Saturday, 06 February 2016 10:59

ወደ የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን በዝተዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በአመት 82ሺ ኢትዮጵያውያን የመን ገብተዋል። 11ሺ ያህሉ ሴቶች ናቸው።
20ሺ የመናዊያን በጦርነት ወደ ጂቡቲ፣ ሶማሊያና ኢትዮጵያ ተሰደዋል።

    ለሥራ ወደ አረብ አገራት መጓዝ የተከለከለው፣ ጉዳት ይደርስባቸዋል በሚል ነበር። በእርግጥም በየጊዜው፣ ለአደጋ የሚጋለጡ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ጥቂት አይደሉም። ነገር ግን፣ እገዳው፣ በጎ ውጤት አላስገኘም። አደጋንና ጉዳትን ከመቀነስ ይልቅ እንዲባባስ አድርጓል።
አይኦኤም ሰሞኑን ባሰራጨው መረጃ እንደጠቆመው፤ እስከ ጥር ወር ድረስ፣ ወደ የመን ለመግባት ከተጓዙት ስደተኞች መካከል 340 ያህሉ ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ደብዛቸው ጠፍቷል። አብዛኞቹ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው - 280 ያህሉ። በህጋዊ ምዝገባ ወደ አረብ አገራት መሄድ፣ የዛሬ ሁለት አመት ከመታገዱ በፊት፣ እንዲህ አይነት እልቂት አይከሰትም ነበር።
ይህም ብቻ አይደለም። ቀደም ሲል፣ አብዛኞቹ ሴቶች ወደ አረብ አገራት የሚሄዱት በህጋዊ ምዝገባ በአውሮፕላን በረራ እንጂ፣ በአደገኛ የባህር ጉዞ ወደ አደገኛዋ አገር ወደ የመን የመሄድ ብዙም ፍላጎት አልነበራቸውም። አሁን ግን፣ በህጋዊ ምዝገባ የመሄድ እድል በእገዳ ስለተዘጋ፣ አማራጭ በማጣት፤ በየመን በኩል የሚጓዙ ሴቶች ቁጥር ጨምሯል - 11ሺ።
የዛሬ አራት አምስት ዓመት፣ ወደ አረብ አገራት የሄዱ ኢትዮጵያውያን ላይ ሲደርስ የነበረው ጉዳት ቀላል አይደለም። የሚያስቆጭ የሚያንገበግብ ነው። ነገር ግን፣ ያንን ጉዳት ለመቀነስ በትጋት ከመስራት ይልቅ፣ ጉዞዎቹን ማገድ አቋራጭ መፍትሄ ሆኗል። ተቆርቋሪነትም ይመስላል። ተቆርቋሪነት ግን አይደለም። ጭካኔ ነው - የአምስት የአስር ሰዎች መሞት የሚቆረቁረው ሰው፤ መቶ፣ ሁለት መቶ፣ ሰዎችን ለሞት የሚዳርግ እገዳ ማወጅ።

Read 1214 times