Sunday, 10 May 2015 15:13

“መድረክ” በኦሮምያ አሸንፋለሁ እያለ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

በአባላቶቻችን ላይ እስር፣ ድብደባና ወከባ ተጠናክሮ ቀጥሏል”

   በዘንድሮ ብሄራዊ ምርጫ ከሚፎካከሩት ፓርቲዎች መካከል የመድረክ ግንባር አባል Yሆነው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ይገኝበታል፡፡ ኦፌኮ መድረክን ወክሎ በኦሮሚያ ክልል 155 ወረዳዎች ይወዳደራል፡፡ የግንባሩ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በሚወዳደሩበት አምቦ አካባቢ ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች ለቅስቀሳ ሲዘዋወሩ ሰፊ አቀባበልና ከፍተኛ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ከአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በዘንድሮ ምርጫም ኦሮምያ ላይ እናሸንፋለን ብለዋል - ዶ/ር መረራ፡፡ 15 ቀናት ብቻ በቀሩት የዘንድሮ ምርጫ፣ የመድረክ የኦሮሚያና አጠቃላይ አገር አቀፍ እንቅስቃሴው ምን ይመስላል በሚለው ዙሪያ ከመድረኩ አመራር ከዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጓል፡፡

መድረክ በኦሮሚያ ክልል እያደረገ ያለው የምርጫ ቅስቀሳ ምን ይመስላል?
በኦሮሚያ ብዙ አካባቢዎች ሰፋፊ ህዝባዊ ስብሰባዎችን አካሂደናል፡፡ ባኮ፣ አምቦ፣ ጀልዱ፣ ጊንጪ የመሳሰሉት አካባቢዎች እኔ የተገኘሁባቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች ተደርገዋል፡፡ በየስብሰባው ከ60ሺህ በላይ የሚገመት ህዝብ ነው ድጋፉን ሲገልፅልን የነበረው፡፡ በተለይ የወጣቱ ድጋፍ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ነው፡፡ “ከዚህ በኋላ የፀረ-ዲሞክራሲ አገዛዝ ይብቃን” የሚሉ ህብረ ዝማሬዎችን እያሰማ ነው ህዝቡ በየስብሰባው ላይ ሲታደም የነበረው፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሲታዩ ቅስቀሳው ስኬታማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ክልሉን እያስተዳደረ ያለው ኦህዴድ፣ በዚህ መልኩ ወጣቱ ለኛ ድጋፍ ይሰጣል ብሎ የገመተ አይመስለንም። አሁን ታዲያ የድንጋጤ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው፡፡ በአርሲ፣ በባሌ፣ በሃረርጌ፣ በባሌ እና በሸዋ አካባቢዎች አባሎቻችንን ማሰር፣ መደብደብና  ማዋከብ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የቅስቀሳ መኪናዎቻችንን መስተዋቶች በድንጋይ የመስበር፣ መኪኖችን በቡና ቤቶች አካባቢ ማሳደር እንዳንችል የማድረግ ሁኔታዎች በስፋት ተስተውለዋል፡፡
በየትኞቹ የኦሮሚያ አካባቢዎች ነው የበለጠ ድጋፍ አግኘተናል የምትሉት?
በሁሉም የኦሮሚያ ዞኖችና አካባቢዎች ተመሳሳይ የሆነ አቀባበል ከህዝቡ አግኝተናል፡፡ በአጠቃላይ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በትግራይ እና በአዲስ አበባ በምርጫው እንወዳደራለን፡፡ በሁሉም ላይ ቦታ ሰፊ አቀባበል ያገኘን ቢሆንም በተለይ ኦሮሚያ ላይ ኢህአዴግ ምርጫውን ካላጭበረበረ በቀር የሚያሸንፍበት መንገድ የለውም፡፡
ወደ ቅስቀሳው ስትገቡ ኦሮሚያ ላይ የተለየ ትኩረት አድርጋችሁ ነበር?
የተለየ ትኩረት ባናደርግም ወደ ስምንት የቅስቀሳ ተሽከርካሪዎችን ወደ ክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች አሰማርተናል፡፡ ወደ ምዕራብ ሃረርጌ፣ ደምቢ ዶሎና ጊምቢ፣ ሰላሌ፣ አምቦ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ አርሲ፣ ባሌ … ወዘተ የቅስቀሳ ተሽከርካሪዎችን አሰማርተን ጠንካራ ስራ እየሰራን ነው፡፡ በራሪ ወረቀቶችንም በሰፊው አሰራጭተናል፡፡
