Tuesday, 14 April 2015 08:50

“ቢገድሉንም አልሞትንላቸውም”

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(7 votes)

ከዛሬ አምስት ዓመታት አስቀድሞ …
… ስብሐት ገብረእግዚአብሔር በተለመደ ስልቱ፤ ሹራቡን ጭንቅላቱ ላይ ጣል አድርጎ፣ አፍላዋን ፀሐይ እየተከላከለ፤ ምናልባትም ፌስታሉን ይዞ ሲጓዝ…
“ከፊቴ አንድ በእድሜ ከእኔ እኩል የሚገመቱ ሰውዬ ቆመው አገኘሁ” ይላል ማስታወሻው ላይ፡፡
እጅ ተነሳሱ፣ ተጨባበጡ፡፡ እና …
“እኔ እንኳ ጌታዬን አውቅዎታለሁ” አሉ በትግርኛ፡፡
“የጌታዬ ልጅ እንጂ” አልኳቸው ይላል ስብሐት “ውቃቢዬ እየወደዳቸው ለምን ሊያገኙኝ ፈለጉ … ምን ላደርግልዎት እችላለሁ?”
“የፃፍኩዋት አጭር ልቦለድ አለችኝ፡፡ ጊዜ ሲያገኙ ቢያነቡዋትና እንዴት ላሻሽላት ወይም ለአንባቢ ላሳምራት እንደምችል ምክር ቢለግሱኝ በሚል ተስፋ ነው፡፡ እኔ የተማርኩት ለማንበብና ለመፃፍ እስከምችል ብቻ ነው፡፡ እርስዎ ግን …”
“ኃላፊነቱን በደስታ ተቀብያለሁ” አላቸው፡፡ እና…
“… ከዚያ በተረፈ፣ አገኛለሁ ብዬ አስቤው የማላውቅ ሰው በአቅሙ ሰውን የመደገፍ አጋጣሚ ስለታደለኝ ነብሴ ተደስታለች፡፡” በማለት ስብሐት ያጠቃልላል፡፡
መፅሐፉ የወታደር ገብረሥላሴ ተስፋዬ ሲሆን “ሁለቱ ድልድዮች - ቢገድሉንም አልሞትንላቸውም” በሚል ርዕስ በ2002 ዓ.ም ታትሟል፡፡ ትልቅ ልግስና ነበር፡፡ ስብሐት የአዛውንቱን የመጨረሻ ምኞት ያሳካበት ሥራ ነው፡፡ ግን ደግሞ አመስጋኙም እራሱ። ልብ ላለው ሰው ተቀባይ አገልጋይ ነው፡፡ ስብሐት “በመስጠቱ” መደሰቱ ለዚያ ነው፡፡
ስብሐት አርትኦት ባደረገው በዚህ መፅሐፍ ላይ ያፈሰሰውን ጉልበትና ጊዜ መተመን ይከብዳል። የስብሐት አስተዋፅኦ ገዝፎ የታየኝ አርትኦት የተሰራበትን ረቂቅ ስለተመለከትኩ ነው፡፡ አርትኦቱ የቃላት፣ የአረፍተ ነገር፣ የሀሳብ እና የአቋም በመሆኑ እንደ ከፍተኛ ደረጃ አርትኦት ማየት ይቻላል፡፡ ቀላል አርትኦት ባለመሆኑ ያልተሰረዘ አንድ እንኳን መስመር ማግኘት ይከብዳል፡፡ ይሁንና ስብሐት አርትኦታዊ አድራጎቱን ሲያበረክት “ቀኝ እጁ” የሰጠውን “ግራ እጁ” አልተመለከተውም፡፡ እንደውም እንዲህ ይላል።
“… ሃሳቦችም ደጋግመው እንደመጡልን እየደጋገምን እንናገራቸዋለን፡፡ ይሄ ለአንባቢ ትኩረት እንቅፋት ስለሚሆን ሰርዤዋለሁ … ያን ያህልም የሰራሁት አርትኦት የለም፡፡”
