Saturday, 16 May 2015 11:31

ልቦለድ በመጨረሻ እስትንፋሱ ላይ

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(2 votes)

በዕውቀቱና ኩንዴራ ምንና ምን ናቸው?
      
   (ካለፈው የቀጠለ)
ሰሞነኛው የልቦለድ ዕጣ - ፈንታ በተለይ ብዙ ለመፃፍ ተስፋ ላደረገ ሰው መብከንከኛው ነው። “ልቦለድ አልቆበለታል፣ መቀጠል አይችልም” የሚል መደምደሚያ ሲነገር በጉብዝናው ወራት እንደሚያውቁትና በመጨረሻው እንዳላማረ ጀግና በሀዘን ሆድ ይላወሳል፡፡ ልቦለድ በሞትና በሽረት መካከል ሆኖ የቀረበለት አማራጭ የጥቃት የመጨረሻው ጥግ ነው፡፡
ልቦለድ ከምናብ ጋር እንደተፋቀረ ወደ መቃብር ይውረድ? ወይስ ጊዜ የሰጠውን “ቅል” (ወግ Essay) አጉራህ - ጠናኝ ይበል?
እዚህ ላይ ልቦለድ ጊዜ የከዳው አሮጌ ጀግና ሆኖ ይታየኛል፡፡ ሰይፍ ቢታጠቅም መሰንዘሪያ ክንድ የከዳው …. ጋሻ ቢያነግብም መመከቻ ጡንቻው የሟሸሸ … ወጥመድ እንደገባ አንበሳ ከወዲያ ወዲህ እየተንጎማለለ በፊታውራሪ መሸሻ ግትር ባህርይ ወደ መሰበሪያው የሚያመራ …
“እጅህን ስጥ አለኝ ወግ
   እጅ ተይዞ ሊወሰድ፣
ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ?
አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ?”
ለመሆኑ ወግን የተጠለለ ልቦለድ በእርግጥ ልቦለድ ነው? ምናቡን የጣለ፣ ግርማውን የተገፈፈ፣ አሻግሮ ከማየት የተነፈገ፣ በደራሲው ኑዛዜ ላይ የተንጠላጠለ .. ፅሑፍ በእርግጥ ልቦለድ ነው? እርጋታውን ተነጥቆ የተንጦለጦለ፣ ለዛውን ተነፍጎ  ይዞ ወደመጣው ታሪክ የተገፈተረ፣ ጥላ ቢስ ከውካዋ … ልቦለድ ካለ ይቆጠራል? በዚያም በዚህም ብሎ ለልቦለድ የቀረበው አማራጭ ሁለት “ሞት” ነው? …
ባለፈው ፅሁፍ ያነሳው አጥኚ ዴቪድ ሺልድ፤ ልቦለድ ከሞት መዳን ካለበት የወግን ምስጢር ቁልፍ ሰብሮ በመግባት በመረጃው የመጠቀም ሽግግር ያስፈልገዋል ይላል፡፡ ቃል በቃል እንዲህ፡- “The novel facing extinction, it might need a transformation to survive; what digital natives call a hack”
ስለዚህ የልቦለድ ፀሐፊያን እነ ቶልስቶይን፣ እነ ዶስተየቭስኪን፣ እነ ዲከንስን ፣ እነ ሔሚንግዌይን፣ እነ ሀዲስ ዓለማየሁን፣ እነ በዓሉ ግርማንና ሌሎቹን ልቦለድ ደራሲያን ሳይሆን ነባሮቹን ወግ ፀሐፊያን ማጥናት ግዳቸው ነው፡፡ የእነ ሞንታኝን ወይም የእነ ጆዋን ዲድየን የወግ መፃፊያ ህግ መከተል፤ ምናብ ወለድ ታሪክ አያዋጣምና ወደ እውነታ መማተር፡፡ ሺልዲ አሁንም ቃል በቃል እንዲህ ይላል፡- “Story telling as self examination montaigne or Joan Didion, true life instead of fake life.”
