Saturday, 23 January 2016 13:30

መስዋዕትነትን እያደነቁና ራስ ወዳድነትን እያወገዙ፣... ስለ ቢዝነስና ስለ ደስታ ማውራት ምን ያደርጋል?

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(6 votes)

በ”ማያ” የቲቪ ዝግጅቶች፣ የኢትዮጵያን ግራ መጋባት አየሁ
     ለራስ ማሰብን እያናናቅን፣... ዞር ብለን ደግሞ፣ የራስን ኑሮ ስለለማሻሻል እንነጋገራለን፡፡ መስዋዕት ለመሆን ማገዶ እየለቀምን፣ እዚያው በዚያም “ደስተኛ ለመሆን፣ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ” ለመዘርዘር እንሽቀዳደማለን። እንዲህ አይነት ተቃራኒ ሃሳቦችን አደባልቀንና “አቻችለን” መሸከመ፤ ለአገራችን አዲስ አይደለም፡፡ ነባር ባህላችን ነው፡፡
በአንድ በኩል፤ ኑሯችን፣... በስራና በምርት፣ በደሞዝና በትርፋማነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ፣ እናውቃለን። እነዚህ የ“ቢዝነስ” ተግባራት ከሌሉ፤ በህይወት መቆየት አንችልም፡፡
በቃ…የሙያችን፣የ እንጀራችን፣ የቤተሰባችን... የህልውናችንና የኑሯችን ዋና አለኝታ፤ ‘ቢዝነስ’  ነው። ነገር ግን፣ ለትርፋማነት፣ ለደሞዝ፣ ለቢዝነስ፣ ያን ያህልም ክብር የለንም። አይገርምም?
በተቃራኒው፣ ያለ ደሞዝ ማገልገልን፣ ትርፍ የማያስገኝ ምፅዋትን፣ በተለይ ደግሞ.. ራስን የመበደልና፣ የራስን ማሰቃየት መስዋዕትነትን በእጅጉ እናከብራለን። ቢዝነስን ሳይሆን፣ ምፅዋትን ነው፤ ‘በጎ ምግባር’ ብለን የምናወድሰው።
የቢዝነስ ባለቤት፣ ለራሱ ጥቅም ብሎ፣ መቶ ሰዎችን ቀጥሮ ደሞዝ ሲከፍል፣ በዚህም የሁለት መቶ ሕፃናት ሕይወት ሲሻሻል ብናይ… ከቁብ አንቆጥረውም። ቢዝነሱን ለማጧጧፍና ትርፋማ ለመሆን አስቦ ነው፣ ለሰራተኞቹ ደሞዝ የሚከፍላቸው፡፡ ራሱን እየጐዳ ደሞዝ የሚከፍላቸው ቢሆን ኖሮ እናደንቀው ነበር፡፡ ትርፋማነቱን ስናይ ግን፤ ጥፋትና በደል የፈፀመ ሆኖ ይሰማናል - የብዙ ሰዎችን፣… የብዙ ህፃናትን ህይወት እንዳሻሻለ ብናውቅም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በምፅዋት ለአምስት ሕፃናት ደብተር የሚገዛ ወይም ለአስር ዓረጋዊያን በዓመት በዓል ምሳ የሚያበላ ሰው ሲያጋጥመን፣... ምፅዋቱ ከእለት ባሻገር የማንንም ሕይወት የማይለውጥ እንደሆነ ብናይም እንኳ፣ ‘በጎ’፣ ‘ቅዱስ’ ብለን እናደንቀዋለን። ኪሱን የሚያጐድል ተግባር ፈጽሟላ፡፡ በተለይ ደግሞ፣ ጦሙን ውሎ ከመፀወተ... ቅዱስነቱ ይጨምራል። ራሱን በድሏል፤ለመክሰር ፈቅዷል፤ መስዋዕት ከፍሏል እያልን ገድል እንዘረዝራለን። የጀግንነት፣ የቅዱስነት መለኪያችን ይሄው ነው።
ተቃራኒ ሃሳቦችን የማቀላቀል መዘዝ
በእርግጥ፤ የመስዋዕትነት አድናቂ ብንሆንም፤...ራስን የመበደልና የማሰቃየት ተግባር (ማለትም መስዋዕት) ለኑሮ ስለማይበጅ፣ እዚያው ሙጭጭ ማለት አያዋጣም። እናም፣ ዞር ብለን፣ ኑሯችን እንዲያምርልን እናልማለን፡፡ ስራችን ተሳክቶ ገቢ ለማግኘት፣ ምርታችን በርክቶ ትርፋማ ለመሆን፣ ውጤታችን ታይቶ ደሞዛችን እንዲያድግ እንመኛለን። ነገር ግን፤ ብዙ ብንመኝም ኑሮን የሚያሻሽሉ አዳዲስ ሃሳቦችንና ዘዴዎችን የማመንጨት ብርታት፣ እንዲሁም ተግቶ የመስራት ፅናት ሲያጥረን እንታዘባለን። ውስጣችንን ስንመለከት፤ ለስኬት የሚያበቃና የሚፍለቀለቅ ሃይል ልናገኝ ይቅርና፣ የሚያላውስ አቅምም እናጣለን፡፡ መስዋዕትነትን በማድነቅ የተጣበበ ሰብእና ስንቀልስ ከከረምን፣ ለቢዝነስ የሚሆን ውስጣዊ ሃይል ቢያጥረን ኑሮን የማሻሻል ተነሳሽነት ብናጣ እንዴት ይገርማል?
