Saturday, 13 June 2015 14:56

ልጅቷ የምን ተማሪ ነች?

Written by 
Rate this item
(7 votes)

       እግር ጥሎኝ ምሳ ልበላ አዲስ አበባ ውስጥ ወደሚገኝ ወደ አንድ ፋስት ፉድ ቤት ጎራ አልኩኝ። በረንዳው ላይ ልቀመጥ ፈለግሁኝ፡፡ ይሁንና ከአንድ አነስተኛ ጠረጴዛና አራት ኩርሲዎች በስተቀር ማስተናገድ የማትችለዋ በረንዳ በደንበኞች ተይዛለች፡፡ አማራጭ አልነበረኝምና ወደ ውስጥ ገባሀኝ፡፡
እየገባሁ ግን እንደልማዴ ሰዎቹን ገርመም አደረግኋቸው፡፡ ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት፡፡ ሕጻን ልጅም ይዘዋል፡፡ ዓይኔ ሴቷ ላይ ትንሽ ቆየ። ቀይ፣ ነጥብ እንኳን የሌለው ጥርት ያለ ፊት፡፡ ያለ ሊፕስቲክ እንዲሁ በተፈጥሮ የቀላ ቀጭን ከንፈር። 17-18-19 ቢሆናት ነው፡፡ ከኩርሲዎቹ በአንዱ ለይ ተቀምጣ፣ ግድግዳውን በመደገፍ፣ አንደኛውን እግሯን ማዶ ካለው የበረንዳው አጥር ላይ እንደ መስቀል አድርጋለች፡፡ ምቾት ፍለጋ እንጂ የቅምጥል አይደለም፡፡ “መለሎ መሆን አለባት፡፡ በዚያ ላይ የደረቷ ሙላት!” ስል ተደመምኩኝ፡፡  
ቤቱ ውስጥ የተወሰኑ ሰዎች አሉ፡፡ ልብ አላልኳቸውም፡፡ ፈጣኑ አስተናጋጅ ገና ከመቀመጤ ሜኑ ይዞ መጣ፡፡ ሜኑውን ማየት ሳያስፈልገኝ “ቺዝ በርገር፣” አልኩኝ፡፡
“የሚሄድ ነው ወይስ…” ጠየቀኝ ጎንበስ ለማለት እየሞከረ፡፡
“አይ፣ እዚሁ የሚበላ፣” ብዬ ሞባይሌን አወጣሁኝና ፌስ ቡክ ከፈትኩኝ፡፡ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡ “አክቲቭ ፍሬንድስ” ላይ ተጫንኩኝ። የተለመዱ ሰዎች እንደተጣዱ ናቸው፡፡ ትቼ ወጣሁኝ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለምን ፌስ ቡክ ውስጥ ዘልዬ እንደምገባ አላውቅም፡፡ “ምን ለማግኘት? ምን ለመጠቀም? በከንቱ ጊዜና ገንዘቤን በ 3ጅብ ለማስበላት?! እንድያው ምን ባደርግ ይሻለኛል?”
