Saturday, 28 March 2015 09:54

ወደ ምንጭ መመለስ

Written by  ገዛኸኝ ሀብቴ
Rate this item
(4 votes)

 መኝታ ከያዘበት ማንኩሽ ኢንተርናሽናል ሆቴል ወደ ሐይቁ ለመድረስ ምን ያህል ደቂቃ እንደሚያሽከረክር ለመገመት ሞከረ፡፡
“…ምን ነካኝ!? በፍጹም በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ መኪና ማሽከርከር ጥሩ ስላልሆነ በሹፌር መሄድ አለብኝ!...” ስልኩን አንስቶ ደወለ፡-
ከ35 ዓመት በኋላ ነው ወደ ሐገር ቤት የተመለሰው፤ ዝብርቅርቅ ያለ ስሜት ተሰምቶታል። እየተገነባ ባለው ፌዴራላዊ ከተማ ተገርሟል። በተደጋጋሚ “እኛ ኢትዮጵያውያኖች እዚህ እንደርሳለን ብዬ አላስብም ነበር!!” ይላል፡፡ ለውጣችን ያስገርመዋል፣ ያስደንቀዋል።
“ይህች የህዳሴውን ሐይቅ ተገን አድርጐ የተፈጠረችው ከተማ የነገዋ ኢትዮጵያ ተምሳሌት ናት! ማህበራዊ ስነልቦናችንን፣ ቀደምት ኪነ-ሕንፃዎቻችንና የምዕራባውያንንም መልካም ስልጣኔ ያካተተች ምርጥ ከተማ…” ይላል፡፡
“ብዙ ነገር ተቀይሯል!” ሲሉት፣ “እሰይ እንኳን የተቀየረ…ህይወት እንደዛ ነው!...ሐገር ወይ በበጐ አልያም በመጥፎ ትለወጣለች…የእኔም ሐገር ይኸው ተለውጣለች፡፡ ድንገተኛ ለውጥ ያስደነግጣል… ያስበረግጋል፡፡ አብዮት አልሰመረልንም፣ ዝግመተ ለውጥ አልተሳካልንም፡፡ ይህ ለውጥ ግን መንፈሳዊ ነው፤ መንፈሳዊ! ሳዖል ወደ ጳውሎስ የተቀየረበት ለውጥ፤ ሸንበቆን ወደ ዓለትነት የቀየረ መንፈሳዊነት። ሕብረት… እለዋለሁ…፡፡” ይህንን ሲናገር ገጽታው ማለዳንም፣ የጀንበር መጥለቅንም ይመስላል፡፡ ማለዳ ቀን ይዞ ይመጣል፤ የጀንበር መጥለቅም ከዋክብትን ጨረቃንና ነገን፣ አልፎ ተርፎም ያልተመረመረውን ጨለማ፡፡
የሐገሩ ፖለቲካ አይገባውም ነበር፡፡ አይገባውም አያውቅም አይደለም፡፡ ሐገርን፣ ብሔራዊ ተቋማትንና ብሔራዊ ስሜትን ግን ኑሮውና ደመነፍሱ አስተምሮታል፡፡ ቡድነኝነትን ይፀየፋል፣ ጐጠኝነትና ጠባብነት አይመጥነውም፡፡ እሱ የሰው ልጅነት፣ እሱ ኢትዮጵያዊነት፣ እሱ አባያዊነት፣ እሱ ውሃነት ነው። የሚሄድም፣ የቆመም፣ የሚከተርም ውሃ ነው፡፡ ጠረን የለውም፤ ቀለም የለውም…ድምፅ እንጂ ቋንቋም የለውም፡፡
ይህ ማለት እኔነቱ የለም ማለት አይደለም፡፡
የተወለደበት መንደር፣ ያደገበት ቀዬ፣ ከእናቱ ማኅፀን ሲወጣ የሸተተው አፈርና ምርጊቱን ዘልቆ የማገው የቀርከሃ፣ የሰንበሌጥ፣ የማንጐ፣ የሙጫና የቴምር ጠረን እሱነቱ አይደለም ያለው ማነው??
የመንደሯ አዛውንቶች እነ አባ አልናስር፣ እነ አባ አልጠይብ፣ እነ እማ ሀጀጀ..እማማ ከልቱም ከነፍሱ የተቋረቡ ናቸውና እንደምን ይተዋቸው??
