Monday, 06 April 2015 08:15

ለተስፋም ጊዜ አለው!

Written by  አብዱልመሊክ ሁሴን
Rate this item
(2 votes)

   እንደ ሀገር ካሰብን፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ወገብ የሚፈትሽ ከባድ ሥራ ከፊታችን ተደቅኖብናል፡፡ ዓለም፤ እንደ ሀገር መፃኢ ጊዜያችንን እንዴት ቅርጽ እንደምናስይዘው ለማየት በአንክሮ ይከታተለናል። ‹‹ኢትዮጵያውያን ወደ ጥንቱ እንቅልፍና ቅዠታቸው፤ ሁከትና ጦርነታቸው ይመለሱ ይሆን?›› እያለ ይጠይቃል፡፡ ‹‹ወይስ ተስፋ ሰጪ አያያዛቸውን ውል አስይዘው አዲስ ታሪክ መስራት ይችሉ ይሆን?›› እያለ ይገምተናል፡፡
ዛሬ ‹‹ኢትዮጵያውያን ተስፋ ሰጪ አያያዛቸውን ያበላሹት ይሆን?›› እያለ የሚጠይቀው የምዕራቡ ዓለም፤ ከ12 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን ተስፋ ያላት ሐገር አድርጎ ለመመልከት ይቸገር እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡ ለዚህ ገዳይ እንደ ማስረጃ የማነሳው ከ12 ዓመታት በፊት ‹‹ዘ ኢኮኖሚስት›› የተሰኘው መጽሔት ያቀረበውን ዘገባ ነው፡፡
ከ12 ዓመታት በፊት ‹‹ዘ ኢኮኖሚስት›› በሽፋን ገፁ ‹‹ተስፋ አልባዋ አህጉር›› በሚል ርዕስ ባቀረበው በዚያ ዘረኝነት የጎበኘው ዘገባ፤ በአፍሪካ ምድር የየታዩትን አንዳንድ ተስፋዎች እንኳን እንደ በርሃ ምትሃት አይቶ አጣጥሏቸዋል፡፡ ‹‹ዘ ኢኮኖሚስት›› ሜይ 2000 (እ.ኤ.አ) ባወጣው ጽሁፍ፤ ‹‹ተስፋ አልባዋ አህጉር›› ሲል ያቀረበው ፍጹም ዘረኝነት የሚንጸባረቅበት ዘገባ፣ የአህጉሪቱን ህዝብ ያጣጥላል፡፡ መጽሔቱ ከርዕሰ አንቀፅ ጀምሮ በውስጥ ገፆች (23-25) በሰፊው ባቀረበው ዘገባ፤ ስለ ሴራሊዮን በማተት ይጀምራል፡-
‹‹ፍሪታውን [ሴራሊዮን] በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጠፍና ወባማ ምድር ብትሆንም በተስፋ የተሞላች ምድር ነበረች፡፡ በእንግሊዝ ሲኖሩ ቆይተው ወደ ሴራሊዮን ለተወሰዱ ድሃ አፍሪካውያን እና ከአሜሪካ ለመጡ የቀድሞ ባሮች መስፈሪያ የተደረገችው ይህች ሐገር፤ እንግሊዝ የባሪያ ንግድን ለማስወገድ ያወጣቸውን ህግ ተፈፃሚ ለማድረግ የተመረጠች የምዕራብ አፍሪካ ዋነኛ የሠፈራ ቦታ ነበረች።›› አያይዞም፤ ‹‹ሆኖም ፍሪታውን በ21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የወደቁ ሰዎች መኖሪያ እና የተስፋ ማጣት ምልክት ሆነች›› ይላል፤ በወቅቱ በሴራሊዮን ስለነበረው አስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት ለመተረክ ሲንደረደር፡፡
‹‹ይሁንና መላው አፍሪካም ከሴራሊዮን ብዙ የተሻለ አይደለም፡፡ ሞዛምቢክና ማዳጋስካር በጎርፍ ተመትተዋል፡፡ በኢትዮጵያም ዳግም ረሃብ ብቅ ብሏል፡፡ ዚምባብዌም በመንግስት ለታገዘ ዝርፊያ፣ እንዲሁም ለድህነትና በሽታ እጇን ሰጥታለች፡፡ አሁንም አፍሪካ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ  በጦርነት እሣት እየተለበለበች ነው›› ይላል፡፡
