Saturday, 06 June 2015 14:44

“...ይህ አይነቱ ትምህርት ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሮ አያውቅም...”

Written by  ዮዲት ባይሳ ከኢሶግ
Rate this item
(5 votes)

ከባለሙያው እውቀት ማነስ ወይም በሌላ ምክንያት በህክምና ላይ የሚፈጠሩ ስህተቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ሁሉም በህክምና ላይ የሚፈጠሩ ስህተቶች በባለሙያው የእውቀት ማነስ የሚከሰቱ ናቸው ማለት ባይቻልም የህክምና ባለሙያዎች ወቅታዊውን የህክምና ሳይንስ ባለማወቃቸው የተለያዩ የህክምና ስህተቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል፡፡
እነዚህን በህክምና ላይ የሚከሰቱ ስህተቶች ለመቀነስ ብሎም የህክምና ባለሙያዎች በየጊዜው ከሚሻሻሉ የህክምና አሰራሮች ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግ CME (Continuous Medical Education) ወይም ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት በሚል በተለያየ የህክምና ስራ ላይ ላሉ ባለሙያዎች መሰጠት ከጀመረ ጥቂት አመታት ተቆጥረዋል፡፡
በዛሬው ፅሁፋችንም ይህን አይነቱ ስልጠና ለእራሳቸው ለባለሙያዎቹ እንዲሁም ለታካሚዎች የሚኖረው ጠቀሜታ በተጨማሪም ስልጠናውን በሀገራችን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ምን ይመስላሉ የሚሉትን ጉዳዮች እንዳስሳለን፡፡
ይህ ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት የህክምና ባለሙያዎች እራሳቸውን በየግዜው ከሚሻሸለው የህክምና ሳይንስ ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግ የሚሰጥ ስልጠና ወይም ትምህርት እንደሆነ የፅንስና ማህፀን ሕክምና እስፔሻሊስት እና በኢትዮጵያ ፅንስና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር የቦርድ አባል የሆኑት ዶክተር መንግስቱ ኃይለማሪያም ይናገራሉ፡፡
#...Continuous Medical Education ወይም CME የእንግሊዝኛ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት ማለት ነው፡፡ ይህ ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት መሰጠት ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያት የህክምና ሳይንስ በየጊዜው የሚለወጥና የሚቀያየር በመሆኑ የህክምና ባለሙያዎች በየጊዜው ከሚሻሻሉ የህክምና ሳይንሶች ጋር እንዲተዋወቁ እና ሙያቸውን እንዲያሻሽሉ ለማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ዘመናዊ የሆነ፣ ሳይንስ ያረጋገጠው እንዲሁም በመረጃ ላይ የተደገፈ አገልግሎት እንዲያገኙ እድል የሚፈጥር ተከታታይ የሆነ የትምህርት ሂደት ነው ማለት ነው፡፡”
ዶክተር መንግስቱ እንደገለፁት ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት በዋናነት የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡት አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀና ህብረተሰቡም ከዚህ ተጠቃሚ መሆኑን ለማረጋገጥ ታስቦ የሚሰጥ ሲሆን ያደጉ የሚባሉት ሀገራት ይህን አይነቱን ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት ስርአት ከጀመሩ ጥቂት አስርት አመታት እንደተቆጠሩ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ባለሙያውም ይህንን ሀሳብ ያጋራሉ፡፡
