Saturday, 07 November 2015 09:56

“የውጭ አገር ህክምና ወጪ እንደሚባለው የተጋነነ አይደለም”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

አብዛኛዎቹ የውጭ ህክምናዎች ከ200ሺ ብር በታች የሚጠይቁ ናቸው


በርካታ ሕሙማን በተለያዩ የጤና ችግሮች ተይዘው ፈውስን ፍለጋ በሚንከራተቱባቸው የጤና ተቋማት በቂ የህክምና እርዳታማግኘት ባለመቻላቸው ይሰቃያሉ፣ ይጉላላሉ፡፡ ችግራቸው ከአገሪቱ የህክምና አገልግሎት በላይ በመሆኑ ውጪ አገር ሄደው መታከምእንዳለባቸው ቢነገራቸውም፣የሕክምና ወጪውን መሸፈን የማይቀመስ በመሆኑ የመዳን ተስፋቸውን አሟጠው ሞታቸውን ቤታቸውቁጭ ብለው ለመጠበቅ ተገድደዋል፡፡ አንዳንዶቹ በየመንገዱ ቁጭ ብለው ተጠየቅን ብለው የሚጠቅሱት የህክምና ገንዘብ ሰሚውንጭምር ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡ ታማሚዎችን ወደ ውጭ አገር በመላክ የሚያሳክሙ አንዳንድ ድርጅቶች፣ ደግሞ የውጭ አገርህክምና ወጪ እንደሚባለው የተጋነነ አይደለም ይላሉ፡፡
“ጌት ዌል ሜዲካል ትራቭል” በውጭ አገር ከሚገኙ አለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው የጤና ተቋማት ጋር በትብብር የሚሰራ አገርበቀል ድርጅት ሲሆን የድርጅቱን መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር በጋሻው ባይለየኝን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሣዬአነጋግራቸዋለች፡፡ ለመሆኑ ድርጅቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ምንድን ናቸው? ከውጭ አገራት ሆስፒታሎች ጋር ያለው የሥራግንኙነትና ትብብር ምን ድረስ ነው? የህክምና ወጪውስ ምን ያህል ነው?----- በአጠቃላይ የውጭ አገር ህክምና ምን ይመስላል?
ዝርዝር መረጃና ማብራሪያ ከተከታዩ ቃለምልልስ ያገኛሉ፡፡


በቅድሚያ የትምህርትና የሥራ ልምድዎን ቢነግሩን…
የህክምና ትምህርቴን የጨረስኩት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ጠቅላላ ሃኪም ነኝ፡፡ ከዚያ በኋላ በተለያዩ አገራት በሥራ ላይ ቆይቻለሁ፡፡ በቅርቡ ደግሞ ለንደን ከተማ ከሚገኘው ካስ ቢዝነስ ስኩል ሲቲ ዩንቨርሲቲ፣ በቢዝነስ አድምኒስትሬሽን ማስተርሴን አግኝቻለሁ። በአሁኑ ወቅት “ጌት ዌል ሜዲካል ትራቭል” የሚባል ኩባንያ አቋቁመን፣የውጭ አገር ህክምናና የጤና ማማከር አገልግሎት በመስጠት ላይ እንገኛለን፡፡
ድርጅታችሁ ለምን አይነት ህሙማን ነው አገልግሎት የሚሰጠው?
እዚህ አገር የማይሰጡ ህክምናዎችን ለማግኘት ለሚፈልጉ ህሙማን ነው አገልግሎት የምንሰጠው፡፡ ታካሚዎቹ ትክክለኛውን ህክምና ወደሚያገኙበት ተቋም ሄደው ጤናቸው ተመልሶ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ የማመቻቸት ሥራ እንሰራለን፡፡
በአጠቃላይ የከፍተኛ ደረጃ ህክምናና የምክር አገልግሎት በጉዞ ወቅት አስፈላጊ በሚሆን ጊዜ ሃኪምና ነርሶችን መመደብና የአየር አምቡላንስ አገልግሎት ማመቻቸት ከምንሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በምን ዓይነት ህክምናዎች ላይ ነው ትኩረት ያደረጋችሁት?