እናም፤ ‹‹አዲሱ ሚሊኒየም ለአፍሪካ ይዞላት የመጣው ተስፋ ሳይሆን ብዙ ውድቀት ነው፡፡ …በ1990ዎቹ ለተወሰነ ጊዜ አንዳንድ የኢኮኖሚ መሻሻል ምልክቶች ታይተው ነበር።… በተመሳሳይ የብዙሃን ፓርቲ ስርዓት በመላው የአህጉሪቱ አካባቢዎች ተስፋፍቶ ነበር፡፡ ጥሩ አመለካከት ያላቸው መሪዎችም ብቅ ብቅ ማለት ይዘው ነበር። በደቡብ አፍሪካ ኔልሰን ማንዴላ፤ በኡጋንዳ ዩወሪ ሙሴቬኒ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ መለስ ዜናዊን የመሰሉ መሪዎች ወደ ሥልጣን መጡ፡፡ እነዚህ መሪዎች ሰላም እና መልካም አስተዳደር እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን የተገነዘቡ ይመስል ነበር›› በማለት ይቀጥላል፡፡
‹‹ምንም እንኳን እነዚህ መሪዎች፤ ቀደም ሲል የሶሻሊስት መርህን ሲያቀነቅኑ የነበሩ ቢሆንም አሁን የነፃ ገበያን የተቀበሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ በአፍሪካ ምድር ዲሞክራሲና የነፃ ገበያ አሰራር የማበብ አዝማሚያ አሳይቶ ነበር፡፡ ሁሉም ሰው ስለ አፍሪካ ህዳሴ መነጋገር ጀምሮ ነበር›› ይልና ሲያጠቃልል፤ ‹‹ግን ይህ የህዳሴ ተስፋ ከንቱ ቅዠት ነበር›› በማለት ይደመድማል፡፡
‹‹አዲስ ትውልድ የተባሉት መሪዎች መልሰው ጦርነት ውስጥ ተዘፈቁ፡፡ ተስፋ አሳድሮ የነበረው የምርት ዕድገትን የሚያሳይ  ስታቲስቲካዊ መረጃ፤ የዝናብ እና የተበላሸ የሐብት ቆጠራ ውጤት ነበር›› የሚለው መጽሄቱ ፤ ‹‹አፍሪካ በጦርነቱ እየተሸነፈች ነው፡፡ ዛሬም አፍሪካ በሁሉም ሰንጠረዦች ከግርጌ ትገኛለች፡፡ በአፍሪካና በቀረው ዓለም ያለው የሐብት ልዩነት በየጊዜው እየሰፋ እንጂ እየጠበበ ሲመጣ አይታይም›› በማለት፤ ፖል ከሊየር የተባሉ አንድ የዓለም ባንክ ሠራተኛ የተናገሩትን ቃል ይጠቅሳል፡፡
ፖል ከሊየር፤ ‹‹ከአፍሪካ ህዝብ ውስጥ ቀጣይነት ያለው ዕድገትና ልማት መፍጠር የሚያስችል ዝቅተኛው ምቹ ሁኔታ  ያለው 15 በመቶው ህዝብ ብቻ ነው፡፡ ቢያንስ 45 በመቶው የአፍሪካ ህዝብ አሁንም በድህነት ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ ይህን አኃዝ በግማሽ ለመቀነስ፤ የአፍሪካ ሀገራት ለ15 ዓመታት 7 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል›› ሲሉ መናገራቸውን አስፍሯል፡
በ1999 ዓ.ም (እኤአ) ከሰሐራ በታች ካሉት ሀገራት ውስጥ ፈጣን ዕድገት ያስመዘገቡት ሦስት ሀገሮች ብቻ መሆናቸውንና እነሱም ኮንጎ ብራዛቪል፣ አንጎላ እና ሩዋንዳ እንደሆኑ የጠቀሰው ዘገባው፤ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ነዳጅ አምራች አገራት እንደሆኑና የነዳጅ ሀብት ልማት ሌሎች የኢኮኖሚ መስኮችን እንደሚያጠፋ ገልፆ የታየው ተስፋ አልፎ ሂያጅ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ፤ የሩዋንዳ ዕድገት