Saturday, 16 May 2015 11:20

ሽብልቅ የአዲስ ትውልድ ምኞት!

Written by  በውሂብ ጌታሁን
Rate this item
(3 votes)

“እየውልህ የሀገሬ የቀልቁለት ጉዞ መነሻው ኢህአዴግ አይደለም፡፡ ደርግም አይደለም፣ ኃይለስላሴም አይደለም፡፡ ሀገሬ የገባችበት የግለሰባዊ ፣ማኅበራዊና ሀገራዊ ቀውስ አረንቋ መሠረቱ ጥልቅ ነው፡፡--”
      
   ፈራ ተባ እየተባለም ቢሆን የዚች ሀገር ሰቆቃና ችጋር መንስዔ ያ ትውልድ መሆኑን ሲነገር ሰምተናል፤ ሲተች አንብበናል፤ ወይም አብረን ወቅሰናል፡፡ (በዚህ መጣጥፍ ያ ትውልድ ስል የእነ ኢሰፓ፣ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ህወሓት--- የአሁን ዘመን ፓርቲዎች ወዘተ-- የሚያጠቃልል ነው፡፡)
ለምን ያ ትውልድ ተጠያቂ ሆነ? የዚህ መጣጥፍ ዋነኛ ዓላማ አይደለም፡፡ ካነሣነው ዘንድ በጨረፍታ ለመንካት ግን ያ ትውልድ ቂመኝነትን፣ ቁጡነትን፣ ነገር ጠምዛዥነትን፣ ደም መቃባትን፣ ስድብንና  ጥላቻን ሲዘራ የኖረ በመሆኑ ነው፡፡ አሁንም ድረስ በገዥውም ይሁን በተቃውሞ ጎራ ያሉ ፖለቲከኞች ከዚህ አዙሪት አልወጡም፡፡
የአዲሱ ትውልድ አባላት በዚያኛው ትውልድ ሲታመሱና ሲበጠበጡ እስካሁን  አሉ፡፡ የራሳቸውን ማንነት እስኪያጡ ድረስ አለማወቃቸው እየተነገራቸው፣ ሀገር ሊሸከም የሚችል ትከሻና የሚያስችል ጥበብ እንዳልተፈጠረባቸው እየተደሰኮረላቸው፣ ‹‹ድሮ ቀረ›› እየተዜመላቸው፣ ቂምና ጥላቻን እንዴት ማዳበር እንዳለባቸው እየተሰበኩ አሉ፡፡
ለዚህ ይመስላል የሀገሪቱ ፖለቲካ ከ60ዎቹ እስካሁን ድረስ አፍርሶ በመጀመር ቅኝት የተቃኘው፡፡ በእርግጥ ይህም በራሱ ወቀሳ ነው፡፡ ወቀሳ ደግሞ የሰለጠንበት ይሁን እንጅ ትርፋማ ያደረገን ልማድ አይደለም፡፡
በዚህ ስሜት እያለሁ ያነበብኩትን መጽሐፍ መዳሰስ ነው ዋና ፍላጎቴ፡፡ (መጽሐፉን ሶስቴ እንዳነበብኩት ስናገር ግነት አይደለም) ርዕሱ ሽብልቅ፣ ደራሲው ሄኖክ ፍቅረማርያም፣ የገጹ ብዛት 236፣ ዋጋው 50 ብር፣ ዓይነቱ ልብ አንጠልጣይ ልቦለድ፡፡ ከመስመር መስመር፣ ከገጽ ገጽ፣ ከክፍል ክፍል ልብ እያንጠለጠለ የሚጓዝ የአዲስ ትውልድ ምኞት!
በፊት ለፊት ገጹ ላይ ጠመዝማዛና ባላባሎሽ እንጨት ላይ የተሰነቀረ ጉራጅ ብረት ይታያል - ‹‹ሽብልቅ››። በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ደግሞ “ሽብልቅ ማለት ወፍራም ግንድ ለመፍለጥና ለመፈርከስ የምታገለግል ከአናቷ ሰፋ ብላ ወደ ታች እየጠበበች በመሄድ፣ ስለት ያወጣች አጭርና የማትሰበር ብረት ናት›› የሚል ትርጓሜ ተቀምጧል፡፡
ከፊትና ከጀርባ ሽፋን መግለጫዎቹ ተነስተን፣ ከዚህ መጽሐፍ ብዙ መጠበቅ እንችላለን፡፡ ጠመዝማዛውና ወፍራሙ ግንድ ማን ነው? ወፍራምነቱ በራሱ ለመፍለጥ አታካች ነው፤ በዚያ ላይ ባላባሎሽ ያለው ጠመዝማዛ ግንድ…. እንደምን ይፈለጣል? ሽብልቁስ ማን ነው?