በስድስት የህክምና ዘርፎች ነው አገልግሎት የምንሰጠው፡፡ እነሱም ካንሰር፣ የህብለ ሰረሰርና የጭንቅላት ቀዶ ህክምና፣ የልብ፣ የሳንባ ህክምናና ቀዶ ህክምና፣ የአንጓና የአጥንት ህክምናና የአካል ንቅለ ተከላ ህክምና እንዲሁም መውለድ ላቃታቸው ጥንዶች የሚሰጥ ህክምና ናቸው፡፡ እነዚህ የህክምና አገልግሎቶች በአገራችን የማይሰጡ በመሆናቸው አገልግሎቱን ማግኘት የሚፈልጉ ህሙማን፤በትክክለኛው ቦታ አገልግሎቱን ለማግኘት እንዲችሉ የማድረግ ሥራ እየሰራን ነው፡፡
ከምን ያህል የውጭ የጤና ተቋማት ጋር በጥምረት ትሠራላችሁ? ተቋማቱን የመረጣችሁበት መስፈርትስ ምንድነው?
በታይላንድ፣ ጀርመን፣ ህንድና ዱባይ ከሚገኙ አስር በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕውቅናና ተቀባይነት ካላቸው የጤና ተቋማት ጋር በጥምረት እየሰራን ነው፡፡ ሆስፒታሎቹን የመረጥንባቸው አራት ዋና ዋና መስፈርቶች አሉን፡፡ የመጀመሪያውና ዋናው ሆስፒታሎቹ ምን ዓይነት አለማቀፋዊ ተቀባይነት አላቸው የሚለው ነው፡፡ መቀመጫውን በአሜሪካ አገር ያደረገና ጆይንት ኮሚሽን ኢንተርናሽናል በሚባለው ድርጅት የሚሰጥ ዕውቅና አለ፡፡ ሆስፒታሎቹ ይህንን ዕውቅና አግኝተዋል ወይ የሚለው ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሆስፒታሎቹ በሚሰጧቸው የህክምና ዘርፎች ያሏቸው ባለሙያዎች ብቃት ምን ያህል ነው የሚለውን በጥልቀት እናጠናለን፣ በሶስተኛ ደረጃ ሆስፒታሎቹ የሚጠቀሙት ምን ዓይነት ቴክኖሎጂዎችን ነው የሚለውና ሆስፒታሎቹ ለዓለም አቀፍ ታካሚዎች ያላቸው ዝግጁነት---ከመስፈርቶቻችን መካከል ይጠቀሳሉ፡፡  
የትኞቹ ተቋማት በምን ዓይነት የህክምና ዘርፎች እንደተካኑ ለይቶ የማወቅ ጉዳይስ---?
ሁሉም ሆስፒታሎች ለሁሉም የበሽታዎች ዓይነት ጥሩ ህክምና ይሰጣሉ ማለት አይቻልም፡፡ እያንዳንዱ ሆስፒታል በአንድ የህክምና ዘርፍ ላይ ብቃት ያለው አገልግሎትን ሊሰጥ ይችላል፡፡ በአንዱ ዘርፍ ላይ በዘመናዊ መሳሪያዎች ተደራጅቶ፣ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ይዞ ጥራት ያለው አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህንን የመለየቱና የማጣራቱን ሥራ እንሰራለን፡፡ ይህንን ማድረጋችን ደግሞ ታካሚዎች ላለባቸው የጤና ችግር ዓይነት ትክክለኛውን ህክምና የሚያገኙበትን ቦታ ለይቶ ለማወቅ ይረዳናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሆስፒታሎቹ የየራሳቸው የዋጋ ልዩነት ስለሚኖራቸው ታካሚው ያሉትን አማራጮች አይቶ የሚፈልገውን እንዲወስንና በአቅሙ ሊጠቀምባቸው የሚችላቸውን ቦታዎች ለማሳየት ይጠቅመናል፡፡
የውጭ አገር ህክምናን ፈልገው ወደ ተቋማችሁ የሚመጡ ህሙማን የሚደረግላቸው ቅድመ-ምርመራ አለ ወይስ እንደመጡ ነው ወደ ውጪ የምትልኳቸው?