ከዚህ ቀደም በተጠሩ ሰላማዊ ሰልፎች ወይም ህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ብዙ ህዝብ አይወጣም ነበር፡፡ አሁን እንዴት ብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ ሊወጣላችሁ ቻለ? የተለየ የቅስቀሳ ስልት ተጠቅማችኋል?
አሁንም ቢሆን ህዝቡ ለስብሰባ እንዳይወጣ የተለያዩ መሰናክሎችን ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ ይሄ የገበያ ቦታ ነው፣ ይሄኛው ቤተ እምነት ነው እየተባልን ብዙ መሰናክሎች ቢገጥመንም ህዝቡ እንግዲህ በሰፊው እየደገፈን ነው፡፡ እስካሁን ወደ 3 ሚሊዮን በራሪ ወረቀቶችም  አሰራጭተናል፡፡
እስኪ የዘንድሮውን የኦሮምያ ክልል የምርጫ ተሳትፎ ከ97ቱ ምርጫ ጋር አነፃፅረው ይንገሩኝ…
የአዲስ አበባን ገና እንጀምራለን፡፡ የኦሮሚያ ግን ከ1997ቱ የዘንድሮው በጣም ነው የሚሻለው፡፡ ለምሳሌ በ1997 የተወዳደርነው በ76 ወረዳዎች ነው፤ በዘንድሮ ምርጫ ግን በኦሮሚያ ብቻ ከ155 በላይ ወረዳዎች ላይ ነው የምንወዳደረው፡፡ የቅስቀሳ አቅማችንም 97 ላይ ውስን ነበር፡፡ አሁን ግን በኦሮምያ ብቻ ከስምንት ያላነሱ የቅስቀሳ ተሽከርካሪዎችን አሰማርተን የቅስቀሳ ስራ እየሰራን ነው፡፡ በሁሉም መንገድ የዘንድሮው የኦሮሚያ እንቅስቃሴያችን የተሻለ ነው፡፡
ኦሮሚያ ላይ እናስመዘግባለን ብላችሁ የምትጠብቁት ውጤት ምንድን ነው?
እኛ ሁለት ነገር ነው የምንጠብቀው፡፡ አንደኛ ኢህአዴግ ካላጭበረበረ በቀር ኦሮሚያ ላይ አያሸንፈንም፣ ሁለተኛ ደግሞ ፖለቲካውን በሚገባ እንዳሸነፍን አሳይተናል፡፡ ሰፊ ድጋፍ እንዳለን አስመስክረናል፡፡ በየትኛውም ሚዛን ከኦህዴድ እንደምንሻል አሳይተናል፡፡ በዚህ ተደናግጠው እኔ በምወዳደርበት አካባቢ ኦህዴዶች ህዝቡን በሬ አርደው ማብላት ሁሉ ጀምረዋል፡፡ የክልሉ ካድሬዎች አሁን አምቦ ከትመዋል፡፡ ሥራ ላይ ናቸው ማለት ነው፡፡
እስቲ የአምቦ ህዝብ ስላደረገልዎ አቀባበል ይግለፁልን?
እለቱ የትምህርት ቀን ባይሆን የበለጠ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ እንዴት እንደሆነ አላውቅም በቴሌቪዥንም በጨረፍታ ታይቷል፡፡ ሁኔታው በጣም የተለየ ነበር፡፡ ህዝቡ ስሜን እየጠራ በሆታ ነው የተቀበለን። ወደ ስቴዲዬም ስገባም መንገዱ ሁሉ በወጣቶች በመዘጋጋቱ ፖሊሶች ናቸው ያስከፈቱልኝ። ወጣቱ መንገድ ዘግቶ ይዘፍን ነበር፡፡ በአካባቢው ሰፊ የህዝብ ድጋፍ እንዳለን እነሱም የተገነዘቡት ይመስለኛል፡፡
የፀጥታ ሁኔታስ እንዴት ነበር? ከፀጥታ ሃይሉ ትብብር ይደረግላችሁ ነበር?
በተለይ ምዕራብ ሸዋ ላይ በሚገባ ተባብረውናል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ግን ካድሬው ሽጉጥ ታጥቆ፣ ጠመንጃ ይዞ እገባለሁ አትገባም የሚል ግብግብ እስከመፈጠር ደርሷል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ መኪናዎቻችን እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገው ተወዳዳሪ እጩዎቻችን ሳይቀሩ ተደብድበዋል፡፡ በየቦታው ትንንሽ ጦርነት የሚመስሉ ነገሮች ነበሩ፡፡ የኛ ቅስቀሳ በተሳካ ቁጥር የእነሱ ብስጭት ይግል ነበር፡፡ ካድሬው ለሆዱ፣ መንግስት ለስልጣኑ በሚገባ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይሄ አመላካች ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ያላገኘነውን ድጋፍ ነው ያገኘነው ብለዋል፡፡ የህዝቡ ድጋፍ ከምን የመነጨ ነው?