ስብሐትን ከደራሲነት ባሻገር በአርታኢነት የመመርመር ፍላጎት ስለነበረኝ ሦስት ያህል ረጃጅም ስራዎች ያረመባቸውን ረቂቆች አሰባስቤአለሁ። ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ከቃላት አንስቶ እስከ ደራሲው አቋም ድረስ በመዝለቅ እርማት ያካሄደው “ቢገድሉንም አልሞትንላቸውም” ብሎ ሰየመው መፅሀፍ ብቻ አይደለም፡፡ እኔ ባገኘኋቸውና ባላገኘኋቸው የተቀሩት ስራዎችም ላይ ይሄንኑ ከማረም ይልቅ ለፈጠራ የቀረበ እርዳታውን አከናውኖ ይስተዋላል፡፡ አንድ አርታኢ የተጣመመ ከማቃናት አልፎ እሰው ስራ ውስጥ ሀሳቡንና አቋሙን ማካተት ትክክል ነው? የአርታኢነት ገደቡ እምን ድረስ ነው? ለመሆኑ አርታኢ የተጨናበሱ ቃላትን በልዋጭ አማራጭ ከመተካትና የተድፈነፈኑ አረፍተነገሮችን ከማፍታታት ባለፈ የደራሲውን ሀሳብና አቋም እስከ መለወጥ መዝለቅ አለበት? … ጋሽ አስፋው ዳምጤ ከደራሲ እምወድሽ በቀለ ጋር ሲወያዩ ያሉትን እንመልከትና እንለፍ፡-
“የአርታኢ ተግባር የፀሐፊውን ሀሳብ አንብቦ በመረዳት እሱ ሊያመጣው ያልቻለውን እንዲመጣ ማድረግና ሰዋሰዋዊ ችግሮችን ማየት፣ የሆሄያትን መምታታት፣ የዐረፍተ ነገር ድግግሞሽ እንዳይኖር በሦስትና በአራት ዓይነት ያንኑ መመላለስና ዝብርቅርቆሹን ማየት ነው፡፡” (ብሌን ቁጥር 3 ታህሳስ 1999)
ስብሐት አርታኢ ሲሆን ስብሀታዊ ሰዋሰውን ብቻ ሳይሆን ስብሐታዊ ሐሳቡን፣ አቋሙንና ፈጠራውን በማካተት ሥራውን የእራሱ ቅጂ ያደርገዋል፡፡ ይሄ ደግሞ የሚጎዳ ባይሆንም የትክክልነት ተጠየቅ ያለበት ይሆናል፡፡ የትኛውም ሥራ “ማንነት” ያለው ይመስለኛል፡፡ ደራሲው ከሌሎች ደራሲዎች እንደሚለይ ሁሉ ስራውም ከተቀሩት ስራዎች የጠባይ፣ የምርጫና የአኳኋን ማንነት ያንፀባርቃል፡፡ ለምሳሌ የሀዲስ ዓለማየሁ፣ የበአሉ ግርማና ራሱ የስብሐት ስራዎች አንዱ ካንዱ በሁለንተናው እንደማይገጥመውና እንደሚለየው ማለት ነው፡፡ አሁንም ለምሳሌ ስብሐት የሀዲስ ዓለማየሁን ሆነ የበአሉ ግርማን ስራዎች አርትኦት እንዲሰራ ቢሰጠው መንፈሳቸውን ለውጦ ፍፁም ስብሐታዊ ማንነት መስጠት አለበት? ጥያቄው ይሄ ነው፡፡ እንደገና ምሳሌ እንስጥና ከ “ቢገድሉንም አልሞትንላቸው” ውስጥ መግቢያውን እንቃኝ፡
“ከመረብ ወንዝ ወዲህና ወዲያ ማዶ እስከ 83 ዓ.ም የነበረው የሦስቱ ኃይሎች፣ ማለትም ደርግ - ወያኔ - ሻአቢያ የፖለቲካ ባህሪ ምን እንደነበረ፣ በመሀከላቸው እየተጨፈለቅኩ ያየሁትንና ያሳለፍኩትን አበሳ ለተከበራችሁ አንባቢያን በትህትና ሳቀርብ፣ ሀቅ የሁላችን ፀጋ ናት በሚል እምነት፣ ይሄ ታሪኬ እኔ በማላውቀው መንገድ ይጠቅማችሁ ይሆናል ብዬ ነው፡፡”
እዚህ መግቢያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ “ስብሐታዊ መንፈስ” ሲንፀባረቅ እናስተውላለን፡፡ ሰለሞን ዴሬሳ ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት እንዳለው ነው፡፡
“የስብሐት የአማርኛ አፃፃፍ የትም ባየውና ባይፈርምበትም የስብሐት መሆኑን አውቃለሁ፡፡ መጀመሪያ መቅለሏ፣ የዐረፍተ ነገሩ ማጠር፣ ቁጭ ብለህ የምትነጋገር ነው የሚመስልህ፡፡”
(ሪፖርተር መፅሔት፤ መስከረም 1991)
ሰለሞን ካለው ውጭ የስብሐት መንፈስ የሚታወቅበት ሌላም የፅሁፍ ባህርይ አለ፡፡ ስብሐት ሆን ብሎ አራት ነጥብን ይሸሻል፡፡ አረፍተ ነገሮቹ በውስጠ ታዋቂ አጭርነት ይታይባቸዋል እንጂ በነጠላ ሰረዝ እየረዘሙ፣ አንዳንዴ የመቋጫ አራት ነጥብ ሳይታይ አንድ አንቀፅ ይዘልቃሉ፡፡ እንደውም አንቀፆች እንኳን በአራት ነጥብ የማይደመደሙበት ጊዜ ይበዛል፡፡ እዚህ መፅሐፍ መግቢያ ላይ የሚታየው ይሄ ነው፡፡ ለስብሐት አርትኦት ያደረገበት ረቂቅ ውስጥ መግቢያው በአራት ነጥብ አይደመደምም። መጨረሻ ላይ “ነው” በሚል ቃላትም አይዘጋም፡፡ አንቀፁ ያለ ደጃፍ ክፍቱን የተተወ ነበር፡፡ መፅሐፉ ሲታተም ግን ምናልባት ደራሲው ወይም ሌላ አርታኢ መግቢያውን “ነው” ብሎ በአራት ነጥብ ያጠቃልለዋል፡፡
ስብሐትን ከአርትኦት አንጻር ካየነው አንድ ነገር ያለመጠራጠር እንመሰክራለን፡፡ ስስት የማያውቅ ለጋስ ነው፡፡ የሚለግሰው ግን አዲስ ሳይሆን ወዙ ያረፈበትንና ጠረኑ የታተመበትን የራሱን አልባስ እራሱን ገፍፎ ነው፡፡ ስብሐት በዓሉን አርትኦት ሲያደርገው ሙሉ ልብሱን አስወልቆ፣ የተነሰነሰ ሽቶውን ገፍፎ፣ የተወለወለ ማማውን ወዲያ ብሎ … ፌስታል ያስይዘዋል፣ ሹራቡን እራሱ ላይ ጣል ያደርግለታል፣ እንደነገሩ ያለብሰዋል … እንደማለት ነው፡፡ ይሄ ስብሐታዊ መንፈስ ያረፈበት በዓሉ፤ እውነት “በዓሉ” ነው? የ“ቢገድሉንም አልሞትንላቸውም” ደራሲስ?
