Monday, 02 March 2015 08:41

“ የግል ሆስፒታሎች ከመንግስት ቢሻሉም ከደረጃ በታች ናቸው”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ለብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪ አማራጭ እንደሆኑ በጥናት ሪፖርት ተገልጿል
በአዲስ አበባ የሚገኙ የጤና ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት በአመዛኙ በመንግስት ስር ካሉት ተቋማት የተሻለ ቢሆንም፣ ግማሽ ያህሉ ገና ከደረጃ በታች እንደሆኑ ተገለፀ፡፡ በመንግስትና በግል ጤና ተቋማት ያለው የክፍያ ልዩነት ከአራት እስከ አርባ እጥፍ ይደርሳል፡፡
የግል ህክምና ተቋማት በአዲስ አበባ የሚሰጡት አገልግሎት ላይ ጥናት የተካሄደው በ“ማህበራዊ ጥናት መድረክ” አማካኝነት ሲሆን፣ ትናንት ይፋ የሆነው የጥናት ሪፖርት ከአገልግሎት ጥራት በተጨማሪ የክፍያ መጠኖችንም በማነፃፀር ዳስሷል፡፡ የግል የጤና ተቋማቱ ከመንግስት የጤና ተቋማት ጋር ሲነጻጸሩ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የጥናት ሪፖርቱ ጠቅሶ፤ ይህ ማለት ግን የአገልግሎት ደረጃን ያሟላሉ ማለት እንዳልሆነ ገልጿል፡፡
አዳዲስ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች የስራ ፈቃድ የሚያገኙት በቅርቡ እንደ አዲስ በተዘጋጀው የጥራትና ደረጃ መስፈርት እንደሆነ በጥናቱ የተገለፀ ሲሆን በመስፈርቱ መሰረትም 34 የግል ሆስፒታሎች ላይ ዝርዝር ጥናት ተካሂዷል፡፡ የጥናቱ ሪፖርት እንደሚገልፀው፤ የጥራት ደረጃ መስፈርቶችን በአግባቡ ያሟላሉ ሆስፒታሎች ከሁለት አይበልጡም፡፡ 17 ያህል ሆስፒታሎች (ማለትም 50% ያህሉ) በመካከለኛ ሁኔታ ላይ እንደሆኑና ማሻሻያ እንደሚያስፈልጋቸው ጥናቱ ገልፆ፤ 15 ያህል ሆስፒታሎች ግን በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው ብሏል፡፡
 ባለፉት አምስት አመታት የግል የህክምና ተቋማት እድገት ማሳየታቸውን ያመለከተው ጥናቱ፤ 42 በመቶ ለሚሆነው የከተማዋ ነዋሪ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነና አገልግሎታቸው ለከተማው ሀብታሞች ብቻ ሳይሆን በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ነዋሪዎችም ጭምር እንደሚደርስ ገልጿል፡፡
ጥናቱ የአገልግሎት ክፍያን በተመለከተ የግል የጤና ተቋማት ከሚሰጡት የአገልግሎት ጥራት ጋር ያልተመጣጠነ ከፍተኛ ክፍያ እንደሚጠይቁ አመልክቷል፡፡ በተለይ ከመንግስት የጤና ተቋማት ጋር ሲነጻጸር ክፍያው የትየለሌ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ፤ ለምሳሌ በኤክስሬይ የዋጋ ልዩነቱ 40 እጥፍ ገደማ ሲሆን በወሊድ አገልግሎትም በተመሳሳይ የክፍያ ልዩነቱ ወደ 40 እጥፍ ይጠጋል፡፡
በእርግጥ የግልና የመንግስት የጤና ተቋማት ክፍያ ተቀራራቢ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ የመንግስት የጤና ተቋማት ስራቸውን የሚያከናውኑት ከክፍያ በሚያገኙት ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከታክስ ከሚሰበሰብ ገንዘብና ከውጭ ከሚመጣ እርዳታ በጀት እተመአበላቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡  

የአገልግሎት አይነት    የግል ሆስፒታል ክፍያ በአማካይ    የጤና ጣቢያ ክፍያ በአማካይ
የካርድ                        100           5
ኤክስሬይ                      180          35
በምጥ ማዋለድ               1940           50
በኦፕራሲዮን ማዋለድ         3550         140
የወንዶች ግርዛት                520          35
ትርፍ አንጀት ቀዶ ህክምና    2850          120
የአልጋ አንደኛ ደረጃ            850          90
የአልጋ ሶስተኛ ደረጃ           350          20

በግል የጤና ተቋማት ውስጥ እንደ ችግር ከተጠቀሱት መካከል ለባለሙያዎች ማበረታቻና ተከታታይ ስልጠና አለመሰጠቱ፣ በህክምና ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሃብቶች የመሥሪያ መሬት ለማግኘት መቸገራቸው፣ የባለሙያዎች እጥረት፣ የብድር እጦት፣ የጉምሩክ ቢሮክራሲና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ይገኙባቸዋል፡፡  





Read 1820 times