“...ይህ አይነቱ ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት በብዙ ሀገሮች ላይ አለ፡፡ በተለይ ያደጉ የምንላቸው እና የህክምና አሰጣጥ ላይ ትልቅ ደረጃ የደረሱትን ሀገሮች ስንመለከት ይህን የስልጠና ስርአት ተግባራዊ ካደረጉ ቆይተዋል፡፡ በእነዚህ ሀገራት ከድሮ ጀምሮ ምናልባትም ከመቶ አመት ጀምሮ የጤና ባለሙያዎቻቸው በሚቆዩባቸው የስራ ግዜያት ውስጥ በየግዜው እራሳቸውን ማሻሻል እንደ ግዴታ የተቀመጠባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ያለውን ሁኔታ ብንመለከት አንድ የጤና ባለሙያ ህጋዊ ሆኖ ለመስራት መውሰድ የሚገባው ኮርሶች አሉ፡፡ ስለዚህ ባለሙያው እነዛን ኮርሶች ወስዶ ማጠራቀም ያለበትን ነጥቦች ካላጠራቀመ የስራ ፍቃዱ አይታደስለትም፡፡ የስራፈቃዱ ደግሞ ካልታደሰ በሀገሪቱ ላይ መስራት አይችልም፡፡”
የስልጠና ስርአቱ የመጨረሻ ግብም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እጅግ ዘመናዊ ወይም ወቅታዊ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የጤና ባለሙያዎች ሙያቸውን የሚያሻሽሉበትን መንገዶች ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ሰአት ይህ ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት ሀገራችን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የሙያ ማሻሻያ ስርአቱን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃርስ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ምን ይመስላሉ?   ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥትውናል፡፡
“...ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት በሀገራችን ያለውን ታሪካዊ ዳራ ያየን እንደሆነ ይህ አይነቱ ስልጠና ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሮ አያውቅም፡፡ በርካታ ባለሙያዎች ከየጤና ሳይንስ ኮሌጆቹ በየግዜው ይመረቃሉ፡፡ ከትምህርት ቤት ከወጡ በኋላም በየቦታው ይመደባሉ፡፡ ነገርግን የሚሰጡት አገልግሎት ተገቢ እና ደረጃውን የጠበቀ ነው ወይ? በሰለጠኑበት ሙያ የሚጠበቀውን አገልግሎት እየሰጡስ ነው ወይ? የሚለውን የምናረጋግጥበት መንገድ አልነበረም፡፡”
ነገር ግን የሙያ ማሻሻያ ስርአቱን ተግባራዊ ከማድረግ በጅምር ላይ ያሉ ስራዎች አሉ ይላሉ ባለሙያው፡፡
“...ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ይህ አይነቱ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ሀገራችን አልነበረም፡፡ ነገር ግን ከአለፈው አመት ጀምሮ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር በመድሀኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን አማካኝነት የጀመረው ስራ አለ፡፡ በዚህም ሁሉም የህክምና ባለሙያዎች በተለይ ደግሞ የእስፔሻሊስት ሀኪሞች የሙያ ፈቃዳቸውን ለማደስ ከመምጣታቸው በፊት  በየአመቱ የተለያዩ ሙያዊ ትምህርቶችን በመውሰድ የተወሰኑ ነጥቦች ማጠራቀም ይኖርባቸዋል፡፡ ነገርግን ያንን ነጥብ ካላጠራቀሙ ፈቃዳቸው መታደስ የለበትም የሚል አካሄድ ተይዟል፡፡ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ የነበረው ባለፈው መስከረም 2007 አመተ ምህረት ላይ ነበር፡፡ ነገርግን መመሪያው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት መከናወን ያለባቸው ስራዎች አሉ፡፡  
