Saturday, 06 February 2016 11:00

ልማታዊ መንግስትና አብዮታዊ ዲሞክራሲ

Written by  ሀብታሙ ግርማ (ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ)
Rate this item
(13 votes)

አብዮታዊ ዲሞክራሲና ነጭ ካፒታሊዝም
የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራንና የፖለቲካ ሰዎች እንደሚተነትኑት፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲና ነጭ ካፒታሊዝም አብረው የሚሄዱ አይደሉም፤ እዚህ ጋር ልብ ልንለው የሚገባው ነገር ቀደም ሲል የተጠቀሱት ሁሉም አይነት የካፒታሊዝም ስርዓት አይነቶች በመሰረታዊነት የግለሰብ መብትን ያስቀደመ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በቅድመ ሁኔታነት የሚጠይቁ መሆኑን ነው፡፡ የነጭ ካፒታሊዝም የፖለቲካ ፍልስፍና የኢኮኖሚ ግልባጭ መሆን የሚገባው (የሆነው) ሊበራል ዲሞክራሲ ነው። የካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ፍልስፍና መሰረቶች የሆኑት ነጻና ፍትሃዊ የውድድር ስርዓት፣ ለግለሰብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መብቶች ቅድሚያ መስጠት፣እንዲሁም ኢኮኖሚው የሚመራው በቢዝነስ ተሰጥኦ በላቁ  ስራ ፈጣሪዎች መሆኑ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ መሰረታዊ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ጋር አያስማማውም፡፡ ካፒታሊዝም በኢኮኖሚው ዘርፍ የመንግስት ጣልቃ ገብነትን ይወስናል፤ አብዮታዊ ደሞክራሲ በአንጻሩ በኢኮኖሚ መስክ ጠንካራ የመንግስት አመራር ያስፈልጋል ይላል፤ በመሆኑም አብዮታዊ ዲሞክራሲና ነጭ ካፒታሊዝም ሊታረቁ የሚችሉበት ዕድል የለም ማለት ይቻላል፡፡
ልማታዊ መንግስትና አብዮታዊ ዲሞክራሲ
እንደ ልማታዊ መንግስት አስተምህሮ፤ ለብዙሃኑ የኢኮኖሚ ጥቅም ሲባል የግለሰቦች የኢኮኖሚ መብቶችና ጥቅሞች ቢነኩ አይኮነንም፡፡ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚያመላክተውም ወደዚሁ አቅጣጫ ነው። አብዮታዊ ዲሞክራሲ የአንድ ጠንካራ ገዢ ፓርቲ አስፈላጊነትን አብዝቶ ይሰብካል፤ ልማታዊ መንግስትም እንዲሁ ነው፡፡ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መሰረታዊ የፖለቲካ ገጾች ከልማታዊ መንግስት አስተምህሮ ጋር ቢያንስ አይጋጩም፡፡ ልማታዊ መንግስት፤ መንግስት በኢኮኖሚው ላይ ያለው ድርሻ ጠንካራ እንዲሆን ይመክራል፤ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፖለቲካዊ መሰረት የሆነው የጠንካራ ፓርቲና መንግስት አስፈላጊነትም ከዚሁ ጋር ይስማማል፡፡
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መዳረሻ ሊበራል ዲሞክራሲ መሆኑን ኢህአዴግ በተደጋጋሚ ይገልጻል፤ ወደዚህ የሚያደርሰው ደግሞ ጠንካራ መካከለኛ ገቢ ያለው ህዝብ ነው፡፡ ልማታዊ መንግስትም በዓላማው ጠንካራ መካከለኛ ገቢ ያለው ዜጋ መፍጠር ነው፡፡ በመሆኑም ልማታዊ መንግስት የአብዮታዊ ዲሞክራሲን የፖለቲካ ግብ ለማሳካት ከነጭ ካፒታሊዝም ይልቅ የተሻለ ነው፡፡
የኢሀአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ተለዋዋጭ ባህሪ መነሾዎች
የታዳጊ አገራትን የኢኮኖሚና ፖለቲካ ፍልስፍና፣ ጥንካሬና ድክመት ከመገምገማችን በፊት ማንሳት ያለብን ቁልፍ ጉዳይ አለ፡፡ ይህም እውን አገራቱ የሚከተሉትን አይዲዮሎጂ በነጻነት የመምረጥ ስልጣን አላቸው ወይ? የሚል ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በርካታ የታዳጊው አለም አገራት (በዋናነትም አፍሪካ)  ከቅኝ ግዛት ነጻ መውጣት ቢጀምሩም የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታቸውን ግን ዛሬም ድረስ አገኝተዋል ማለት አይቻልም፡፡ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማጣት ማለት  መንግስታት ከአገራቸው ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የሚዛመዱ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂ የመቅረጽና ተግባራዊ የማድረግ ስልጣን ማጣት ማለት ነው። የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታቸውን የተነጠቁት በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ያለፉ አገራት ብቻም ሳይሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ነጻነታቸውን አስጠብቅው የኖሩ፣ ነገር ግን የኢኮኖሚ ህልውናቸው በምዕራባዊያን ብድርና እርዳታ የሚወሰን አገራት ጭምር ናቸው፡፡  የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና፣ተለዋዋጭ ባህሪውን ስንፈትሽ ይህን ዕውነት ማገናዘብ አለብን፡፡  
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሁለት ጊዜ የኢኮኖሚ ገጹን (የኢኮኖሚ ፍልስፍናውን) ቀይሯል፡፡ የመጀመሪያው በ1983 ዓ.ም ከሶሻሊዝም ፍልስፍናው ወደ ነጭ ካፒታሊዝም ያደረገው ለውጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በ1998 ዓ.ም ገደማ ከነጭ ካፒታሊዝም ወደ ልማታዊ መንግስት ያደረገው ነው፡፡ ለመሆኑ ለዚሁ ለውጥ መነሾዎች (ገፊ- ምክንያቶች) ምን ነበሩ?
ከሶሻሊዝም ወደ ነጭ ካፒታሊዝም
በትጥቅ ትግል ዓመታት ኢህአዴግ ሲከተለው የነበረው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከማዖ ፍልስፍና የመነጨውና ወደ ሶሻሊዝም ሽግግር በሚደረግበት ወቅት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚው የሚመራበት ስርዓት ሲሆን በኢኮኖሚ ግቡ ሶሻሊዝምን፤ በፖለቲካው ደግሞ የአንድ ፓርቲ አገዛዝን ማስፈን ነበር፡፡ ኢህአዴግ የ17 አመታት ትግሉ ፍሬ አፍርቶ ስልጣን ሊይዝ በተቃረበበት ወቅት የሶሻሊዝም ህልውና ተዳክሞ ነበር፤ ካፒታሊዝምና ሊበራል ዲሞክራሲ (ነጭ ካፒታሊዝም) ደግሞ አለማቀፍ የበላይነት የያዙበት ጊዜ ሆነ፡፡ እናም በትግል ወቅት ያራምድ የነበረውን የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ይዞ መቆየቱ፣እንደማያዋጣው ተገነዘበ፡፡ ብቸኛ አማራጩ፣በኢኮኖሚ ፍልስፍናው ካፒታሊዝምን፤በፖለቲካው ደግሞ ዲሞክራሲን መከተል ነበር፡፡ እናም ኢህአዴግ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተምህሮውን በዚህ መልኩ ለወጠ፡፡
ከነጭ ካፒታሊዝም ወደ ልማታዊ መንግስት
ከ1983 ዓ.ም እስከ 1990ዎቸ መጨረሻ ድረስ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አርሶአደሩን ዋነኛ መደቡ አድርጎ ነበር፤ በአንጻሩ የከተማው ህዝብና ዋነኛ የኢኮኖሚ ዋልታው የሆኑት የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች ትኩረት አልተሰጣቸውም ነበር። ከ1990ዎቹ መጨረሻ ወዲህ ባሉት ዓመታት ግን ገጠርን ማዕከል ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በይፋ ባይሆንም እንደማያዋጣ ታምኖበት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ በዚህም ነጭ ካፒታሊዝም በልማታዊ መንግስት አስተምህሮ ተለወጠ። የዚህን ለውጥ  ገፊ ምክንያቶች ውስጣዊ (መነሻቸው አገራዊ የሆኑ) እና ውጫዊ (አለማቀፍ ለውጦች)  በሚል መከፋፈል ይቻላል፡፡ ውስጣዊ ምክንያቶቹ ደግሞ ሁለት ናቸው፤ የመጀመሪያው የግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ በተግባር ተጨባጭ ዕድገት ሊያስገኝ አለመቻሉ ሲሆን ሌላው ደግሞ የ1997ቱን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ የተከሰተው ህዝባዊ አመጽ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ጉልህ አለማቀፍ ለውጥ ተከስቷል፡፡ ይኸውም፤የምስራቁ ዓለም በተለይም የቻይና አለማቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ኢኮኖሚ ሆና መውጣትና ለዘመናት በምዕራባዊያን ተይዞ የኖረው የአለም የኢኮኖሚ የበላይነት ማብቃት ነው። ይህም በተለይ ታዳጊ አገራትን (ኢትዮጵያን ጨምሮ) ከምዕራባዊያን ተጽዕኖ በመጠኑም ቢሆን እንዲላቀቁና የራሳቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲቀርጹ ነጻነት ሰጥቷቸዋል፡፡
ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት ከ1983 ዓ.ም እስከ 1990ዎቹ መጨረሻ ድረስ  በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተምህሮው መሰረት፤ ዋነኛ የኢኮኖሚ መሰረት አድርጎ የሚያየውን አርሶአደሩን መካከለኛ ገቢ ያለው መደብ ለማድረግ፣ ለግብርናና ገጠር ልማት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ነበር፤ በጊዜው የተቀየሰው የግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ (Agricultural Development Led-Industrialization /ADLI/) ገበሬውን ኢንዱስትሪያሊስት ለማድረግ ያለመ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር ADLI የኢንዱስትሪ መሰረት የሆነውን ካፒታልና ጥሬ እቃ ከግብርናው ዕድገት ለማግኘት ያለመ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ነዋሪነቱ በገጠር እንደመሆኑና የአገሪቱ ሀብት መሬትና ጉልበት ከመሆኑ አንጻር ግብርናና ገጠርን ማዕከል ያደረገ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲ መከተሉ ተገቢ ነበር፡፡ ችግሩ የከተማ ልማት፣ የኢንዱስትሪውና አገልግሎት ዘርፉ ትኩረት መነፈጉ ነው።  
በዚያ ላይ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የሚጠበቅበትን ዕድገት ባለማሳየቱ፣ አርሶአደሩ ካፒታል ሊያፈራና ለኢንዱስትሪው ጥሬ ዕቃ የሚሆን የተትረፈረፈ ምርት ሊያመርት ቀርቶ ለምግብ ፍጆታ እንኳ አልተረፈውም። እናም የግብርናና ገጠር ልማትን መሰረት ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ፤አርሶአደሩን መካከለኛ ገቢ እንዲኖረው ያለመውን የአብዮታዊ ዲሞክራሲን የኢኮኖሚ ግብ ሊያሳካ አልቻለም፡፡ ይህም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቋሚ  ነበር፡፡
ኢህአዴግ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲያደርግ ያስገደደው ሌላኛው ውስጣዊ ምክንያት የ1997ቱን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ በኢህአዴግ ላይ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ነበር፡፡ የተቃውሞው ሞተር ደግሞ የከተሜው ነዋሪ ነበር፡፡ በእርግጥም ከተሜው፣ በተለይ ወጣቱ ክፍል በስራ አጥነትና በከፍተኛ የትምህርት እድል እጦት ተስፋ የቆረጠበት ወቅት ነበር፡፡ ከ1997 ዓ.ም በኋላ ግን ኢህአዴግ አርሶአደሩን ጠበቅ፣ ከተሜውን ላላ አድርጎ የመያዙ አቅጣጫ እንደማያዛልቀው በመገንዘብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ አደረገ፡፡ በዚህም የከተማው ህዝብና ኢኮኖሚ መሰረቱ የሆኑት የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች ትኩረት ተሰጣቸው፡፡ የከተማውን ነዋሪ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ልማት የማደራጀት ስራዎች በስፋት መተግበር ተጀመረ፤ የውጭ ባለሃብቶች በተለይ በቀላል ኢንዱስትሪ ልማት እንዲሳተፉ የሚስቡ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችም የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ሆነ፤ እየጨመረ የመጣውን  የወጣቱን የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተደራሽነት ጥያቄ ለመመለስም መንግስት በርካታ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆችን ገነባ፡፡