አቶ ቢተው የዚህ ሀገር ውጥንቅጥ ያሰለቻቸው የእንስሳት ሀኪም ናቸው፡፡ የህክምና ትምህርታቸውን ተምረው እንደጨረሱ ገጠር ገቡ፡፡ ለሃያ ዓመታት ገጠር ውስጥ ሽብልቅ ሲቆርጡ፣ ሲያቀልጡ፣ ሲቀርጹ ኖሩ፡፡ ይህ ሽብልቅ በእሳት አይደለም የተቆረጠው፣ በግለት አይደለም የቀለጠው፣ በመዶሻ አይደለም የተቀጠቀጠው፤ በእውቀትና በጥበብ እንጂ፡፡  ሽብልቁ ዋለልኝ ነው፡፡
አቶ ቢተው ሚስታቸው ጥላቸው የሄደችው ገጠር ጠላሁ ብላ ነበር፡፡ የከተማ ህይወት አምሯት፡፡ አቶ ቢተው ገጠር የከተሙት ሀገር በቀል ጥበብን ፍለጋ ነው። የሀገሪቱ የፖለቲካ ቅርሻት ለእሳቸው ትርጉም የለውም። የዜጎች ዕለት ከዕለት መኳተን አንድም ለሆድ፣ አንድም ለዝና ስለሆነ ጠልተውታል፡፡ ዘመናዊ እውቀት እየተባለ የሚነገረው ሁሉ ዲቃላ ትውልድን ያፈራ እንደሆነ  እንጂ ሀገር አይቀይርም፤ ለአቶ ቢተው፡፡
ስለዚህም ስር ነቀል ለውጥ፣ አዲስ ለውጥ፣ አዲስ መንገድ ለዚች ሀገር ያስፈልጋታል፡፡ ገጠር ተዳፍነው መሪ ካርታና ፖሊሲ ያዘጋጃሉ፡፡ በዚህ ጥበብ ነው ዋለልኝን የቀረጹት፡፡ ዋለልኝ በቀለም ትምህርቱ እሳት የላሰ ነው፡፡ በሚያኮራ ውጤት አዲስ አበባ  ዩኒቨርሲቲ ይገባል፡፡  አቶ ቢተው ሲሸኙት ይህን ይሉታል፡-
‹‹የኔ ሽብልቅ …. አንተ የምትሄደው ተምረህ ራስህን ለመለወጥ አይደለም፡፡ ተምረህ አባትህን ለመርዳትም አይደለም፡፡ ተምረህ  እናትህን ለመለወጥ ነው…….አዎ ውቧ እናትህ ያለችው እዚህ ነው፡፡ ሉባንጃዋ የሚማርከውና ወዟ የሚፍለቀለቀው ኢትዮጵያ ያለችው እዚህ ነው፡፡ ኩሩና ቆፍጣናዋ እመቤት ያለችው እዚህ ነው፡፡ አንተ የምትሄድበት አዲስ አበባ ያለችው ኢትዮጵያ እብዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ከቆሻሻ ገንዳ ልቅምቃሚ የምትበላዋ.. ጠረኗ የማያስጠጋው… እድፍና ጉድፏ የሚያስጠይፈው ኢትዮጵያ ናት፣ ያዲሳባዋ እናትህ በራሷ የማትተማመን ዝርክርክና ብርክርኳ ኢትዮጵያ ናት እዚያ ያለችው፡፡ ኢትዮጵያ ራሷን የሳተችና ራሷን የማታውቅ ወፈፌ ናት፤ በደም ነፍስ የምትራመድ እግሯ ወደመራት የምትሄድ ወፈፌ፡፡ የፈረንጅ የቆሻሻ ገንዳ ካገኘች እዛው በልታ እዛው የምታድር ማፈሪያና የባዕድ ሀገር መጠቋቆሚያ ናት፡፡
እንዲህ የሆነችው በባህር ማዶ ሰው ነው፡፡ እዚህ የባህር ማዶ ዛፍ እንጂ የባህር ማዶ ሰው የለም፡፡ እንደዚህ ባህር ዛፍ ግዙፍ የሰው ዛፎችና ግንዶች ያሉት አንተ የምትሄድበት አዲሳባ ነው (እነዚህን) ከሃገሬ ለማጥፋት አንተን ሰርቻለሁ፡፡ በእነዚያ እሳት በሚያፈልቁ ደብተሮች ጭንቅላትህን አቅልጬ ሰርቼሀለሁ፡፡ አሁን ያንተ ጭንቅላት ስለት አውጥቷል፡፡  አንተ የኔ ሽብልቅ ነህ (ገጽ-19)
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያገኘሁት ታላቅና አዲስ ሐሳብ፣ ሀገሪቱ መለወጥ ካለባት ስለ ወንበር ፖለቲካና ፖለቲከኞች ማውራት የለብንም የሚል ነው፡፡ በእርግጥ በውዴታና በጥላቻ ጽንፍ ተወጥሮ እዚህና እዚያ ጥላቻን ለሚሰብክ ሁሉ ይህ ሊዋጥ የሚችል ሐሳብ አይደለም። ገዥው ፓርቲ ተቃዋሚዎቼን ሳላጠፋ አልተኛም ይላልና፣ ተቀናቃኞችም ገዥውን ፓርቲ  ድምጥማጡን ሳናጠፋ እንቅልፍ የለንም ይላሉ፡፡ በዚህ መካከል ለሀገር የሚሰጥ ትኩረት እምብዛም ይሆናል፡፡ ለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጫጫታ ስለ ምንድን ነው? ስለ እኩልነት? ስለ ፍትህ? ስለ ዴሞክራሲ? እነዚህ ቃላት እኮ ምናባዊ (subjective) ናቸው፡፡ ለምንድን ነው ብርቱ ሀገር ስለ መገንባት፣ መቼም መሠረቷ የማይናወጽ ሀገር ስለመመስረት፣ ገዥዎች ቢቀያየሩ ዕለት ተዕለት አጀንዳዋ የማይለዋወጥ ሀገር ስለ ማነጽ የማይተጉት? ስለዚህስ የማይሰብኩን ለምንድን ነው? ይህ መሠረታዊው የ“ሽብልቅ” መጽሐፍ ማጠንጠኛ ስለሆነ መጽሐፉን ከልቤ ወደድኩት፡፡   
 “እየውልህ የሀገሬ የቀልቁለት ጉዞ መነሻው ኢህአዴግ አይደለም፡፡ ደርግም አይደለም፣ ኃይለስላሴም አይደለም፡፡ ሀገሬ የገባችበት የግለሰባዊ ማኅበራዊና ሀገራዊ ቀውስ አረንቋ መሠረቱ ጥልቅ ነው፡፡ መቼም ሩቅ ነው.--” ስትለው ነዘረው፤ የሆነ ነገር ውርር አደረገው “አንተ ከምሁራኑ ጋር ምን አተካራ አስገባህ? ምሁራን የምትላቸውስ የትኞቹን ነው?››
“በቅድሚያ እንደ ሀገሬ የመኪና ሹፌር እየገጩም እያጋጩም ቢሆን የፖለቲካውን መሪ ጨብጠው የሚያሽከረክሩ በግንባር ቀደምትነት ምሁራን ስለሆኑ ነው፡፡ ምሁራን የምልሽም በቅድሚያ ከፍተኛ የሆነ የሀገር ሀብት እየፈሰሰባችሁ የምትማሩትን እናንተን ሲሆን በመቀጠል የባህልና የሀይማኖት ሊቃውንትንም የሀገርና የመንደር ሽማግሌዎችንም፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ የህጻናት መሪ ወላጆችንም ነው” (ገጽ-59)
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ደራሲው መደባበቅና መሸፋፈንን አልፈለገም፡፡ ለማለት ያሰበውን ሁሉ በግልጽ ብሎታል፡፡ የሀሳብ ወጥነት ወይም እንደ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ አባባል “ወርጅናሌነት” አለ፡፡ በዚህ ዳሰሳ ጸሐፊ እይታና የንባብ ደረጃ የማትሽመደመድ ሀገር ለመገንባት አዲስ ቅያስ የቀየሰ ልቦለድ የሄኖክ ፍቅረ ማርያም “ሽብልቅ” ነው፡፡ መንገዱም አዲስ ትውልድ - ‹‹ሽብልቅ›› መፍጠር!
