Monday, 11 January 2016 11:15

2.4 ቢሊዮን ብር ከወጣበት አይቀር!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(12 votes)

• አዎ፣ “እግርኳስ ዳቦ አይሆንም”። ግን፣ ልንማርበት እንችላለን።
• የእውነትን፣ የኑሮንና የማንነትን ሚስጥር፣ ከእግርኳስ ውድድር!

በድሃ አገር ውስጥ፣ ለአንድ ስታዲዮም ግንባታ፣ 2.4 ቢሊዮን ብር ማፍሰስ! ይሄ ነገር፣ “አሳዛኝ ብክነት ላይሆን ይችላል”... የሚል አሳማኝ ሃሳብ ማቅረብ ከባድ ነው። ቢሆንም፣ እንሞክር። የውድድር ስፖርቶች፣ የብዙዎቻችንን መንፈስ የሚያነቃንቅ፣ ‘ተዓምረኛ’ ኃይል የሚኖራቸው፣ በምን ምክንያት እንደሆነ ካልተገነዘብን፤... ሙከራችን ሁሉ፣ ከንቱ ድካም ከመሆን አይድንም።
በእርግጥ፣ ከድካም የሚገላግሉ ‘አቋራጭ መንገዶች’ አሉ። “ስታዲዮሙ... በቃ፣ አሪፍ ነው። ዲዛይኑ ያምራል። ያኮራል”... የሚሉ ድፍን የብዥታ ሃሳቦችን በመወራወር፣ ግንባታውን ከነወጪው ማወደስ፣... ከባድ አይደለም። ግን፣ ምን ዋጋ አለው? እንዲህ አይነቱ፣ አየር ላይ የተንሳፈፈ፣ ባዶ ውዳሴ፣... ከጭፍን ስሜት የዘለለ ክብደት የለውም። ስንዝር አያራምድም።  ነገሩን ከምር ካየነው፣... “የአገሬውን አሳዛኝ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ የስታዲዮሙ ድርሻ ምን ያህል ነው?” ተብለን ብንጠየቅ፣ የሚያወላዳ መልስ የለንም። ከግዙፍ ወጪው ጋር የሚመስተካከል፣ (ከ2.4 ቢሊዮን ብር ጋር የሚመጣጠን)፣ ተጨባጭ የኑሮ ጠቀሜታ ያስገኝልናል? ለምሳሌ ምን? አስቸጋሪ ነው።
የተራቀቅን በመምሰል፣... “ጥቅሙ ለአገር ነው” ብለን ለማለፍ ብንሞክርም፣ አያዋጣም። ለሕዳሴ ግድብ ወይም ለኮንዶሚኒዬም ግንባታ፣ ቢሊዮን ብሮች እየተመደበ፣ “ጥቅሙ ለአገር ነው” ቢባል፣ ትርጉሙ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመትና መዘርዘር አያቅተንም። ግድቡ፣ የኤሌክትሪክ ሃይልና መብራት ለማመንጨት ይጠቅማል። የኮንዶሚኒዬም ግንባታ ደግሞ፣ የመኖሪያ ቤት እጥረትንና እጦትን ለማቃለል ይረዳ ይሆናል።
በተመሳሳይ መንገድ፣ የስታዲዮም ግንባታ፣ አገርን እንዴት ሊጠቅም እንደሚችልስ፣ በግልፅ መናገር እንችላለን?
በእርግጥ፣ ማብራሪያ የሚመስሉ የማደናገሪያ አባባሎች የሉም ማለቴ አይደለም። “የስታዲዮሙ ግንባታ፣ እግር ኳስን በማሳደግ፣ በዓለም መድረክ የኢትዮጵያን ደረጃ ከፍ ለማድረግ፣ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል”፤... “ትልልቅ የእግርኳስ ውድድሮችን በማዘጋጀት፣ የኢትዮጵያን ስም ለማስጠራትና ገፅታ ለመገንባት ይረዳል”፤... “ጥቅሙ ለአገር ነው”... እያልን ብዙ እንተርትረው። ግን፣ ከዚያስ?
