Saturday, 04 July 2015 11:06

በ7 ቋንቋዎች የህፃናት መፅሃፍት ሊዘጋጁ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    በህፃናት ላይ የሚሰራው ዊዝ ኪድስ፣ በ7 ሃገርኛ ቋንቋዎች የተለያዩ የህፃናት መፅሃፍትን ለማዘጋጀት ማቀዱን ገለጸ፡፡ መፅሃፎቹ በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በሃዲያ፣ በሶማሊኛ፣ በሲዳሞኛ፣ በኦሮምኛና በወላይትኛ ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ሲሆን በቀጣይ ሳምንት በሚያካሂደው የ7 ቀናት ወርክሾፕ ላይ የመፅሃፎቹ ዝግጅት ይከናወናል ተብሏል፡፡
ከመስከረም ወር ጀምሮም መፅሃፎቹ ለገበያ እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል።  የዊዝ ኪድስ ወርክሾፕ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ብሩክታዊት ጥጋቡ፤ ድርጅታቸው በአዲሱ ትውልድ ልብ ውስጥ የንባብ ልማድና ፍቅርን ለማስረጽ በማለም ወደ መፅሃፍት ዝግጅት መግባቱን ጠቁመው፣ የህፃናትና  ታዳጊዎች ንባብ መጎልበት ሃገሪቱ ለምትሻው የትምህርት ጥራት አጋዥ ይሆናል ብለዋል፡
በሰባቱ ሃገርኛ ቋንቋዎች የሚዘጋጁት መፅሃፍቱ፤ህፃናትን የሚያነቃቁ የተለያዩ ታሪኮችና ርዕሰ ጉዳዮችን የሚያካትቱ  ይሆናሉ፤ የህፃናቱን እድሜ የሚመጥኑ እንዲሆኑም ይደረጋል ተብሏል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር የዘርፉ ተግዳሮቶች ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል አስፈላጊ የሆኑ አጋዥ መፅሃፍት እንደልብ አለመገኘት አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ብሩክታይት፤ ድርጅታቸው ይህን እጥረት ለመቅረፍ ከትምህርት ስርአቱ ጋር የተጣጣሙ ጥራት ያላቸውን ተነባቢ መፅሀፍት በተለያዩ የሃገሪቱ ቋንቋዎች ማዘጋጀቱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ዊዝ ኪድስ በአሁን ወቅት እድሜያቸው ከ3-17 ዓመት ለሆናቸው ህፃናትና ታዳጊዎች 3 የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እያዘጋጀ ሲሆን ከዚህ ቀደም በ5 ሃገርኛ ቋንቋዎች፣ከ35 በላይ የህፃናት መፅሃፍት አሳትሟል፡፡

Read 1489 times