Saturday, 07 February 2015 12:31

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር፤ በፓርቲዎች ክፍፍልና በፖለቲካ ውዝግቦች ዙሪያ

Written by 
Rate this item
(12 votes)

ውህደት ለመፈፀም ተደጋጋሚ ድርድሮችን ሲያካሂዱና ስምምነት ሲፈፀሙ የቆዩት አንድነት ፓርቲ እና መኢአድ፣ የውህደት ጅምራቸው ካለመሳካቱም በተጨማሪ በየፊናቸው ለሁለት ለሁለት ተከፍለው ሲወዛገቡ ነው የከረሙት፡፡ በመጨረሻም የምርጫ ቦርድ፣ ከመኢአድ ፓርቲ በአቶ አበባው መሃሪ ለሚመራ ቡድን፣ ከአንድነት ፓርቲ ደግሞ በአቶ ትዕግስቱ አወሉ ለሚመራው ቡድን እውቅና ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡ እውቅና ያልተሰጠው በአቶ በላይ የሚመራው የአንድነት ቡድን ብዙም ሳይቆይ፣ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ተቀላቅሏል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ መሪዎች ቀደም ሲል አንድነት ፓርቲ ውስጥ እንደነበሩና በክፍፍል ምክንያት ወጥተው ፓርቲ እንዳቋቋሙ የሚታወስ ሲሆን የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤ በፓርቲዎች ክፍፍል እና በወቅታዊ የፖለቲካ ውዝግቦች ዙሪያ ለጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ የሰጡትን አስተያየት አቅርበናል፡፡