መጥፎነቱ ደግሞ፣ ተሳክቶልን ሃብት ብናፈራ እንኳ፣ የተመኘነውን ያህል እርካታና ደስታ ሳናገኝ እንቀራለን። መስዋዕትነትን እንጂ ቢዝነስን የማያከብር አስተሳሰብ ታቅፈን እያደርን፣... በማናከብረውና በማናደንቀው ተግባር (ማለትም በ‘ቢዝነስ’ ሥራ) እርካታና ደስታ ባናገኝ ምን ይገርማል?
ምናለፋችሁ ኑሯችንና አድናቆታችን ለየቅል ሆኗል፡፡
ለኑሮና ለሕይወት የሚበጀን ነገር ሌላ! የምናደንቀውና የምናከብረው ነገር ሌላ! ለኑሮ የሚበጅ የስኬታማነት ውስጣዊ ሃይል በማጣት አቅመቢስነትን እንሸከማለን - ራስ ወዳድነት ስለምናወግዝ። አንድ ሁለቴ፣ ሕይወትን የሚያሻሽል ስኬት ላይ ለመድረስ ብንታደል እንኳ፣ እርካታና ደስታ በራቀው፣ ኦና ጐደሎ ስሜት፤ የህይወት ጣዕምና ትርጉም ይጠፋብናል - መስዋዕትነትን ስለምናመልክ፡፡
ይሄ አጣብቂኝ፣ እርግማን አይደለም። ተቃራኒ ሃሳቦችን፣ ‘አቻችለን’ ለመሸከም ፈቃደኛ በመሆናችን ምክንያት፣ ራሳችን የፈጠርነው ጣጣ ነው። “የኋላቀርነት ዋጋ” “ኋላቀርነት መዘዝ” ልንለውም እንችላለን። ኋላቀርነትኮ ሌላ ነገር አይደለም፡፡ ተቃራኒ ሃሳቦችን አደባልቆ የያዘ፣ የአስተሳሰብና የአኗኗር ቅኝት ነው፡፡ ኋላቀርነት፤…  ሙሉ ለሙሉ፣ ውሸትን፣ ጥፋትን፣ ኪሳራን፣ ክፋትንና ውርደትን ብቻ አጭቆ መያዝ ማለት አይደለም። እነዚህ አሉታዊ ነገሮችን ከእውነት፣ ከምርት፣ ከትርፋማነት፣ ከመልካምነትና ከክብር ጋር አደባልቆና ቀይጦ የመያዝ ፈቃደኝነት፣…ቀስ በቀስ እየተለመደና ስር እየሰደደ ይሄዳል፡፡ ከዚህ የባሰ “ኋላቀር ባህል” ከየት ይመጣል?