ድንገተኛ ዝናብ ካዘዝኩት ምግብ ጋር እኩል መጣ፡፡ “እንኳንም ውስጥ ገባሁኝ፡፡” በረንዳው ላይ የነበሩ ሰዎች ፒዛቸውን እንደያዙ ገቡና ከፊት ለፊቴ ያለውን አነስተኛ ጠረጴዛ ከበው ሰፈሩ፡፡ ልጅቷና አንደኛው ሰውዬ ጀርባቸውን ሰጥተዉኝ ተቀመጡ። ያኛው ሰውዬ ህጻኗን እቅፍ አድርጓት ከፊት ለፊት ለፊታቸው ተቀመጠ፡፡ አባቷ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በጣም ይመሳሰላሉ፡፡
“ይሄኛውስ ሰውዬ ለዚህችኛዋ ቆንጆ ምኗ ይሆን?” ስል አሰብኩኝ፡፡ “መቼም ጓደኛዋ አይሆንም፤ ምክንያቱም ሰፊ የእድሜ ልዩነት ይታየኛል፡፡ የሱ ቢያንስ የሷ ሲባዛ ሁለት ሲደመር አንድ ይሆናል፡፡ … እንዴ፣ እኔ ምን አገባኝ…? ለምን ባሏ አይሆንም? …. ደግሞስ ፍቅርን ዕድሜ  ይወስናል ያለው ማን ነው? ጀኒፈር ሎፔዝ በ42 ዓመቷ የ18 ዓመት ወጣት “ጠብሳ” አልነበረም እንዴ? እኛስ ጎረቤት ጋሽ አህመድ አዲሷን ሚስታቸውን በ41 ዓመት ይበልጧት የለምን? ማን ናቸው ባላምባራስ….” እያልኩኝ ነገሩንና በርገሩን አንድ ላይ ሳላምጥ ጎርነን ያለ ድምፅ ከሃሳቤ አባነነኝ፡፡
“አስራ ሁለተኛ ክፍል’ኮ ነች፤ አታውቅም እንዴ? ኢንትራንስ ተፈታኝ ነች፣” ልጅቷ አጠገብ ያለው ሰውዬ ነበር፡፡
“አስራ ሁለተኛ? ከመቼው? እኔኮ ዘጠነኛ ወይ አስረኛ መስላኝ ነበር፣” አለ የህጻኗ አባት፡፡
“ምን የዘመኑ ልጆች እንደሆኑ ይገርማሉ፡፡ ገና ትምህርት ቤት ከመግባታቸው ሚኒስትሪ ደርሰው ታያለህ፡፡ ያ ሲገርምህ ድንገት ይጠፉብሃል፡፡ “የት ሄደው ነው?” ስትል ዩኒቨርሲት ገቡ ትባላለህ፡፡”
“በእውነት እኔ ኢንትራንስ ተፈታኝ ትሆናለች ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡”
“እንዴት ነው ግን ጥናት?” አለ አጠገቧ ያለው ሰውዬ ወደ ልጅቷ ዞሮ፡፡
ልጅቷ ሾል ያለውን የፒዛውን ጫፍ በትንሹ ገመጥ አድርጋ ትከሻዋን ከፍ ዝቅ አደረገች፡፡
“እንዴ?!” አለ ሰውዬው፡፡ “ፒዛ የተጋበዝሽው’ኮ ሳይኮሎጂካሊ ለፈተናው ዝግጁ እንድትሆኚ ነው፡፡ ደርሷል’ኮ”
ፈገግ አልኩኝ፤ በሆዴ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ዘመዷ መሆን አለበት፡፡ አቀማመጣቸውና አነጋገሩ እንደዚያ ዓይነት ፍንጭ ይሰጣል…፡፡
“ተናገሪ እንጂ… እያጠናሽ ነው?” አላት፡፡
የህፃኗ አባት ልጁን ሚሪንዳ በጠርሙስ እያስጎነጫት ተራ በተራ ያያቸዋል፡፡
“እንዴ አዋ… እያጠናሁ ነው” አለች፡፡ ለስለስ ያለ ድምጽ አላት፡፡
 “እንደዚያ ከሆነ እስቲ ጥያቄ ልጠይቅሽ” አለና ማሰብ ጀመረ፡፡
“ኢንትራንሱ ተጀመረ” አልኩኝ ጥያቄው እንዳያመልጠኝ ማኘኬን ቆም አደረግሁኝ፡፡ ምን ዓይነት ጥያቄ ይሆን?
“እ… የአድዋ ጦርነት መቼ ተካሄደ?”