“አሁን ጠይሟና መሀኗ የእናቴ ጓደኛ፣ እማማ ከልቱም አልወለዱኝምና እናቴ አይደሉም ልል ነው??...” ሲያስበው እንኳን ያንገሸግሸዋል፡፡ ይህ ተፈጥሯዊው ደሴትነቱ ነው፡፡ ይህ ደሴትነት ሁለንታ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያዊነቱ ነጠላ ሰደንቅ ነው፡፡ ይህ ኢትዮጵያዊነት የተገነባባት ጡብ ነው፡፡
አይኖቹ ቦዘዙ፡፡ ላዕላይ አምሮቱ ከማንጐ ዛፍ ላይ ተሰንቅሮ ቀረ፡፡ የእጆቹ ጣቶች ግን አሁንም የሸበቱ የአገጭ ፂሞቹን ይፈልጋሉ! ረጅሙን የመሐል ጣት አንጓ በባህላዊ መንገድ የሚሰራው የበርታዎች የወርቅ ቀለበት ጋርዶታል፡፡ ነፀብራቁ ግን ለጣቶቹ ግርማን ሰጥቷል፡፡
አእምሮው ሸፈተበት፡፡
ለእናቱም ለአባቱም ብቸኛ የስጋ ልጃቸው፡፡ ነው ዘወትር ስለማይገባውና ስለተደጋገመው የአባቱ ምስል ያስባል፡፡ ለጋ፣ ልስልስ ያለና የወዛ ጥቁር ፊት አላቸው። ከእራሳቸው የማያወርዱት የሙስሊሞች ቆብ፣ ሰርስረው የሚያዩ፣ በትንንሽ አይኖች ላይ ሰፊና ጥቋቁር ብሌኖቻቸው ይመጡበታል፡፡
አምስት ሜትር በስምንት ሜትር በምትሆን የመንደሯ ጉሊት ላይ ከሱዳን የመጣ ስኳር፣ ኦሞ፣ ቡና፣ ጨው፣ ክብሪት፣ ዛላ ሚጥሚጣ፣ ቲማቲም፣ ሸንኮራ እና የተለያዩ ቀለማት ያሏቸው እንደ ኳስ የተድቦለቦሉ የሱፍ ክሮች ተዘርግተው ይሸጣሉ፡፡ አባቱና ሁለት አዛውንቶች ሶስት ማዕዘን ሰርተው፣ ከመሬት ስንዝር ከፍ በምትል ከቀርከሃና ከቆዳ በተሰራች በርጩማ ላይ እግራቸውን አጠላልፈው ይቀመጡ ነበር፡፡ የዚህ ሁሉ ኅብር በልጅ አእምሮው አይገለጥለትም ነበር፡፡
ከሁሉም ተለይቶ ይህ ምስል ለምን በአእምሮዬ ተነቅሶ እንደቀረ ሊባኝ አልቻለም?”
የተደወለለት ሹፌር መጣ፡፡ ሰላምታውን በፈገግታ መለሰ፡፡ የመኪናውን ፍጥነት እየሸሹ ወደ ኋላ የሚቀሩት አሁኖቹ፣ በልጅነቱ ትዝታ ተተኩ፡፡
የዱር ሙጫ የቀለመበትን፣ ቀርከሃ የሸፈነውን ምድር፣ የማንጎውን ደን፣ የአባይን ወንዝ፣ ከፀሐይ ይሁን ከሰው ዓይን ለመከለል በግራና በቀኝ የጋረዱትን የቴምር ዛፎች፣ የታጠበባቸውን የበለስ፣ የአይማ፣ የዳቡስ፣ የሸርቆሌና የጡነት ወንዞችን አሰበ።
ልጅነት ምንድነው? ልጅነት ማነው? ምንድነው ራሱ ማነው? ማነው ራሱ ምንድነው? ከትዝታህ ውስጥ እውቀትህ ምን ያህሉ ነው? ወይስ ትዝታህ ውስጥ እውቀትህ የለም?
