Saturday, 25 April 2015 10:40

ጽናቱን ይስጠን…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“እኔም ተመለስሁ፣ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፡ እነሆም የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፣ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፣ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፣ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም፣”
ይላል መጽሐፈ መክብብ፡፡ የተገፉትን እንባ ያድርቅልን፡፡
ብሞት እሄዳለሁ ከመሬት ብገባ
ከዛ ነው አፈሩ የእማማ ያባባ
ስሳብ እሄዳለሁ ቢሰበርም እግሬ
አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ አገሬ
   አለብኝ ቀጠሮ
ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ፡፡
ብሎ ነበር ገብረ ክርስቶስ ደስታ፡፡ ከትውልድ አገራቸው ጋር ‘ቀጠሮ ያላቸው’ ሚሊዮኖች ወገኖቻችን በየአገሩ እየተንከራተቱ ነው፡፡ ማንም ከማንም የማይለይባት፣ ከልጅ ልጅ የማይመረጥባት የተስፋይቱ ምድር ከሆነች አገራቸው ጋር ቀጠሮ ያለባቸው ብዙዎች አሉ፡፡
ከትውልድ አገራቸው ጋር የነበራቸው ቀጠሮ በአጭሩ የተቀጨባቸው ወገኖቻችንን እግዚአብሔር በሰማይ ቤት ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን፡፡
ይሄ ሰሞን ለኢትዮዽያውያን የመከራ ሰሞን ነው፡፡ በተከታታይ ቀናት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ባሉ ወገኖቻችን ላይ የደረሱ ሰቆቃዎች ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው እንኳን ሊቀበላቸው፣ ይሆናሉ ብሎ የሚያስባቸው አይደሉም፡፡ በሌላ በኩል የሰው ልጅ እውነትም ከእንስሳት ሁሉ በባሰ ጨካኝ ሊሆን እንደሚችል ማሳያ ናቸው፡፡ በሊቢያ ከሰው ጋር ሊመደቡ የማይችሉ አውሬዎች በንጹሀን ወገኖቻችን ላይ የፈጸሙት ጭካኔ በምን አይነት ቃላት መግለጽ እንደሚቻል አንድዬ ይወቀው፡፡ የክፋትም፡ የጨካኝነትም፣ የአውሬነትም፣ የነውረኝነትም የሆኑ መስመሮች አሉ፡፡ የእነኚህኞቹ ግን በምን አይነት መለኪያ ላይ የሚቀመጥ አይደለም፡፡
ድንግል አገሬ ሆይ ጥንተ ደናግሎ
ሕፃናቱም ታርደው ያንቺም ልብ ቆስሎ
ልጅሽ ተሰደደ አንቺን ተከትሎ
የህፃናቱን ደም አዘክሪ ኩሎ፤
ይላል ዮሐንስ አድማሱ፡፡
በሀዘን ስሜትም ውስጥ ሆነን ግን ጊዜው ራሳችንን መልሶ መመልከቻ መሆን አለበት፡፡ ጓዳ ጎድጓዳችንን የምንፈትሽበት ጊዜ ነው፡፡ ወገኖቻችንን “ለምን ይሰደዳሉ?” የሚል ጥያቄ ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል፡፡ ለምን እንደሚሰደዱ ግልጽ ነውና፡፡
ከሳውዲ ዓረቢያ ከዛ ሁሉ ሰቆቃ በኋላ ወደ አገር ቤት ተመልሰው የነበሩ ብዙዎቹ እንደገና በህገ ወጥና እጅግ አደገኛ በሆኑ መንገዶች ለመሄድ የሚሞክሩት ለምን እንደሆነ እውነቱን ፊት ለፊት መጋፈጥ አለብን። ተስፋ ቢያጡ፣ የደከሙ እናት አባቶቻቸውን መደገፍ ቢያቅታቸው፣ ቤተሰቦቻቸውን አብልቶ ማሳደር ቢያቅታቸው፣ መልካም ኑሮ የመኖር ህልማቸውን ለማሳካት መንገዱ ሁሉ እሾህና ጋሬጣ ቢሆንባቸው…መአት ምክንያቶች መደርደር ይቻላል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ወገኖቻችን በቀይ ባህርና በሜዲቴራንያን ውሀ ስለመበላታቸው፣ በየበረሀው የአውሬና የወሮበላ ሲሳይ ስለመሆናቸው እየሰማን፣ በራሳቸውም ይሁን በአሠሪዎቻቸው ከፎቅ እየተወረወሩ ሬሳቸው አስፋልት ላይ ተዘርግቶ በማህበራዊ ድረ ገፆች እያየን፣ በየመንና በሌሎችም ስፍራዎች የድረሱልን ጥሪያቸውን እየሰማን ባለንበት ወቅት… የስደትን አስከፊነት የማያውቅ ይኖራል ማለት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ችግሩ በቀጥታም በተዘዋዋሪም የአብዛኛውን ህዝብ በር አንኳኩቷልና!