አሃ፤ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ መሆን አለባት፡፡ ወደ ልጅቷ ዞርኩኝ፡፡ ጀርባዋን ሰጥታኝ ስለተቀመጠች ፊቷን ማንበብ አልቻልኩም፡፡ ግን ልጅቷ ከኋላም ቆንጆ ነች፡፡ ከወገቧ ቀጠን ብላ ከመቀመጫዋ ሞላ ብላለች፡፡ “ናኑ ናኑ ነዬ” ትዝ አለኝ፡፡
ትንሽ አሰብ ካደረገች በኋላ፣ “1984” አለች፡፡
“እህ…?!!” የሚል የስቅታና የድንጋጤ ዓይነት ድምጽ ሰማሁኝ፡፡ ሰው ቤተ መጻህፍት ውስጥ ሆኖ ድንገት ሳያስበው ከኋላው በቀዝቃዛ ሹል ነገር ወጋ ቢደረግ የሚያወጣው ዓይነት ድምጽ ነው፡፡
አብሯቸው ያለው ሰውዬ ድንገት አገጩን ጣለና አፉ ውስጥ ያለው ምግብ ታየኝ፡፡ ዓይኖቹ ወጣ ወጣ ብለው ልጅቱ ላይ ተተክለዋል፡፡
ማን ነው ግን ያን ድምጽ ያወጣዉ? እኔ ነኝ እንዴ? ማለቴ ሰው ምግብ ሲውጥ ቢደነግጥ፣ እንደዚያ ዓይነት ድምጽ ሊያወጣ ይችላል? በሃፍረት ዙሪያዬን ቃኘት አደረግሁኝ፡፡ ዞሮ የሚያየኝ የለም። ተመስጌን!
“አስራ-ዘጠኝ-ሰማኒያ-አራት?” አላት ዘመዷ እያንዳንዷን ቃል ረገጥ እያደረገ፡፡
ልጅቷ ዝም አለች፡፡
ወዲያው የሆነ አጋጣሚ ትዝ አለኝ፡፡ ለአንድ ከዩኒቨርሲቲ ለተመረቀ ሰው ከጠቅላላ ዕውቀት በመነሳት ስለ ሶላር ሲስተምና ፕላኔቶች በፀሐይ ዙሪያ ስለሚያደርጉት ዑደት ገለጻ እያደረግኩኝ ሳለ የአንደኛዋ ፕላኔት ስም ጠፋብኝ፡፡ “ማን ነበረች…? ማን ነበረች…? ማታ ማታ እኮ ፀሐይ እንደጠለቀች ሰማዩ ላይ ጎልታ የምታበራዋ ኮከብ ነች፡፡ እንዴ…” እያልኩኝ ሳስብ ሳሰላስል ሰውየው ሊያስታውሰኝ ፈልጎ “ኦዞን?” አለኝ፡፡
ይህችኛዋ ልጅ የባሰች ናት፡፡ አድዋ የተካሄደው አስራ ዘጠኝ ሰማኒያ አራት ነው ትበል?
“አድዋ፣ አስራ-ዘጠኝ-ሰማኒያ-አራት?” አለ ዘመዷ እንደገና፡፡
“አዋ፣” አለች ልጅቱ፡፡ “እንደዚያ መሰለኝ፡፡”
አይ… በቃ ይህቺ ልጅ በርግጠኝነት የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ አይደለችም፡፡ ብትሆን ኖሮ ሂስትሪ ትምህርት ላይ ስለምትማር  ሰማኒያ ስምንት ዓመት ቀንሳ አትናገርም ነበር፡፡  የፈረንጆቹን የዓመት አቆጣጠር ከተጠቀመች ማለቴ ነው፡፡
“እንዴ አስራ ዘጠኝ ሰማኒያ አራትማ አይደለም።” አላት ዘመዷ፡፡
ልጅቷ ትከሻዋን ከፍ ዝቅ አደረገች፣ በግድ-የለሽነት፡፡
ቢጨንቀው ነው መሰለኝ የህፃኗ አባት “በኢትዮጵያ ነው በፈረንጅ?” ብሎ ጠየቃት፡፡ ሳቄን ያዝ አደረግሁት፡፡
አፏን በሶፍት እየጠረገች፣ “በኢትዮጵያ” አለች፡፡
አሁን እንኳን አልቻልኩም፡፡ የያዝኩትን አስቀምጬ ከት ብዬ ሳቅሁኝ፣ ምንም እንኳን በሆዴ ቢሆንም፡፡
“በኢትዮጵያ 1984 ማለት’ኮ ትላንት ነው፤ ምናልባት አንች ተወልደሽ ሊሆን ይችላል” አላት የህጻኗ አባት፡፡
ልጅቷ መልስ ሳትሰጥ ህጻኗን ከፒዛው እየቆነጠረች ማጉረስ ጀመረች፡፡
“የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ትሆናለች፤ ለምን በታሪክ ጥያቄ ያስጨንቋታል?” ስል አሰብኩኝ፡፡
“ቆይ ከ1984 ወዲህ ስንት ዓመት ነው?” ብሎ ጠየቀ የህጻኗ አባት፡፡ እስካሁን ግርምቱ አልለቀቀውም፡፡ ግን አገጩ ወደ ትክክለኛው ቦታ ተመልሷል፡፡ እሱ ይሆን እንዴ የቅድሙን ድምፅ ያወጣው?