“…ከሩቅ! ከሩቅ! አቧራ እያስነሱ የሚመጡትን መኪኖች ስናይ እንፈነድቃለን፡፡ አይኖቻችን ደካሞች ናቸው፤ የሚመጡትን መኪኖች እንዳናይ መሐላችን ገብቶ የሚያጥበረብረን ብርሃን ይከልለናል፤ እንበሳጫለን፡፡ የልጅነት ብስጭት፡፡ ትዕግስታችንን አጥተን እንጠብቃለን፤ የልጅነት መጠበቅ አሁንን ነው፡፡ መጓጓታችን ቅፅበትን ነው፡፡ ክፋታቸው ቶሎ አይደርሱም! ጥበቃችን ያይላል፡፡
“ይደርሳሉ”
“መድረሳቸውና መቆየታቸው አፍታ ነው። መጠበቃችን የትየለሌ፡፡ በአጠገባችን ውልብ ይላሉ። እንከተላቸዋለን፡፡ በማግኘታችንና በማጣታችን፣ በደስታችንና በቁጭታችን መሃል የስሜት ህዋሳታችን የሚለኩት ጊዜ የለም፡፡”
“አቧራቸውና ድምፃቸው እስኪቀር እየሮጥን እንከተላቸዋለን፡፡ እናቶቻችንም የሸፈነን አቧራ እስኪረጋ ልባቸው አይረጋም፤ ከማንም በላይ የእማማ ከልቱም መንሰፍሰፍ፡፡
“ሌላ ካሚዮን እስኪመጣ ስንት ለሊት ይነጋ ይሆን። የዕለት ተዕለት ጥያቄያችን ነበር፡፡ ለመኪኖች ልዩ ፍቅር ነበረን፣ በያኔው እውቀታችን፡፡  ከአባይ፣ ከበለስ፣ ከአይማ፣ ከዳቡስ፣ ከሸርቆሌና ከጡነት የምንጨልፈው ውሃ አንድ ይመስለን ነበር፡፡ ዛሬ ከቀዳነው ወራጅ ውሃ ላይ ነገም የምንቀዳ ይመስለን ነበር፡፡”
“ጉባ ዩኒቨርስቲ” የሚል አነበበ፡፡ አለፍ ብሎ ደግሞ “ዳቦስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል”
እኔነቱ ከአካባቢው ባህል፣ ወግ፣ ልማድ ጋር ተገምዷል፡፡ ያወዳድራል፣ ያነፅፅራል…ድሮና ዘንድሮን ባካተተ “ስልጣኔ” ይመሰጣል፡፡
“…ድሮ የምዕራባውያን “ስልጣኔ” የሰራው ትምህርት ቤት የለም፣ ትምህርት ግን አለ፤ የባህላዊ ህክምና እንጂ ክሊኒክ የለም፤ የወገኔ ሌጣ እግር የጠረገው ጐዳና እንጂ አስፓልት ወይም የባቡር ሃዲድ የለም፤ ብርሃን እንጂ የኤሌትሪክ መብራት የለም፤ ውሃ እንጂ ቧንቧ የለም፡፡ ያኔ ስሰደድ…”
“ያኔ! ሐገሬን ትቼ ስሄድ! ያኔ! የሰው ፍቅር እንጂ የሐገር ፍቅር የለኝም ነበር፤ ያኔ! ሐገር ማለት ጠባብ ግን ረጅምና ጥልቅ ወራጅ ውሃ ነበር…ያኔ! አባይ ለእኔ እንደ ሚሲሲፒ፣ እንደ ዛየር፣ እንደ ዛምቤዚ፣ እንደ ኒጀር፣ እንደ አማዞን፣ እንደ ቮልጋ ወንዝ ብቻ ነበር፡፡”
ያኔ እውነቱን ነው፡፡ በወንዙ ዳር ዳር በበቀሉት የዘንባባ ዛፎች ግርጌ ከተቀበሩት ዘመዶቹ መቃብር ላይ ጥርኝ አፈር ዘግኖ፣ በትንሽ የቆዳ ከረጢት ቋጥሮ ወደ ወንዙ ወረወረ፡፡ የወገኖቹን ቅሪት ቀድሞ አሰደደ፤ አስቀድሞ ወደ ተጓዥነት ቀየረ፡፡ ቀጥሎም ዕጣውን ለመተንበይ ተጣደፈ፡፡
የአባይን ወዛም ከንፈር ያለበሱትን አቧራማ መንገዶች ይዞ ተፈተለከ፡፡ እንዳቅሚቲ እያቦነነ ከነፈ። አይኖቹ ግን የሉል ቅንጣት በሚመስሉ እንባዎች ተሸፈኑ፡፡