ፈረንሳዊው የዘመናዊ ወግ ጀማሪ ሚካኤል ዴ ሞንታኝ (1533-1529) “ሙከራ” (Attempts) ብሎ ያስተዋወቀውን ወግ ሲገልፅ፤ “የእኔ ፍላጎት ሁሉም ሰው በመፅሐፌ ውስጥ እኔን እንደኔነቴ አድርጎ እንዲመለከተኝ ነው፡፡ ያለ ምንም መቀባባትና ሐፍረት” (My intention is that everyone see me in my book just as I am, without any shame or artifice) ብሏል፡፡ አክሎም፤ “መፅሐፌን ስታነቡ እኔን፣ እኔን ስታዩ መፅሐፌን ታውቃላችሁ” የሚል መደምደሚያ አስቀምጧል፡፡
እንግዲህ የዚህ ዘመን የልቦለድ ነፍስ አድን ባታሊዮን አባል ደራሲዎች የመጀመሪያ እርምጃቸው ኮሽታ እንደሰማች ኤሊ ወደ ውስጣቸው መግባት ነው፡፡ እዚያ ያገኙትን እውነት ያለ ሀፍረትና መቀባባት እንዳለ ማቅረብ፡፡
የቀረበውን (ድርሰቱ) ከአቅራቢው (ደራሲው) መለየት እስኪያቅት ድረስ አንደማድረግ፡፡ ከዚያ “ከሞንታኝ አመራር ጋር ወደፊት!” ማለት፡፡
ወግን “hack” ካደረጉ ልቦለድ ደራሲያን ውስጥ አውራውን ሚላን ኩንዴራን አንስተን ወደኛዎቹ እንደረደራለን፡፡ በትውልድ ቼክ በዜግነት ፈረንሳዊ የሆነው ኩንዴራ ደራሲነቱ “በዓመተ ፍዳ” እና “በአመተ ምህረት” የተከፈለ ነው፡፡ ኩንዴራ በሶሻሊዝም ንውዘት፣ ሀገሩ ቼክ ደግሞ በስታሊን መቅሰፍት ሥር የሚዳክሩበት ዘመን “አመተ ፍዳ” ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ስታሊን በቼክ ደራሲዎች ላይ የጣለውን ቅድመ ምርመራ በመቃወም ከሶሻሊስቱ አለም ጋር ከተቃቃረ በኋላ፣ ስደቱን ተከትሎ የተተካው ዘመን ደግሞ “ዓመተ ምህረቱ” ነው፡፡ በሁለተኛው አካፋይ ማለትም ከ1967 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ብቻ አስር ልቦለዶችን ፅፏል፡፡
የኩንዴራን ልቦለዶች፤ በተለይም “The Book of Laughter and Forgetting” ማንበብ ያልተደራጀው የኩንዴራ እሳቤ ውስጥ ገብቶ ዋዣቃ ባህር መቅዘፍ ነው፡፡ ቀጥ ያለ መንገድ የለም። ኩንዴራ እንደ አዲስ አበባ ሚኒባስ ታክሲዎች እያቆራረጠ ካንዱ እውነት ወደ ሌላው ሲያጋባን ይውላል፡፡ መንዱ ብቻ ሳይሆን “የአየር ሁኔታው” እጅግ ፈጣን፣ ተለዋዋጭ ነው፡፡ አንዳንድ የኩንዴራ “መንገዶች” እና “የአየር ሁኔታዎች” ተደጋግመው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የመፅሐፉ መጀመሪያ ላይ የሚተርከው የፕሮራግ ፖለቲከኞቹ ጉዳይ….
