Saturday, 14 February 2015 13:37

Infection… የሰውነት የመከላከል አቅም እና በሽታ አምጪ ሕዋሳት ውጊያ ውጤት...

Written by 
Rate this item
(25 votes)

“...ትዳር ከያዝኩኝ ከአስራ ሁለት አመት በሁዋላ ነበር ያረገዝኩት፡፡ እርግዝናው ከመከሰቱ

አስቀድሞ በእኔም ይሁን በባለቤቴ ቤተሰቦች ዘንድ የተመሳሰለ ቅሬታን አስተናግጃለሁ፡፡ በጣም የሚያሳዝን ነበር፡፡ የእሱም ቤተሰቦች እኔን መሐን ሲሉ ...የእኔም ቤተሰቦች እሱን መሐን ሲሉ ...እጅግ የሚያስጨንቅ ሁኔታ ነበር ሁለታችንንም የገጠመን፡፡ እኔ እንዲያውም ቢቸግረኝ... ባለቤቴን ...በቃ ልጅ አስወልደህ አምጣ...የሚል ፈቃድ ሰጥቼዋለሁ፡፡ እሱ ግን በምንም ምክንያት አንቺን ትቼ ሌላ ጋ አልሄድም በማለቱ ኑሮአችን በቤተሰብ ውጥረት ሲሰቃይ ቆይቶአል፡፡ በሁዋላ ግን ሕክምናው ...ጸበሉ ...የተቻለው ሁሉ ተደርጎ ሳይሳካ ከቆየ በሁዋላ እርግዝናው ሳይታሰብ ተከሰተ፡፡ እኔ እንዲያውም ሕመም ይሆናል እንጂ መቼም እርግዝና አይደለም ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ሐኪሞቹ ግን ሕመም አይደለም ...እርግዝና ነው... በማለታቸው ተደሰትን፡፡ ምን ያረጋል... ደስታው ደስታ እንደሆነ ቢዘልቅ ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን አልሆነም፡፡ በማህጸኔ ውስጥ ኢንፌክሽን በመኖሩ ምክንያት ጽንሱ መቀጠል ስላልቻለ እና እኔም በጣም ስለታመምኩ እርግዝናው እንዲቋረጥ ተደረገ፡፡ ከምንጊዜውም በላይ እጅግ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ ከዚያም በሁዋላ ማርገዝ አልቻልኩም፡፡         ትእግስት ሺፈራው ከኮተቤየትእግስት ደብዳቤ የደረሰን በፖስታ ነበር፡፡ እኛም ገጠመኙን ይዘን ወደሕክምና ባለሙያ ነበር ያመራነው፡፡ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ በጳውሎስ ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻ ሊስት በማህጸን ኢንፌክሽንና እርግዝና ዙሪያ ለዚህ እትም ማብራሪያ እንዲሰጡ  ተጋብዘዋል፡፡ ዶ/ር ታደሰ እንደሚሉት ኢንፌክሽን ሲባል መገለጫው ብዙ ነው፡፡  በሽታን ሊያመጡ የሚችሉ ተሀዋስያን መገኘት የሌለባቸው ቦታ ላይ ከተገኙ ኢንፌክሽን ወይንም መመረዝ ይከሰታል፡፡ የማህጸን ኢንፌክሽንን ለይተን ስናይ ደግሞ በተለምዶ ብዙ አይነት ሲሆን ምንጩ ባክቴሪያ፣ ፈንገስ፣ ቫይረስ ወይንም ሌሎች ፓራሳይትስ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኢንፌክሽኑ ያጠቃውስ የትኛውን
የማህጸን ክፍል ነው የሚለውን መለየትም ያስፈልጋል፡፡ ኢንፌክሽኑ በታችኛው የማህጸን ክፍል ውስጥ የሚገኝ ከሆነ ብዙውን ጊዜ ቀላል የሆነ ኢንፌክሽን ነው፡፡ ቀላል ሲባልም ...ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ምልክታቸውም በፍጥነት የሚታይ ነው፡፡  በታችኛው የማህጸን ክፍል የሚከሰተው ኢንፌክሽን በአብዛኛውም በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ የሚተላለፍ እንደ ጨብጥ (ጎኖሪያ) የመሳሰሉት ስለሆኑ ምልክታቸው በታየ ጊዜ ሕክምናው ስለሚሰጥ በቀላሉ ሊድኑ የሚችሉ ናቸው፡፡ ስለዚህም ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ምንም ችግር አያስከትሉም፡፡/ር ታደሰ እንደሚሉት የታችኛው የማህጸን ክፍል በኢንፌክሽን ተያዘ ሲባል ብዙ ጊዜ ኢንፌክሽኑ ወደላይኛው የማህጸን ክፍልም የመዛመት እድል ይኖረዋል፡፡ በዋናው ማህጸን ክፍል ወይንም በዘር መተላለፊያው እንዲሁም በዘር ፍሬ መፈጠሪያው አካባቢ ወይንም ዙሪያውን ያሉትን የሰውነት ክፍሎች የተዛመተው ኢንፌክሽን ጉዳት ሊያስከትል የሚችልበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡
ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ችግር የሚፈጠረው ኢንፌክሽኑ ወደላይኛው የማህጸን ክፍል ከገባ በሁዋላ፡-
የማህጸን የውስጥ ክፍል የመቁሰል እና ጠባሳ ምልክት ሊያሳይ ይችላል፡፡የዘር መተላለፊያ ቱቦው ሊቆስልና ሊዘጋ ይችላል፡፡የዘር ፍሬ የሚመረትበት አካባቢ መግል የመቋጠርና የመያያዝ ሁኔታ ሊኖረው ይችላል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት ሁኔታዎች እርግዝና እንዳይከሰት ማድረግ ወይንም እርግዝናው ቢከሰትም እንዳይቀጥል ምክንያት የመሆን አለበለዚያም ከማህጸን ውጭ እርግዝና እንዲከሰት የማድረግ አቅም አላቸው፡፡ ይህም የረጅም ጊዜ ጠንቅ ተብሎ ይገለጻል፡፡ ኢንፌክሽኑ ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ጉዳት ያስከትላል ሲባል በሰውነት ክፍል ውስጥ ስለተገኘ ብቻ ሳይሆን ለመራቢያ የሚያገለግሉ የሰውነት ክፍሎች ላይ በሚያደርሱት ጉዳት ነው፡፡ የመራቢያ አካላቱ ጉዳት ደረሰባቸው ሲባልም የሰውነት የመከላከል አቅም እነዚህን በሽታ አምጪ ሕዋሳት ለማጥፋት ሲል የሚያደርገው ጦርነት  ውጤት ነው፡፡ ለምሳሌም የዘር ማስተላለፊያ ቲዩብ ቆስሎ ቢገኝ  ምክንያቱ ሰውነታችን እነዚያን እየተባዙ ያሉ ጀርሞች ለማጥፋት በሚያደርገው ቁጣ የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህም በዋናነት ከኢንፌክሽኑ በላ ችግር የሚሆነው ሰውነት ተሐዋስያኑን ለማጥፋት ሲል በሚወስደው ተፈጥሮአዊ እርምጃ ሰውነት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ነው፡፡ ኢንፌክሽን ሲከሰት ጉዳት እስኪያደርስ ድረስ የተወሰነ ጊዜ ስለሚወስድ በዚህ መሀል እርግዝና ሊከሰት ይችላል፡፡ በማህጸን የታችኛው ክፍል የሚታይ ችግር ከሆነ በቀላሉ ሊታከም የሚችል ሲሆን በላይኛው የማህጸን ክፍልም ቢሆን ምልክት ሲታይ እርግዝናውም ቢኖር ሕክምናው ይሰጣል፡፡ በእርግዝና ጊዜ ማህጸን ይዘጋል... ስለሆነም ምልክቶቹን እንዴት ማየት ይቻላል?  ለሚለው ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ እንደሚሉት የተጎዳው ክፍል የታችኛው የማህጸን ክፍል ከሆነ የፈሳሽ መኖር የደም መፍሰስ የመሳሰሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላል፡፡ ኢንፌክሽኑ የደረሰው በላይኛው የማህጸን ክፍል ላይ ከሆነ ደግሞ ከፈሳሽ ይልቅ ሌሎች ምልክቶች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌም ትኩሳት፣ በሆድ አካባቢ ከበድ ያለ ህመም (በምርመራ ወቅት በትንሽ እንኩዋን ሲነካ ከፍተኛ ሕመም የመሰማት ሁኔታ) ይከሰታል፡፡ ከዚህም ባለፈ የላቦራቶሪ ምርመራ የመሳሰሉት ተደርገው በማህጸን ውስጥ
ኢንፌክሽን ካለ ጽንሱ እያለም ቢሆን ሕክምና ይደረጋል፡፡ በእርግጥ ሕክምናው ጠንከር ያለና