በእርዳታ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን በመግለፅ፤ በአጠቃላይ ከሰሐራ በታች ባለው የአፍሪካ ክፍል፤ ከደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና እና ሞርሺየስ በቀር ሌሎቹ ሀገራት ለዕድገት አስፈላጊ የሆነ መዋቅራዊ ሁኔታ እንደሌላቸው አትቷል፡፡ አያይዞም፤ በአፍሪካ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መነቃቃትን ሊፈጥር የሚችለው በከተማ የሚኖረውና የተማረው መካከለኛ መደብ የህብረተሰብ ክፍል ቢሆንም ይህ የህብረተሰብ ክፍል በኤድስ እያለቀ በመሆኑ፤የወደፊቱ የአፍሪካ ሁኔታ ተስፋ የለሽ እንደሚሆን ይገልፃል፡፡ ስለዚህ አፍሪካ፤ ቁጥሩ የበዛ ድሃ፣ በትምህርት ያልገፋ እና አብዝቶ ተስፋ ያጣ ህዝብ የሚኖርባት አህጉር ትሆናለች ይላል፡፡
ይህን ሁሉ ካለ በኋላ፤ ‹‹ዘ ኢኮኖሚስት›› አንድ ጥያቄ ያነሳል፡፡ ‹‹አፍሪካ ኋላ ቀር እና ልማት መፍጠር የተሳናት አህጉር ሆና እንድትቀር ያደረጋት ባህርያዊ ችግር አለባት እንዴ?›› ይልና ለጥያቄው ምላሽ ይሰጣል፡፡ ‹‹አንዳንዶች አፍሪካ ባህርያዊ ችግር አለባት ብለው ያስባሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች፤ ጦርነት እና ሙስና የአፍሪካ ባህርያዊ ችግሮች ናቸው፡፡ የአፍሪካ ህብረተሰብ ዘላቂነት ያለው መንግስት መፍጠር አይችሉም የሚል እምነት አላቸው፡፡ ባለፉት ጊዜያት፤ ከአህጉሪቱ ውጭ ያሉ ወገኖች የአፍሪካን ውድቀቶች ከዘር ጋር አያይዘው ይመለከቱት ነበር። አንዳንዶች ዛሬም ድረስ ከዘር ጋር ያያይዙታል›› ይላል፡፡
እነዚህ ወገኖች፤ ‹‹ጥቁር ህዝብ ማሰብ አይችልም። እርሱ ሊገዛ የተፈጠረ ነው›› የሚል አስተሳሰብ እንዳላቸው ገልፆ፤ ‹‹በአፍሪካ የሚታየው ጦርነት፣ ሙስና እና ጎሰኝነት የማይለወጥ የአፍሪካ ተፈጥሮ ነው፡፡ እናም የአፍሪካ ህብረተሰቦች የጸና መንግስት ለረጅም ዘመን ማቆም አይችሉም›› የሚል ሐሳብ እንደሚያንጸባርቁ ያትታል፡፡
‹‹ዘ ኢኮኖሚስት›› አያይዞ፤ ‹‹ይህ ስህተት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ለአፍሪካ ወድቀት መንስዔ የሆኑ ባህላዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ለችግሩ አስተዋጽዖ አላቸው የሚለው ጉዳይ ዝም ተብሎ ሊታለፍ የሚችል አይደለም›› ይልና፤ ‹‹አንዳንድ ሰዎች ችግሩን፤ ዓለም ለአፍሪካ ካለው አመለካከት ጋር በማያያዝ፤ በባሪያ ንግድ እና በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈጸመውን ብዝበዛ ለችግሩ በምክንያትነት ይጠቅሳሉ፡፡ ከአፍሪካ ነጻ መውጣት በኋላ ባሉት 30 ዓመታት፤ በተለይም በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን አምባገነን መንግስታትን ለመደገፍ ሲደረግ የነበረውን ሽኩቻ በማውሳት ይወቅሳሉ›› ይላል፡፡ አክሎም፤ ‹‹ዛሬ ደግሞ የአህጉሪቱን ሰቆቃ ከብድር፣ ብዝበዛ ከተጠናወተው የንግድ ግንኙነት ጋር ያያይዙታል፡፡ IMF እና World Bank የሚፈጥሩትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጫና ለአፍሪካ ውድቀት መንስዔ አድርገው ያቀርቡታል›› ብሏል፡፡