የደረስንበት ደረጃ ስለ ስደት አስከፊነት ለበርካታ ዓመታት ሲሰጡ የነበሩ ትንታኔዎችን በመድገም ጊዜ የምናባክንበት አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህን ለመገመት እንኳን አስቸጋሪ ሆኖ የመጣውን መጠነ ሰፊ ስደት ለማቆም ምን መደረግ እንዳለበት መምከር ነው ያለብን፡፡
የኢትዮዽያ ልጆች ሰቆቃ የዓለም ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የምሽት ዓበይት ዜናዎች ማጀቢያ መሆኑ መቆም አለበት፡፡ ግን በፉከራ የሚቆም ነገር አይደለም… በ“በለው በለውና አሳጣው መድረሻ…” የሚለወጥ ነገር አይኖርም፡፡  
ይልቁንም ግን ለምንድነው በዚሁ ሁሉ ስቃይ መሀል ወጣቱም፣ አዛውንቱም የሚተመው ብለን እውነት፣ እውነቱን የማየት ድፍረት ያስፈልጋል፡፡ ከፖለቲካ የነጻ፣ ከዘር የነጻ፣ ከኃይማኖት የነፃ፣ ከበቀልና ከቁርሾ የነፃ፣ ከጥላቻ የነፃ አተያይ ያስፈልገናል፡፡ በቃላትና በመዝሙር፣ በትልልቅ ባንዲራና በአሼሼ ገዳሜ እየሸፋፈንን የምናልፋቸውን ነገሮች አደባባይ አውጥተን እውነቱን የማየት ድፍረት ያስፈልገናል፡፡
አንዲት ከሳውዲ ዐረቢያ ተመልሳ መጥታ የነበረች ወጣት እንደገና እሄዳለሁ ስትል “እዛ ሰዉ ሲሞት እያየሽ እንዴት እሄዳለሁ ትያለሽ?” ስትባል የመለሰችው መልስ አስደንጋጭም ምናልባትም የብዙዎቹን ድምዳሜ የሚያንጸባርቅ ሊሆን ይችላል። “እዚህም እኮ ሞት አለ…” ነው ያለችው። አገር እንዲህ ማለት ሲጀምር በእጅግም አስቸጋሪ ዘመን ውስጥ መሆናችንን ማሳያ ነው፡፡  
እንደሚባለው ሁሉ እውን የተመቻቸ የሥራ ሁኔታ ለሁሉም አለ ወይ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ እውን ከፖለቲካ አመለካከት ሙሉ ለሙሉ የነጻና ‘የተመቻቸ’ የሥራ ሁኔታ በአገሪቱ በሙሉ አለ ወይ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ እውን ከዘርና ከጎሳ ጠባብ አመለካከት ሙሉ ለሙሉ የነጻና ‘የተመቻቸ’ የሥራ ሁኔታ በአገሪቱ በሙሉ አለ ወይ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡
ሰፋ ካለው ዘር የጠበበ በመንደር መሰባሰብ እየተለመደ ባለበት ጊዜ፣ ጠባብነት ወደ አምቻና ጋብቻ እየወረደ ባለበት ጊዜ እውን ከአድልዎ የነጻና ‘የተመቻቸ’ የሥራ ሁኔታ አለ ወይ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ የኮሌጅ ዲግሪያቸውን ይዘው ሥራ ለማግኘት አራትና አምስት ዓመታት የሚንከራተቱ በሺህ  የሚቆጠሩ ወጣቶች ባሉበት ሁኔታ እንደሚባለው እውን ለሁሉም እኩል የሆነና ‘የተመቻቸ’ የሥራ ሁኔታ አለ ወይ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡
መከራ ተረግዛ ተወልዶ ችግር
ሥቃይ ተሞሽራ ሲዘፈን በአገር
ኃዘን ስትዘፍን አታሞ ስትመታ
ድህነት ሲሸልል እየገፋ እምቢልታ
ረሀብ ሲያቅራራ በጣለው ሰለባ
ቀጠና ደረሰ ድምጹ እያስተጋባ
ቡትትም አጊጣ ከድሪቶ ጋራ
ዝተትና ማቅም ሆነው በየተራ
መጡ ከእኔ ዘንዳ አብረውኝ ሊኖሩ
ተስማምተው ደረሱ እየተባባሩ
ብሏል ዮሐንስ አድማሱ፡፡ እንዲህ አይነት እንጉርጉሮ የማንስማበት፣ ረሃብ የማያቅራራበት፣ ሥቃይ የማትሞሸርበት፣ ድህነት የማይሸልልበት ዘመን ማምጣት የምንችለው እኛ ብቻ ነን፡፡ ለዚህ ደግሞ ልባችንን ክፍትና ንጹህ አድርገን ራሳችንን መፈተሽ አለብን፡፡ መለወጥ ያለብንን ለውጠን፣ መያዝ ያለብንን ይዘን ለመቀጠል በኢትዮዽያ ስም መማማል አለብን፡፡
እንዴት ነው ነገሩ?
