Saturday, 26 March 2016 10:55

አሜሪካና አውሮፓ ሲደናቀፉ፤ እኛ እንፈጠፈጣለን

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(11 votes)

የአለማቀፍ ጉዳዮች ምሁር ፋሬድ ዘካሪያ፣ በሲኤንኤን የሚያቀርቡትን ሳምታዊ ትንታኔ፣ በሁለት ስንኞች ነበር የጀመሩት።  
Things fall apart, the center cannot hold;
Mere anarchy is loosed upon the world.
ግራ ቀኝ የምናየው ነገር ሁሉ፣ ምሶሶው እንደተነቃነቀ ቤት ይብረከረካል። እየተፍረከረከ፣ የፍርስራሽ ክምር ይሆናል። የትርምስ በሽታ፣ በየአቅጣጫው፣ በምድሪቱ ላይ የተዛመተ ይመስላል።
ምነው? የ‘ዲሞክራሲ’ ሥርዓት፣ አደጋ ላይ ወደቀ?
እነዚህን ሁለት ስንኞች ለማሰላሰል የምንገደድበት ጊዜ ላይ ደርሰናል አሉ ፋሪድ ዘካሪያ። ዘካሪያ፣ ይህንን የተናገሩት፣ የሶሪያንና የየመንን ወይም የደቡብ ሱዳንንና የማሊን ትርምስ በማየት አይደለም። በአፍሪካ እና በአረብ አገራት፣ የዲሞክራሲ ነገር፣... ለጊዜው ተስፋ እንደሌለውና ብዙ አመታትን እንደሚፈጅ፣... ገና ድሮ ተናግረዋል። ይልቅስ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ የአውሮፓና የአሜሪካ አዝማሚያም አስጊ እየሆነ መምጣቱ ነው ያሳሰባቸው።
ስጋት ያደረባቸው ምሁር፣ ዘካሪያ ብቻ አይደሉም። ሌላኛው ታዋቂ የፖለቲካ ምሁር ፍራንሲስ ፉክያማ፣ ተመሳሳይ ስጋታቸውን ባለፈው አመት ባሳተሙት መፅሃፍ በስፋት ገልፀዋል - Political Order and Political Decay ይላል የመፅሃፉ ርዕስ።
ሁለቱ ምሁራን፣ በዝንባሌ ይለያያሉ። በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ፣ ዘካሪያ ወደ ዲሞክራቶች አስተሳሰብ፤ ፉክያማ ወደ ሪፐብሊካን አስተሳሰብ ያዘነብላሉ። እንዲያም ሆኖ፣ ተመሳሳይነታቸውም ትንሽ አይደለም። በአፍሪካ እና በአረብ አገራት፣ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲሰፍን መደገፍና ተፅእኖ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያምኑ ነበር - ዘካሪያ እና ፉክያማ። ከጊዜ በኋላ ግን፣ ተስፋ ቆርጠዋል። ዲሞክራሲን በቁንፅል ለማስፈን መሞከር፣ ትርፉ ድካም ብቻ ነው። አገራትን ከማናወጥ ያለፈ ውጤት አይኖረውም ባይ ሆነዋል።
በጎሳ የመቧደን አባዜን በማራገፍ ነው ጉዞው መጀመር ያለበት ይላሉ ዘካሪያ። ፉክያማም በበኩላቸው፤ ከሁሉም በፊት፣ ከጎሰኛ ስርዓት መላቀቅ እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ፤ ህግ ሊያስከብር የሚችል አገር አቀፍ የመንግስት ሥርዓት መመስረት፣ ከዲሞክራሲ ይቀድማል ይላሉ። ትንሽ አለመረጋጋት በተፈጠረ ቁጥር፤ በጎሳ በብሔረሰብ ተወላጅነት የተሰባሰቡ ደርዘን ቡድኖች ከየስርቻው እየተፈለፈሉ፣ አገሬውን የሚቀራመቱ ከሆነ፤ ገና ገና ለአቅመ ዲሞክራሲ አልደረሱም ማለት ነው። ብዙ ብዙ ይቀራቸዋል። በወጉ “አገር” የሚባል ነገር አልመሰረቱማ። ነገር ግን፣ ከጎሰኝነት ወይም ከዘረኝነት መላቀቅ ብቻውን በቂ አይደለም።