በአጠቃላይ የኦሮሞ ህዝብ የሚተዳደረው በሞግዚት አስተዳደር ነው፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ለመብትና ለነፃነቱ ድሮም ሲታገል ነበር፤ አሁንም ትግሉን ይቀጥላል፡፡ አሁን ባለው የፖለቲካ አሰላለፍ፣ ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ የተሻለ በኦሮሚያ አብሮት ሊንቀሳቀስ የሚችል ፓርቲ ምርጫ ውስጥ የለም፡፡ ኦህዴድና ህዝቡ  ከተለያየ ቆይቷል፡፡ ያው በኢህአዴግ ጃንጥላና ጠመንጃ ስር ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ እነሱም እንደማያሸንፉ ያውቃሉ። እኛ በ97 እኮ አሳይተናቸዋል፡፡ በወቅቱ እነ አባዱላን ያሸነፉት እኮ የ6ኛ እና 7ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ ኦህዴድ በኦሮሚያ ሊሸነፍ እንደሚችል በ97 ምርጫ ነው ያረጋገጥነው፡፡
መድረክ በአጠቃላይ ከአገር አቀፍ ምርጫ የሚጠብቀው ውጤት ምንድን ነው?
በአጭሩ የኢትዮጵያ መንግስት ደጋግሞ እንዲያስብበት የምመክረው ምርጫውን እንዳያጭበረብር ነው፤ ውጤቱ የፈለገ ይሁን፡፡ ምርጫን አጭበርብሮ አሸንፌያለሁ የማለት ጊዜ ማብቃቱን ማወቅ አለበት። ያንን ካላደረገ ሃገሪቷንና ህዝቦቿን ለበለጠ ተስፋ መቁረጥ ነው የሚዳርገው፤ ይሄ በተግባር እየታየ ነው። ወጣቱ ከቀይ ባህር እስከ ሜዲትራኒያን ድረስ የባህር ሲሳይ የሚሆነውና በረሃ ውስጥ እንደዚያ የሚታረደው፣ ደቡብ አፍሪካ እንደዚያ የሚቃጠለው በሃገሩ ተስፋ ስላጣ ነው፡፡ ኢህአዴግ በጠራው ሰልፍ ላይ እንኳ “የስደት ዘመን ይብቃ” ብሎ ከፖሊስ ጋር እንዴት እንደተጋጨ ተመልክተናል፡፡ አጥፍቶ የመጥፋት ፖለቲካ ይብቃ! የኢህአዴግ ባለስልጣናት ደጋግመው ያስቡበት። ህዝቡንም ወጣቱንም ተስፋ ማስቆረጥ ለማንም አይጠቅምም፡፡ በተለይ ወጣቱ በሃገሬ የተሻለ ሥራ አገኛለሁ የሚል ተስፋ ሊያድርበት ይገባል፡፡ ይሄንን ወጣት ተስፋ ማስቆረጥ ለሁላችንም አይበጅም፡፡
በቅርቡም 7 የሃይማኖት ተቋማት አባቶች፤ ሁሉንም የምርጫው ተሳታፊ አባላትን ጠርተው ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡ ኢህአዴግን ሳያስፈቅዱ መቼም ይሄንን አያደርጉም፣ ግን ዘላለም በምርጫ እየተፈለገ ህዝቡ ወቅት፣ እየተደበደበ፣ እየታሰረ… ምርጫ ብሎ መቀለድ አያዋጣም፡፡ የኢህአዴግ መሪዎች ልቦና ይስጣችሁ እላለሁ፡፡
እና መድረክ ከምርጫው ምን ውጤት ይጠብቃል?
እኛ በ1997 ምርጫም አይተናል፡፡ አሁን ደግሞ መድረክ በገባባቸው ቦታዎች ያለውን አቀባበል አይተናል። በእርግጠኝነት የምነግርህ ኢህአዴግ ካላጭበረበረ እናሸንፋለን፡፡ ችግሩ ግን ደጋግሜ እንደምለው፣ ኢህአዴግ ጠመንጃና ምርጫ ቦርድን እንደ ምርኩዝ ይዞ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ እንግዲህ ቀጣዩ ምን ይሆናል የሚለውን ጊዜው ሲደርስ ነው የምንነጋገረው፡፡ እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው ግን መድረክ ትግራይን ጨምሮ ሊያሸንፍ እንደሚችል ነው፡፡ ለኢህአዴግ የማስተላልፈው መልዕክት፤ ልቦና ይስጣችሁና በተለይ ወጣቱን ተስፋ አታስቆርጡ የሚል  ነው፡፡
ምናልባት “መድረክ” አብላጫ ድምፅ ካገኘ ጥምር መንግስት ይመሰርታል?
 እኛ በፕሮግራማችን ላይ በግልፅ አስቀምጠናል። በሽግግሩ ጊዜ ጥምር መንግስት ያስፈልጋል ብለናል። ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድና ለመሳሰሉት ዲሞክራሲያዊ ሂደቶች መልክ ማስያዣ ይሆን ዘንድ የብሄራዊ አንድነት መንግስት ያስፈልጋል፡፡ ከማን ጋር ይመስረት የሚለው በድርድር የሚከናወን ይሆናል፤ ነገር ግን አግላይ ፖለቲካ ውስጥ አንገባም፡፡
አንድ ፓርቲ ሌላውን አግልሎ ኢትዮጵያን መንግስተ ሰማያት ያደርሳል የሚሉ ካሉ ወይ የፖለቲካ ሳይንስ ያልገባቸው ወይም እስከቻልን ድረስ በፈላጭ ቆራጭነት ረግጠን እንግዛ የሚሉ ናቸው፡፡ በተረፈ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ ለማምጣት መታለፍ ያለበት አንዱ ሂደት የብሄራዊ አንድነት መንግስት ማቋቋም ነው።

Read 4239 times