ብንሄድ  ብንሄድ ጎዳናው አያልቅም
ሽቅብ ብናንጋጥጥ ጀንበር አትጠልቅም
ጊዜ ቆሟል መሰል አይነቃነቅም
ጋሪያችን ይሮጣል እኛ አንንፏቀቅም
እንዴት ነው ነገሩ?
ብሏል ኑረዲን ኢሳ በአንድ ግጥሙ፡፡ ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ ችግሮቻችንን መልካቸው እየቀየሩ ሲሄዱብን… “እንዴት ነው ነገሩ?” እያልን ነው፡፡ እንደ ትናንትና እንደ ትናንት ወዲያው ሁሉ ዛሬም ስደታችን ሲበዛ፣ ፍልሰታችን ሲበዛ፣ ችግሮቻችን ካሉበት ፈቅ ሳይሉ ሲቀሩ…“ጊዜ ቆሟል መሰል…” እያልን ነው፡፡
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ የነበረው ግፍ በሀያኛው ክፍለ ዘመን ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ ነው፡፡ ድፍን አፍሪካ ለመብታቸው ሲታገሉላቸው የኖሩ ህዝቦች፣ በተለይም ኢትዮዽያ በዓለም አደባባይ በፖለቲካውም ሆነ በስፖርቱ ሽንጧን ገትራ ስትሟገትላቸው የነበሩ ህዝቦች የጭካኔ ስለታቸውን ውለታ በዋለችላቸው አገር ህዝቦች ላይ ሲሰነዝሩ እጅግ፣ እጅግ አሳፋሪና ድፍን ደቡብ አፍሪካን አንገት ማስደፋት የሚገባው ድርጊት ነው፡፡
ጥቃቶቹ ገና እንደተጀመሩ መቆጣጠር እየተቻለ በአገሪቱ ወሳኝ ሰዎች በነበረ ዳተኝነት ከሚገባው በላይ ጥፋት ደርሷል፡፡ እንደእነ ናይጄርያ ጥግ ባንሄድም የአገሪቱ መንግሥት በግዛቱ ውስጥ ያሉ ኢትዮዽያውያንም ሆኑ የሌሎች አገሮች ስደተኞች ደህንነት የመጠበቅ ዓለም አቀፍ ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለበት ጮክ ብለን መናገር ይገባን ነበር፡፡
ሪቻርድ ዳውደን የተባለ እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ ከሰባት ዓመታት ገደማ በፊት ስለ አፍሪካ በጻፈው መጽሐፍ ላይ ስለ ደቡበ አፍሪካ ሲያሰፍር… “ደቡብ አፍሪካ እንደ ሌላ የአፍሪካ ሀገር አይደለችም፣…” ይልና “…ደቡብ አፍሪካ የሰው ልጅን ህልሞች የተሸከመች መሆኗ አይገርምም…” ሲል ያንቆለዻዽሳታል፡፡
ይህ እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ የሰሞኑን ድርጊት ሲያይ ምን ብሎ ይሆን! እኛ የምንለው ግን ግልጽ ነው...“የሰው ልጅን ህልሞች የተሸከመች…” ባላት አገር ያየነው የሰው ልጅን የጭካኔ ጥግ ነው!
