Monday, 31 August 2015 09:48

የዓውዳመት ግርግር

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(11 votes)

    ቡሄ ካለፈ በኋላ የዐውደ-ዓመት መአዛ ከተሞችን ያሽቆጠቁጣል፡፡ ወትሮ የተለመዱት ነገሮች ሳይቀሩ አንዳች ቀለም ይረጭባቸዋል፡፡ የሆነ መአዛ ያሳብዳቸዋል፡፡ ሳሩና ቅጠሉ የግዱን አይን ይሰርቃል፡፡ አበቦች እንኳ አፋቸውን ፈትተው “የምስራች” ባይሉም፣ ገና በዋዜማው ሳቅ ሳቅ የሚላቸው ምትሃታዊ ቋንቋ ይነበብባቸዋል፡፡
ከዚያ ባሻገር መንደሮች በአውራ ዶሮና በሲካካ ዶሮዎች ሽር ጉድና ፍልሚያ መናጣቸው የግድ ነው፡፡ እንዲያውም ድሮ-ድሮ በጐች የሚዋጉባቸው መስኮች ናቸው ዛሬ ለአውራ ዶሮ መናከሻ የዋሉት እንጂ ጉዳዩ ሌላ ነበር፡፡ ይህንንም አያሳጣን ማለትን የለመደው የአለታ ወንዶ ሰው ብቻ አይደለም፡፡ ሀገር ሁሉ ነው፡፡
እትዬ አረጋሽም እዚህ ማርያም ሰፈር ልጅነታቸውን ፈጅተው፣ አዋቂነታቸውን አጣጥመው ኖረዋል፡፡ ከጥቁር ቦቃ በግ እስከ ጥቁር ገብስማ ዶሮ ለእንቁጣጣሽ፣ ከዳለቻ በግ እስከ ወሰራ ለመስቀል እያረዱ ዘልቀዋል፡፡
ዘንድሮ እንዳምናው ባይቀናቸውም እንኳ ጥቁር ገብስማ ዶሮዋቸውን ገዝተው ለቅቀዋል፡፡ አንዳንድ ጐረቤቶቻቸው ቀይ፣ ሌሎቹ ነጭ ገብስማ አሰማርተዋል፡፡ ያ-ነገረኛ ከፈለኝ ግን ቁርጥ የራሳቸውን የመሰለ ጥቁር ገብስማ ዶሮ ገዝቶ ስለለቀቀ፣ ነገር እንዳይመጣ ፈርተው፣ እግሩ ላይ ቀይ ጨርቅ ያሰሩት ዛሬ ነው፡፡
“አማከለች ልብ አድርጊልኝ… ኋላ ለሃይማኖትሽ ትመሰክሪያለሽ… ቀኝ እግሩ ላይ ምልክት አድርጌያለሁ” አሏት - ልጅ እግርዋን ጐረቤታቸውን፡፡ እሷም ተሽቆጥቁጣ…. “ኧረ የትም ብሄድ እመሰክራለሁ… አለች፡፡ ለነገሩ ሳታይም ቢሆን ከመመስከር አትመለስም፡፡ አለዚያ ያ ሰካራም ባልዋ በዱላ ሲነርታት ማን ይደርስላታል?.... ቢያማት፣ ቢርባት፣ ሀዘን ቢደርስባት… እትዬ አረጋሽ ናቸው ከትንፋሽዋ ፈጥነው የሚደርሱላት!
እሳቸው ዶሮም ሆነ በግ ሳያርዱ አውደ አመት አያልፍም፡፡ ይፈራሉ፡፡ ለጤንነታቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለዘመዶቻቸው ሁሉ ሰላም የሚሆነው ይህን ሲያደርጉ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ባለቤታቸው ናቸው ይህንን የማይወዱላቸው፡፡ “ባንድ ጐን ፈጣሪ፣ በሌላ ጐን ጥንቆላ - ምንድነው!” በማለት ይቆጣሉ፡፡
“አዩ ያያት የቅድማያቶቼ ነው…. ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው፡፡ እናቴ አልለማመን ብላ ነው የሞተችው…. አባቴም እንዳንቱ ሲያንጓጥጥ ነው በሽተኛ ሆኖ አልጋ ላይ የወደቀው፡፡ የኋላ ኋላ ፈጣሪ ረዳው እንጂ!”
