Saturday, 31 January 2015 12:41

የአንድነት አባላት በፀጥታ ሃይሎች ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ተናገሩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

“ተመጣጣኝ እርምጃ ነው የተወሰደው” - የአ.አ ፖሊስ ኮሚሽን

  የከተማ አስተዳደሩ እውቅና ሣይሰጠው ሊካሄድ ተሞክሯል በተባለው የባለፈው እሁድ የአንድነት ፓርቲ ሠላማዊ ሠልፍ ላይ ፖሊስ በወሰደው የሃይል እርምጃ በርካታ ሠልፈኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው ፓርቲው አስታውቋል፡
ፓርቲው ሰሞኑን “ሠላማዊ ትግሉን በጭፍጨፋና በውንብድና ለማቆም መሞከር ሃላፊነት የጐደለው ተግባር ነው” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፣ “በእሁዱ ሠልፍ በፀጥታ ሃይሎች የተፈፀመው አሠቃቂ ድብደባ ወደር የማይገኝለት ነው” ብሏል፡፡ በድብደባው የፓርቲው አባላት የአጥንት መሠበርን ጨምሮ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውና በየሆስፒታሉ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን የፓርቲው አመራሮች ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የፀጥታ ሃይሎች ፈፅመውታል በተባለው ድብደባ የፓርቲው የኤዲቶሪያል አባልና “የሚሊዮኖች ድምፅ” ጋዜጣ አዘጋጅ ስለሺ ሃጐስ በድብደባው በደረሠበት ከፍተኛ ጉዳት ለሰአታት ራሱን ከመሣቱም በላይ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ ላይ ጉዳት ደርሶበት በህክምና ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡ የጋዜጠኛ ስለሺ የግራ እጅ አጥንትም መሠበሩ በህክምና መረጋገጡን የፓርቲው አመራሮች ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው የፓርቲው አባላትም ጉዳት የደረሰበትን የሰውነት ክፍላቸውን ለጋዜጠኞች አሳይተዋል፡፡ የፓርቲው የብሔራዊ ም/ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ፀጋዬ አላምረው፤ በእለቱ ፖሊስ በአራት አቅጣጫዎች እንደመጣባቸውና፣ ሲቪል የለበሱ የደህንነት ሃይሎችም በስፍራው እንደነበሩ አስረድተው፣ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ፋታ ሣይሰጡ ሰዎችን እየመረጡ መደብደብ ጀመሩ ይላሉ፡፡ “ፖሊሶች ሲደበድቡም ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የአካል ክፍል ሣይመርጡ” ነው የሚሉት አቶ ፀጋዬ፤ ጭንቅላቴ እንዳይመታ ጥረት ባደርግም እግሬና ጀርባዬ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኛል ብለዋል።
አንድነት ፓርቲ ሲመሠረት ጀምሮ በፓርቲው የተለያዩ ሃላፊነቶች ላይ ስታገለግል መቆየቷን የገለፀችው ወ/ት ልዕልና ጉግሣ በበኩሏ፤ በድብደባ የበለዘ የአካል ክፍሏን ለጋዜጠኞች ያሳየች ሲሆን በሆዷ፣ በትከሻዋና በእግር ጡንቻዎቿ ላይ የድብደባ ምልክቶችን ለመታዘብ ተችሏል፡፡ “በጣም ያጠኑኝ በሚመስል መልኩ ነው ተረባርበው የደበደቡኝ” የምትለው ተጐጂዋ፤ “የአለም ህዝብ በሀገሪቱ ያለው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የደረሰበትን ደረጃ እንዲታዘብ እፈልጋለሁ፡፡” ብላለች፡፡
የፀጥታ ሃይሎቹ ሆዴን ሲመቱኝ እንዲተውኝ ለምኛቸዋለሁ ያለችው ወ/ት ልዕልና፤ “አቅሌን ስቼ ከወደቅሁ በኋላ መሬት ላይ ጐትተው ወደ አንድ ጥግ አስቀምጠውኝ ሄደዋል” ስትል አማራለች፡፡ ሞባይሏን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶቿን የያዘው የእጅ ቦርሣዋ መነጠቁንም አክላ ገልፃለች፡፡
ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው የፓርቲው አባላትም የቆሠለ አካላቸውን ለጋዜጠኞች በማሳየት የጉዳታቸውን መጠን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ድብደባው ፓርቲው በሚያዘጋጃቸው ቀጣይ ሠልፎች ላይ ከፊት ተሠልፈው ድምፃቸውን ከማሰማት እንደማይገድባቸው ተጐጂዎቹ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አስራት በበኩላቸው፤ በድብደባው ከፍተኛ የአካል ጉዳት በትከሻቸውና በጀርባቸው እንዲሁም በእግራቸው ላይ መድረሱን አመልክተው ድብደባውን ሲፈፅምባቸው የነበረው ፖሊስ በቴሌቪዥን ተደበደብኩ ብሎ መግለጫ ሲሰጥ መመልከታቸው አግራሞትን እንደፈጠረባቸው ጠቁመው፤ የፓርቲው አባላት ተቃውሟቸውን በሠላማዊ መንገድ ከማካሄድ ውጭ ጠቁመው፤ በፀጥታ አካላቱ ላይ ድብደባ አለመፈፀሙን አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ፤ ሠልፈኞቹ ያልተፈቀደ ሠልፍ እያደረጉ በመሆኑ በተደጋጋሚ እንዲያቆሙ በፀጥታ ሃይሎች የተነገራቸውን ማሳሰቢያ ቸል ብለው የፀጥታ ሃይሎችን ጥሰው ለመውጣት ባደረጉት ህገወጥ እንቅስቃሴ ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡ ሠልፈኞቹ ከፖሊሶች ጋር በፈጠሩት ግብግብም ሁለት የፀጥታ ሃይሎች ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ተገልጿል፡፡
ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የሠላማዊ ሠልፍ ጉዳይ የአዲስ አበባ አስተዳደርና ፓርቲዎችን እንዲሁም የፀጥታ ሃይሉን እያወዛገበ ሲሆን በየጊዜው የሚካሄዱት ሠልፎች ገደብ ሊኖራቸው እንደሚገባም ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሣለኝ መግለፃቸው ይታወሣል፡፡ በግንቦት የሚካሄደውን ብሔራዊ ምርጫም የሚያውኩ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች በገደብ የለሽ ትዕግስት እንደማይታለፉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡
በሀገሪቱ ያለው የመሰብሰብና ሠላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ነው የሚሉት የመድረክ አመራርና የፖለቲካል ሣይንስ ምሁሩ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ የመናገር፣ የመፃፍ፣ ሠላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብቶች በህገ መንግስቱ ነፃ ሆነው የተደነገጉ እንደሆኑ ጠቁመው መንግስት በአሠራር ደረጃ የተደነገጉትን ህጐች ይጥሣል ብለዋል፡፡ “ህጉና አሠራሩ እየተጋጩ ነው” የሚሉት ምሁሩ፤ “ማሣወቅ” የሚለው የህጉ ድንጋጌ በአሠራር ሌላ ትርጉም እየተሰጠው ነው ሲሉም ተችተዋል፡፡
“መንግስት ህገ መንግስቱን ማስከበር ሲገባው አሁን ተቃዋሚዎች ናቸው ህገመንግስቱን ለማስከበር እየጣሩ ያሉት” ብለዋል - ዶ/ር መረራ፡፡ ሌሎች ሃገሮች ሠልፍ አይከለክሉም፤ ሠልፈኞች ንብረት ሊያወድሙ ወይም ጥቃት ሊፈጽሙ ሲያቅዱ ብቻ ነው ወደ መበተን የሚኬደው የሚሉት ምሁሩ፤ ወደ ሌላ አቅጣጫ ያመራ ሠልፍ የሚበተነውም በዱላ ሳይሆን አስለቃሽ ጭስ፣ ውሃና የመሳሰሉትን በመጠቀም ነው ብለዋል፡
አለማቀፍ የህግ ምሁሩ ዶ/ር ያዕቆብ ሃይለማርያም በበኩላቸው፤ ሠላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብትን መከልከል አለማቀፍ ህጐችን መፃረር ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ሠላማዊ ሠልፎች በተደረጉ ቁጥር ሠዎች መታሠራቸውና መደብደባቸው እነዚህን አለማቀፍ ህጐች የሚፃረር ነው ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤ ሰዎች የጦር መሣሪያ ሣይዙ የተሠማቸውን ቅሬታ የመግለፅ ሰብአዊ መብት አላቸው” ብለዋል፡፡
በቅርቡ በአንድነት አባላት ላይ ተፈጽሟል የተባለው ድብደባ በህግ ከተረጋገጠ፣ ድርጊቱን የፈፀሙትም ሆኑ እንዲፈፀም ትዕዛዝ የሰጡት አካላት በህግ ያስጠይቃቸዋል ብለዋል ዶ/ር ያዕቆብ፡፡  


Read 2902 times