እሺ፤ ይሁን። እግር ኳስ ተመነደገ እንበል። አለማቀፍ ውድድሮችንም በማዘጋጀት፣ የኢትዮጵያ ስም በታሪክ መዛግብት ውስጥ ተፃፈ እንበል። ግን፣ አሁንም ጥያቄው አልተመለሰም። የ‘እድገት’ አይነቶችን፣ ዘርዝረን መንዝረን ስናበቃ፣ መጨረሻ ላይ ሂሳብ ለማወራረድ ስንሞክር ነው፣ ችግሩ የሚታየው።
የእግር ኳስ ቢመነደግ፣ በፊፋ ሰንጠረዥ የኢትዮጵያ ስም ከመቶኛ ወደ ሃምሳኛ ደረጃ፣... እንዲያው ወደ አስረኛ ደረጃም ቢደርስ፣... ምግብ፣ ልብስ፣ መኖሪያ ቤት ይሆንልናል? የትራንስፖርት፣ የመብራት፣ የስልክ አገልግሎት ለማበራከት፣ በዚህም ሥራ ለማቀላጠፍ፣ ወጪ ለመቀነስና ጊዜ ለመቆጠብ ያግዘናል? አንዳች ገቢ ያስገኝልናል? በጭራሽ! እንዲያውም፣ ለተጨማሪ ወጪ ይዳርገናል (የስታዲዮም መግቢያ ትኬት ለመቁረጥ)። የኑሮ ጊዜያችንንም ይሻማብናል (ውድድሮችን ለመመልከት)።
የሆነ ሰው፣ ‘በሆነ ምክንያት’ ተነሳስቶ፣ በሆነ ዘዴ ትርፍና ኪሳራውን አስልቶ፣ ከራሱ ኪስ ወይም ከራሱ የባንክ ሂሳብ፣ ለስታዲዮም ግንባታ ከቢሊዮን ብሮችም አልፎ፣ ትሪሊዮን ብር ቢያወጣ፣... ምናልባት፣ ‘ብልህነቱ’ ባይታየን እንኳ፣ ‘መብቱ’ ነው። ወጪውን ለመሸፈን፣ የራሱን ኪስ ብቻ ሳይሆን፣ የሌሎች ሰዎችንም ኪስ፣ በግድ ለመበርበር እስካልሞከረ ድረስ፣ ችግር የለውም። መሞከር የለበትም። መሞከር ብቻ ሳይሆን፣ ያሻውን ያህል ገንዘብ፣ ከዜጎች ኪስ እየወሰደ ከሆነስ? የገናና መንግስት ባህሪ፣ እንደዚያ ነው። መቼስ ምን ይደረግ!
እንግዲህ አስቡት። መንግስት ያሻውን ያህል ገንዘብ፣ ከዜጎች ኪስ የሚወስድ ከሆነ፤... ቢያንስ ቢያንስ፣ የገንዘብ አወጣጡ፣ በብልህነት መሆን አይገባም?
ከራስ ኪስ ሳይሆን፣ ከዜጎች ኪስ የተወሰደ ገንዘብ ስለሆነ፣... መንግስት ለማንኛውም ነገር ገንዘብ ሲወጣ፣... በዚያ ላይ በድሃ አገር ውስጥ ስለሆነ፣... በዚያ ላይ 2.4 ቢሊዮን ያህል ብር ወጪ ሲደረግ፣... ነገርዬው፣ አንዳች ጥቅም እንደሚያስገኝልን፣ እርግጠኛ ለመሆን መሞከር አያስፈልግም? ትርፍንና ኪሳራን ሳያሰላ፣ “መሰለኝ... አሰኘኝ” በሚል የስሜት ብዥታ፣ ይህን ሁሉ ብር ወጪ ከተደረገኮ፣ የዜጎችን ኪስና የችግረኞችን ኑሮ፣ መጫወቻ ሆነ ማለት ነው።
የስታዲዮም ግንባታው፣ በተጨባጭ ኑሮን የሚያሻሽል ምን አይነት ጥቅምና አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚችል መግለፅ ካቃተን፣... በእርግጥም “ግንባታው፣ ብክነት ላይሆን ይችላል” የሚል አሳማኝ ሃሳብ ማቅረብ ከባድ ይሆናል።
ምናልባት፣ “የውድድር ስፖርት፣ መዝናኛ ነው። ስለዚህ የስታዲዮሙ ግንባታ፣ ከንቱ ብክነት አይሆንም” በማለት ብንከራከርስ? ትንሽ ያስኬዳል። ግን፣ ‘መዝናኛ’ ስንል፣ እንደተለመደው፣ ‘ጊዜ ማሳለፊያ’ ማለታችን ከሆነ፣... ለ2.4 ቢሊዮን ብር አይመጥንም።  
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ግንባታው፣ ‘ብክነት’ ከመሆን ሊድን የሚችለው፣... “የውድድር ስፖርት”፣ አንዳች መንፈሳዊ ጥቅም የሚሰጠን ከሆነ ብቻ ነው።
ደግሞም፣ ትልቅ መንፈሳዊ አገልግሎት አለው። ለዚያውም፣ ከኪነጥበብ ጋር የሚዛመድ ተመሳሰይ አገልግሎት።