ጎሽ! እንደዚህ ሂሳብ ነክ ጥያቄ ይሻላል፣ ከትምህርቷ ጋር የሚሄድ”… ስል አሰብኩኝ። “ግን የአድዋን ጦርነት ዓመት እቅጩን እንኳን ባያውቁ፣ እንዲያው ተቀራራቢ ግምት ለመስጠት የግድ የሕብረተሰብ ሳይንስ ወይም የታሪክ ተማሪ መሆን ያስፈልጋል እንዴ? በየዓመቱ የካቲት 23 መታሰቢያው ይከበር የለ?”
ልጅቷ ከ1984 ወዲህ ስንት ዓመት እንደተቆጠረ ለመመለስ አይኗን ጣሪያው ላይ ተከለች፡፡ እኔም አይኖቿን ተከትዬ ጣሪያው ላይ አንጋጠጥኩኝ፡፡ ልክ እንደ ግድግዳው ሁሉ ጣሪያውም በበርገርና በፒዛ ስዕሎች አሸብርቋል፡፡ የትኛውን መምረጥ እንዳለባት የተቸገረች ይመስል አይኖቿን ከአንደኛው ስዕል ወደ ሌላኛው ታንከባችልላለች፡፡
ጨነቀኝ፡፡ መቶ ዓመት እንዳትል ብዬ ፈራሁኝ፡፡
በመጨረሻም ዓይኖቿን ከጣሪያው ላይ አንስታ ጠያቂዋ ላይ አኖረች፡፡ አውጥታ አውርዳ ያገኘችውን መልስ ነገረችው፤ “ከ1984 ወዲህ… እኔ እንጃ ፡፡ ስንት ዓመት ነው?”
“የባሰው መጣ!! ቆይ ይህቺ ልጅ የምን ተማሪ ናት? ታሪክ ካላወቀች የህብረተሰብ ሳይንስ ተማሪ ላትሆን ትችላለች፡፡ ሂሳብ ላይ ዜሮ ከሆነች የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ አይደለችም ማለት ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት የሂሳብ ችሎታ ይዞ ሳይንስ የሚደፍር የለም፡፡”
“አንቺ ልጅ በዚህ ሁኔታ ነው ኢንትራንስ የምትፈተኚው? ማጥናት’ኮ አለብሽ!” አላት ዘመዷ፡፡
“እያጠናሁ ነኝ፡፡”
“እያጠናሽ ነው?” አለ በፌዝ ቅላፄ፡፡ “እንደዚያ ከሆነ እሽ ሌላ ጥያቄ ልጠይቅሽ፡፡ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመቼ እስከ መቼ ተካሄደ?”
“ይሄ ደግሞ ምኑ ጦረኛ ነው?” አልኩኝ ለራሴ፡፡ “ሌላ ጥያቄ የለውም?”
