Saturday, 14 February 2015 13:12

በጫትና ሺሻ ላይ ገደብ የሚጥል አዲስ ህግ ሊወጣ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(12 votes)

አምና ከጫት  ኤክስፖርት ከ5 ቢ. ብር በላይ ተገኝቷል

    በጫትና ሺሻ አመራረት፣ ንግድና አጠቃቀም ላይ የሚያተኩር አዲስ ህግ ሊወጣ ሲሆን ፍትህ ሚኒስቴር ጫትና ሺሻን አስመልክቶ ያዘጋጀውን ረቂቅ ህግ የዓለም ጤና ድርጅትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እንዲወያዩበት ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጿ፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ ሰሞኑን በሒልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ጫት በዜጎች ላይ እያስከተለ ያለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችልና በጫትና ሺሻ አመራረት፣ ንግድና አጠቃቀም ላይ ገደቦችን የሚጥል አዲስ ረቂቅ ህግ ወጥቷል፡፡ በፍትህ ሚኒስቴር የተዘጋጀው ይኸው ረቂቅ ህግ፤ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚካሄደው አገር አቀፍ ሲምፖዚየም ላይ ለውይይት ቀርቦ ማስተካከያዎች ከተደረጉበት በኋላ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ በቅርቡ ይካሄዳል በተባለው አገር አቀፍ የጫት ሲምፖዚየም ላይ ታላላቅ የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚገኙና ጫት በዜጐች ላይ እያስከተለ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አስመልክቶ በምሁራን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚቀርቡ ዶ/ር ከሰተብርሃን ጨምረው ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአውሮፓና አሜሪካ ያላት የጫት ሽያጭ በእጅጉ በመቀዛቀዙ ምርቶቿን በአብዛኛው የምትልከው ለየመን፣ ሶማሊያና አረብ አገራት ሲሆን ባለፈው ዓመት ጫት ከአገሪቱ የኤክስፖርት ምርቶች በአራተኛነት ደረጃ ላይ ሆኖ፣ 270 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቶበታል፡፡  


Read 6359 times