‹‹ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ሰበቦች፤ አፍሪካ አሁን የሆነችውን እንድትሆን ያደረጓት ምክንያቶች አይደሉም›› የሚለው መጽሄቱ፤ ‹‹አህጉሪቱ የውጭ ተፅዕኖዎች ሰለባ ነች የሚሉ ወገኖች ማስተዋል ያለባቸው፤ በእስያም ተመሳሳይ የቅኝ ግዛት ታሪክ ያላቸው ሀገሮች መኖራቸውን ነው። እነዚህ የእስያ ሐገሮች ከነፃነት በኋላ በአንድ ትውልድ ዕድሜ ውስጥ የፀና መንግስትና ስኬታማ ኢኮኖሚ ሲፈጥሩ አይተናል፡፡ ያልተሳካላቸው የእስያ ሐገራትም፤የቀድሞ የቅኝ ገዢ ጌቶቻቸውን ሲወቅሱ አናያቸውም›› ሲል ሐሳቦቹን ያጣጥላል፡፡
በሌላ በኩል፤ ‹‹አፍሪካ ራስን የማጥፋት ዓመል የተጠናወታት አህጉር ናት›› ብለው የሚያስቡ  ወገኖች መኖራቸውን የጠቀሰው መፅሔቱ፤ ‹‹በአፍሪካ የሚስተዋሉት እንከኖች በሌሎች ሀገሮች የሚታዩ እንከኖች መሆናቸውን መቀበል አለብን›› ይልና፤ ‹‹በአፍሪካ ያለው ሙስና በእስያ እና በአየርላንድም አለ፡፡ አምባገነን መንግስትም በሰሜን ኮርያ አለ፡፡ ሙስና ከሞላ ጎደል በየትም ቦታ ይታያል። በአጭሩ የአፍሪካ ችግር የእርሷ የብቻ ችግር የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን የአፍሪካ ሐገራት ችግሮች ቅንብር፤ ከሌሎች ሐገራት የተለየ ሳይሆን አይቀርም›› በማለት ይደመድማል፡፡
መፅሔቱ ዝም ብሎ ዳር- ዳር እያለ ይግደረደራል እንጂ ማለት የፈለገው አንድ ነገር ነው፡፡ ‹‹ዘ ኢኮኖሚስት›› ፖለቲካዊ ትክክለኝነት እንዳያጣ ፈርቶ ነው እንጂ፤ ‹‹ጥቁር ህዝብ ሰው አይሆንም›› ማለት የፈለገ ይመስለኛል። ለመሆኑ ‹‹የአፍሪካ ችግሮች ቅንብር ከሌሎች የተለየ ነው›› ማለት ምን ማለት ነው? ‹‹ቅንብሩ የተለየ ነው›› ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ፤ በማያሻማ መንገድ መግለፁ ቀርቶ፤ በደፈናው እንኳን ማብራሪያ አልሰጠም፡፡ ይልቅስ የጀመረውን አንጠልጥሎ ትቶ፤ ቀጥሎ በሚያመጣው ንዑስ ርዕስ (“Nature’s bad hand” -የተፈጥሮ መጥፎ እጅ)፤ ሥር ሐተታውን ይቀጥላል፡፡
‹‹አፍሪካ አውሮፓውያን የአህጉሪቱን ጫፍ እንኳን ከመርገጣቸው በፊት ደካማ ነበረች፡፡ ተፈጥሮ የጨከነችባት ምድር ነች፡፡ የሰው ዘር የትውልድ ሥፍራ ልትሆን ትችላለች፡፡ ግን የሰው ዘር ሁሉ መኖር የሚፈልገው ከአፍሪካ አህጉር ውጭ ነው፡፡ ይህ ነገር ሊያስደንቀን አይገባም›› ይላል፡፡