ባህል ከሆነ ደግሞ፣ በየመስኩና በየጊዜው፣ እንኖረዋለን ማለት ነው። “ማያ” በተሰኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ የቀረቡ ዝግጅቶችን፣ በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።
ከሳምንት በፊት የተሰራጨውን ዝግጅት አስታውሱ፡፡ “ደስታ ምንድነው? ደስታ እንዴት ይገኛል?”... በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ፣ የተለያዩ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች፣ አስተያየት ሲሰጡና ሲወያዩ ታይተዋል።... ከዚያ በፊት ደግሞ፣ ‘ስራ ፈጠራ’ የሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ፣ ሌላ ዝግጅት ቀርቧል - በ “ማያ” ፕሮግራም።
እነዚህ ሁለት ዝግጅቶች፣ ጥርት ያሉ ሃሳቦችን አንጥረው ለማሳየት ባይበቁም፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ ኑሮን የማሻሻል እና ደስተኛ የመሆን ጥያቄዎችን በአወንታ አንስተዋል። ምን ዋጋ አለው? እነዚህን ጉዳዮች የሚያፈርስ ተቃራኒ ሃሳብ፣ ለበርካታ ሳምንታት፣ የ “ማያ” ዝግጅት ሲሰበክ ከርሟል፡፡ ዝግጅቱ የቀረበው “ትውልድ” እና “አገር” በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ቢሆን፤ የመስዋዕትነት ስብከት ቢባል ይሻላል፡፡
በርካታ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች፣ እንዲሁም ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በተስተናገዱበት በዚሁ ዝግጅት፣ ያልተነካ ጉዳይ የለም ማለት ይቻላል። ከባህል እስከ አብዮት፣ ከጦርነት እስከ ኢኮኖሚ፣ ከትምህርት እስከ ስደት፣ ከቴክኖሎጂ እስከ ምፅዋት... ብዙ ብዙ ተብሏል። እጅጉን እየተደጋገመ የተነሳውና በስተመጨረሻም ገንኖ የወጣው ግን፣ “መስዋዕትነት” የሚል ሃሳብ ነው።
መስዋዕትነት፣ ከሁሉም በላይ የተከበረ ተግባር መሆኑን የገለፀ በርካታ ተሳታፊዎች፣ “በአሁኑ ዘመን መስዋዕትነት እየደበዘዘ ነው” የሚል ስጋትና ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ የሁሉም ተወያዮች ሃሳብ፣ አንድ አይነት ነበር እያልኩ አይደለም። አማራጭ ሃሳብ ያቀረቡም ነበሩ፡፡ ግን፣ “መስዋዕትነት”ን የሚቃረን ወይም የሚቃወም  ሃሳብ የሰነዘረ የለም፡፡ “መስዋዕትነት፣ መልካም ነው ወይ?” ብለን ጉዳዩን መመርመር አለብን የሚል ሃሳብ እንኳ አልቀረበም። በቃ፤ መስዋዕትነት ቅዱስ እንደሆነ፣ ሁሉም ይስማሙበታል።
የሃሳብ ልዩነታቸው ምን ላይ ነው?
አንዳንዶቹ፣ “የመስዋዕትነት ባህል ቀንሷል” በማለት ሃዘናቸውን ሲገልፁ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ፤ “መስዋዕት መክፈል፣ የግድ ህይወትን አሳልፎ መስጠትና መሞት እንደሆነ ተደርጎ መታሰብ የለበትም። የመስዋዕትነት መንፈስ አልቀነሰም፣ መልኩ ተቀየረ እንጂ አልደበዘዘም” በማለት ተከራክረዋል። “በእርግጥ፣ እንደ ድሮ የሕይወት መስዋዕትነት ብዙ ላይታይ ይችላል። ነገር ግን፣ የሕይወት መስዋዕትነት እንዳይቀንስ በመስጋት፤ የግድ ጦርነት መፍጠር አያስፈልግም” በማለትም ለማስረዳት ሞክረዋል።