ማዘንጊያ አይዋጥላቸውም፡፡ እርሳቸውም ለነገሩ ሃይማኖተኛ አይደሉም፡፡ ልብስ ይሰፋሉ፣ ይበላሉ፣ ይጠጣሉ - በቃ! … ፈጣሪን በልባቸው ነው! ግን ተቀጥላ ነገር አይወድዱም፡፡ ልምምጥ - አይሆንላቸውም፡፡
“ቅመም የሌለው ዶሮና ሥጋማ አይዋጥልኝም… እናቴ ሀገር ያወቃት ባለሞያ ነበረች፡፡ ዳቦ እንኳ ስትደፋ የሰፈሩ ሰው እንደ ተአምር ነበር የሚያወራላት!... አሁንማ ምን ሴት አለ፡፡” ሲሉ ይመፃደቃሉ፡፡
አቶ ማዘንጊያ ገበያቸው እንደድሮ ስላልሆነ ለሚስታቸው ለአውደ አመት ምንም አልሰጡዋቸውም፡፡ አሁን ሰው ጣቃ አስቀድዶ ልብስ ማሰፋት ትቷል፡፡ ሁሉም ሬዲ-ሜድ ለባሽ ሆኖዋል፡፡ በተለይ ቻይና ከገባ ወዲህ የልብስ ሰፊ ገበያ ደክሟል፡፡ ልብስ ሰፊ፤ የቻይና ነገር ቆሽቱን ያሳርረዋል፡፡
አንዳንዴ እትዬ አረጋሽም ይከፋቸዋል፡፡
“እነዚያ ኩባዎች ገዳም ነበሩ፤ … ይላሉ፡፡” ወደው ግን አይደለም፤ ያኔ በደርግ ጊዜ ኩባ ደንበኞች ነበሯቸው፡፡ ጠጅ ቤታቸውን ግጥም አድርገው ሞልተው ነበር የሚጠጡት፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ጥሬ ሥጋ ይገዙና ቀዩን ሥጋ በልተው ጮማውን እንዳለ ነበር የሚሰጧቸው፡፡ በተለይ ታናሽና ሽንጥ ከገዙ ብዙው ለሳቸው ነበር የሚቀረው፡፡
ደግነቱ መኖሪያ ቤት ሰርተዋል፡፡ እርሷን ባያከራዩ ምን ይውጣቸው ነበር! በደጉ ጊዜ ቀበሌ መሬት በነፃ ሰጥቷቸው፣ የቤት ባለቤት ሆነዋል፡፡ ያኔ ሳንቲሙም በረከት ነበረው ይላሉ፡፡  እንዲያም ሆኖ ይመስገነው ማለታቸው አልቀረም … ሦስት ሰርቪሶች ለመንግሥት ሠራተኞች አከራይተዋል፡፡ ይህን ሲያስቡ ዘውድ ያልደፋ ንግስትነት ይሰማቸዋል፡፡
ትዳራቸው ብዙም ግጭት፣ ብዙም ፍቅር የለውም፤ ለሰስ ያለ ነው፡፡ ሲያገቡዋቸውም አብደው ክንፍ አውጥተው አይደለም፡፡ በምግብና በመጠጥ ነው የደለሏቸው፡፡ ያኔ ማዘንጊያ የሚያማልሉ ፈርጣማና ተደባዳቢ ነበሩ፡፡ እንዲያውም ከክቡር ዘበኛ ሠራዊት ከድተው ነው የመጡት ይባላል፡፡ የአለቃቸውን አፍንጫ ሰብረው ትንሽ ጊዜ ከተደበቁ በኋላ ነው ብቅ ያሉት፡፡
አለታ ወንዶ ከተማ ዲላ ሰፈር ልብስ ስፌት ጀምረው ተወዳጅነት ቢቀዳጁም ማታ-ማታ መጠጥ ቤት ያመሻሉ፡፡ ጥሎባቸው ጠጅ ይወድዳሉ፤ እትዬ አረጋሽ ደግሞ የጠርሙስ ጠጃቸው ሀገርን ያፋጀ ነበር፡፡ በወረፋ ነበር የሚጠጣው፡፡
አቶ ማዘንጊያ በዚያ ተላመዱ፡፡ አረጋሽም ወደዱዋቸው፡፡ “ቆፍጣናና ጐበዝ እወዳለሁ፡፡ …ጀግና ነው!” ይላሉ፡፡ ሁለቱም አላወቁት አልጋ ላይ ወደቁ፡፡ ከዚያ ጣት የሚያስቆረጥም ቅንጬ ጧት ጧት፣ ቀን በቅመም ያበደ ዶሮ፣ ማታ ክትፎ ሲለምዱ ገነት የገቡ መሰላቸው፡፡ ቀሩ - ቀሩ፡፡ አሁን አሁን ግን ልጅ ስላልወለዱ ይነጫነጫሉ፡፡ መጠጡም የባሰባቸው ለዚያ ነው፡፡ ባእድ አምልኮማ ማየት ጠልተዋል፡፡ እድሜያቸው እየጨመረ ሲመጣ ይሁን በሌላ አያውቁትም፤ ደስተኛ አይደሉም፡፡ ልባቸው ላይ አሎሎ ድንጋይ፣ ነፍሳቸው ላይ እሾህ የተተከለ ያህል ያማቸዋል፡፡ እናም ሁለንተናቸውን አረቄ ውስጥ ይዘፈዝፋሉ፡፡ ያኔ የምድረ በዳ ዋሽንት… የጨረቃ ልቅሶ… የፀሐይ ማላዘን - አይሰማቸውም፡፡ ….ድርግምግም ይላሉ - በሮች ሁሉ፡፡