…. ጊዜው የካቲት 1948 ነው፡፡ ፕራግ ውስጥ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ፊት ኮሙኒስታዊ መሪ ክሌመንት ጎትዋልድ ወደ መድረክ ይወጣል። ጓዶቹ አጠገቡ ነበሩ። የአየር ሁኔታው ብርዳማ ስለነበር በቅርቡ የነበረው ክሌመንቲስ ኮፍያውን አውልቆ የጎትዋልድን ፀጉር አልባ ራስ ይሸፍናል። የፕሮፓጋንዳው ክፍል ጎትዋልድ ያንን ኮፍያ እንዳደረገ በጓደኞቹ ተከብቦ ፎቶ ያነሳዋል፡፡ ፎቶውን በብዙ መቶ ሺዎች አባዝቶ በትምህርት ቤት፣ ለመገናኛ ብዙሃን፣ ለሙዚየም ይበትነዋል፡፡ በፖስተር አሳትሞ በየአካባቢው ይለጥፈዋል፡፡
ከአራት ዓመት በኋላ የኮፍያው ባለቤት ክሌመንቲስ በአገር መክዳት ተወንጅሎ በስቅላት ይቀጣል፡፡ የፕሮፓጋንዳው ክፍል ወዲያውኑ ክሌመንቲስን ከታሪክ እንዲሁም ከሁሉም ፎቶግራፍ ላይ ያጠፋዋል፡፡ እዚያ የ1948ቱ ፎቶግራፍ ላይም ክሌመንቲስ ተሰርዞ በቦታው ላይ ግድግዳ ተተክቷል። የክሌመንቲስ ትውስታ ከራሱ ላይ ገፍፎ ጎትዋልድ ጭንቅላት ላይ ያኖረው ኮፍያው ብቻ ይሆናል፡፡
ኩንዴራ ይሄን የሚነግረን ከምናቡ አውጥቶ አይደለም፡፡ ታሪኩ የስታሊን እና የኬጂቢው ባለሥልጣን የኒኮላይ የሾቭ ነው፡፡ የሾቭ በአገር መክዳት ተወንጅሎ በስታሊን ከተገደለ በኋላ ከታሪክና ከፎቶግራፍ ሁሉ ተሰርዞ እንዲጠፋ ተደርጓል፡፡ የኩንዴራ ትርጓሜ ሰውን ያህል ትልቅ ፍጡር በጉድጓዳ ጨርቅ ተተክቶ እንዲታየን ያደርጋል፡፡ ኩንዴራ ይሄንን ታሪክ እየመላለሰ በማምጣት የብዙ ትረካዎች ማንፀሪያ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ ፍራንዝ ካፍካ የተሰኘውን ደራሲ የድርሰት መድረክ በጎትዋልድ የፖለቲካ መድረክ እየፈከረ የመፅሐፉ ክፍል ስድስት ላይ ያቀርብልናል፡፡
የኩንዴራ ልቦለዶች በፖለቲካ፣ በወሲብ፣ በፍቅር፣ በሥነ-ፅሑፍ እና በሌሎችም ጉዳዮች መጨናነቅ የበዛበትን የደራሲውን ነፍስ የሚወክሉ ናቸው፡፡ ብዙ ቁርጥራጭ ገጠመኞችና ሁናቴዎች ሳይሰደሩ በሥራው ውስጥ ይስተዋላሉ፡፡ ኩንዴራ እነዚህን ገጠመኞችና፣ ሁኔታዎች ተሰድረው መታወሳቸውን “የህይወት ታሪክ” ይለዋል። ምንም እንኳን ማህበራዊ ህይወት ውስጥ የሚኖረንን ቦታ እና የምንሻውን ደረጃ በማገናዘብ የአስፈላጊነትና ያለ አላስፈላጊነት ደረጃ ብናወጣላቸውም በራሳችን ጠንቅቀን አንረዳቸውም ይላል፡፡ የአንድ ደራሲ ኃላፊነት እነዚህን ቁርጥራጭ የህይወት ታሪክ ክፍሎች ሳይሰለቹ፣ ከተቻለ አስቂኝ አድርጎ ማቅረብ።