እንዴት ነው ነገሩ? መስዋዕትነትን ለማየት ጦርነትን መመኘት፣... ይሄ እንደ ጤናማ ሃሳብ ተቆጥሮ፣ መነጋገሪያ ሲሆን፣…ትንሽ ቆም ብሎ ማሰብ አያስፈልግም? ያሰፈልጋል፡፡ ግን አላደረጉትም፡፡ “መስዋዕትነት”፣ ቅዱስ እንደሆነ... ከዚያም አልፎ፣ የቅዱስ ተግባራት ሁሉ አውራ እንደሆነ በመስማማት፣ በየፊናቸው የተለያዩ የ“መስዋዕት” ሰበቦችንና የተለያዩ የመማገጃ ስፍራዎችን ሲዘረዝሩ ነው የሰማነው፡፡
የመስዋዕት ሰበቦችና መማገጃ ስፍራዎች
“ነባር ባህልና ማህበራዊነት፣ እምነትና ሃይማኖት... እየተሸረሸሩ ነው” በሚል ስሜት ቅሬታቸውን የገለፁ የውይይት ተሳታፊ፤ ከዚህም ጋር የመስዋዕትነት መንፈስ መቀነሱ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል። ሌላኛው ተሳታፊ ደግሞ፣ “የራስን ኑሮ ለማሻሻል መሯሯጥና የራስ ወዳድነት መንፈስ እየተበራከተ መጥቷል” በማለት ሃዘናቸውን ገልፀዋል። “መስዋዕትነት ድሮ ቀረ” በሚል ስሜትም ተክዘዋል።
“ራስ ወዳድነትና የብልፅግና ሩጫ” እንደትልቅ ጥፋት በምሬት ሲወገዝ ስትሰሙ ፣... ሌላ ውስብስብ ትርጉም የያዘ እንዳይመስላችሁ። “ሌሎች ሰዎችን እያታለለና እየዘረፈ  ራሱን ለመጥቀም የሚሞክር ሰው... መጥፎ ነው” ለማለት ፈልገው አይደለም። “በራስ ጥረትና በምርታማነት፣ የራስን ኑሮ ለማሻሻልና ለመበልፀግ መትጋት”... ይሄ ነው ራስ ወዳድነት። ይሄ ነው የብልፅግና ሩጫ። ይህንንም ነው፣ እንደ ሃጥያትና እንደ አስፈሪ ጥፋት የቆጠሩት። ለምን? ያው፣ የራስን ኑሮ ለማሻሻል መጣር፤ ከመስዋዕትነት መንፈስ ጋር ይቃረናል።
የራስን ኑሮ ለማሻሻልና ለመበልፀግ ሳይመኙ፣ የዚህን ዓለም ሕይወት ለማጣጣም ሳይጓጉ፣... ቢጓጉም እንኳ፣ እያማራቸው፣ እየከነከናቸው፣  እየቆጫቸው፣... ንቀው በመተው፤ ሕይወታቸውን አሳልፈው መስጠት፣... ሙሉ ለሙሉ ለሃይማኖት ትዕዛዛት፣ ለፓርቲያቸው፣ ለመንግስታቸው... አገልጋይና ሟች መሆን...ይሄ፣ አንዱ የመስዋዕትነት አማራጭ ነው። ሌላም አለ፡፡
“ከራስ ጥቅም በፊት፣ የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም፣... ማለትም የሌሎችን ሰዎች ጥቅም ማስቀደም”... ይሄም ሌላኛው የመማገጃ አማራጭ ነው። “ከራስ ጥቅም በፊት አገርን፣ ባህልን፣ ብሄርን ማስቀደም”... ይሄኛውም ሌላ የመስዋዕት መቀበያ ስፍራ ነው።
የመስዋዕት መለኪያ፣ ያንተ መጐዳት፣ ያንቺ መሰበር
የመማገጃው ስፍራ የትም ይሁን የት፣ ዋናው ነገር፣ አንተ ራስህን ስትጎዳ ወይም አንቺ ራስሽን ስትሰብሪ ማየት አለብን። የግል ጥቅምን በማሽቀንጠር፣... ስለ ደሞዝና ስለ ትርፋማነት፣ ስለ ጤንነትና ስለ ምቾት፣ ስለ ደስታና ስለ እርካታ ማሰብን እርግፍ አድርጎ ከመተውም በተጨማሪ፣ ውድ የኑሮ አለኝታዎችንና አጓጊ የሕይወት ጣዕሞችን እንደ ከንቱ ቆጥሮ፣ ህዝብንና አገርን ለማገልገል ሕይወትን አሳልፎ መስጠት፣… ይሄ ነው የክብር ሁሉ ክብር?
እርስዎ፤ የመስዋዕትነትን ትርጉም በደንብ ካልተገነዘቡ፤ “ህዝብንና አገርን ለመጥቀም... በአዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራና በአነስተኛ ዋጋ፣ ብዙ ምርት ለገበያ ማቅረብ እፈልጋለሁ” ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። በእርግጥም፣ ሃሳብዎ ሰምሮ፣ ስራዎ ተሳክቶ፣ ህዝብንና አገርን ሊጠቅም ይችላል (ማለትም ብዙ ሰዎችን ሊጠቅም ይችላል)። ነገር ግን፣ ይሄ መስዋዕትነት አይደለም። እርስዎም’ኮ ትርፋማ ይሆናሏ።
በእርስዎ ስራ፣ ብዙ ሰው ትልቅ ጥቅም ማግኘቱ አይደለም ቁምነገሩ። ተግባርዎ፣ “መስዋዕትነት” ተብሎ፣ በክብር ሊመዘገብ የሚችለው፣ ነገርዬው የእርስዎን ኑሮ የሚያጎድልና የሚያከስር ከሆነ ብቻ ነው። ዋናው ነገር ይሄው ነው። “‘አገር’፣ ‘ህዝብ’፣ ‘መጪው ትውልድ’፣ ምን ያህል ተጠቀመ?” የሚል አይደለም ዋናው ጥያቄ። “እርስዎ፣ የራስዎን ኑሮ ለማጉደል፣ ለመክሰርና ለመሰቃየት፣ ምን ያህል ፈቃደኛ ሆኑ?” የሚል ነው ጥያቄው።
“ከእርስዎ፣ ምን ያህል ጥቅም አገኘን?” በሚል ሚዛን አይደለም፣ ለእርስዎ ያለንን ክብር የምናሰላው። የጥቅም ጉዳይ አያሳስበንም። ይልቅ፣ በእርስዎ ጉዳትና ኪሳራ ላይ ነው የምናተኩረው። ስቃይዎ በበዛ ቁጥር፣ አክብሮታችን ይንራል። ሰይጣናዊ የምቀኝነት ክፋት የተጠናወተን ይመስላል። ግን፣ ምንም ማድረግ አንችልም። “የቅዱስነት አውራ፣ መስዋዕትነት ነው” ብለናል። የመስዋዕትነት መለኪያችን፣ ስቃይ ነው። ስለዚህ፣ እንድናደንቅዎ ከፈለጉ፣ በስቃይ ሲንፈራፈሩና ደምዎ ሲንዠቀዠቅ ማየት አለብን። መስዋዕትነት የሚለካው በዚህ ነዋ። በአገራችን፣ የ1960ዎቹ ዓ.ም ‘አብዮተኛ ተማሪዎች’፣ በአድናቆት ሊወደሱ እንደሚገባ ሲነገር የምንሰማው ለምን ሆነና!
በሌሎች አገራት እንደታየው፣ አብዮተኛ ሶሻሊስቶች፣ በኢትዮጵያም ብዙ ጥፋቶችን አስከትለዋል - ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር እያሉ መተላለቅ፣ የጅምላ ውግዘትና እስር፣ ጦርነትና ስደት፣ የንብረት ውርስና ‘ራሽን’፣ ድህነትና ረሃብ...።
ታዲያ እንዲህ አይነቱ የአብዮተኞቹ ተማሪዎች ተግባር፣ አገርንና ህዝብን ያጠፋል እንጂ ይጠቅማል እንዴ? ተግባራቸው አገርን ባይጠቅምም፣... አገርን ቢያጠፋም፤... ለብዙ ጥፋትና እልቂት መንስኤ ቢሆኑም፣... ያን ሁሉ ጥፋት የፈፀሙት፣...  የራሳቸውን ኑሮ ለማሻሻል፣ ለማትረፍና ለመበልፀግ ሳይሆን፤ በመስዋዕትነት መንፈስ ነው። ቤት ንብረታቸውን፣ ኑሯቸውንና ሕይወታቸውን አሳልፈው በመስጠት መስዋዕት ሆነዋል። ስለዚህ ክብር ይገባቸዋል። ዋናው መመዘኛ፤ መስዋዕትነት ነው ብለናላ።
አብዮተኛው ተማሪ፣ ህዝብን የሚጨርስ ተግባር ቢፈፅምም ችግር የለውም። አያስጨንቀንም። የምንጠላው ነገር ሌላ ነው፡፡ ለራሱ ሕይወት ዋጋ በመስጠት፣ ኑሮውን ሲያሻሽል ማየትን ነው የምንጠላው።
የእርስዎን ውርደት እንናፍቃለን