ያው፤... የዚያን ትልቅ መንፈሳዊ አገልግሎት፣ ምንነት በትክክል አንገነዘበው ይሆናል። የኋላቀርነት ነገር ሆኖ፤ በሌሎች ብዙ ነገሮች ላይም፣ ግንዛቤያችን ትንሽ አይደል? እንዲያውም፣ በውድድር ስፖርቶች ዙሪያ፣ የተሻለ ግንዛቤ ሳይኖረን አይቀርም። እንዴት ቢባል፤ በፖለቲካ ወይም በኢኮኖሚ፤ ኢንዱስትሪና በከተሜነት፣ በስነምግባርና በሳይንስ ዙሪያ ካለን የግንዛቤ መጠን ጋር ልናነፃፅረው እንችላለን። ያለ ጥርጥር፣ በእግር ኳስ ላይ ያለን ግንዛቤ፣ በእጅጉ የተሻለ ነው። ለዚያውም፣ ይህችኑን ግንዛቤ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ፣ በስነምግባርና በሳይንስ ጉዳዮች ላይም ብንጠቀምባትና ብንማርባት፤ ብዙ እርምጃ ወደ ፊት መራመድ እንችላለን።  
ልዩነታቸውን ተመልከቱ።
በእግር ኳስ ዙሪያ፣ ብዙውን ጊዜ፣ ዋና ዋና ነገሮችን፣ አንስታቸውም። አዝናኝና ጠንካራ ውድድሮችን፣ ውጤታማና ምርጥ  ተጫዋቾችን ለይተን ለማወቅ ብዙም አንቸገርም። ብዙዎች፣ የአለም ዋንጫን፣ አልያም የነእንግሊዝና የነስፔን ሊግ ውድድሮችን፣ ለማየት የሚጓጉት ለምን ሆነና? ከዚያም ውስጥ፣ ቅድሚያ ሰጥተው የትኛውን ውድድር ለማየት እንደሚፈልጉ ያውቃሉ። ይሄ፣ በተግባር የሚታይ የዘወትር ትዕይንት ነው። የምንጓጓው፣ የሚስኪኖችን ጨዋታ ለማየት ሳይሆን፣ በምርጥ ተጫዋቾች የሚካሄድ ብቃትን አጉልቶ የሚያሳይ ጠንካራ ውድድርን ለማየት ነው።
ይህንን በፖለቲካ ወይም በኢኮኖሚ ዙሪያ ካለን አስተሳሰብ ወይም ባህርይ ጋር አነፃፅሩት። ስኬታማ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓቶች ያጓጉናል? ብዙ ጉድለቶች ቢኖሩትም እንኳ፣ ከሌሎች አገራት በተሻለ ደረጃ፣ በአመዛኙ በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተ ‘ሊበራል’ የፖለቲካ ስርዓትን፤ እንዲሁም በግል ንብረት (በነፃ ግብይት) ላይ የተመሰረተ ‘ካፒታሊስት’ የኢኮኖሚ ስርዓት የተስፋፋባቸው እንደ አሜሪካና እንግሊዝ የመሳሰሉ፣ የነፃነትና የብልፅግና አገራት ይማርኩናል? “ቅድሚያ፣ ለራስህ ሕይወት፣ በራስህ ጥረት” በሚል ሃሳብ ላይ የተመሰረቱ ‘የራስ ወዳድነት’ ስርዓቶች ናቸው።
በተቃራኒው፤ “ቅድሚያ ለህዝብ ጥቅም” በሚል የሶሻሊዝም መፈክር፣ “ቅድሚያ ለአገር፣ ለብሔር ብሔረሰብ” በሚል የናሽናሊዝም መፈክር፤ “ቅድሚያ፣ ለሃይማኖት ተቋምና መሪ” በሚል ሃይማኖታዊ መፈክር ላይ የተመሰረቱ የመስዋዕትነት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓቶች፤ ውለው አድረው... የመጠፋፋትና የስቃይ፣ የድህነትና የረሃብ ገሃነሞች እንደሚሆኑ፣ በተደጋጋሚ ታይቷል። እና የትኛው ነው የሚማርከን? በራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረቱ የነፃነትና የብልፅግና ሥርዓቶች ወይስ፤ በመስዋዕትነት ላይ የተመሰረቱ የመጠፋፋትና የድህነት ሥርዓቶች? በአብዛኛው፤ የመስዋዕትነት አስተሳሰብ ምርኮኞች ነን።  