የእኛን አገልግሎት ፈልገው ወደ ተቋማችን የሚመጡ ህሙማን፣ የህክምና አገልግሎቱን ወደሚያገኙባቸው አገራት ከመሄዳቸው በፊት የሚደረግላቸው የጤና ምርመራ አለ፡፡ አንድ ታካሚ ወደ እኛ ሲመጣ፣ በቅድሚያ የህክምና ሰነዱን እንመረምራለን፡፡ ህመምተኛው ያለበትን ሁኔታ እናያለን፡፡ ታካሚው ውጪ አገር ሄዶ ቢታከም የሚያገኘው ጥቅም መኖርና ያለመኖሩ  በደንብ እንዲጣራ ይደረጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ውጪ አገር ቢሄዱም ምንም ጥቅም የማያገኙ ታማሚዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከደረጃ 4 በላይ የሆኑ የካንሰር ህመሞች፣ ብዙውን ጊዜ ገንዘብ ማስወጣትና ህመምተኛውም ማንገላታት እንጂ ምንም ጥቅም አይኖረውም፡፡ የታካሚውን ሰነድ አይተን ህመምተኛው ወደ ውጪ አገር ሄዶ ቢታከም ጠቀሜታ እንዳለው ካመንን በኋላ ከሃኪሞቹ ጋር በቅርበት በጉዳዩ ላይ እንነጋገራለን፡፡ ከዚያም የህክምና ወጪውን መጠን ካወቅን በኋላ ከታካሚው ጋር እንወያያለን፡፡ ውሳኔ ላይ ሲደረስ አስፈላጊ ነገሮች ከተሟሉና ከተስተካከሉ እንዲሁም ከሀኪሙ ጋር ቀጠሮ ከተያዘላቸው በኋላ ታማሚዎቹ ወደ ውጪ አገር ሄደው ህክምናቸውን እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ህክምናው ካለቀ በኋላ ታማሚውን በቅርበት የመከታተል ሥራም እንሰራለን፡፡
አንድ ሰው በውጪ አገር ህክምና ለማድረግ በአማካይ ምን ያህል ጊዜ ይወስድበታል?  
እንደ በሽታውና እንደሚሰጠው ህክምና ዓይነት ይለያያል፡፡ ለምሳሌ የኩላሊት ንቅለ-ተከላ ህክምናን ብንወስድ፣ ሥራው የራሱ የሆነ ሂደት ያለው በመሆኑ ትንሽ ሰፋ ያለ ጊዜን ይፈልጋል፡፡ ህክምናው የሌላ ሁለተኛ ወገንን ድጋፍ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ይህ ደግሞ በራሱ የሚከተላቸው የአሠራር ሂደቶች ስለአሉት ጊዜ ይወስዳል፡፡ በአማካይ ወደ ሁለት ወር ገደማ ሊፈጅ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ብዙዎቹ የህክምና አይነቶች በአማካይ ከ10-15 ቀናትን የሚወስዱ ናቸው፡፡
የህክምና ወጪውስ ምን ያህል ይሆናል?