ቻይና ፊቷን ወደ አፍሪካ ማዞሯን ተከትሎ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ አጋርነታቸውን ከምዕራቡ ዓለም ወደ ምስራቁ መለሱ፡፡ በዚህም ታዳጊ አገራት እንደቀደመው ጊዜ የልማት ፈንድ ለማግኘት ከምዕራባዊያን የርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ ቅድመ ሁኔታዎች ነጻ ሆኑ፡፡ የኢኮኖሚ ነጻነታቸውን በተወሰነ መልኩ ስላገኙም በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታዎች የተቀኙ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን መከተል ጀመሩ። ኢትዮጵያም በ1998 ዓ.ም የነጭ ካፒሊዝም ርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብን በመተው፣ የልማታዊ መንግስት ፍልስፍናን መከተል ጀመረች፡፡
የልማታዊ መንግስት አስተምህሮ እንደሚለው፤ ዋነኛ የመንግስት ትኩረት አቅጣጫ መሆን ያለበት የመሰረተ ልማት፣ የኢንዱስትሪና የሰው ሃይል ዘርፎች ልማት ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ከ1990ዎቹ መጨረሻ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት በነዚህ ዘርፎች ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ያፈሰሰው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም  የኢኮኖሚው ቁልፍ ሀብት የሚገኘው ከከተማ ሆነ፤ እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ ትልቁን የኢኮኖሚውን ድርሻ ይዞ የቆየው ግብርና፣ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ቦታውን ለአገልግሎት ዘርፍ ለቀቀ።
የልማታዊ መንግስት አስተምህሮ ለኢትዮጵያ አዋጭ ነው?
ኢህአዴግ የኢኮኖሚ ፍልስፍናውን ወደ ልማታዊ መንግስት ካዞረ በኋላ የተሻለ የኢኮኖሚ ዕምርታ ታይቷል፡፡ ለዚህ መሰረታዊ መነሾው የልማታዊ መንግስት አስተምህሮ ከነጭ ካፒታሊዝም በተሻለ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ ገጽ ጋር ስለሚጣጣም ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ልማታዊ መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ያስችላል ብሎ ሙሉ ለሙሉ ለመደምደም ጊዜው ገና ነው፡፡
በመሰረቱ ልማታዊ መንግስት በብዙ መልኩ የኢኮኖሚ ብሄርተኝነትን ይጠይቃል፤ እንደ ኢትዮጵያ ባለ የብሄር (የቋንቋ) ፌዴራሊዝም የተዋቀረ አስተዳደር ባላት አገር ግን የፌዴራሉ መንግስት፣ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲዎቹን በሙሉ ስልጣን ለማስፈጸም ይቸግረዋል። ኢትዮጵያ ላቀደችው የኢንዱስትሪ ልማት፣ ቁልፍ ሚና ይጫወታል በሚል በማዕከላዊው መንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የተዘጋጀው የአዲስ አበባ አስተዳደር እና የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን አስተዳደር የጋራ ማስተርፕላን ለማጽደቅና ለማስፈጸም አለመቻሉ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ልማታዊ መንግስት፣ የመንግስት ቢሮክራሲ መመራት ያለበት በችሎታቸው በላቁ ሰዎች እንደሆነ ያስቀምጣል፤ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ግን የፌዴራል መንግስት፣ ቢሮክራሲን ለመምራትና ለማዋቀር ዋናው መስፈርቱ የብሄር ተዋጽዖ እንጂ ችሎታና ብቃት አለመሆኑ የልማታዊ መንግስት ስኬታማ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡  
አብዮታዊ ዲሞክራሲን እንደ አንድ ርዕዮተ ዓለም መውሰድ ይቻላል?