ታዲያ በዚህ ልቦለድ ውስጥ ሐሳባዊነት ብቻ ሳይሆን እውናዊነትም አለ፡፡ አሁን ባለንበት የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሊሆን የሚያስቸግር የሚመስለው አዲስ ትውልድ የማግኘት ራዕይ ሰው በመሆን ሀቅ እየተከሸነ ስለቀረበ ተአማኒነቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ከፍ ሲል እንደተባለው ከገጽ ገጽ፣ ከምዕራፍ ምዕራፍ ልብ የመስቀል ሀይሉ ከፍተኛ ነው፡፡ የታሪክ ትውስቡ ምንጭ ደግሞ አሁን ያለው የሁለት ሶስት ትውልድ ባህርይና ስነምግባር ነው፡፡ ልቦለዱ እንደ ሲድኒ ሼልደን ልቦለዶች ጭልጥ ብሎ በምናብ አለም የሚያስዋኝ ወይም እንደ ዳን ብራውን ስራዎች ትርፍ በሌለው የታሪክ ውስብስቦሽ መደመምን የሚፈጥር ብቻ አይደለም፡፡ እየወደድን እናነበዋለን፤ እያተረፍንም፡፡
ያ ትውልድን እንለፈውና እዚህኛው ትውልድ ውስጥ ያለች የያ ትውልድ ቅሪት ይህን ትላለች (ሲመስለኝ ደራሲው ሀቃችንን እየጨለፈልን ነው)
“እክህ ፖለቲካ የሚባል አረንቋ ውስጥ እንዳትገባ አደራህን፡፡ አባቴ ከፖለቲከኝነት ያተረፈው ሲጋራ ይሄውልህ ለእኔም ተርፎኛል፡፡ እኔ ሲጋራ ከመጀመሬ በፊት እሱ የሚያጨሰው ሮዝማን ሽታው እንደ ፓሪስ ሽቶ ይጣፍጠኝ ነበር፡፡ አጫጫሱ ምሁርና አዋቂ አድርጌ እንዳስበው ያደርገኝ ነበር፡፡ እኔም ወደ ዩኒቨርሲቲ ስገባ የምሁርነትና የአዋቂነት አንዱ መስፈርት ማጨስ መስሎኝ ይሄው ተዘፍቄ ቀረሁ፡፡ ፖለቲከኛ ከሆንክ እንደዚህ ሲጋራ የምትነድና የምታነድ ነው የምትሆነው፡፡ የኔ አባት የቅንጅ አባል ነበር፤ ቅንጅት ሲሞት የኔ አባት ራሱን በሲጋራ እያነደደ ነው፤ጋፊዎቹን ደግሞ ሲጋራ ሆኖ እያነደዳቸው ነው›› አለችው፡፡ “……..ተርታው ህዝብ የጤፍ ወይም የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ውስብስቡንና ድብስብሱን ችግር ረስቶ ለዋጋ ግሽበቱና ለእለት ጉርሱ በአንድ ጀምበር መፍትሄን ይሻል፡፡ የዚህ መፍትሄ ደግሞ የወንበር ፖለቲካ ድርጅት ነው ብሎ ማሰቡ የፖለቲካ ነጋዴዎችን የፖለቲካ ድርጅት እንዲያቋቁሙ  እድል ፈጥሮላቸዋል……ድርጅቱ የቆመው የሰራተኛ ደሞዝ እየከፈለ ስራ አጥን ለመቀነስ አይደለምና የቁጥር ቁማር መጫት አለበት። የቁማር ጨዋታው በካርድ ቀጠሮ ወይም ምርጫ ከሆነ ማንኛውንም እኩይና በጎ የጭንቅላት ጨዋታ ሊጫወት ይችላል፡፡ የቁማር ጨዋታው የተበላ እቁብ ከሆነ እቁብ ሁልጊዜ ለአንድ ሰው እንደወጣ ለማሳመን የሥራም የሴራም ጨዋታ ሊጫወት ይችላል……. ነገር ግን የኔ ጉዳይ ህዝባዊ ለውጥ ነው፡፡ ሀገርን ለመለወጥ የወንበር ፖለቲከኛ መሆን ሳይሆን ህዝብን መለወጥ ነው፡፡  ህዝብን ለመለወጥ ከህዝብ ጋር መጣላት ተገቢ የሚሆንበት አጋጣሚም ይሄ ነው” (ገጽ 69-72)
አዎ ሽብልቆች ህዝብ ለመለወጥ ከህዝብ ጋር ይጋጫሉ፡፡ የፓርቲ መቀያየር ሀገር ይለውጣል ብሎ የሚያምን፣ ከአማኝነት ይልቅ ሀይማኖተኝነት ይበጀኛል ብሎ የሚያስብ፣ ከማዕከላዊነት ይልቅ ጽንፈኝነት ይልቃል የሚል፣ ከሀገራዊነት ይልቅ ጎሰኝነት ያዋጣል ብሎ የሚያስብ ሁሉ ከሽብልቆች ጋር ይጋጫል፡፡ ሽብልቆችም ከዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ጋር ይላተማሉ፡፡ የወደድኩት መጽሐፍ! እባክዎ እርስዎም ያንብቡት፡፡  

Read 1760 times