ልጅቷ እንዳልሰማች ህጻኗን ማጫወት ጀመረች።
“መልሽ እንጂ”
“እያሰብኩ ነው”
“ይሄ’ኮ ማሰብ የሚያስፈልገው አይደለም። በአንዴ ተረክ የሚደረግ ነው፡፡” አላት ዘመዷ እንዳያሳፍራት ሳቅ እያለ፡፡
“በ1911 ነው የተጀመረው፣” መለሰች፡፡
“አይደለም፡፡ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተካሄደው፣ ትሰሚያለሽ፣ ከ 1939 እስከ 1945 ነው።” አላት ቃላቶቹን ረገጥ እያደረገ፡፡ ልጅቷ ዝም አለች፡፡ “እሺ ለጦርነቱ መጀመር ዋናው ምክንያት ምንድነው፣ አጣዳፊውስ ምክንያት ምንድነው?”
ዝም፡፡
“ማን ተገድሎ ነው ጦርነቱ የተጀመረው?”
ዝም፡፡
ምናልባት እዚህ ጋ ሰውዬው የኦስትሪያውን አልጋ ወራሽ የፍራንሲስ ፈርድናንድን መገደል አስቦ ከሆነ ተሳስቷል ማለት ነው፣ ምክንያቱም ይሄ ለአንደኛው የዓለም ጦርነት መለኮስ አጣዳፊው ምክንያት ነው እንጂ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጋር አይገናኝም፡፡
“እሺ ዘመነ መሳፍንት ከስንት ዓመተ ምህረት እስከ ስንት ዓመተ ምህረት ተካሄደ?”
ዝም፡፡
“እሺ ዘመነ መሳፍንትን ያስቆመው ንጉስ ማን ነው?” እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ከኢትዮጵያና ከዓለም ታሪክ እያቀላቀለ ጠየቃት። ልጅቷ ግን አንዱንም እንኳን ስትመልስ አልሰማሁም። ሰውዬው ግን የተወሰነ የታሪክ ዕውቀት እንዳለው ተገንዝቤአለሁ፡፡
“አንቺ ልጅ ዋ! ዩኒቨርሲቲ ሳትገቢ ትቀሪና!”
“እንዴ! እገባለሁ፡፡ ኮራ ብዬ ነው ለዛውም”
እስከ ጆሮዎቼ ድረስ ፈገግ አልኩኝ፡፡ ከሕፃኗ አባት ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጨን፡፡ ፈገግ አለ እሱም። አፍሬ ዓይኔን ጣሪያው ላይ ተከልኩኝ፡፡ ወዲያው ሃሳብ ይዞኝ ሄደ፡፡ ይህቺ ልጅ አሁን ምንና እንዴት ተምራ ነው እስከዚህ የደረሰችው? የትምህርት ቤቷንና ሀገር-አቀፍ ፈተናዎችን እንዴት አልፋ ነው ዩኒቨርሲቲ ለመግባት አንድ ሐሙስ የቀራት? ምንስ ብትተማመን ነው ዩኒቨርሲቲ እንደምትገባ እርግጠኛ ሆና የምትናገረው?
በርግጥ በእነዚህ ጥያቄዎች ብቻ ስለ ልጅቷ ዕውቀትና ትምህርት ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ማግኘት ባይቻልም፣ መሠረታዊ የሒሳብ ዕውቀት ከሌላት፣ ስለ ወሳኝ የዓለምና የሀገራችን ክስተቶች መሠረታዊ ግንዛቤ ከሌላት፣ ሌላ ምን ማለት ይቻላል?
“ወንድም ይቅርታ… ልወጣ ስለሆነ ሒሳብ ትሰጠኛለህ?... ካላስቸገርኩህ?”
ከሀሳቤ ተመለስኩኝ፡፡ “ኧረ ችግር የለውም፡፡”
ሰዎቹ የሉም፡፡ ዞር ብዬ ወደ ውጭ አየሁኝ፤ ዝናቡም ቆሟል፡፡ እንዴ መቼ ወጡ?

Read 5609 times