ወንዙም ወንዝ ነውና፣ ሂያጅ ነውና እንደለመደው የእናት አባቱን፣ የአያት ቅድመ አያቱን ቅሪት ተሸክሞ ነጐደ፡፡ መነሻውን ያውቃል፣ መድረሻውን ግን ይመኛል፡፡ የስደት ነገር! ከረጢቷ በእልፍ አዕላፍ---------ትመሰላለች፡፡
አይኖቹ በዕንባ ቢጋረዱም ብዙ ሮጠ፡፡ አሁን ተረታ፡፡ በጉልበቱ ወደቀ፡፡ ጮኸ፡፡
“አንች ሐገር… አንቺ ምድር… ስለምን አባቶቻችን የጠረጉት ስልጣኔ ላይ እሾህና አሜኬላ የሚያፈራ ትውልድ አበቀልሽ…ስለምን እንደ ዳይኖሰር እርስ በእርሱ ተበላልቶ የሚያልቅ ትውልድ ፈጠርሽ? ስለምን “ጋራሽ ሸንተረሩ በአበቦች አጊጧል”…በተዘፈነልሽ ፋንታ ህፃን፣ የአስከሬን እናቱን ጡት ሲጠባ አየን? ስለምን? የሦስት ሺህ ዘመን ባለታሪክ ሆነሽ፣ የዳቦ ቅርጫት ነች እየተባልሽ ጨቅላ ከዓይነምድር ላይ ጥሬ ሲለቅም አየን?...” ጩኸቱን የገደል ማሚቶ አስተጋባች፡፡
ይህ ድምፅ ታላቅ ድምጽ ነውና በሞገድ ለሁለንታ ተዳረሰ፡፡ የደቀቀ አሸዋውንና አፈሩን ደምስሩ እስኪገታተር ድረስ ጨብጦ በተነው፤ ድምፁ እስኪታፈን የእጁ ጥፍሮች እስኪነቃቀሉ መሬቱን ጐደፈረው፡፡ ላቡ መላ አካሉን አጥለቀለቀው፤ የቆላው ሙቀት ላቡን ከገላው ላይ ሲያተነው ታየ። ይህ ማንነቱን ቆንጥሮ የወጣው ፈሳሽና እንፋሎት ሰውነቱ ላይ ነጭ መም ሰራ፡፡
ለሽራፊ ሰከንድ ብልጭ ያለች ፈገግታው ተገለጠች። ከዚህ በኋላ ተሰደደ ብቻም ሳይሆን፣ ተሳደደ፡፡ አሁን! ከዚህ ዘላለማዊ ከሚመስለው ትዝታ መንግሎ ያወጣው ህዳሴው ሐይቅ መድረሱ ነበር፡፡
አሽከርካሪው መኪናውን በትክክለኛው ቦታ እስኪያቆም ያለው ጊዜ የትየለሌ ሆነበት። ተቁነጠነጠ። አካባቢው ከተለያዩ አህጉራትና ሀገራት በመጡ ቱሪስቶች ተጥለቅልቋል፡፡ በውሃው ዳርቻ እና ተወዛዋዥ አልጋዎች ላይ ተሰጥተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ወፈ ሰማይ ፈረንጅ ሊጥ የመሰለ ቆዳውን በፀሐዩዋ ግለት ሊያጠይም ነው! የእሱ ግን ይለያል። በሃሳቦቻቸው ያነጡትን ማንነት ሊያጠቁር ነው፡፡
ከውሃው በላይ በተዘረጋው ተንጠልጣይ ድልድይ ሄደ፡፡ በሐይቁ ዙሪያ ከተገነቡት ሆቴልና ሪዞርቶች መካከል አንዱ የባምዛ ሪዞርት ንብረት ወደ ሆነችዋ ጀልባ ተጣደፈ፡፡ ጉባ ወይም “ብርሃን” ትባላለች፡፡ ሳቂታው ካፒቴኗ በደስታ እየተፍለቀለቀ ተቀበለው። ፊቱን አይቶ በርታ እንደሆነ ገባው፡፡ በአይኖቻቸው ብቻ ተግባቡ፡፡
የካፒቴኑ ነጭ ጥርስ፣ ፀሐይ ከሀይቁ ውሃ ላይ ካስፈነጠረችው ፀዳል ተውሶ አንፀባረቀ፡፡ ጀልባዋ ተንቀሳቀሰች፡፡ የውሃው ቀለም የባለቤቶቹን የቆዳ ቀለም ይዟል፡፡ እጁን ወደ ውሃው መሰገ፣ ሰንጥቆ ገባ። ጉባም ተፈተለከች፡፡ እጁ ውሃውን እየቀረደደ ሄደ፡፡ በጣም ጮኸ፡፡ ሀይቁን በአይበሉባው ጠፈጠፈው፡፡ እመር ብሎ እጀልባዋ አፍንጮ ላይ ቂብ አለ፤ እጆቹን መስቀለኛ ዘረጋቸው፡፡