ይህም እንደ በሽታውና ህክምናው አይነት የተለያየ ነው፡፡ በእርግጥ በውጪ አገር የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን ለማግኘት የምንከፍለው የገንዘብ መጠን አገር ውስጥ ከምንከፍለው ከፍ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም ህክምናው በአገር ውስጥ ስለሌለና የምንሄደው ለከፍተኛ ህክምና በመሆኑ ከፍ ያለ ወጪን ማስወጣቱ አይቀርም፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለቪዛ፣ ለአውሮፕላን ትኬት፣ ለማረፊያ ወዘተ--- የሚከፈሉ ወጪዎች ስለሚኖሩ ክፍያው ይህንን ሁሉ ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን ለውጪ አገር ህክምና ይከፈላል ተብሎ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታመነው ወይም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ሰዎች ለውጪ አገር ህክምና ተጠየቅን እያሉ እርዳታ የሚጠይቁበት የገንዘብ መጠን እጅግ በጣም የተጋነነ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ገንዘብ ለምን ዓይነት ህክምናና ለየትኛው ሆስፒታል እንደሚከፈል ግራ ያጋባል፡፡ እነዚህ ዋጋዎች ከየት እየመጡ እንደሚነገሩ አላውቅም፡፡ ዋጋዎቹ  እውነታውን አመላካች ናቸው ብዬ አላምንም፡፡
እንደው በአማካይ ምን ያህል ይሆናል ክፍያው?
የውጪ አገር ህክምና ክፍያ እንደምትፈልጊው የህክምና አገልግሎት ይለያያል፡፡ በትንሹ ከ1ሺህ እስከ 2ሺ ዶላር በሚፈጅ ወጪ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶች ያሉ ሲሆን በአብዛኛው ከ250-300ሺህ ብር ድረስ ወጪን የሚጠይቁ ህክምናዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ለምሳሌ እንደ ጉበት ንቅለ ተከላ ህክምና ያሉት ህክምናዎች ወሰብሰብ ያሉ በመሆናቸው ከፍ ያለ ክፍያን ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ እስከ 40ሺ ዶላር ድረስ ሊሄድ ይችላል፡፡
ከዚያ ውጪ ያሉ አብዛኛዎቹ ህክምናዎች ከ10ሺ ዶላር ወይም ከ200ሺ ብር በታች ያሉ ወጪዎችን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ይህንን ጉዳይ ግን ህብረተሰቡ በግልጽ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ውጪ አገር ሄዶ መታከም የማይቻል፣ የማይደረስ ተደርጐ ነው የሚታሰበው፡፡ ይህ የመረጃ እጥረት መኖሩን የሚያመለክት ነው፡፡ በዓለም ላይ አቅምን ያገናዘቡና ኪስን የማይጐዱ የህክምና አገልግሎቶች የሚሰጥባቸው ማዕከላት አሉ፡፡
ታካሚው ለህክምና በሚሄድበት ወቅት አስታማሚ አብሮት ይሄዳል?
አስታማሚ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ለቼክአፕ የሚሄድ ወይም የፀና ህመም የሌለበት ታካሚ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ወደ ውጪ አገር ለህክምና የሚሄድ ሰው አስታማሚ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህ ለብዙ ነገር ይጠቅማል፤አንዱና ዋንኛው ለታማሚው የሥነልቦና ድጋፍ እንዲሰጠው ለማድረግ ሲሆን ከዚህ ሌላ ለሚካሄደው የህክምና ዓይነት ምስክር እንዲሆን፣ በተጨማሪም ሃኪሙ ከታማሚው ጋር የሚኖረው ግንኙነት ቀላል እንዲሆን ለማድረግ አስታማሚው አብሮ የመሄዱ ጉዳይ ወሳኝነት አለው፡፡
የአስታማሚው ወጪስ እንዴት ነው የሚሸፈነው? ከህክምናው ወጪ ጋር አብሮ የሚታሰብ ነው?