ሌላውን ለሌላ ጊዜ ረጅም ጥናት ልተውና ወዳስገረመኝ አንድ ጉዳይ ልለፍ፡፡ ስብሐት “ቢገድሉንም አልሞትንላቸውም” የተሰኘውን ሥራ ሆነ ሌሎቹንም ልቦለዶች “ሲያርም” ባለመብቱ ደራሲ አልፎ - አልፎ የሚፅፈው ማስታወሻ አለው። ስብሐት የሰረዘው ፅሑፍ ከበዛ ወይም ዋና ጉዳይ ከመሰለው ከጎን ምክንያቱን ለደራሲው ይገልፃል። በ “ቢገድሉንም አልሞትንላቸውም” ረቂቅ ላይ ለደራሲ ገብረሥላሴ የተተዉ ብዙ ማስታወሻዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ አስገራሚ የተቀሩትም አስቂኞች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ረቂቁ ላይ በደራሲው አንድ ህልም ቀርቧል። ህልሙ ውስጥ ያለው መልአክ ከባለታሪኩ ጋር የሚያደርገው ዘለግ ያለ ቃለ-ምልልስ አለ፡፡ ስብሐት ይሄንን የመልአክና የሰው ንግግር በሙሉ ካስወገደ በኋላ ለደራሲው እንዲህ የሚል ማስታወሻ ይተዋል፡-
“ህልም ከሆነ መልአክ እንደሰው ወሬ አያበዛም። መልዕክቱን መንገር ብቻ!”
ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ደራሲው ስለአንድ ከሞት ጋር የመጋፈጥ ጉዳይ እንዲህ በማለት ይተርካሉ። “አየሩ ቢመታ - ቢቃጠል አብሬ እጠፋ ነበር፤ እንዴት ቢባል፣ የማይቀር ከሆነ አብሬህ ልሙተው እንደማለት አቋም ነበረኝ፡፡” ስብሐት ይሄን ዐረፍተ ነገር ይሰርዝና ደራሲውን እንዲህ ይላቸዋል፡-
“ለገብረሥላሴ፣ እኔ ስለማውቅህ አምንሀለሁ ለማያውቅህ አንባቢ ግን ጉራ መንፋት ስለሚመስል ሰርዤዋለሁ፡፡”
የመጨረሻ አንድ ልጨምርና ልሰናበት …
… ማስታወሻዋ ቀደም ሲል የአቋም አርትኦት ላልነው ምሳሌ የሚሆንም ጭምር ነው፡፡ ደራሲው ስለ ኢትዮ ኤርትራ መዋሃድና መለያየት፣ ያላቸውን አቋም በሦስት ገፅ አቅርበዋል፡፡ ስብሀት እነዚህን ገፆች በመሰረዝ ለደራሲው ይሄን ማስታወሻ ይተዋል፡-
“አያ ገብረሥላሴ፣ እስከ ገፅ 36 ድረስ ድንቅ የሀቅ ዘገባ ስለሆነ እኔም በበኩሌ በቀረችኝ አጭር ዕድሜም ቢሆን፣ ብዙ ብዙ ሰዓትና ጉልበት አዋጥቼ ይህን የመሰለ Masterpiece ለህትመት ማድረሳችን የመሰጠኝን መንፈሳዊ እርካታ ልትገምት ትችላለህ፡፡
የዘመንህ ቋሚ ምስክር ሆንክ! “ማጠቃለያ” ያልከው ግን፣ ያሁኑን የመለስና የኢሳያስ፣ ፍጥጫ እያወቅክ፣ ለEthio Eritrean Re-Union አቅጣጫና በቂ ምክንያት እያቀረብክ ይመስልሀል እንጂ፤ እኔም አንተም በጨረፍታ ብቻ የምናውቀው የሀገር ጉዳይ ውስጥ ምንም ልዩነት ላታመጣ “ሳይጠሩህ ጥልቅ ብለህ” የቀረችህን ሰላማዊ ኑሮ አደጋ እንዳታደርስባት አደራህን፤ ከዚህም ጋር እኔ አርታኢ፣ አቤል አሳታሚ በመሆናችን፣ እስከዛሬ በጥንቃቄ ገለልተኛ በነበርንበት ፖለቲካ ውስጥ ገባችሁ ተብለን …”
በሌሎቹ የስብሐት አርትኦቶች በሌላ ጊዜ እስክንገናኝ እንሰነባበታ፡፡

Read 5688 times