“…ከእኔና ከዘመዶቼ ውጪ እትብቱና አስክሬኑ በውሃ ውስጥ የተቀበረ ይኖር ይሆን??...የሸርቆሌ፣ የኩምሩክ፣ የጉባ…አባቶች እናቶች ሆይ፣ የልጆቻችሁ እትብት፣ የእናንተ አስክሬን ከፈርዖንም፣ ከነገስታቶችም፣ ከባለፀጐችም በላይ በሶስቱ የኦርዮን ኮከቦች መሃል በታላቁ ሕዳሴ ሐይቅ ውስጥ እንዳለ ለነፍሳችሁ አንሾካሹካለሁ፤…”
የፍርሃቱ መጠን ጨመረ፣ የጀልባዋ ፍጥነት በጣም ከቀነሰ በኋላ ሞተሯን አጠፋው፡፡ ስሜቱን ፈርቶታል። “ዋና…?”  “…እነሆ ለልጅ ልጆቻችሁ እላችኋለሁ ስሰደድ እትብቴ አዋይ፣ አፅማችሁ አድባር ነበር፡፡ ዛሬ ግን መንፈሳችሁ በሀይቁ ላይ ሰፎ አየሁ…!! ስሙኝ እናንተ፣ የያኔ አሳዳጆቼ፣ የአሁን የስደት ጓዶቼ፤ ዛሬ አልፈራም ዘመን ተቀይሯል፤  መንፈሳዊ እርቅ ታውጇል፡፡
የተጓዝንባቸው መንገዶች፣ ያስጠለሉን ሀገሮች፣ የተሳቀቅንበት ሐበሻነት፣ በስደት ሐገር ቀርቷል፡፡ ስማችን በረሃብና በስደት የሚነሳበት ቀን አልፏል…ኢትዮጵያዊነት ለዓለም ዜግነት የሚለመንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡
ከተሞቻችን በሮም፣ በአቴንስ፣ በፓሪስ፣ በኒው ዮርክ፣ በማድሪድ፣ በለንደን እና በጥንታዊው ስልጣኔያችን ተቀይጠዋል፡፡ የልቦቻችን ሃሳቦች፣ የመንፈሶቻችን ከፍታዎች ግን ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በትግራይ፣ በሐረሪ፣ በሱማሌ፣ በአማራ ይገነባሉ፡፡
“እናንተ እንደ አድባር ንፍሮ በየቦታው የተበተናችሁ ወገኖች ሆይ! ኑ! ለልጅ ልጆቻችን የሚሆን የማንነታችን የአፈር እና የውሃ ቅይጥ እዚህ ሐይቅ ውስጥ አለ…፡፡ የእኔ በሌለበት፣ የእኛ በሆነበት ከሰንበሌጥ በተሰራው የአልካለዋ ዳስ ተሰብስበን እንጠብቃችኋለን፡፡ አልካለዋ የኢትዮጵያ ተምሳሌት ነው፡፡
ኑ! የነፍሶቻችሁን መክሊት፣ የልቦቻችሁን መስዋዕት እንጂ የቁሶቻችሁን ክምር የማትሻ እናት አለቻችሁ፡፡ ልባችሁ እንደ እጃችሁ ከምን ወደማትባሉበት ወደ ታላቁ አልካለዋ ግቡ፡፡ አልካለዋ ዘር፣ ብሔር፣ ፆታ፣ ሃይማኖት ሳይለይ ሁሉም የየፍላጐቱን ጥሪት የሚገበይበት ታላቅ ምኩራብ ነው።
ወደ ውሃው ተወረወረ፡፡ የጀልባው ካፒቴን ደነገጠ “አዞ…አዞ…” ጮኸ፡፡
መስመጥ ፈልጓል፤ ወደ ጥልቁ መግባት ሽቷል፤ ሐይቁ የተነጠፈ መስታወት ይመስላል፤ አላሰጥም አለው፡፡ ተፍጨረጨረ፤ የእሱነቱን ምንጭ፣ የኢትዮጵያዊነት ክምችትን ሊያገኝ ታተረ፡፡
ሌላ፣ ሌላ፣ ትልቅ የዝንተ ዓለም ድንጋይ ፍለጋ። ባይደክመውም እንደ ፈጣሪ ማረፍ ፈለገ፡፡ በጀርባው ተንጋሎ ውሃው ላይ ተኛ፡፡ በተራራው አናት እና ጥግ ጥጉን የከተመችው የአልካለዋ ከተማ ጥላ ህዳሴው ሀይቅ ላይ ወድቋል፡፡
አሰበ፣ አሰበ፡፡ ከትከት ብሎ ሳቀ፣ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ…
“…ከሚሊዮን ዓመታት በኋላ አርኪዎሎጂስቶች በባህር ውስጥ የእትብት ቅሪት ፈልገው ያገኙ ይሆናል!!”

Read 4269 times