እንደ መግቢያ ገልጾታል። እንደ ወትሮዬ የአዲስ አድማስ ጋዜጣን ሳገላብጥ ዓይኔን የሳበው ይህ ርዕስ ለማንኛውም ሰው አቅል ጎታች መሆኑ ግልጽ ነው። ከዚህም አንጻር ፍሰቱን ተከት የበአራድኛ ቋንቋ የተጠናቀሩትን አጫጭር ዓረፍተ ነገሮች በፈገግታ ረካሁባቸው። ደራሲው በሚመራኝ ሰፈሮች አብሬ በመጓዝ ላይ እያለሁ  አንድ የቅርብ ጓደኞቼን አባት ታሪክ እጅግ የሚያወርድ ትንታኔ ላይ ስደርስ  ግንባሬን አኮስኩሸ በትዕግስት ተከታተልኩት። በእርግጥ አዲስ አድማስ ይህን ጽሑፍ ላንባቢ ከማድረሱ በፊት መጠነኛ አርትዖት እንዳደረገበት ከጅምሩ ጠቁሞናል። አርትኦት ማለት የሰዋሰው፣ የቃላት አመራረጥ፣ ያገላለጽ ዘይቤ፣ ያጻጻፍ ሥነ-ምግባር፣ የታሪክ ወይም የሌላ ይሁን ግን ለእኔ ግልጽ አይደለም።
በዚህ “አሸናፊ” በተባለው ድርሰት መጨረሻ አካባቢ በተካተተው “የሞኝ አንግስ” ቤቶች ወሬ እኔንና አያሌ የጓደኞቼን ቤተሰቦች  እጅግ አሳዝኗል። ዕውነታን መሠረት ባደረገም ይሁን በልብ ወለድ ትረካ ውስጥ ለሚጠቀስ የግለሰብ ስም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ የግድ ነበር፣ ምክንያቱም ስሙ የጎደፈበት ግለሰብ ራሱን ይከላከል ዘንድ በሕይወት ስለማይኖር። የዚህ ስሙና ታሪኩ በጎደፈበት ሰው ልጆችና የልጅ ልጆች ላይም ብርቱ የሞራል መፋቅ ማስከተሉ አይቀርምና ድርሰቱ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ቀርቧል እላለሁ። በዚህ “በነቄ የስድስት ኪሎ” “የሞኝ አንግስ” ቤቶች ትረካ ከተካተቱት ወጎች አንዱ የጓደኞቼ አባት የነበሩት የአቶ አየለ ስብሐቱ ስም ነው። በተራኪው አቀራረብ ከተዘገበው የአየለ ስብሐቱ የትውልድ አገርና አስተዳደግ ሁኔታን አንብቤ የዕውቀት ማነስን ታዝቤያለሁ፣ እግረ መንገዴንም  የአቅም አድማሱን በስንዝር ለክቸዋለሁ። ያም ሆነ ይህ የማንኛውም ሰው ማንነት ከቤተሰቡ ይጀምራልና ለመጣጥፉ ባለቤትም ሆነ በዕለቱ የወጣውን የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላነበቡ ሁሉ የአየለ ስብሐትን እውነተኛ ታሪክና ተጋድሎ ማስተዋወቅ እሞክራለሁ።
የአየለ ስብሐት የትውልድ አገር ደራሲው እንደ ከተበው በሸዋ ክፍለሐገር በወይራ አምባ አይደለም። በቀድሞው የትግራይ ጠቅላይ ግዛት በአጋመ አውራጃ፣ በስሩክሶ ወረዳ ዓድ ዒሮብ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በዳልጌዳ መንደር ነው። (ወጣቱ ደራሲ ተከተለኝ)፦  ለትምህርት ካላቸው ከፍተኛ ፍቅርም በራሳቸው አነሳሽነት አሊቴና በሚገኘው የካቶሊክ ትምሕርት ቤት ነበር የገቡ። በአሊቴና የካቶሊክ ትምሕርት ቤት የሚሰጠውን ትምሕርት ካገባደዱ በኋላም አዲስ አበባ በሚገኘው የአላያንስ ፍራንሲ ትምህርት ቤት ቀጥለዋል።
የፈረንሳይኛ ቋንቋ ዕውቀታቸውን የተገነዘቡት ልጅ እያሱ፤ ትምሕርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከእርሳቸው ጋር ይሠሩ ዘንድ ሐሳብ አቅርበውላቸው ነበር። አቶ አየለ ግን ለትምሕርት ካላቸው ብርቱ ፍቅርና የውጭውን ዓለም ዕውቀት ለመቅሰም ከነበራቸው ጉጉት የተነሳ የልጅ እያሱን ሐሳብ አልተቀበሉም። ከዚህም አንጻር በራሳቸው ወጭ በባቡር ወደ ጅቡቲ ተጉዘው፣ በመርከብ ወደ አሌክሳንደሪያ ግብጽ ቀጠሉ። እንደ ገና  ወደ ፈረንሳይ ተሳፍረውም መጀመሪያ ማርሴይ ከዚያም ወደ ፓሪስ ሔደው በታዋቂው የሰርቦን ዩንቨርሲቲ የሕግ ትምሕርት ተከታትለዋል። እኒህ የሕግ ምሑር “ጃን ሜዳን ሽጠዋል” ብሎ የሚያስብ  የእኒህን ሰው የሕግ ዕውቀት ያላገናዘበ ሰው ብቻ ነው።