ስለ አገራችን ያለን አመለካከት መጥራት አለበት። የራሱን ቤተሰብ እስከ አያቱ እንኳን መጥራት የማይችለው ሁሉ የሺዎች ዘመን ታሪካችንን ለማጠልሸት የሚያደርገውን እኩይ ተግባር በማስረጃ ጭጭ ማሰኘት መቻል አለብን፡፡
ይቺ አገር የሉሲ አገር ናት፣ የቅዱስ ያሬድ አገር ናት፣ የዘርአያዕቆብ አገር ናት፣ አክሱምን ያቆሙ፣ ላሊበላን የፈለፈሉ ጠቢባን አገር ናት፡፡ ይቺ አገር አፍሪካ ከእንቅልፏ ሳትነሳ ነጭ ወራሪዎችን ምሳቸውን ሰጥታ የጥቁር ህዝብ ምሳሌ የሆነች አገር ነች፡፡  
አንድ ነገር አለ፡፡ እነ እከሌ አይወዱንም ምናምን ስንል ዝም ብሎ የሚመጣ ነገር አይደለም፡፡ መታበይም አይደለም፡፡ የዚችን አገር ታሪክ በደንብ ላስተዋለ በእርግጥም ጠላቶቿ በርካታ መሆናቸውን ይገነዘባል፡፡ ጊዜ የሚጠብቁላት መአት እንዳሉ ምስጢርም ሊሆን አይችልም፡፡ እነኚህ ‘ቱባ፣ ቱባ’ መገናኛ ብዙኃን ስለ አገራችን ባወሩ ጊዜ ሁሉ የቃላት አደራደራቸውንና አጽንኦት የሚሰጡበትን ነጥብ ነገሬ ብሎ ማየት ይበቃል፡፡
እንደምንም ብለው የአገራችንን ገጽታ ምን ጊዜም ከበርካታ አሥርት ዓመታት በፊት ከነበረው ረሀብ ጋር በማስተሳሰር ትልቁን ስዕል ለመሸፈን ይሞክራሉ፡፡ አዲስ አበባ የባቡር ሀዲድ እየተዘረጋ መሆኑን በሚዘግቡበት ዜና ላይ የወሎ ድርቅን ምስሎች የሚደረድሩት ዝም ብለው አይደለም። በዓለም ላይ በየዘመናቱ ሚለዮኖች በረሀብ የረገፉባቸው አገራት እያሉ  አገራችንን በመዝገበ ቃላታቸው ‘የረሀብ ምሳሌ’ ማድረጋቸው ዝም ብለው አይደለም፡፡ አወሮፓም በተራበ ጊዜ እኛም እኮ ለተራቡ አውሮፓውያን የአቅማችንን እርዳታ ልከናል፡፡ ምነው ወደኋላ ሄደው እነሱም እንደ እኛ እርቧቸው እንደነበር አያነሱም! አዲስ አበባ የመጣ ቱሪስት ጉራንጉር ገብቶ የቆሻሻ ክምሮችና የወደቁ ደሳሳ ጎጆዎችን የሚያነሳው አገሩ በሳሎኑ ግድግዳ ላይ ሊለጥፍ አይደለም፡፡
የሰሞኑ ጭካኔ ተግባራት መገናኛ ብዙኃን ላይ ብቅ ብለው የወረዱበትን ፍጥነት ነገሬ ላለ ይገባዋል።
ይሄን መገንዘብ አለብን፡፡ አዎ፣ ቢመራቸውም ይቺ አገር ታላቅ ነበረች፣ ታላቅም ትሆናለች፡፡
“በደም ሥሮቹ ውስጥ በረዶ የሚፈስ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮዽያን በችግሯ ሰዓት መርዳት የማይፈልግ፣ በኢትዮዽያ የነጮች ኢምፔሪያሊዝም ወረራን ድባቅ መምታት የማይፈልግ አንድም ኔግሮ አይኖርም፣” ይላል በ1930ዎቹ የነበረ እውቅ ጥቁር አሜሪካዊ ጋዜጠኛና ደራሲ፡፡ “ኢትዮዽያ በጣልያኖች የምትሸነፍና የምትገዛ ከሆነ ለዓለም ጥቁር ህዝቦች ትልቅ ውድቀት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ውስጥ ያለ እያንዳንዱ የተማረ ጥቁር አስተያየት ነው፡፡”
እንዲህ የተባለላት ታላቅ የነበረችና… ለሚመራቸው ቢመራቸውም… ታላቅም የምትሆን አገር ናት፡፡ እስከዛው ግን የጨካኞችን ዓይኖች ከራሳችን ላይ ይንቀልልን፡፡
ጊዜ ሆይ
ሕያው ጊዜ ሆይ
በማይሞላው ገፅህ ላይ
የወጣችን ያቺን ቀን
ያቺን
የነቀርሳ እባጭ መሣይ
የመርዝ ከረጢት ሥራይ
ሥሯን በርብረህ ንቀል
ዕጯን ፈልገህ ግደል፤
ብሏል ደበበ ሰይፉ፡፡
ለሁላችንም ጽናቱን ይስጠን፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3040 times