እዚህ ላይ ኩንዴራ ከኛው ደራሲ ከበዕውቀቱ ስዩም ጋር አይመሳሰልም? እንደውም አንድ ቀን አንቶኒ ሊሒን ከተሰኘ እንግሊዛዊ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፡፡ “ለምን ቀልዶችን እንደ አንድ የሥነ ፅሑፍ መሣሪያ አድርገህ ትጠቀማለህ?” የሚል፡፡ ሲመልስ፡
“ምናልባትም፣ በአፕሪል ዘ ፉል ቀን ስለተወለድኩ ይሆናል” ብሏል፡፡ በእርግጥም የተወለደው ኤፕሪል 1, 1929 ዓ.ም ነው፡፡
በዕውቀቱ ስዩም ሚላን ኩንዴራን እንዳነበበው አውቃለሁ፡፡ ሁለታችንንም በአንድ ወቅት ያስነበበን ሟቹ ደራሲ ደምሴ ፅጌ ነበር፡፡ በዕውቀቱ ኩንዴራን እንደወደደው አስታውሳለሁ፡፡ እሱን በወደደበት ዘመንም “መግባትና መውጣት” የተሰኘ ልቦለዱን ፅፏል፡፡ “መግባትና መውጣት” እንደ ኩንዴራ ሥራ ሁሉ “ወጋዊ ልቦለድ” (Essay Novel) ነው፣ ከዚህ ከቅርፅና ከአተራረክ ባሻገር በለዛም ሁለቱ ደራሲዎች የሚጋሩት ነገር አለ፡፡ በዕውቀቱ የተወለደው “በአፕሪል ዘ ፉል” ዕለት ይሁን፣ አይሁን ባይታወቅም እንደ ኩንዴራ ሁሉ ቀልድን የሥነ -ፅሀፉ እንድ አላባ አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ ቀልድን የፖለቲካ ማሽሟጠጫ አድርገው ማቅረባቸውም ያመሳስላቸዋል። “መግባትና መውጣት” ውስጥ ካሉ ፖለቲካዊ ሽሙጦች ይሄን መጥቀስ ጥሩ ምሳሌ ነው….
… ልጁ ዝናብ አሳዶት ካፌ በረንዳ ላይ እየተጠለለ ነው፡፡ በኋላ ሲያባራ ከመሄድ ይልቅ ወደ ካፌው ገብቶ ይለምናል፡፡ ልጁ በተራኪው ሲገመገም፣ ሽሙጡ ብቅ ይላል፡፡ “ልጁን … ከላይ እስከ ታች ገመገምሁት፡፡ “የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው” የሚል ጥቅስ የተፃፈበት ለአዋቂ የሚሆን ቲ-ሸርት ለብሲ ነበር፡፡ በእርግጥ በጥቅሱ ላይ ያለው ‹እግዚዘ› የሚለው ቃል በእድፍ ስለ ተዋጠ “የጥበብ መጀመሪያ … ብሔርን መፍራት ነው” የሚለው ፅሁፍ ብቻ ይታያል፡፡”
ዳር ዳር ያልኩት ኩንዴራ የበዕውቀቱ መንገድ ጠራጊ ነው ለማለት አይደለም፡፡ ኩካንዴራ በበዕውቀቱ የተወደደው የምርጫ አንድነት ስለነበራቸው ነው፡፡ ይሄንን ለማረጋገጥ የበዕውቀቱን “እንቅልፍ እና ዕድሜ”ን መመልከት ነው፡፡ በዕውቀቱ ይሄን ልቦለድ የፃፈው ኩንዴራን ሳያውቅ በፊት ነው። የሚገርመው ግን የሥራው ለዛ፣ ቅርፅ፣ የፍላጎት አዝማሚያ ከኩንዴራ “The Joke” ጋር መሣ ለመሣ የሚታይ ነው፡፡ “The Joke” ደግሞ አራት ተራኪዎች አንዱን ታሪክ ከየራሳቸው ጥግ እያዩ ቀለም የሚሰጡበት ስራ ነው፡፡ ቀልድን የልበሎለድ የሙያ ዕቃ አድርጎ ማቅረብም እዚህ የበዕውቀቱ ሥራ ላይ የተተገበረ ጉዳይ ነው፡፡ እንደውም ይሄ ልቦለድ በወጣ ሰሞን ሐያሲ አብደላ እዝራ “ሚዩዚክ ሜይ ዴይ” የሥነ ፅሑፍ መድረክ ላይ አንድ ጥናት አቅርቦ ነበር፡፡ የአብደላ ገለፃ እስካሁን አእምሮዬ ላይ ታትሞ አለ፡፡ እንዲህ ነበር ያለው፡- “እንቅልፍ እና እድሜ ውስጥ ቀልድ የሸፈነው የረጋ እንባ አለ፡፡ ላጥ ሲያደርጉት ሐዘን ኩልል ብሎ ይወርዳል፡፡”
የበዕውቀቱ ሁለቱ ሥራዎች ከምናብ ወጥቶ ወደ እውነታ መሸሸግ ብቸኛ አማራጩ ለሆነው ሰሞንኛ  ልቦለድ መሪ ኮከቦች ናቸው፡፡ እንደ ሰብአ ሰገሎች ከተከተላቸው አዲስ ተስፋ ወደተወለደበት የሥነ ፅሁፍ “ጋጣ” ያደርሱታል፡፡ ለመሆኑ “እንቅልፍ እና ዕድሜ” ሆነ “መግባትና መውጣት” ወጋዊ ልቦለድ መሆናቸውን በምን እናረጋግጣለን? እኔ ጥቂት ፍተሻ በማድረግ የደረስኩባቸው እውነቶች አሉ፡፡ በጥያቄ መልክ ለእናተ ላቅርብና እናንተም በየራሳችሁ ፍኖት ልትደርሱባቸው ሞክሩ፡-
“እንቅልፍ እና ዕድሜ” ውስጥ ተራኪዎች አሉ ብለናል፡
አንዱ ገጣሚ፤ ሌላኛው ሰዓሊ፤ ሶስተኛው የሥጋ መብል ጠል (Vegetarian) የሆነው የስነ - ልቦና አማካሪ ነው፡፡ ይሄ ከበዕውቀቱ ጋር በምን ይገናኛል? “መግባትና መውጣት” ላይ ያለው ተራኪ የጀርመንኛ ቋንቋ ተማሪ፣ ምዑዝ የሚባል ጓደኛ ያለው፣ ጆሮውን ታማሚ፣ ነገሮችን ገልብጦ የሚረዳ፣ …. ነው፡፡
እህስ? በዕውቀቱን በመፅሐፉ፣ መፅሐፉን በበዕውቀቱ ለይተን እናውቃለን? መፅሐፎቹ ውስጥ ቁርጥራጭ የህይወት ገጠመኞቹ እውነታን ወክለው ተቀምጠዋል? በህይወት የነበሩ ሰዎች ከበደ ሚካኤል፣ አፄ ቴዎድሮስ እና አባ አርጌኔስ ልቦለዱ ውስጥ መገኘታቸው ምንን ያመለክታል?...
(አማርኛ ልቦለድ፣ አማርኛ ወግን አጉራህ ጠናኝ ያለበት ሥራ የበዕውቀቱ ብቻ እንዳልነበር ባለፈው ፅሑፍ ጠቆም አድርገን ነበር፡፡ ነገር ግን ‹አንድ ሀረግ ሲመዙ ዱር ይነቀንቁ› ሆኖብን ጊዜና ቦታ እያጠረን ሄደ፡፡ ወደፊት ተለይቶ ባልተነገረ ዕለት ጉዳዩን ዳግም ቀስቅሰን ሌሎቹን ደራሲዎችና ሥራዎች ለመፈተሸ እንሞክራለን፡፡ እስከዚያው ለልቦለድ ትንሳኤ ያውርድ፡፡ አሜን!)

Read 2169 times