ለአስታማሚ የሚወጣው ተጨማሪ ወጪ ለትኬት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ የሚቆየው ከታካሚው ጋር በመሆኑ ለማረፊያ የሚወጣ ወጪ አይኖርም፡፡ ስለዚህ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ እኛ የምንጠይቀውም የምናስከፍለውም ወጪ ግን የህክምና ወጪውን ብቻ ነው፡፡ ታማሚውን በተመለከተ የትኬት፣ የቪዛ፣ የህክምና ወጪዎችን መሸፈን፣ እዛ የሚቀበሏቸውን ሰዎች ማስተካከል፣የሚያርፉበትን ቦታ ማዘጋጀት፣ከሃኪሞች ጋር ቀጠሮ መያዝና ህክምናውን በቅርበት መከታተል፣ ታካሚው ህክምናውን ጨርሶ ወደአገሩ ሲመለስም ክትትል የማድረጉ ሥራ የሚሸፈነው በእኛ ድርጅት ነው፡፡
ታካሚዎች ህክምናቸውን አጠናቀው ከመጡ በኋላ ተመልሰው የመሄድ አጋጣሚ ይኖራል?
ታካሚዎች ተመልሰው የሚሄዱባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ፡፡ አንዳንድ ቀዶ ህክምናዎች በአንድ ጊዜ ሊጠናቀቁ የማይችሉ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ታካሚዎች ተመልሰው መሄድ የሚኖርባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ብዙዎቹ የህክምና ዓይነቶች ግን መመለስ አያስፈልጋቸውም፡፡ ይህ ማለት ግን ክትትል አያስፈልጋቸውም ማለት አይደለም። በተለያዩ መንገዶች ከሃኪሞቻቸው ጋር በመገናኘት ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
ታካሚዎች ህክምናቸውን ጨርሰው ሲመለሱ ክትትል የምታደርጉላቸው ለምን ያህል ጊዜ ነው?
ታካሚዎቹ ህክምናቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ዝም ብለን አንለቃቸውም፡፡ የክትትል ፕሮግራም እናዘጋጅላቸዋለን፡፡ በተወሰነ ቀጠሮ መጥተው እናያቸዋለን፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሌም በእኛ እንክብካቤ ሥር ይሆናሉ ማለት አይደለም፡፡ እዚህ አገር በዛ የህክምና ዘርፍ ውስጥ በሚሰሩና በቂ ዕውቀትና ልምድ ባላቸው ሃኪሞች ክትትላቸውን እንዲቀጥሉ በማድረግ ከመሀል እንወጣለን፡፡
የመሀንነት ህክምና የሚፈልጉ ደንበኞች ምን ያህል በአገልግሎታችሁ ይጠቀማሉ?  
መሀንነት በአገራችን በከፍተኛ ደረጃ ችግር እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ትልቅ ችግር ትኩረት ሰጥተን አላየነውም እንጂ የብዙ ሰዎችን ህይወት የሚያናጋና ለብዙ ትዳር መፍረስ ምክንያት እየሆነ የመጣ፣ የአዕምሮ ጫናን የሚያሳድር ችግር ነው፡፡ ግን መፍትሔዎች አሉት። እኛም ለዚህ ችግር መፍትሔ ከሚሰጡና በዘርፉ የዳበረ ዕውቀትና ልምድ ካላቸው ዱባይና ህንድ ከሚገኙ የጤና ተቋማት ጋር አብረን እየሰራን ነው፡፡ በርካታ ጥንዶች አገልግሎቱን ፈልገው መጥተው ወደ ጤና ተቋማቱ ልከናቸው ሃሳባቸውን አሳክተው ተመልሰዋል። ለዚህ ህክምና ሁለቱም ጥንዶች ወደ ሥፍራው መሄድ ይኖርባቸዋል፡፡ ህክምናው ሁልጊዜም በመጀመሪያው ዙር ሙሉ በሙሉ የተሳካ ላይሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መሞከር ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ጥንዶቹ በድጋሚ አብረው መሄድ ላይጠበቅባቸው ይችላል፡፡ ዘሮቹን ፍሪዝ አድርገው ማስቀመጥ የሚችሉ ክሊኒኮች አሉ፡፡ በዛ ቴክኖሎጂ መጠቀም ይቻላል፡፡ ይበልጥ ተመራጭ የሚሆነው ግን አብሮ መሄዱ ነው፡፡
እስከ አሁን ምን ያህል ህሙማንን ወደ ውጪ አገር ለህክምና ልካችኋል? ውጤታማነታችሁስ ምን ያህል ነው?