በዚያን ወቅት አልጋ ወራሽ የነበሩት ተፈሪ መኮንን ፈረንሳይን በጎበኙበት ወቅት በክብር ካስተናገዷቸው ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች መካከል አየለ ስብሐት አንዱ ነበሩ። የኢትዮጵያ ኤምባሲ በፈረንሳይ ይቋቋም ዘንድ አንጋፋውን ሚና የተጫወቱ ብቻም ሳይሆን የመጀመሪያውን የኢትዮጵያዊያን ማሕበር “የኢትዮጵያ ልጅ”ን ከመሠረቱት አንዱና በፕሬዚደንትነትም የመሩ ሳተና ምሑርና አገር ወዳድ ሰው ነበሩ። ብዙ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ትምሕርታቸውን በፈረንሳይ አገር ይከታተሉ ዘንድ ከፍተኛ ጥረትም አድርገዋል ( እነ አክሊሉ ሐብተወልድን የመሳሰሉ)። ትምሕርታቸውን ለመከታተል የገንዘብ እጥረት ለነበራቸው ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎችም ለአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን በማመልከት በጀት ያስፈቀዱ አርቆ አሳቢ ሰው ነበሩ።
በ1928 ዓ.ም አጼ ኃይለሥላሴ በዙፋን ላይ እንደ ተቀመጡ ለዘመናዊ ሥልጣኔና ለሥርዓት መሻሻል በር ይከፍታሉ የሚል ዕምነት ካሳደሩ ወጣት ምሑራን መካከል አየለ ስብሐት አንዱ ናቸው። ከዚህም አንጻር ከእነ ሎሬንሶ ትዕዛዝና ከሐኪም ወርቅነህ ጋር ወደ አገራቸው ተመለሱ።( ዝክረ ነገር ገጽ 606፣ ተራ ቁጥር 85 ይመለከቱ) ። ከተመለሱ በኋላም በአገር ግዛት ሚንስትር በዳሬክተርነት አገልግለዋል። ብዙ ሳይቆይ ፋሽስቱ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በመውረሩ  ሥርዓተ- አገር ፈረሰ። በዚህ የጭንቅ ዘመን ባሕሉንና ቋንቋውን ወደ ተላመዱት ፈረንሳይ አልሸሹም። ወደ አገራቸው ወደ ዓዲ ዒሮብ በመዝመት አሲምባ በረሓ መሽገው ከነበሩ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ጋር በመሰለፍ አምስቱን የጠላት ወረራ ዓመታት በጽንዓት በመታገል አሳለፉ እንጅ።
ከነፃነት በኋላም አገራቸዉን በቅንነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ወደ ኋላ ግን ከመሳፍንቱ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በፈቃዳቸው ራሳቸውን ከሥልጣን አግልለዋል። ይህ ውሳኔያቸው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በማስከፋቱ፣ በግዞት እንዲቆዩና በግል ሥራም እንዳይተዳደሩ ማዕቀብ ተጥሎባቸው ነበር። አዝማች አየለ ስብሐት (በአርበኝነት ዘመን ያስተባበሩት ያርበኛው ሕብረተሰብ  እንደሚጠሯቸው) ከላይ በተጠቀሰው ቅጣት አኩርፈው አገራቸውን በመጥላት መሰደድን አልመረጡም።“የአሸናፊው” ድርሰት ባለቤት አዲስ ዓለማየሁ እንዳቀረበው፤ አየለ ስብሐት  “አጥንተ ድሕነቱ የከበደውና የለበሰውን ቡትቶ አሽንቀጥሮ የጣለ” ሳይሆኑ በግል ጥረታቸው ወደ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ልጅና ምርጥ ምሑር ነበሩ። እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህልም፣ “የስድስት ኪሎ ነቄዎች” ድርሰት ጸሐፊን የስም ሞክሸነት የሚጋሩትና በዘመኑ የኢኮኖሚና የልማት ሚንስትር የነበሩ ታዋቂው ደራሲና አርበኛ ሐዲስ ዓለማየሁ ላንድ ወዳጃቸው የጋብቻ ሽምግልና ወደ አቶ አየለ ቤት በሔዱበት ወቅት “ እነ አቶ አየለ ስብሐት ከፈረንሳይ ሲመለሱ እኛ ገና ወጣቶች ነበርን። የአቶ አየለን አለባበስ፣ ቁመናና አንደበተ ርቱዕነት ለመታዘብ እጅግ እንጓጓ ነበር” ማለታቸውን በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ያወጉ ነበር። በኒህ ታላቅ ሰው የቀብር ስነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው የሕይወት ታሪካቸዉን ያነበቡት ቢትወደድ አስፍሐ ወልደሚካኤልም  ትዝታቸውን ወደ ኋላ በማጠንጠን “ አቶ አየለ ስብሐት ጎፈሬያቸውን አበጥረው፣ ዝናራቸውን ታጥቀውና ጠበንጃቸውን አንግበው ከአሲምባ በረሓ በወጡበት ወቅት የተቆጣ አንበሳ ይመስሉ ነበር” ሲሉ ገልጸውታል። አቶ አየለ ስብሐት ልጆቻቸውንና አያሌ የቅርብ ቤተሰብ አባላት ልጆችን አስተምረው ለቁም ነገር ያበቁ ታላቅ ሰው ስለነበሩም በብዙ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ በጎ ሰው ነበሩ።
በአርበኝነት ዘመን ያልተለዩአቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ ከፈይ ዘውገ ለረጅም ግዜ በፈረንሳይ አገር የኖሩና የአጼ ምንይልክ የመሣሪያ አቅራቢ የነበሩት የአንኮበሬው የነጋድራስ ዘውገ ኃይሉ ልጅ ናቸው። አዲስ ዓለማየሁ “ከሞኝ አንግስ ቤቶች” በወረሰው ትረካ የአቶ ስብሐቱን ትውልድ ከአዲ ኢሮብ  ወደ ወይራ አምባ ያጓጓዘውም ከዚህ ውዥንብር የተነሳ ይመስለኛል። አየለ ስብሐት “አጥነተ ድሕነቱ የከበደው” ሳይሆኑ ወደ አገራቸው ከመመለሳቸው በፊት  በሊግ ኦፍ ኔሽን የምሥረታ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ልኡክ (ዴሊጌት) ከነበሩት ሶስት ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ። በዚህ የምሥረታ ጉባኤ ላይ ከኢጣሊያዊው ወኪል የቀረበው የተቃውሞ ሙግት ቀላል አልነበረም። ኢጣሊያዊው ደሊጌት “ በኢትዮጵያ ውስጥ ባርያ ይሸጣልና ከዚህ የሰለጠነ ማሕበረሰብ ማሕበር በአባልነት ሊካተቱ አይገባቸውም” የሚል የመከራከሪያ ነጥብ አንስቶ ነበር። አቶ አየለ ይህን የተቃውሞ ሓሳብ ውድቅ ለማድረግ የወሰዱት እርምጃ ነፃ የወጡ ባርያዎች ስም ዝርዝር ይላክላቸው ዘንድ በወቅቱ አልጋ ወራሽ ለነበሩት ለተፈሪ መኮንን አስቸኳይ መልዕክት እንዲደርሳቸው ማድረግ ነበር። ይህ በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን የተላከ ነፃ የወጡ የባርያዎች የሥም ዝርዝር እንደ መረጃ መቅረቡን ታሪክ ይዘግባል። በSept 10- Oct 4 1930 በተካሓደው “The eleventh section of the Assembly “ የተካፈሉ የደሊጌት አባላት  አየለ ስብሐት፣ ነጋድራስ መኮንንና Leone Legard (ሊየን ለጋህድ) እንደ ነበሩ ዶሴዎች ይጠቁማሉ።የዚህ መጣጥፍ ዋና ዓላማ በማንኛውም  ድርሰት ውስጥ በስም በሚጠቀሱ  ግለሰቦች ታሪክ ላይ የሚለጠፉ ባሕሪያት ከሥነ-ጽሑፋዊ ሥነ-ምግባርና ከትዝብት አንጻር ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ማሳሰብ ነው። በየጠጅ ቤቱና “ሞኝ አንግስ” ቤቶች ከሰዓት በኋላ የሚነሱ ወጎችን እንደ ዋቤ ማቅረብም አግባብ አይመስለኝም። ድርሰትን እንዳሻው ሰነቃቅሮ ምርጥና ተነባቢ ማድረግ ይቻላል፣ የግለሰቦችንና የቤተሰባቸውን ስም በጭቃ ለውሶ የድርሰቱ መዋቢያ ማድረግ ግን ዕውቀትን ማዕከል ያላደረገ ድፍረት ነው። ለዚህም ነው አሜሪካዊያን “Ignorance Is Blessed” የሚሉት።
ዋቢ መረጃዎች፡(*LeagueNationsPhotoArchive.  www.indianaedu~legue/11thordinaryasembely.httm)
*ወመዘክር ገጽ 606 ተራ ቁጥር 85 (ከ1928 ዓ.ም በፊት ተምረው ወደ አገራቸው የተመለሱ ሰዎች ሥም ዝርዝር)
አስማማው ኃይሉ

Read 3629 times