የምርጫ ሰሞን የፓርቲዎች ክፍፍል
በየምርጫው የፓርቲዎች ግጭትና ክፍፍል የተለመደ ቢሆንም የዘንድሮው ይለያል፡፡ በመንግስት አቋም ተወስዶበት የተሰራ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ በራሱ ስራና ብቃት መመረጥ እንደማይችል አውቋል፡፡ ስለዚህ ህዝቡን አማራጭ ማሳጣት ይፈልጋል፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ ጥቃቅን ስህተቶችን በማጉላት እንዲሁም ሬዲዮ ፋናን፣ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንንና ምርጫ ቦርድን  በመጠቀም፣  “የተቃውሞው ጎራ እርባና ቢስ ነው፤ ብትወደኝም ባትወደኝም ከእኔ ጋር ትኖራለህ” በሚል ህዝቡ ላይ ጫና ለማሳደር የመጫን ስራ ሆን ብሎ እየሰራ ይገኛል፡፡ ለዚህም  ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአንድነት ላይ የወሰደውን ውሳኔና የሰጠውን መግለጫ ማየት ይቻል፡፡ “የእነ ትዕግስቱ ቡድን ለእኛ ስለሚታዘዝና በእኛ ሃሳብ ስለሚስማማ እንጂ የራሱ ድክመት አለበት” በማለት አንድነትን ለእነሱ አፅድቆላቸዋል፡፡ ሌላው በእኛ በሰማያዊ ፓርቲ ላይ ቦርዱ
የጀመረው ዘመቻ ነው፡፡ ይቅርታ እንድንጠይቅ ደብዳቤ ፅፎብን ነበር፡፡ እንደ ጥፋት ያቀረባቸው
ነገሮች ግን እዚህ ግባ የማይባሉና ጥፋት ያልሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ትብብር ለምን ሰራችሁ፣ ያልተመቸንን ስብሰባ ትተን መውጣት መብራታችን ሆኖ ሳለ እንዴት ረግጣችሁ ትወጣላችሁ በሚል ነው የመጨረሻ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ  የፃፈልን፡፡ ሬዲዮ ፋናንና ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ብንመለከት፣ እንደሌሎቹ ፓርቲዎች እኛ ላይ ፕሮፓጋንዳ ለመስራት ጠሩኝ፡፡ አክብሬ ሄድኩኝ፤ እዚያው ሬዲዮ ፋና ስቱዲዮ ውስጥ ለሁለት ሰዓት ከተቀረፅኩኝ በኋላ መጨረሻ ላይ ፊልሙ ተበላሽቷል አይተላለፍም አሉኝ፡፡ እኛ የቀረፅነው ስላለ እንስጣችሁ አልናቸው፤ አልፈለጉም፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተመሳሳይ ጥያቄ ይዞ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታንን ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል አነጋገራቸው፤ ግን በቴሌቪዥን አልተሰራጨም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ለእነሱ ፕሮፓጋንዳ የሚመች መልስ ስላልሰጠን ነው፡፡ ይህን ሁሉ ስመለከተው መንግስት ሆን ብሎ ፓርቲዎችን ጥላሸት ለመቀባት ለህዝብ ለማሳየት እየተደረገ ያለ ጥረት መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡“አንድነት” ለሁለት ስለመሰንጠቁእኔ በበኩሌ አንድነት ለሁለት ተሰነጠቀ ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ምክንያቱም ቅር ተሰኘን የሚሉ ጥቂት ሰዎች ሄደው ለምርጫ ቦርድ ቅሬታ አቀረቡ፡፡ ከስራ አስፈፃሚው እስከ ታች ያለው የፓርቲው መዋቅር ግን በእነ አቶ በላይ ፍቃዱ የሚመራ ነው፡፡ የፓርቲው የብሔራዊ ም/ቤት አፈጉባኤ፣
ምክትል አፈጉባኤ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች ኃላፊ…  ከእኛ ጋር ቀላቀሉት ናቸው፡፡ ሌላው አንድነት የት አለ? ከእኛ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፓርቲው ትልቁን የኃላፊነት ቦታ የያዙት ስለሆኑ እኔ አንድነት ተሰነጠቀ አልልም፤ ከኛ ጋር ተዋሃደ እንጂ አልተሰነጠቀም፡፡ በአሁኑ ሰዓት እዚህ እየመጡ እየተመዘገቡ ነው በክልልም ለምርጫው እጩ እስከማቅረብ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን ከእኛ ጋር የተቀላቀሉትን ብዛት በቁጥር ለመግለፅ እቸገራለሁ፡፡ በአጠቃላይ በአቶ በላይ ፈቃዱ ሲመሩ የነበሩት እውነተኛዎቹ የአንድነት አባላት ከነመዋቅራቸው ወደ እኛ መጥተዋል፡፡ “አንድነት ሰማያዊ ሴራ ፈረሰ” ስለመባሉበብዕር ስም ተፅፎ የወጣው፤ ዘገባ ሃሰት ነው፡፡ ምክንያቱም በእስር ላይ ያሉትን እነ ሃብታሙ አያሌውን ሁልጊዜ እናገኛቸዋለን፡፡ እንደውም ወደፊት አብረን ስለምንሰራበት ሁኔታ በየጊዜው እንወያያለን፡፡ ከሃብታሙም ሆነ ከየሺዋስ ጋር ጓደኛሞች ነን፡፡ የአንድነት ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ወደ ሰማያዊ ፓርቲ በመግባታቸው ኢህአዴግ በደረሰበት ድንጋጤ ሆን ብሎ የሚያስወራው ነው፡፡ እዚያ ዘገባ ላይ ከተፃፈው አንድ ምሳሌ ልንገርሽ፡፡ በበላይ ፍቃዱ የሚመራው ቡድን በዶ/ር ያዕቆብ ሸምጋይነት ከሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ጋር በተናጠል ሲደራደር ቆይቷል ተብሎ ተፅፏል፡፡ ይሄ አይን ያወጣ ውሸት ነው፡፡ እኔና በላይ ፍቃዱ ከጓደኝነታችን የተነሳ ለመገናኘት ሽማግሌ