ቀደም ሲል ለማብራራት እንደተሞከረው አንድ ርዕዮተ ዓለም ማሟላት ያለበት ቢያንስ አራት ጉዳዮች አሉ፡፡ ከሁሉ በፊት ደግሞ የፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊው ገጹ ግልጽ መሆን አለበት፡፡  አንድ ርዕዮተ ዓለም መሰረታዊ ይዘቱ ጊዜና ሁኔታዎች በፈቀዱት መጠን ሊታደስ የሚችልበት ሁኔታ ቢኖርም መሰረታዊ ይዘቱን ግን ሊቀይር አይገባውም፡፡ ከዚህ አንጻር ታዲያ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እነኚህን መሰረታዊ የርዕዮተ ዓለም ጠባያት ያሟላል? በሌላ አነጋገር አብዮታዊ ዲሞክራሲን እንደ አንድ ርዕዮተ አለም መውሰድ ተገቢነቱ ምን ያህል ነው?
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተምህሮ ተለዋዋጭነት፣ ግልጽ የሆነ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍልስፍና እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ባለፉት 25 ዓመታት የሄደባቸው ፍጹም ተቃራኒ መንገዶች የዚህ ማሳያ ነው፡፡
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የቆመለት መደብም እንዲሁ ተለዋዋጭ ሊሆን ይችላል፡፡ የመደብ ይዘቱ በውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ምክንያቶች ሊቀየር ይችላል፡፡ ቀደም ሲል እንዳየነው፤ ኢትዮጵያን የገጠሟት ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በብቸኝነት የሚቆምለትን የአርሶአደሩን መደብ ያስለወጠና የከተሜውን ህዝብም ከግምት ውስጥ እንዲያስገባ ያስገደደ ነበር፡፡ በመሆኑም አብዮታዊ ዲሞክራሲ እንደ አንድ ርዕዮተ ዓለም ማሟላት የሚጠበቅበትን መሰረታዊ ጉዳዮች አያሟላም፤ እናም እንደ አንድ ርዕዮተ ዓለም መውሰድ (መጥቀስ) ያስቸግራል፡፡
የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሁልጊዜም ከሁኔታዎች ጋር አስተምህሮቱና አቅጣጫው ስለሚለወጥ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ገጾቹም በዚያው ልክ ይለዋወጣሉ፤ በመሆኑም አስተምህሮቱን በግልጽ ለመረዳት ከማስቸገሩ ባሻገር ይህ ተለዋዋጭ ባህሪው በፓርቲው የውስጥ ፖለቲካ እንዲሁም በሚመራው መንግስትና ህዝብ ላይ ተጽዕኖ የማሳደር ዕድል ይሰጠዋል፡፡
የፖለቲካ ተንታኞችና ታዛቢዎች እንደሚሉት፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ህልፈት ተከትሎ ኢህአዴግ የፖለቲካ፣ የአካዳሚክ እንዲሁም የአመራር ክህሎት ያለው መሪ ያገኘ አይመስልም፡፡ ይህም በፓርቲው የወደፊት አቅጣጫ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ጉልህ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ በአጠቃላይ እንደሁኔታው የሚለዋወጠው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍልስፍና፣ አንድ ወጥ አስተምህሮ እንዳይኖር ስለሚያደርግ፣ ፓርቲው የአንድ ሰው አይዲዮሎጂ ጥገኛ እንዲሆን ሊያደርግ የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው፡፡   
 ኢኮኖሚያዊ አንድምታዎች
በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ መመሪያውን ከሶሻሊዝም ወደ ነጭ ካፒታሊዝም ማዞሩን ተከትሎ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የኢኮኖሚ ገጽ ለውጥ አሳየ፤ነገር ግን የፖለቲካ ገጹ አልተለወጠም ነበር፡፡  በፖለቲካዊ ገጹ የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሚገንበት፣ የመንግስት እጅ ጠንካራ እንደሚሆን የሚመክረውን አብዮታዊ ዲሞክራሲ መከተሉን የቀጠለ ሲሆን በኢኮኖሚ ፍልስፍናው ደግሞ የግለሰብ መብት ቅድሚያ በሚሰጠው፣ የመንግስት ጣልቃ ገብነትን አጥብቆ በሚኮንነው ነጭ ካፒታሊዝም ተተካ፡፡ እናም የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ገጾቹ ሊጣጣሙ አልቻሉም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የወጡት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፖለሲዎች አቅጣጫ የሌላቸው ሆኑ፡፡ የዚህ ነጸብራቅ ደግሞ ኢህአዴግ ነጭ ካፒታሊዝምን ትቸቼዋለሁ ብሎ እስካወጀበት 1990ዎቹ አጋማሽ ድረስ የተከተላቸው የኢኮኖሚም ሆነ ማህበራዊ ፖሊሲዎች ውጤታማ አለመሆናቸው፣ እንዲሁም በአገሪቱ የረባ የሚባል የኢኮኖሚ ዕድገት አለመመዝገቡ ነው፡፡   
በሌላ በኩል የልማታዊ መንግስት አስተምህሮን ከ1997 በኋላ መከተል የጀመረው የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ከነጭ ካፒታሊዝም በተሻለ የሚጣጣም የኢኮኖሚ ፍልስፍና ያገኘ ይመስላል፡፡ ይህም ኢኮኖሚው የሚመራበት ፖሊሲ ግልጽ ራዕይና አቅጣጫ እንዲኖረው ያደረገ ነው፤ ይህ አንጻራዊ የፖሊሲ ጥራት ላለፉት አስር አመታት አገሪቱ ላስመዘገበችው የኢኮኖሚ እምርታ የራሱ የሆነ ድርሻ እንደነበረው መገመት ይቻላል፡፡  
ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወደ ሊበራል ዲሞክራሲ……..መቼ?
የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ግብ፣ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መደላድል የሆነው መካከለኛ ገቢ ያለው መደብ መፍጠር ነው፡፡ ኢህአዴግ ለዚህ እየሰራ አንደሆነ፣ አገሪቱም እ.ኤ.አ በ2025  ይህን ግብ እንደምታሳካ ይገልጻል፡፡ ከዚያ በኋላ ኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲን በሊበራል ዲሞክራሲ ይተካል ማለት ነው? ምናልባት ይህ የየዋህ ጥያቄ ነው የሚሉኝ እንዳሉ እገምታለሁ፡፡ በእርግጥ እንደ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተምህሮ ከሆነ፣ ኢህአዴጎች ከአስር ዓመት በኋላ የፖለቲካ ፍልስፍናቸውን በሊበራል ዲሞክራሲ፤ የኢኮኖሚ ፍልስፍናቸውን ደግሞ በካፒታሊዝም ሊቀይሩ ግድ ይላቸዋል፡፡ ይህ የሚሆነው ታዲያ ሁልጊዜ የሚለዋወጠው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተምህሮ በጊዜ ሂደት ከተቀየረ ብቻ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ኢህአዴግ ይህን ተግባራዊ የማድረግ አንጀት አለው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህን ለማድረግ ቁርጠኝነት ካለው፣ በተደጋጋሚ የሚተችበትን የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፣ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ተቋማትን መፍጠርና ማጠናከር፣ ራሱን ለብዝሃ-ፓርቲ ስርዓት መርሆች በጥብቅ ማስገዛት፣ ወዘተ….ለነገ የማይለው የቤት ስራው ነው፡፡ የነገ ሰው ይበለን!
ውድ አንባቢያን፡-ጸሀፊው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆን በ E-Mail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ; This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.   ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 9098 times