እስከ አሁን ከ200 በላይ ህሙማንን አይተናል። ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ ወደ ውጪ አገር ሄደው ታክመው፣ ጤናቸው ተመልሶ፣ ወደ አገራቸው መጥተዋል፡፡ የምክር አገልግሎት ሰጥተን የመለስናቸውም ህሙማን አሉን፡፡
እንደው ለየት ያለ ታካሚ በመሆኑ የሚያስታውሱት አሊያም አስጊ በሆነ ደረጃ ላይ ደርሶ መለስነው ብለው የሚያስታወሱት ታካሚ አለ?
በርካታ አሉ፡፡ ግን አንድ በደም ካንሰር በሽታ የተያዘ የስምንት አመት ልጅ ፈጽሞ ከህሊናዬ አይጠፋም፡፡ ህፃኑ ወደ እኛ ከመምጣቱ በፊት ባንኮክና ህንድ ሄዶ ህክምናውን ሳያገኝ ነበር የተመለሰው፡፡ ወደ እኛ ጋ ሲመጣ በሽታው እጅግ አድክሞት በጣም ተጐድቶ ነበር፡፡ በዛ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ መሄድ አይችልም ነበርና የደም ምርመራዎች አዘዝንለት፡፡ ውጤቱ በጣም የሚያስደነግጥ ነበር፡፡ በአውሮፕላን ተሣፍሮ አገር ለቆ ለመሄድም የሚያስፈልግ የጤንነት ሁኔታ አለ፡፡ ታዳጊው ይህንን አያሟላም ነበር። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ወደ ውጪ ለህክምና እየሄዱ አውሮፕላን ውስጥ የሚሞቱት እንዲህ አይነት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ እናም ህፃኑ ወደ ሆስፒታል ገብቶ ደም እንዲሰጠው አደረግን፡፡ ዘጠኝ ዩኒት ደም ከወሰደና ጤናው እየተሻሻለ ከመጣ በኋላ ህክምናውን በትክክል ለማግኘት ወደሚችልበት አገር እንዲሄድ አደረግነው፡፡ አሁን ታዳጊው በጣም ተሽሎት ህክምናውን አጠናቆ ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮች በሰው ህሊና ውስጥ የመቅረት አቅም አላቸው፡፡
ከህክምና ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ ማወቅ ይገባዋል የሚሉት ጉዳይ ይኖር ይሆን?
እንደ ደም ግፊት፣ ስኳር፣ ካንሰር---ያሉ ህመሞች በአገሪቱ ትልቅ ችግር እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በአገራችን ለእነዚህ በሽታዎች በቂ የሆነ ህክምና መስጠት የሚያስችል አቅም እስከምንገነባ ድረስ ዋጋቸው እጅግም ኪስ በማይጐዱና ህክምናው በበቂ ሁኔታ በሚሰጥባቸው አገራት ሄዶ በመታከም ጤንነትን ማግኘት ይቻላል። ይህንን ደግሞ በባለሙያ ታግዞ ማድረጉ የበለጠ ይጠቅማል፡፡
ወደፊት ምን አቅዳችኋል?
ለወደፊቱ በዕቅድ ከያዝናቸው ጉዳዮች መካከል፣ በአገሪቱ የማይሰጡ ህክምናዎችን ቀስ በቀስ ወደ አገራችን ማምጣት፣የሰው ሃይላችንን ብቃት ለማሳደግ ወደ እነዚሁ ሆስፒታሎች ባለሙያዎችን በመላክ ስልጠናና ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ ማንም ሰው መዳን የሚችልባቸው ዕድሎች እያሉ ሕይወቱን እንዳያጣ ለማድረግ የምንችለውን ጥረት ሁሉ እናደርጋለን፡፡  
   

Read 4959 times