በእርግጥ፣ ጎሰኝነትን አራግፎ፤ ሕግ የሚያስከብር አገራዊ መንግስት መመስረት፣ አመታትን የሚፈጅ ከባድ ስራ ነው። ቢሆንም፣ በቂ አይደለም። ሕግ የሚያስከብር መንግስት ቢመሰረት እንኳ፤ ሕጎቹ መጥፎ ከሆኑ፣ ግማሽ መንገድ ላይ ተንጠልጥሎ እንደመቅረት ይሆናል። ሕጎቹ፣ መመርመር፣ ማሻሻልና የግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። መንግስትም ሕግ አስከባሪ ብቻ ሳይሆን ሕግ አክባሪ መሆን ይኖርበታል። በሌላ አነጋገር፣ የሕግ የበላይነት (rule of law) መስፈን አለበት። ይሄም፣ ቀላል ነገር አይደለም። የአስተሳሰብንና የትምህርትን አቅጣጫ ለመቀየር በትጋት መስራት፣ የተቋማትንና የባህልን ቅኝት ለመለወጥ ሳይታክቱ መጣር ያስፈልጋል። በርካታ አመታትንም ይፈጃል።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው፤ ሰላማዊ የዲሞክራሲ ስርዓት መፍጠር የሚቻለው።
በፉክያማ ትንታኔ፣ በቅድሚያ ከጎሰኝነት መላቀቅና ሕግ የሚያስከብር አገራዊ የመንግስት ሥርዓት መመስረት፤ ከዚያም የግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተ የህግ የበላይነት ስርዓትን ማጠናከር ያስፈልጋል - የተረጋጋ የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት። አለበለዚያ ግን፣... ከፈረሱ በፊት ጋሪውን ካስቀደሙ ግን፣... ምኑንም ሳይጨብጡ ‘ዲሞክራሲ’ን በቁንፅል አንግበው ቢነሱ፣... ያው በኢራቅ፣ በሊቢያ፣ በሶሪያ ወዘተ እንደታየው፣ አንዴ በትርምስ እየተቃጠሉ፣ ሌላ ጊዜ በአምባገነንነት እየነደዱ፣ ማምለጫ የሌለው የጥፋት አዙሪት ውስጥ ከመንከባለል ያለፈ ውጤት እንደማያስገኝ ያስረዳሉ።
ፋሬድ ዘካሪያም ተመሳሳይ ትንታኔ አቅርበዋል።
ዘካሪያ፣ ከ10 ዓመት በፊት ባሳተሙት መፅሃፍ፣ እንዲህ ብለዋል።-“በአንዳንድ የማዕከላዊ ኤስያ አገራት፣ ዲሞክራሲ ለአምባገነኖች አመቺ መንገድን ጠርጓል። በሌሎች አገራትም፣ ዲሞክራሲ የቡድን ግጭትንና የጎሳ ውጥረትን አባብሷል። ዩጎዝላቪያና ኢንዶኔዢያ በመሳሰሉ አገራትም፣ በዲሞክራሲ የተሻለ ሕይወት አልተፈጠረም። ወደ ዲሞክራሲ ከመሸጋገራቸው በፊት፣ ከአክራሪነት የራቁና ደህና የመቻቻል አዝማሚያ የሚታይባቸው አገራት ነበሩ። ዲሞክራሲያዊ ባልሆኑ በርካታ አገራት ውስጥ፣ የፖለቲካ ምርጫ በማካሄድ፣ ያን ያህልም የሚሻሻል ነገር አይኖርም። በአረብ አገራት፣ ነገ ምርጫ ቢካሄድ፣ አሁን በስልጣን ላይ ካሉት አምባገነኖች የባሱ ገዢዎች ስልጣን ላይ ሊወጡ ይችላሉ...” ሲሉ ፅፈዋል ዘካሪያ (ከአስር ዓመት በፊት ያሳተሙት The Future of Freedom... ገፅ 22)።
የቁንፅል ዲሞክራሲ አጣብቂኝ
የፉክያማ እና የዘካሪያ ትንታኔ፣ ለአምባገነን መንግስታት የሚመች ሊመስል ይችላል። አምባገነኖች፣ ‘ዲሞክራሲ፣ ብጥብጥንና ትርምስን ይፈጥራል’ በማለት በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያገለግል መከራከሪያ ካገኙ ይጠላሉ? ነገር ግን፣ ሁለቱ ምሁራን እንደገለፁት፣ አምባገነንነትን የሙጢኝ ይዞ ከዲሞክራሲ መሸሽም መፍትሄ አይሆንም።
“ዲሞክራሲ በተስፋፋበት ዓለም፣ የዲሞክራሲ ጉዞን ለመግታት የሚንገታገቱ መንግስታት፣ የተቃወሰ ማህበረሰብን ይፈጥራሉ - በአረብ አገራት እንደምናየው። ሕዝቡ፣ በነፃነት እጦት ይማረራል። ምሬቱ ደግሞ ከወትሮው ይብሳል፤ ምክንያቱም ህዝቡ የሌሎች አገራትን ሁኔታ በነ ቢቢሲና ሲኤንኤን ይመለከታል” በማለት ዘካሪያ ፅፈዋል። የዲሞክራሲ መፈክርን በማንገብ የሚነሱ ተቃውሞዎችንና አመፆችን ማስቀረት ለአምባገነኖች ከባድ ነው - በሆስኒ ሙባረክና በጋዳፊ እንዳየነው።
እንዲያም ሆኖ፣ ይላሉ ዘካሪያ...