አያስፈልገንም፤ ሁልጊዜም ቢሆን እየተገናኘን በአገራችን ወቅታዊ በጎና መጥፎ ጉዳዮች ላይ ሌት
ተቀን የምንነጋገር የምንከራከር ነን፡፡ እኔና ዶ/ር ያዕቆብ አንድ ላይ ሆነን ሻይ ጠጥተን እንደማናውቅ ላረጋግጥልሽ እወዳለሁ፡፡ ይሄ ሁሉ የሚመራብን ወሬ  የኢህአዴግን ድንጋጤ የሚያሳይ ነው፡፡
እንደ ክፍፍሉ ውህደቱ መፍጠኑአሁን ጥቃቅንና አነስተኛ የፕሮግራም ልዩነቶችን እያነሳን ጊዜ የምናባክንበት ወቅት ላይ አይደለንም፡፡ በመሰረቱ አንድነትና ሰማያዊ በአብዛኛው ፕሮግራሞቻቸው ላይ ልዩነት የላቸውም፡፡ ስለዚህ ዋና ዋናዎቹ ላይ ከተስማማን በጥቂትና ጥቃቅን የፕሮግራም ልዩነቶች ላይ በሂደት በውይይትና በክርክር የምንስማማባቸው ይሆናሉ፡፡ አብረን ለመስራት የሚከለክሉን ስላልሆኑ ይሄ
አያስጨንቀንም፤ በአሁኑ ሰዓት እንደ ቁምነገር የምናነሳው አይደለም፡፡ የአንድነት አባላት በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ የሚኖራቸው የአመራር ቦታቀደም ብዬ እንደተናገርኩት ወደኛ የመጡት የአንድነት ሰዎች በትልልቅ የአመራር ቦታ ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ በፓርቲው ስልጣንና ሹመት ውስጥ ብቻ ሳይሆን አሁን አዲስ አበባ ላይ በምናቀርባቸው እጩዎች ላይ ጥሩ ጥሩ ተፎካካሪዎችን ማቅረብ ይችላሉ፡፡ የመመረጥ መብታቸው እስከ ከፍተኛ አመራር ድረስ ክፍት ስለሆነ መብታቸው ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በተደጋጋሚ ተነጋግረንበታል፡፡ አሁን ከተቀላቀሉን ውስጥ ብዙዎቹ ጥሩ ጥሩ የአመራር ብቃት ያላቸው ስለሆኑ ለፓርቲያችን ያስፈልጉናል፡፡ በፓርቲው ወሳኝ ወሳኝ ቦታ ላይ ገብተው የመስራት መብት አላቸው፡፡ በቀሪው አንድ ሳምንት ውስጥ በእጩነት እንዲገቡም እናደርጋለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁሌም “ፓርቲዎች ትከፋፈላላችሁ፤ አትግባቡም” እንባለለን፡፡ ይሄ ቁጭት በውስጣችን እያለና ገዢው ፓርቲ ሆን ብሎ “ተጣልተዋል፤ ተከፋፍለዋል” የሚለውን ስራዬ ብሎ በተቆጣጠራቸው ሚዲያዎች እያናፈሰ ባለበት አስቸጋሪ ሰዓት ፓርቲያችንን የሚያግዝና የሚያጎለብተን ኃይል ሲመጣ እንዴት አንደሰትም፡፡ ከዛ በተረፈ በሁለቱም ፓርቲዎች በኩል ያለን ሰዎች የምንተዋወቅና የምንግባባ ስለነበርን እንደ አዲስ አንተያይም፤ አብረን ለመስራት ሁሉንም ነገር ያቀልልናል፡፡ለምርጫ ስላቀረቧቸው እጩዎች ብዛት እስካሁን ፓርቲያችን በአገር አቀፍ ደረጃ ወደ 400 የሚጠጉ እጩዎችን አስመዝግበናል፡፡ አሁን ደግሞ እጩ የማስመዝገቡ ሂደት ለአንድ ሳምንት ተራዝሟል፡፡ በዚህ በቀረን አንድ ሳምንት አዲስ ከተቀላቀሉን ሰዎች ውስጥ የምናስመዘግባቸው ይኖራሉ፡፡ በአጠቃላይ የእጩዎቻችን ቁጥር ወደ 500 ከፍ ሳይል እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡ መጀመሪያ ላይ ልናስመዘግብ ያቀድነው የእጩዎች ብዛት 300 ነበር፡፡ በምርጫ ዘመቻ የፓርቲዎች ስህተትና ትኩረትምርጫው እየቀረበ እንደመሆኑ መጠን በውስብስብና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ በትናንሽ ጉዳዮችና በእርስ በርስ ፉክክር ላይ ከማተኮር ይልቅ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ትልቁን የአገራቸውን ምስል እንዲያዩ እመክራለሁ፡፡ ልዩነትም ቅራኔም ቢኖር መቻቻልና ቅራኔን በጥበብ
በመያዝ ለውጤት ወደሚያበቃ ትግል ተጠናክረን መግባት አለብን፡፡ ዛሬ የምንሰራው ስህተት ልብ ሰብርና ህዝቡን ተስፋ የሚያሳጣ እንዳይሆን በመጠንቀቅ በጥበብ መጓዝና ለምንታገልለት ህዝብ የተስፋ ብርሃን መፈንጠቅ ይኖርብናል፡፡ ፓርቲዎች የገዢውን ፓርቲ ከፋፋይ ሴራ በማወቅ፣ ከፍተኛ
ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡

Read 5197 times