‹‹ሰው በአፍሪካ ምድር ለመኖር አይሻም። አህጉሪቱ ተስፋ ያላት አይደለችም›› የሚለው መጽሄቱ፤ ይህን ብሎ አይበቃውም፡፡ በመቀጠል፤ ‹‹አፈሩ ብዙ ጊዜ ያልዳበረና የሳሳ በመሆኑ ከጥቂት የአዝመራ ጊዜ በኋላ ምርት አይሰጥም፡፡ ፀሐዩ ያቃጥላል፡፡ ዝናቡም፤ ወይ ጨርሶ አይመጣም (እንደ ኢትዮጵያ)፤ ወይ ያገኘውን ሁሉ ጠራርጎ የሚወስድ አደገኛ ጎርፍ ይሆናል (እንደ ሞዛምቢክ)። የአፍሪካ ተባዮች እና ነፍሳት ትላልቅ ናቸው። ይናደፋሉ፡፡ ይናከሳሉ፡፡ አፍሪካ ለሰው ልጅ፣ ለሰብል እና ለእንስሳት ሁሉ ጠንቅ የሚሆኑ በሽታዎች የሞላባት አህጉር ናት›› ይላል፡፡ ይህን የመሰለ የተዛባ አመለካከት የሚያቀርበው መፅሔቱ፤ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ የምዕራብ ዘዬ ዲሞክራሲን ገሸሽ እያደረጉት መሆናቸውን ከጠቀሰ በኋላ ‹‹የኡጋንዳን የፓርቲ አልባ (No- party) ዲሞክራሲ፤ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለመቅዳት አልሞከሩም፡፡ የአፍሪካ ዲሞክራሲ የእርዳታ ሰጪዎች ዲሞክራሲ (Donor democracy) ነው›› ይላል። በመቀጠል፤ ‹‹ዲሞክራሲ ለአፍሪካ ብዙ አይጠቅማትም። በአፍሪካ ያሉ የዲሞክራሲ አስተዳደሮች ከአምባገነን አስተዳደሮች የተሻለ መረጋጋት ያላቸው አይደሉም። የእርስ በእርስ ጦርነት በየቦታው ይታያል›› በማለት ይደመድማል። ዲሞክራሲ የሚባል ነገር የማታውቀው ሱዳን፤ የ7 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኗንም በአስረጅነት ይጠቅሳል፡፡
ይሁንና ‹‹አብዛኛው አፍሪካ የሚገዛው በዝናብ እንጂ በፖለቲካ አይደለም›› የሚለው ‹‹ዘ ኢኮኖሚስት›› ፤ዛሬ ዘፈኑን ሳይቀይር አይቀርም። ዓለምም ‹‹ኢትዮጵያውያን ወደ ጥንቱ እንቅልፍና ቅዠታቸው፤ ሁከትና ጦርነታቸው ይመለሱ ይሆን?›› እያለ ይጠይቃል፡፡
ይህ ጥያቄ ለኢትዮጵያውያን ፈታኝ ተግዳሮቶችን የያዘ ጥያቄ ነው፡፡ በአለፉት ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግበናል፡፡ ዓለም ይህን ያውቃል፡፡ ጥያቄው ይህ ዕድገት አስተማማኝ ጎዳና ይዞ ይቀጥላል ወይስ የበርሃ ምትሃት ሆኖ ይቀራል? የሚለው ነው፡፡ እንደኔ አስተያየት፤ የዚህ ጉዞ ቀጣይነት የሚወሰነው መንግስት በሚያራምደው ፖሊሲ ወይም በስርዓቱ ባህርይ መሆኑ ባይቀርም፤ እጅግ ወሳኙ ግን ህዝቡ ነው፡፡ ህዝቡ ‹‹ተሻግሬው ወደ መጣሁት ሸለቆ ተመልሼ አልገባም›› የሚል ቁርጠኛ ፅናት በመያዝ-አለመያዙ ይወሰናል፡፡
በተስፋ ያለች ሐገር
ሀገራችን አሁን የያዘችው ጉዞ አጓጊ ነው፡፡ በአፍሪካ አህጉር በሁለተኛ ደረጃ የሚያስቀምጥ የህዝብ ብዛት ያላት ኢትዮጵያ፤ በዓለም ሦስተኛ ደረጃ የያዘ (ከቻይና እና ህንድ ቀጥሎ) ፈጣን ዕድገት ያለው ኢኮኖሚ ባለቤት ሆናለች፡፡ የእንግሊዙ የኢኮኖሚ ኢንተላጀንስ ዩኒት አምና (ታች አምና) ባወጣው አንድ ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ በመጭዎቹ ዓመታት ዛሬ ተቀዳሚ የሆኑትን ህንድና ቻይናን የምትስተካከል ሀገር እንደምትሆን ግምቱን አስቀምጧል፡፡
በአሁኑ ጊዜ፤ 32.3 ቢሊየን ዶላር (470 ቢሊየን ብር) በሆነ ጠቅላላ ዓመታዊ የምርት መጠን የአፍሪካ አራተኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ ተፈጥሯል። በምስራቅ አፍሪቃ ቀዳሚ የነበረውን የኬንያ ኢኮኖሚ በመቅደም በአፍሪካ ቀንድ ክፍለ- አህጉር ትልቅ ኢኮኖሚ መገንባት ተችሏል። የተጀመረው የ5 ዓመት የትራንስፎርሜሽን እና ዕድገት ዕቅድ (2011-2015) በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ኢንዱስትሪ በአማካይ የ20% ዕድገት  ያስመዘግባል፡፡ የዕቅዱ መሳካት ኢትዮጵያን በአህጉሩ ሦስተኛ ደረጃ የሚይዝ ኢኮኖሚ ባለቤት ያደርጋታል፡፡