“እንዲያም ሆኖ፣ ወደ ዲሞክራሲ የተሸጋገሩ አገራት፣ በአብዛኛው የይምሰል ዲሞክራሲ ስለሚሆኑ፣ ተስፋ የለሽ ቅሬታን፣ ቅጥ የጠፋው ስሜትን፣ ግጭትንና አዲስ አይነት አምባገነንነትን ያስከትላሉ”።
‘ተስፋ አስቆራጩ አጣብቂኝ’ ይሉሃል ይሄ ነው። ወደ ዲሞክራሲ መሻገርም ሆነ፣ ዲሞክራሲን ለመግታት መንገታገት፣ ከቀውስ አያድንም።
ግን መውጫ ማምለጫ የሌለው አጣብቂኝ አይደለም። ለብቻው ተነጥሎ የተንጠለጠለ የዲሞክራሲ መፈክር፣ በጊዜያዊ ሆይሆይታ እልል ቢያሰኝም፣ ውሎ አድሮ ወደ ትርምስ አልያም ወደ አምባገነንነት ማምራቱ አይቀርም። ይህንን ማስቀረት የሚችሉ ቁልፎች ግን አሉ - የግለሰብ ነፃነት፣ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚና የሕግ የበላይነት በማለት ይዘረዝራሉ ዘካሪያ። ፉክያማ ከዘረዘሯቸው ሃሳቦች ጋር ይመሳሰላሉ።
በጎሳ ወይም በሃይማኖት የመቧደን አባዜን ማስቀረት የመጀመሪያው እርምጃ ነው የሚሉት ዘካሪያ፣ በጎሰኝነት ምትክ፣ በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ። በእርግጥም፤ እያንዳንዱ ሰው፣ አእምሮውን የመጠቀም፣ የማሰብና ሃሳቡን የመግለፅ፣ የየራሱን ማንነት (ሰብዕና) የመገንባት ነፃነት እንዳለው መገንዘብ፤ ዘረኝነትን፣ የሃይማኖት አክራሪነትን የፕሮፓጋንዳ አፈናን ለማስወገድ ያግዛል። አእምሮና ማንነት፣ የግል እንጂ የቡድን አይደለምና።
እያንዳንዱ ሰው፣ ሕይወቱን የመምራትና ንብረት የማፍራት ነፃነት እንዳለው መገንዘብም፤ ምን አይነት የኢኮኖሚ ስርዓት እንደሚያስፈልግ ለማወቅ ይረዳል። የግለሰብ ነፃነት፣ የንብረት ባለቤትነት መብትን ስለሚያካትት፣ ከዚህ ጋር የሚጣጣም የነፃ ገበያ ስርዓት ያስፈልጋል - ይሄ ሁለተኛው እርምጃ ነው።
ሦስተኛው እርምጃ፣ የህግ የበላይነት ነው። “የመንግስት ሥራ፣ የግለሰብ ነፃነትነትን ማስከበር ነው። መንግስት ከዚህ ስራ ውጭ እንዳሻው እንዳይፈነጭ፣ ስልጣኑን በህግ የተገደበ መሆን አለበት። የሕገመንግስት ትልቁ አገልግሎትም ይሄው ነው - የመንግስትን ስልጣን ይገድባል። መንግስት ለህግ ይገዛል፤ ሕግ አስከባሪ ብቻ ሳይሆን ህግ አክባሪም ይሆናል”... የህግ የበላይነት፣ ሲዘረዘርና ሲመነዘር ብዙ ቅርንጫፎች ቢኖሩትም፤ በአጭሩ ይህንን ይመስላል።
ሦስቱን እርምጃዎች (ምሶሶዎች) ያካተተ ሥርዓት፣ “ሕገመንግስታዊ ሊበራሊዝም” ሲሉ ይጠሩታል - ዘካሪያ።
ታዲያ፣ ሦስቱ ምሶሶዎች... ማለትም፣ የግለሰብ ነፃነት፣ ነፃ ገበያ እና የህግ የበላይነት... ከዲሞክራሲ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው የገለፁት ዘካሪያ፤ በዲሞክራሲ የሚመጡ ነገሮችም አይደሉም ይላሉ። ዲሞክራሲን ከእነዚህ “የሕገመንግስታዊ ