Saturday, 19 September 2015 09:02

የታሪክ ባህሪያትና ዓላማ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

(በፕ/ር መስፍን “አዳፍኔ” መነሻነት

   በአማርኛ ቋንቋ ከሚጽፉ እጅግ ጥቂት ኢትዮጵያዊያን ምሁራን መካከል አንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አንዱ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ በሚጽፏቸው በሳል ጽሁፎችና በሚያነሷቸው አዳዲስ ጉዳዮች የምሁርነትን ልክ አሳይተውናል ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት በየሁለት አመቱ ልዩነት ማለት ይቻላል በተከታታይ ግማሽ ደርዘን የሚሆኑ መጽሀፍትን አስነብበውናል፡፡ ባለፈው ዓመትም (በ2007) ‹አዳፍኔ፡ፍርሃትና መክሸፍ› በሚል ርዕስ አዲስ መጽሀፍ አሳትመዋል፡፡
‹አዳፍኔ› ፕሮፌሰሩ በ2005 ዓ.ም ያሳተሙት ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› መጽሀፋቸው ተከታይ ክፍል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ሁለት አስረጂዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንደኛው ከጭብጥ አኳያ ብዙ ተመሳስሎሽ አላቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹አዳፍኔ› ከያዛቸው አስር ምዕራፎች ውስጥ ሶስቱ (ይህም የመጽሀፉን ዘጠና ስድስት ገጾች ወይም 40 በመቶ ያህል ይሸፍናል ማለት ነው) በ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› ላይ በተለያዩ ጸሀፍት ለተሰነዘሩ ትችቶች ምላሽ የሰጡበት (በመጽሀፉ እንደተገለጸው የ‹ ትችቶች ትችት›) ነው፡፡
በዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ አተያይ፤የመጽሀፉ ዋነኛ መገለጫዎች (መልኮች) ሁለት ናቸው፤እነዚህ ሁለት መገለጫዎችም የመጽሀፉ ውበቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው መጽሀፉ በይዘቱ ሰፋ ያለ መሆኑ ነው፤ከዚሁ ጋር የተያያዘው ሁለተኛው፣ መጽሀፉ በቅርጹና አቀራረቡ የራሱ የሆነ አዲስ ቀለም ይዞ መምጣቱ ነው፡፡ አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ እጅግ በርካታ ጉዳዮችን ይዳስሳል፤ታሪክ፣ባህል፣ስልጣንና አገዛዝ (ፖለቲካ)፣ኢኮኖሚክስ፣ስነመንግስትና አስተዳደር (አገር፣ህዝብና መንግስት)፣ሀይማኖት፣ትምህርትና ዕውቀት እንዲሁም ዕውነት፣ ስነ-ልቦና፣ፍልስፍና እና በሌሎች የጥናት ዘርፎች ዙሪያ የሚሽከረከሩ ጽንሰ ሀሳቦችን ያነሳል፡፡ ሌላው የመጽሀፉ መልክ ለጥናትና ምርምር፣ለጥልቅ ውይይትና ክርክር የሚጋብዙ ሀሳቦችን ማንሳቱና በዚሁ በተቃኘ አቀራረብ መዘጋጀቱ ነው፡፡
ወጣቱ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ በመክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ መጽሀፍ ዙሪያ ያለውን አተያይ ከሁለት አመታት በፊት ገደማ በአንድ መጣጥፉ አስነብቦናል፡፡ ዲያቆን ዳንኤል በመጣጥፉ ካነሳቸው በርካታ ቁም ነገሮች አንዱ የክሽፈት ታሪክ እንጂ የታሪክ ክሽፈት የሚባል ሊኖር አይችልም የሚለው አንዱ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፤ በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፋቸው ‹የትችቶች ትችት› በሚለው ምዕራፍ ውስጥ ለዚህ መልስ ሰጥተዋል፤ ነገር ግን መልሱ አጥጋቢ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡  መልስ የተሰጠበት አግባብ የተደራጀና ግልጽ አይደለም፡፡ እንዲያም ሆኖ የአዳፍኔ ዋነኛ ጭብጥ በክሽፈት ታሪክና በታሪክ ክሽፈት ዙሪያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሀሳቦቹ እዚህም እዚያም ተበታትነው የቀረቡ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ አንባቢ የጠራ ግንዛቤ እንዳይኖረው ያደርጋል የሚል ስጋት አለኝ፡፡