በእግር ኳስ ግን፤ በራሳቸው ጥረት፣ ራሳቸውን ስኬታማ ለማድረግ የሚጥሩ ተጫዋቾች የሚያደርጉት፣ ጠንካራ ውድድር ነው የሚማርከን። ከራሱ ስኬት በፊት፣ ለሌላው ቡድን ስኬት ቅድሚያ የሚሰጥ፤ በአዛኝነት ጎል ከማግባት የሚቆጠብ፣ ተፎካካሪዎቹ ጎል እንዲያስቆጥሩበት በመስዋዕትነት ራሱን አሳልፎ በሚሰጥ ተጫዋች የተሞላ ውድድር፣ ለማየት እንጓጓለን? ይሄ የ“መስዋዕት አምልኮ”፣ ከጤናማ ሰው አይጠበቅም። በፖለቲካና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ግን፤ ዋነኛው መርህ፣ የ“መስዋዕት አምልኮ” ሲሆን እናያለን።
የብዙዎቻችን አድናቆትና አክብሮት፣ ወዴት ወዴት እንደሆነ በማየትም፣ ሁለቱን ተቃራኒ አቅጣጫዎች ማነፃፀር እንችላለን።
በእግር ኳስ፣ ወይም በሌሎች የውድድር ስፖርቶች፣ የብዙዎቻችን አድናቆትና አክብሮት፣ ለስኬታማና ለምርጥ ተጫዋቾች፣ ለስኬታማና ለምርጥ አሰልጣኞች... ነው። ትናንሽ የዝንባሌ ልዩነቶች መኖራቸው ባይቀርም፣ የአድናቆትና የአክብሮት መመዘኛዎቻችን፣ ብዙም አከራካሪ አይደሉም - ብቃትና ስኬት፣ ጥረትና ውጤት ናቸው መመዘኛዎቹ።
በፖለቲካና በኢኮኖሚ ላይ ግን፣ ይሄ የብቃትና የስኬት መመዘኛ፣ አይሰራም። እንዲያውም እንደ ሃጥያት ነው የሚቆጠረው። በራሳቸው ጥረት ሃብት ያፈሩ ስኬታማ የቢዝነስ ሰዎችን በአድናቆትና በአክብሮት እንመለከታለን? ከዚያ ይልቅ፣ ምን ያህል ብር መፀወተ? የሚል የሚስኪንነት መመዘኛ ነው የምናመጣው። የእግርኳስ ተጫዋቾችን ግን፣ ምን ያህል አሮጌ ጫማ ለገሰ? ብለን አንመዝንም።
ትክክለኛውን መመዘኛ አንስተውም። የጨዋታ ብቃቱንና ብርታቱን፣ ችሎታውንና ጥረቱን ከስኬቱ፣ ጋር ያማዋሃደ ነው፤ የአድናቆትና የአክብሮት መመዘኛችን። ከራሱ ስኬት በፊት፣ ለሌሎች ስኬት ቅድሚያ በመስጠት፣ ጎል ከማስቆጠር ይልቅ ጎል እንዲቆጠርበት፣ ከምርታማነት ይልቅ ሚስኪንነት፣ ከትርፋማነት ይልቅ ክስረትን በመሸከም ራሱን ለማዋረድ የሚሽቀዳደም ተጫዋች፣ “የዓለም ምርጥ” ብለን በክብር እናደንቀዋለን? በራሱ ብቃትና ጥራት፣ ለራሱ ስኬት የሚያስመዘግብ አሪፍ ተጫዋች ነው የምናደንቀው። ጀግና (በቀድሞው የግዕዝ ትርጓሜም፤ ቅዱስ) የሚል የክብር ማዕረግም ይጎናፀፋል።
በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ግን፣ በተቃራኒው፤ ብቃትና ስኬት፣ የጀግንነት (የቅድስና) መመዘኛዎች አይደሉም። ሚስኪንነትንና መስዋዕትነትን፣ ዋና ስነምግባርና የክብር ምንጭ አድርገናቸዋል።
ለዚህም ነው፤ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ዙሪያ ካለን ግንዛቤ ይልቅ፤ በእግር ኳስ ዙሪያ ያለን ግንዛቤ ይሻላል የምለው። ከዚህ የእግር ኳስ ግንዛቤ ትምህርት በመቅሰም፤ በስነምግባር፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ መስኮች የያዝናቸውን የጥፋት አስተሳሰቦች ለማረም ብንሞክርስ? ለዚህም፤ የስታዲዮም ግንባታው፣ ትልቅ አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይችላል። ታዲያ፤... ዋና ዋና አስተሳሰቦችን ለማስተካከልና ወደ መልካም ጎዳና ለማቃናት ማገዝ፤... ትልቅ መንፈሳዊ አገልግሎት አይደለም?        

Read 5661 times