Monday, 06 April 2015 08:44

“ዜጋ” መጽሐፍ እየተነበበ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

በአንጋፋዋ ጋዜጠኛ ፍሬወይኒ ግደይ የተፃፈውና በግብረሰዶማዊያን እውነተኛ ታሪኮች ላይ የሚያጠነጥነው “ዜጋ” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ በቃ። በአንድ ኤምባሲ ስለተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ጥናት እንድታካሂድ ተጠይቃ፣ ከብዙ ማመንታት በኋላ ጥናቱን መስራቷን ከትናንት በስቲያ በጊዮን ሆቴል ሳፋሪያን አዳራሽ በመፅሐፉ ዙሪያ ለጋዜጠኞች በሰጠችው መግለጫ የተናገረችው ጋዜጠኛ ፍሬወይኒ፤ ጥናቱ ላይ ተመስርታ መጽሐፉን ማዘጋጀቷን ገልፃለች፡፡
የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት በአገራችን በርካታና ውስብስብ ችግሮች እያስከተለ እንደሆነ፣ የችግሩ መጠንና ጥልቀትም አሳሳቢ መሆኑን በጥናቷ ማረጋገጧን የገለፀችው ጋዜጠኛዋ፤ ጥናቱ አስቸጋሪና እልህ አስጨራሽ እንደነበር ተናግራለች። ለኤምባሲው ጥናቱን ጨርሳ ካስረከበች በኋላ ግብረ ሰዶማዊያኑ ያሉበት መጠነ ሰፊ የጤናና የስነ - ልቦና ችግር፣ ማህበረሰቡ የሚሰጣቸው ግምትና የእነሱ ያልተጠበቀ ሰብዕና እንዲሁም በጥናቷ ወቅት ያገጠማት ችግሮች ማህበረሰቡን እንደሚያስተምርና በዚህ ችግር ውስጥ ላሉትም መፍትሔ ሊሆናቸው እንደሚችል በማሰብ መጽሐፉን አዘጋጅታ እንዳሳተመችው ገልፃለች፡፡
“ማንም ሰው ይህን መጽሐፍ ለመንቀፍም ሆነ ለመደገፍ እስከመጨረሻው እንዲያነበው እማፀናለሁ” ብላለች ጋዜጠኛዋ፡፡
መጽሐፉ ከችግሩ ሰለባዎች፣ ከታሪካዊ ዳራዎች፣ ከሃይማኖት፣ ከስነ - ልቦናና ከጤና አኳያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተደረጉ ቃለ ምልልሶች ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ሲሆን ከሁሉም አቅጣጫ ለሚነሱ ጥያቄም መልስ ለመስጠት ይሞክራል ተብሏል፡፡ በ169 ገፆች የተቀነበበው  መጽሐፉ፤ በ50 ብር ከ60 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡

Read 3115 times