በዚህ መጣጥፍ አቅራቢ እምነት፤ የክሽፈት ታሪክ እና የታሪክ ክሽፈት የሚሉት ሁለት ሀሳቦች ብዙ ጉዳዮችን ያዘሉ በመሆናቸው በጥልቀት መታየት አለባቸው፡፡ በመሆኑም  አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ ስለ ክሽፈት ታሪክና ስለ ታሪክ ክሽፈት ያነሳቸውን ሀሳቦች በማሰባሰብ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ መጽሀፉ ከአደረጃጀት አንጻር በዚህ ሁኔታ ቢቀርብ መልዕክቱን በይበልጥ ለመረዳት ያስችላል፤በመጽሀፉ በተነሱት ጉዳዮች ላይ በአንባቢያን የሚቀርቡ የውይይትም ሆነ የክርክር ሀሳቦች ቅርጽ እንዲይዙ ለማድረግም ያግዛል፡፡
የታሪክ ምንነት፣ባህሪያትና ዓላማ
የታሪክ ፍልስፍና ዘይቤ አባት በመባል የሚታወቀው አውግስ ሚኖስ፤ የታሪክ ምንነትና ዓላማን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡-
ታሪክ መንግስት መቆሙንና መፍረሱን፣ ህዝቦች ማደጋቸውንና መውደቃቸውን ያትታል፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት አምላክ ባቀደው መሰረት የሰውን ዘር ወደ እውነተኛው ብርሃን ለመምራትና ለማዳን ሲል ነው፡፡
የፕሮፌሰር መስፍን የታሪክ ምንነትና ዓላማ አረዳድም ከአውግስ ሚኖስ ጋር በይዘቱ አንድ ነው፣ቋንቋው ቢለወጥም፡፡ እንደፕሮፌሰሩ አገላለጽ ታሪክ ማለት፡-
“…..ለአንድም ሰኮንድ የማያቋርጥ የኑሮና የአኗኗር ጅረት ነው፡፡ ……..ታሪክ የአንድ ህዝብ የስራ መዝገብ ነው፡፡” (ገጽ 98-99)
የታሪክ ዓላማ ደግሞ ህዝቡ ያለፈውን ዘመን ከፍታና ዝቅታ አስታውሶ፣ የአሁኑ ትውልድ ካለፈው ትውልድ በጎ ጎኖች ትምህርት ወስዶ፣ ከችግሮቹ ተምሮ፣ በኑሮው መሻሻል እንዲያሳይ ማድረግ ነው (ገጽ 28፣29 )፡፡  
በአጠቃላይ፡- ታሪክ ማለት የትናንት ዕውነትን (በጎም ሆነ በጎ ያልሆኑ) መመርመር ነው፡፡የታሪክ ዓላማ የሰው ልጅ የትናንት በጎ ተግባራቱን አዳብሮ፣ከስህተቱ ደግሞ ተምሮ የዛሬና የነገ ህይወቱን እንዲያቀና ማድረግ ነው፡፡ በዚህም አውግስ ሚኖስ የታሪክን አስፈላጊነትና ዓላማ ከመለኮታዊ ሀይል ዓላማ ጋር ያዛምደዋል፡፡ በዚህም የታሪክ ዓላማ የፈጣሪ አላማ ነው፡፡
ስለታሪክ ባህሪያት
በግሌ የታሪክ ባህሪ ከአምላክ ባህሪ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ ታሪክ አምላካዊ ባህሪዎችን ሁሉ ይወርሳል፡፡ ታሪክን ከአምላካዊ ባህሪ ጋር ለማንጸር ያደረግሁት ጥረት ያልተመቻቸው የአምላክን ባህሪ የማያውቁ ናቸው ባይ ነኝ፡፡ ለመሆኑ የአምላክ ባህሪያት ምንድናቸው? የታሪክ ባህሪያትስ ?
በመሰረቱ የአምላካዊነት መሰረት ሀቅ ነው፤የታሪክ መሰረቱም እንዲሁ ሀቅ (እውነት) ነው፡፡ ፈጣሪ የሰው ልጆችን ጨምሮ በአጠቃላይ በፍጡራን ላይ ፍጹም ስልጣን አለው፤ታሪክም ይህ ስልጣን አለው፡፡ የፈጣሪ ዓላማ የሰው ልጆች ሁሉ በቀና መንገድ እንዲያልፉ ማስተማር ነው፤የታሪክ ዓላማም እንደዚሁ ነው፡፡ ወደር የለሽ ትዕግስትና ሆደ-ሰፊነት አምላካዊ ባህሪ ነው፤ዓላማውም ሰዎች በራሳቸው ከጥፋት መንገድ እንዲታቀቡ፣ካለፈው ስህተታቸው እንዲታረሙ ጊዜ መስጠት ነው፡፡ የታሪክ መንገድም ይህ ነው፡፡ በመሰረቱ ዕውነትን (ታሪክን) መበረዝ ወይም ማጥፋት የሚቻል ሊመስለን ይችላል፡፡ መሪዎችም ይህን ለማድረግ የቻሉ ሊመስለን ይችላል፡፡ ግን በጥልቀት ከመረመርነው አልቻሉም፡፡ የፈጣሪን ትዕግስት ዓላማ ያልተረዱም በስህተት ላይ ስህተት እየፈጸሙ፣ በመጨረሻም ከነጭራሹ የፈጣሪን ስልጣን ሲመኙ፣ሲብስም ህልውናውንም ሲክዱ፣መቀበሪያቸውን ጉድጓድ እየማሱ እንደሆነ ሳይታወቃቸው፣የትዕግስቱ መብዛትም በቆፈሩት ጉድጓድ እንዲቀበሩ ያደርጋቸዋል፡፡ የታሪክም መንገድ ይህ ነው፡፡ ታሪክ ከስህተት ለመማር እድል ይሰጠናል፡፡ ይህን ማድረግ ያልቻሉ ግን በቆፈሩት ጉድጓድ ይቀበራሉ፡፡ በታሪክ ማህደር እንደተዘከረው፤ በታሪክ ላይ የዘመቱ ሁሉ መጨረሻቸው መጥፋት ነበር፡፡ በእርግጥም በዘመናት ሂደት ያለፉ፣ታሪክ ላይ ያመጹ አገዛዞችና ነገስታት አነሳስና አወዳደቅን ለመረመረ ይህ ይገለጥለታል፡፡ ታዲያ የፈጣሪ የቅጣት በትር ፍጹም ፍትሃዊ እንደሆነው ሁሉ የታሪክ ቅጣትም ጊዜ ወይም ቦታ የማይቀይረው፣ ለማንም የማይወግን ፍጹም ፍትሃዊ ነው፡፡ ትናንትም ይሁን ዛሬ በታሪክ ላይ ያመጹ ሁሉ በጥፋታቸው ልክ ተቀጥተዋል፤ነገም እንዲሁ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡

Read 4244 times