ለምሳሌ በቅድሚያ ኮርሱን የሚሰጠውን ድርጅት ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ትምህርቱን የሚሰጡት ዩንቨርሲቲዎች፣ በጤና ዙሪያ የሚሰሩ የሙያ ማህበራት ወይም ሌሎች በዚህ ጉዳይ ላይ ልምድ ያላቸው ተቋማት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት ትምህርቱን ከመስጠታቸው በፊት ከሚመለከተው አካል ማለትም ከኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሀኒትና ጤና ከብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን ፍቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ መመሪያው በስራ ላይ ከመዋሉ በፊት እነዚህ ነገሮች ሁሉ መስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡”  
በሀገራችን የጤና ባለሙያዎችን ምዝገባና የሙያ ፍቃድ አሰጣጥ ለመቆጣጠር በሚል የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሀኒትና ጤና ከብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን ተቋቁሞ በስራ ላይ ይገኛል፡፡
ባለሙያው እንደጠቀሱት ባለስልጣኑ ይህንን አይነቱን ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት ለመቆጣጠር በአዋጅ ቁጥር 661/2002 አንቀፅ 55 ንኡስ አንቀፅ እና ደንብ ቁጥር 299/2006 መሰረት የጤና ባለሙያዎች የሙያ ስራ ፈቃድ አሰጣጥ አስተዳደር እና ቁጥጥር መመሪያ አውጥቶ  ተግባራዊ ለማድረግ በስራ ላይ ይገኛል፡፡
ባለስልጣኑ ባወጣው መመሪያ መሰረት “ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ” ማለት ማንኛውም የጤና ባለሙያ በስራ ላይ እያለ በሙያው ያገኘውን እውቀት እና ክህሎት ጠብቆ እንዲቆይ እና የሙያ ብቃቱን ለማጎልበት በየግዜው የሚወስደው ስልጠናና ሌሎች የሙያ ማጎልበቻ ስራዎችን እንደሚያካትት ተገልፆአል፡፡
መመሪያውን ማውጣት ያስፈለገበት ዋና አላማም፡-
የጤና ባለሙያዎችን ምዝገባና የሙያ ስራ ፈቃድ አሰጣጥ አስተዳደርና ቁጥጥር ስርአትን በማጠናከር የህብረተሰቡን ደህነት ለመጠበቅ
ህብረተሰቡ ሙያዊና ስነ ምግባራዊ ብቃት ባላቸው የጤና ባለሙያዎች አገልግሎቱን እንዲያገኝ ለማስቻል እንዲሁም
የጤና ባለሙያዎች ምዝገባና  የሙያ ስራ ፈቃድ አሰጣጥ አስተዳደር እና ቁጥጥር ስራ በግልፅነትና ተጠያቂነት ስርአት እንዲፈፀም ለማድረግ ነው፡፡
በሚል በዝርዝር ተቀምጧል፡፡  
እንደ ባለሙያው ከሆነ ትምህርቱ በክፍል ውስጥ፣ በኢንተርኔት ወይም በተለያየ ግዜ በሚደረጉ የሙያ ማህበራት አመታዊ ስብሰባዎች ላይ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ የሙያ ማህበራት አመታዊ ስብሰባዎች በተወሰነ የህክምና ዘርፍ ላይ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች ህብረት በመሆኑ በዘርፉ የሚኖሩ ለውጦችን ለባለሙያዎች ለማሳወቅ አይነተኛ መንገድ ነው፡፡ በዚህም በሙያው ዙሪያ ያሉ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች ይቀርባሉ በተጨማሪም በሙያው ላይ ያሉ አዳዲስ አሰራሮችም ይተዋቃሉ፡፡
አዲስ በወጣው መመሪያ መሰረት የጤና ባለሙያዎች እንደዚህ አይነት የሙያ ማሻሻያ ትምህርቶችን ተከታትሎ መውሰድ እና የሙያ ፈቃዳቸውን ለማደስ የሚያስችላቸውን ነጥብ በተገቢው ግዜ አሟልተው መገኘት እንዳለባቸው ተጠቅሷል፡፡
ስለዚህም ይላሉ ዶክተር መንግስቱ፡-
“..ስለዚህ ዋናው ነገር እያንዳንዱ የጤና ባለሙያ ከሙያው ጋር የተገናኘውን ኮርስ መውሰድ አለበት፡፡ ለምሳሌ የማህፀንና ፅንስ ሀኪሞች መውሰድ ያለባቸው ከሙያው ጋር የሚገናኝ ኮርስ ነው፡፡ ነገርግን ትምህርቱን ከመውሰዳቸው በፊት ስልጠናውን የሚሰጠው ተቋም ከሚመለከተው የመንግስት አካል እውቅና የተሰጠው መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አጠቃላይ የስልጠና ሂደቱ የተቀናጀ አይነት አካሄድ ላይኖረው ይችላል፡፡”
ይቀጥላል

Read 2930 times