ክትትል የሚያስፈልገው ስለሚሆን ሆስፒታል እስከመተኛት የሚያደርስ ሊሆን ይችላል፡፡ የጽንሱ ሁኔታ እናትየው ሕክምናውን እየወሰደች እድገቱን ሊቀጥል ይችላል... አለበለዚይም ሕመሙ ከፍተኛ ከሆነ ሊያጨናግፈውም ይችላል፡፡ ኢንፌክሽን መኖሩ ብቻ ጽንሱን የሚያቋርጠው ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ሰውነትዋን ከመረዘው ምናልባት የሚኖር አጋጣሚ ነው፡፡ በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ የሚተላለፉት እንደ ጨብጥ፣ ቂጥኝ የመሳሰሉት ኢንፌክሽኖች በእርግዝና ወቅት ሊከሰቱ ወይንም ከእርግዝናም በፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ናቸው፡፡ እንደዚህ ያሉት ኢንፌክሽኖች እርግዝናው እንዲወርድ ምክንያት ሊሆኑ ሲችሉ ከዚህም ባለፈ ወደ ጽንሱ የመተላለፍ አቅም አላቸው፡፡ ጽንስ ሆድ ውስጥ የመቀጨጭ፣ጽንስ ሆድ ውስጥ የመጥፋት ወይንም ያለቀኑ መወለድ ወይንም... እነዚህ ሁሉ ሳይከሰቱ ቀርተው ልጅ የኢንፌክሽኑ ተጎጂ ሆኖ ሊወለድ ስለሚችል እናትየውን ቶሎ በማከም ልጁንም ማዳን ይቻላል፡፡ባለሙያው እንደሚገልጹት እርጉዝ ሴቶች እንደተገኘ ወይንም በቀላሉ መድሀኒትን አይጠቀሙም ቢባልም በአንዳንድ ምክንያቶች ግን የተለየ ሕክምና ይሰጣል፡፡ ነገር ግን በጽንስ ላይ ችግር የሚያስከትሉ ...ፈጽሞ በእርግዝና ወቅት የማይወሰዱ ተብለው የተለዩ መድሀኒቶች አሉ፡፡ንስ ላይ ምናልባት ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ግን የመድሀኒቱ ጠቀሜታ ከጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል ተብሎ የሚሰጡ አሉ፡፡ ጽንስ ላይ ችግር ያምጣ አያምጣ አይታወቅም፡፡ ግን የመድሀኒቱ ጠቀሜታ ለእናትየውም ይሁን ለጽንሱ ጠቀሜታ አለው የሚባሉ መድሀኒቶች አሉ፡፡ ፈጽሞ በጽንስ ላይ ምንም ችግር አያመጡም የሚባሉ የመድሀኒት አይነቶች አሉ፡፡
ስለዚህ እነዚህ መድሀኒቶች በውል ተለይተው የሚታወቁ ሲሆን እንደሌላው መድሀኒት ዝም ተብሎ በቀላሉ የሚወሰድ ሳይሆን በሐኪሞች ልዩ ትእዛዝ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሰጡ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ያለው ግንዛቤ ከማህጸን ፈሳሽ ከታየ እንደ ኢንፌክሽን የመቁጠር ዝንባሌ ያለው ነው፡፡ ነገር ግን በተለይም በእርግዝና ወቅት በማህጸን አካባቢ ብዙ ለውጥ ያለ ሲሆን ከነዚህም አንዱ የፈሳሽ መብዛት ነው፡፡ አንዳንድ እርጉዝ ሴቶች አልፎ አልፎ ሞዴስ እስከመጠቀም የሚደርሱበት ሁኔታም ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን ፈሳሽ ከኢንፌክሽን የመጣ ነው የምንለው መቼ ነው የሚለውን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ መብዛቱ አንዱ ምልክት ቢሆንም ብቻውን ግን ኢንፌክሽን ነው አያሰኘውም፡፡ ከዛ ባለፈ ግን የማሳከክ ወይንም የማቃጠል ስሜት ካለው ወይንም መልኩ ከሌላ ጊዜ የተቀየረ ሲሆን ...ወዘተ ኢንፌክሽን መሆኑን ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ ስለዚህም ሕክምናውን በጊዜው ማድረግ ተገቢ ነው ይላሉ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ፡፡ በስተመጨረሻም ዶ/ር ታደሰ በተለይም በእርግዝና ወቅት ከሚኖረው የአካል ገጽታ ጋር በተያያዘ የገለጹትን እናስነብባችሁ፡፡ “...አንዲት እናት ከማርገዝዋ በፊት እና በእርግዝና ላይ እያለች የሚያመሳስላት ነገር     ቢኖር ስምዋ ብቻ ነው፡፡” ለምን? የሚለውን ጥያቄ መልስ በቀጣዩ እትም እናስነብባችሁዋለን፡፡ ይቀጥላል

Read 52618 times