Saturday, 14 February 2015 13:10

የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከዶ/ር ቴዎድሮስ ጋር ተወያዩ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ሩስያ ለግብጽ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ልትገነባ ነው

     የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሹክሪ፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያው አቻቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር ትላንትና በአዲስ አበባ የሁለትዮሽ ውይይት አደረጉ፡፡ በውይይቱ ላይ የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር እንደተገኙም ታውቋል፡፡ ሁለቱ ሚንስትሮች በአገራቱ መካከል የተጀመሩ የሁለትዮሽ ግንኙነት ውይይቶችን እንደሚቀጥሉ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ባድር አብደል አቲ ገልጸዋል፡፡በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ፤ በሰሜናዊ ሲና አካባቢ ታጣቂዎች ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ጋር ሊያደርጉት የነበረውን ውይይት ሰርዘው ወደአገራቸው መመለሳቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ የኢትዮጵያው አቻቸው ያደረጉላቸውን ግብዣ በመቀበል ውይይቱን ለመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ጠቁሟል፡፡በሌላ በኩል ሩስያ፤ ለግብጽ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ልትገነባ እንደሆነ የሁለቱ አገራት መሪዎች ባለፈው ማክሰኞ በካይሮ በሰጡት የጋራ መግለጫ እንዳስታወቁ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ከግብጹ አቻቸው አብደል ፋታህ አል ሲሲ ጋር የሃይል ማመንጫ
ግንባታ ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ስምምነቱ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሚደረስበት ከሆነ፣ ጉዳዩ የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ ግንባታ ብቻ ሳይሆን በግብጽ አዲስ የአቶሚክ ኢንዱስትሪ ጅማሬ ይሆናል ብለዋል፡፡ግብጽ ከዚህ በፊት ባቋቋመችውና ከአሌክሳንድሪያ የወደብ ከተማ ምዕራባዊ የሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ ላይ በምትገኘው ዳባ ከተማ ውስጥ ባለው የኒውክሌር ምርምር ጣቢያ ላይ የሚገነባው ይህ የሃይል ማመንጫ፣ እያንዳንዳቸው 1ሺህ 200 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው አራት ማብላያዎች እንደሚኖሩት ተገልጿል፡፡ግንባታው በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት እየተስፋፋ ላለባት ግብጽ ሁነኛ መፍትሄ ይሆናል ተብሏል፡፡ የግብጹ አሽራቅ አል አውሳት ድረገጽ በበኩሉ፤ ምንም እንኳን የአገራቱ መሪዎች በይፋ ባያረጋግጡትም፣ አገራቱ ከሃይል ማመንጫ ግንባታው በተጨማሪ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት ፈጽመዋል ሲል ኢንትራ ፋክስ የዜና ተቋምን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

Read 4270 times