 “የራስ ጥቅምና ትርፍ” ሲባል፤ በገንዘብና በንብረት፣ በኑሮና በአካል ጉዳዮች ብቻ የታጠረ አይደለም። መንፈስንም ጭምር ያካትታል። የራስን ኑሮ መበደል ብቻ ሳይሆን፣ ራስን ማዋረድም ያስፈልጋል - በመስዋዕትነት ለመምጠቅ።
ልብ ይበሉ። “መስዋዕትነት ፈፅሜለሁ” በማለት፣ አንዳች የመንፈስ እርካታ ለማትረፍ ከሞከሩ፣ መስዋዕትነትዎ ይረክሳል። አንቺም፤ ድርሰት ፅፈሽ ካሳተምሽ በኋላ፣ በራስሽ ኪሳራ፣ ለአዳሜና ለሄዋኔ ሁሉ በነፃ ብታከፋፍይ፣ እንደ “መስዋዕት” ሊቆጠርልሽ ይችላል። ነገር ግን፣ መፅሃፉ ላይ ስምሽን በማስፈር፣ ለስራሽ የሚመጥን አድናቆትን፣ ምስጋናንና እውቅናን ለማትረፍ ማሰብ የለብሽም። ጨርሶ አይፈቀድም - “ራስ ወዳድነት” ነዋ። (በእርግጥ እንዲህ ስንልሽ፣ የምቀኝነት አባዜ የተጠናወተን ሊመስል ይችላል፡፡ ገና ምኑን አይተሽ!)።
“የራሴን ጥቅም በማሽቀንጠር፣ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም ሃሳብ አፈልቃለሁ፤ ይህንኑም አላማ በመምረጥ ተግባራዊ አደርጋለሁ”... ብለው በመነሳት ብቻ፣ የመስዋዕትነትን መመዘኛ ማሟላት የሚችሉ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ይሄ ግን እውነተኛ መስዋዕትነት አይደለም። በራስ የመተማመንና በራስ የመመራት አዝማሚያዎች ይታዩበታል፡፡ በራሱ ያፈለቃቸው ሃሳቦችና የወጠናቸው ተግባራት... የቱንም ያህል ትክክልና ጠቃሚ ቢሆኑ እንኳ፣ እነዚሁኑን ሃሳቦችና ውጥኖች መስዋዕት ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለበት። “ሃሳቤ”፣ “አላማዬ” የሚሉ ቃላትን በመተው፤ “ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም፣ የሚጠበቅብኝን ማንኛውንም ነገር ለመስራት ታዛዥ እሆናለሁ” ብሎ ባርነትን በፀጋ መቀበልና ትልቅ ወራዳነትን መላበስ ይኖርበታል። ይሄ፣ የመስዋዕትነት ልዩ ተሰጥኦ ነው።
“ለአልባሳት ስራ ልዩ ፍቅርና ልዩ ችሎታ ቢኖረኝም፤ የእንጨት ስራ ወይም ሜካኒክነት እንድማር ከተወሰነ፣... የቱንም ያህል ቢያስጠላኝ፣ ተልእኮዬን ተቀብዬ የመሰማራት እዳ አለብኝ። የሰራሁትንና ያመረትኩትን ነገር፣ በተነገረኝ የዋጋ ተመን መሸጥ፣... ‘ለህዝብ ጥቅም ይፈለጋል’ ከተባልኩም፣ በታዛዥነት ማስረከብ ግዴታዬ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ለመብት መከራከር፣ አስነዋሪ የራስ ወዳድነት ተግባር ስለሆነ፤ እርም ብያለሁ። የማሰብና የመናገር ነፃነት፣ የማምረትና የንብረት ባለቤትነት መብት፣ በአጠቃላይ፣ የራስን ሕይወት የመምራት ነፃነት ይከበር... ብሎ መከራከር፣ ፀረ መስዋዕትነት ነው” --- እንዲህ አይነቱን “ቅዱስ ጀግና”፤ በአርአያነት አጉልተን ለማሳየት እንጣጣራለን - የመስዋዕትነት አድናቆት ሲጠናወተን።
የኑሮና የደስታ መሰረቶችን ገነዳድሶ መጣል የሚችል ልዩ መሳሪያ ነው - የመስዋዕትነት አምልኮ፡፡

Read 3542 times