የ85% የሀገሪቱ ህዝብ ከቀለብ በማያልፍ የግብርና ምርት ላይ የተንጠለጠለ ነበር፡፡ ኢኮኖሚው፤ ግብርና ሰፊ እጅ የያዘበት ኢኮኖሚ ነበር፡፡ ሆኖም ከአለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ግብርና ለጠቅላላ አገራዊ ምርቱ ያለው አስተዋፅዖ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ በ2001 ዓ.ም የአገልግሎት ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ 45% ሲደርስ፣ የግብርናው 43% ሆኗል። በ2002 ዓ.ም የአገልግሎት ዘርፉ ድርሻ 46% ሲሆን  ግብርና 41% ነበር፡፡
ኢኮኖሚያችን መዋቅራዊ ለውጥ እየፈጠረ ለመሆኑ ማሳያው፤ በ2002 ዓ.ም ሰኔ ወር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገቢ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ በተጠቀሰው ዘመን ዋነኛ የኤክስፖርት ምርት የነበሩት እህል እና ቡና ከፍተኛ ዕድገት አሳይተው የተገኘው ገቢ 842 ሚሊየን ዶላር ነበር። ታች አምና በሁለተኛው መንፈቀ ዓመት ከቅባት እህሎች ኤክስፖርት ከተገኘው ገቢ ይልቅ የወርቅ በልጦ ነበር፡፡
በአጠቃላይ በዕድገት እና ትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ ዘመን (2011-15) የኢንዱስትሪው ዘርፍ ድርሻ 20% እንደሚሆንና በግብርናው እና በአገልግሎት ዘርፍም ዕድገቱ እንደሚቀጥል ተተንብይዋል፡፡ አንዳንድ ተንታኞች፤ በቀጣዮቹ 15 ዓመታት የጠቅላላ አገራዊ ምርት መጠን 472 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ፤  በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ወደ 4000 ዶላር እንደሚያድግ ትንበያ አድርገዋል። ይህም ኢትዮጵያን በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙ ሦስት ኃያል ኢኮኖሚዎች አንዱ እንደሚያደርጋትም ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡
በዚህ ሂደት የምንፈጥራቸው ወይም የሚገጥሙን ለውጦች ተፈላጊ ሆኑም አልሆኑ፤ከፊታችን የምናገኛቸው ለውጦች ለብዙዎቻችን አቅል የሚነሳ ረብሻ የሚያስታቅፉን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሂደት የምናገኘው ውጤት በኢኮኖሚ መስክ ብቻ የሚታይ ሳይሆን፤ ከዚያ ክበብ አልፎ የሚሄድ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ አህጉራዊና ክፍለ አህጉራዊ ትስስራችንም ያጠናክረዋል።
