Saturday, 30 January 2016 11:48

የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ

Written by  ሀብታሙ ግርማ (ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ)
Rate this item
(4 votes)

ካለፈው የቀጠለ
የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲን በመቅረጽ ረገድ የፓርቲው የረጅም ጊዜ መሪ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ በትጥቅ ትግሉ ዓመታት የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና ከማዖ ‹የአዲሱ ዲሞከራሲ› ፍልስፍና ጋር የሚመሳሰል ነበር፡፡
በኢኮኖሚ ግቡ ሶሻሊዝምን ማስፈን፤ በፖለቲካ ግቡ ደግሞ  የአንድ ፓርቲ የበላይነት የነገሰበት ስርዓት ዕውን ማድረግ ነበር።  ነገር ግን ፓርቲው ስልጣን ሊይዝ በተቃረበበት ዓመታት የአለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ስርዓት ወደ ዲሞክራሲና ካፒታሊዝም በማጋደሉ ኢህአዴግ ይህን ያገናዘበ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍልስፍና ለውጥ አደረገ፡፡ እከተለዋለሁ የሚለው አብዮታዊ ዲሞክራሲ በፖለቲካ ግቡ ሊበራሊዝምን ማስፈን፤ በኢኮኖሚ ግቡ ደግሞ ኢንዱስትሪ (ካፒታሊዝም) እንደሆነ ገለጸ፡፡ እናም የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከሶሻሊዝም ወደ ካፒታሊዝም በሚደረግ ሽግግር ፖለቲካው የሚመራበት ስርዓት ነው፡፡
አብዮታዊ ዲሞክራሲ ለፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግቦቹ መሳካት የሚሰራ ጠንካራ የፖለቲካ አመራር (ፓርቲ) መገንባት ያስፈልጋል ይላል፡፡ የመሪ ድርጅቱ አወቃቀርም በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ የተቃኘ ይሆናል፤ በዲሞክራሲ ማዕከላዊነት መርህ መሰረት የፓርቲ ውሳኔዎች የሚተላለፉት ከፓርቲው የበላይ አመራሮች ሲሆን ሌሎች የፓርቲ አባላት ሃላፊነት መመሪያውን ተቀብለው ማስፈጸም ብቻ ነው፤  ለውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲ ብዙም ግምት አይሰጥም፡፡
የኢህአዴግ አብዮታዊ አስተምህሮ እንደሚለን፤ ዲሞክራሲን ለማስፈን የህዝብ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልጋል፤ ይህም ከዲሞክራሲ (ከነጻነት) ዳቦ ይቀድማል የሚል ዕምነት የያዘ ይመስላል፡፡ በጥቅሉ የዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት  ጠንካራ የመካከለኛ ገቢ ያለው መደብ መፍጠር ቅድሚያ ሊሰጠው ያስፈልጋል። በኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካዊ ፍልስፍናውን እንደየጊዜውና ሁኔታው የሚቀያይር መሆኑ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ዋነኛ መለያ ባህሪ ነው፡፡  
ምሁራንና ፖለቲከኞች ስለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምን ይላሉ?
ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ‹የኢትየጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ህልሞች፡ የኢህአዴግ ቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ› በሚለው መጽሃፋቸው (ገጽ 73-75) ላይ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ ገጾችን እንደሚከተለው ቃኝተዋል፡-
(የአብዮታዊ ዲሞክራሲ) ፍልስፍና መሰረት ስልጣን ላይ መምጫው መንገድ የማኦው ፍልስፍና የሆነው ‹‹ ስልጣን የሚመጣው ከጠመንጃ አፈሙዝ ነው  የሚለው ነው፡፡
የመሪ ድርጅትና የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ጽንሰ ሃሳቦች የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዋነኛ መሳሪያዎች ናቸው፡፡ ዓላማውም የመንግስትን ስልጣን ጨምድዶ ለመያዝና ከመንግስ ስልጣን የሚመነጩትን ጥቅሞች ብቻ ዓላማዎቹ አድርጎ ለሚንቀሳቀስ ሃይል ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡
በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አንድ ገዥ ፓርቲ የመሪነት ሚና ይኖረዋል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎች እንዲኖሩ ባይከለክልም የሚሰጣቸው ሚና የይምሰል እንጂ ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ በመውጣት ስልጣን እንዲይዙ አይፈቅድላቸውም፡፡ የፓርቲዎቹ ሚና የገዢው ፓርቲ አገልጋይ መሆን እንጂ ተቀናቃኝ መሆን አይደለም፡፡
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አሰተሳሰብ በፓርቲና  በመንግስት መካከል ፍጹማዊ አንድነትን ይፈቅዳል፡፡ (በዚህም) ልዩ ልዩ የመንግስት ተቋማትም የገዢው ፓርቲ ጉዳይ አስፈጻሚዎች መሆን አለባቸው፡፡……ሁሉም የመንግስት ተቋማትና ሰራተኞቻቸው የገዢውን ፓርቲ ፍጹማዊ አመራር መቀበል አለባቸው፡፡….. ይህ ማለት ለሲቪል ሰርቪስ የተቀጠሩ ሰራተኞች የዲሞክራሲያዊ ስርዓት በዳበረባቸው ሀገgሮች እንደሚደረገው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር ነጻ መሆን አይችሉም፡፡ እንደዚህም በመሆኑ ‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ› ለታማኝነት እንጂ ለዕውቀትና ችሎታ ብዙም የማይጨነቅ የካድሬዎች አስተዳደር ይሆናል፡፡
(በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተምህሮ መሰረት ነጻ የመንግስት ተቋማት እንዲጠናከሩ ስለማይፈለግ የዘመናዊ የውክልና ዲሞክራሲ መሰረተ ድንጋይ የሆኑት የስልጣን ክፍፍል እና አንዱ የሌላውን ስልጣን መቆጣጠር አይኖሩም፡፡
በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ነጻ የሲቪል ማህበራት እንዲያብቡ አይፈቀድም፡፡ ነጻው ፕሬስ የአድሃሪ ሃይሎች መmሰያ ስለሚሆን ቢታፈን ችግር የለውም፡፡…
የዶ/ር መረራ ትንተና እንደሚያስረዳው፤ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሶስቱም የመብት ክፍሎች ማለትም የፖለቲካ፣ የንብረት ባለቤትነት እንዲሁም የሲቪል መብቶች አይከበሩም፡፡
አንጋፋው የህወሃት ታጋይ አቶ ገብሩ አስራት ‹ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ. በተሰኘውና በ2007 ዓ.ም ለህትመት በበቃው መጽሃፋቸው ገጽ 148 ላይ አብዮታዊ ዲሞክራሲንና ሊበራል ዲሞክራሲን ሲያነጻጽሩ እንዲህ ይላሉ፡-
‹……….አ.ብዮታዊ ዲሞክራሲ መደባዊ ይዘትንና ወገንተኝነትን ሲያመለክት ሊበራል ዲሞክራሲ ደግሞ ዜጎች ሁሉ ያለምንም አድልዖ እኩል ናቸው ይላል፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የአንድን አገር ዜጎች እንደጠላትና ወዳጅ ይከፋፍላል፤ በሊበራል ዲሞክራሲ አይን ደግሞ ሁሉም ዜጎች እኩል ናቸው። አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጨቋኝ መደቦች መብትና ነጻነት ሊነፈጉ እንደሚገባቸው ሲያመላክት፣ ሊበራል ዲሞክራሲ ደግሞ ነጻነትና መብት ለሁሉም ዜጎች እኩል መሰጠት እንዳለበት ያስረግጣል፡፡ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተምህሮ ማንኛውም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ በመሪ ድርጅት ቁጥጥር ስር መሆን አለበት ሲል፤ ሊበራል ዲሞክራሲ ደግሞ ብቃት ያላቸው ዜጎች ተወዳድረው ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውንና ማህበራዊ እንቅስቃሴውን እንዲመሩ ያደርጋል፡፡
ሀብታሙ አለባቸው የተባሉ ምሁር ‹Settling the Accounts, of ‘Revolutionary Democracy’ in Ethiopia after Meles› በሚለው ጽሁፋቸው፤ በገብሩ አስራት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ትንታኔ አይስማሙም፡፡
ገብሩ አስራት እንደሚሉት አብዮታዊ ዲሞክረሲ በኢትዮጵያ ሊሰራ አይችልም፤ ገብሩ አስራት በ2002 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ክርክር ወቅት እንዳነሱት፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ (ከፊውዳሊዝም) ወደ ሶሻሊዝም በሚደረግ ሽግግር የፖለቲካው አመራር ምን መምሰል እንዳለበት የሚያሳይ ሀልዮት ነው ሲሉ ሞግተው ነበር፤ እናም እንደ አቶ ገብሩ ከሆነ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጊዜው ያለፈበት ስለሆነ አይሰራም፡፡
ገብሩ ይህን በሚሉበት ወቅት ግን መለስና ኢህአዴግ የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ፍልስፍና ትርጓሜ ፈጽሞ በተቃራኒው ቀይረው ስለነበር የገብሩ አስራት አረዳድ ጊዜውን ያልጠበቀ ነበር፡፡ በእርግጥ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከሶሻሊዝም ወደ ካፒታሊዝም (ኒዮ ሊበራሊዝም) በሚደረገው የሽግግር ጊዜ ፖለቲካው የሚመራበትን መንገድ የሚተነትን አስተምህሮ ነው፡፡ መemocracy’  ry  Democracy’  in cracy as Alternative to Revolutionary Democracy’
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የኢኮኖሚ ገጾች
መርስኤ ኪዳን የተባሉ ምሁር ‘Making the Case for Liberal Democracy as Alternative to Revolutionary Democracy’ በሚለው ጽሁፋቸው እንዳሰፈሩት፤ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የኢኮኖሚ ፍልስፍና ወሰን ሰፊ ነው፤ ከሶሻሊዝም የዕዝ ስርዓት እስከ ሙሉ በሙሉ የኒዮ ሊበራሊዝም አክራሪ የገበያ ስርዓት ድረስ ያሉትን አማራጮች ሁሉ ሊጠቀም ይችላል፡፡ እንደየሁኔታውና ጊዜው አስገዳጅነት ሊቀየር እንዲሁም ከሁለቱም አይዲዮሎጂዎች አጣምሮ ሊቀርጽ ይችላል። ኢህአዴግ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት እመራበታለሁ ብሎ ያወጃቸው ሁለት የኢኮኖሚ አስተምህሮች ማለትም ነጭ ካፒታሊዝምና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍጹም ተቃራኒ መሆናቸው የዚህ ማሳያ ነው፡፡
(ይቀጥላል)
ውድ አንባቢያን፡-ጸሀፊው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆን በ E-Mail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ; This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.   ማግኘት ይቻላል፡፡



Read 7538 times