እትዬ አረጋሽ የዶሮዋቸውን ቀኝ እግር በቀይ ጨርቅ ካሰሩ በኋላ፣ አማከለችን ምስክር ጠርተው፤ ቅመማቸውን - አስጥተው የጐረቤት ቡና ጠጥተው ፣ ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡
አቶ ማዘንጊያ ለምሳ ወደ ቤት አልተመለሱም፡፡ ለነገሩ - ደስ ያላቸው ቀን ይመጣሉ፣ ደስ ካላላቸው እዚያው ከጓደኞቻቸው ጋር ምናምኗን ቀማምሰው ይውላሉ፡፡
አረጋሽ ግን ትንሽ ቀማመሱና ወደ ዴላ ገበያ ለመሄድ ተነሱ፡፡
“አማከለች እንግዲህ ሰፈሩን አየት-አየት አድርጊ!... መጣሁ፡፡ አሏትና ነጠላቸውን አሰማምረው ዘንቢል ይዘው ተነሱ፡፡
“በሉ ጠንቀቅ ይበሉ!... የዓመት ባል ሌባ - እንደጭልፊት ነው የሚናጠቀው”
“እኔ ያንቺ እናት - ለዚህ እንኳ ቆቅ ነኝ፤… ተሰረቀች ሲባል ሰምተሽ ታውቂያለሽ!?”
“እሱስ አልሰማሁም! ብቻ አንድዬ ይጠብቅ ማለት ነው”
“እርግጥ ነው … እርግጥ ነው”
ተሰናብተው ቁልቁል ወረዱ፡፡ በከፈለኝ ቤት በኩል ሲወጡ ቤቱ ዝግ ነው፡፡ ሾፌር ስለሆነ ይሄኔ ካገር ሀገር ይንከራተታል፡፡ ከአለታ ወንዶ ሀገረሰላም፣ ቀባዶ፣ ተፈሪ ኬላ፣ ጩኮ፣ ይርጋለም… የማይሄድበት የለም፡፡ “ይሰራል፣ ይበላል፣ ግን አይጠጋውም!...” ይሉታል እትዬ አረጋሽ፡፡ በልባቸው ረግመውት አለፉ፡፡
“እመቤቴ ከሰፈሩ ንቅል ታድርግህ አንተን!” አሉና ለራሳቸው ገረማቸው፡፡ በሌለበት ምን አሳደበኝ የሚል ስሜት በውስጣቸው አደረ፡፡
ሼል ማደያ አካባቢ ሲደርሱ ከዲላ ሰፈር በኩል የብዙ ሰዎች የጭፈራ ድምፅ ሰሙ፡፡ ጠጋ እያለ ሲመጣ ጭፈራው የምን እንደሆነ ለዩ፡፡ ሌባ ተይዞ ነው፡፡“የቱ ነው የፈረደበት?!” አሉና ጥግ ጥጉን ይዘው ቁልቁል ወረዱ፡፡ ሕፃናት ልምጭ ነገር ይዘው ሌባውን ከብበዋል፡፡ እየተጠጉ ሲሄዱ ከፈለኝን አዩት፡፡ “እሱን ደ‘ሞ ሕግ አስከባሪ ያደረገው ማነው!” ብለው አጉተመተሙ፡፡ ያዩትን ነገር አይናቸው ማመን ሲያቅተው ዘንቢላቸውን ወርውረው ሮጡ፡፡
ጠዋት አቶ ማዘንጊያ የተናገሯቸው ትዝ አላቸው፤ “ይህንን ለሰይጣን የገዛሽውን ዶሮ ሸጬ ጉድ ባልሰራሽ!” ብለዋቸው ነበር፡፡
አረጋሽ በድንጋጤ፤ “በሕግ አምላክ! ዶሮው የኔ ነው!” እያሉ ሮጡ፡፡ ዶሮው እግር ላይ ግን ቀይ ጨርቅ የለም!... “ማዘንጊያ ጉድ ሆኗል” አሉ - በልባቸው፡፡ ባለቤታቸው ለከፈለኝ ወጥመድ መዳረጉን እያሰላሰሉ፡፡

Read 4317 times