ኢትዮጵያ የምትፈጥረው ሀብት ለአካባቢው ሀገሮችም ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው በግልፅ እየታየ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጥንካሬ እና ዕድገት የጋራ ልማትን የሚያጎለብት እንጂ ሥጋት አለመሆኑም ግንዛቤ እያገኘ  ነው፡፡ ኢትዮጵያ ልማቷን ከጎረቤቶችዋ ሰላም ጋር አስተሳስራ የምታይ መሆኗ በተጨባጭ ሲረጋገጥ፤ የእርሷም ሰላም  ዋስትና እያገኘ ይመጣል። የእስካሁን አካሄዷም በጎረቤቶቿ ዘንድ የነበራትን ጥርጣሬ እየገፈፈው መጥቷል፡፡  
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት፤ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም በኋላ ወሳኝ ሆኖ በመጣው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አብዮት በፈጠረው በረከት (መርገምት) እየተቃኘ የሚቀጥል ይሆናል። እነዚህና ሌሎች ጉዳዮች የጉዞው ጭፍራ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች የሚፈጥሩት በረከት ወይም መርገምት አሁን ማወቅ ከቻልነው አድማስ የሚሻገር ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው ማሰብም ተገቢ ነው፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ ተስፋ ሊሳካና ‹‹የኢትዮጵያ የልማት ደመራ ወዴት ይወድቅ ይሆን?›› እያለ በአንክሮ የሚመለከተው የዓለም ህዝብ፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን ተስፋቸውን አላመከኑትም›› ብሎ፤ በአድናቆት ሊጨብጠን የሚጋፋው፤ ኃላፊነቱን መወጣት የሚችል ንቁ ህዝብ እና አመራር፤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚያመርት አርሶ/አርብቶ አደር እና ወረቱን የማይበላ ታታሪ ባለሐብት መፍጠር ከቻልን ብቻ ነው፡፡
በተጨማሪም፤ አሁን ተግባራዊ እያደረግነው ባለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና በትብብር መንፈስ የተቃኘ አካሄድ መከተል ለልማት እና ሰላማችን መረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ከጀርመኖች ታሪክ መማር የሚገባን ጉዳይ አለ። ጀርመኖች ከባዶ ተነስተው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲቀዳጁ፤ ከስህተታቸው ተምረው፤ ከወደቁበት አመድ ተነስተው በአጭር ጊዜ ወደ ቀደመ ሥፍራቸው በተመለሱ ጊዜ፤ ብዙዎች ጀርመናዊያን ብልፅግናው የሚያስገኘውን የኃያልነት መንፈስ በጽኑ ጥርጣሬና ሥጋት ይመለከቱት ነበር። እብሪት ያመጣባቸውን መከራ በደንብ ስለተረዱ፤ አብዛኛው ጀርመናዊ በኃያልነት ቀይ ምንጣፍ ላይ መራመድን እንደ ጦር ይፈራው ነበር፡፡ የእኛም መሪዎች ከሰሩት ይልቅ፤ ሊሰሩት የሚገባው ነገር እየታያቸው እንቅልፍ የሚያጡ መሆን አለባቸው፡፡

Read 2343 times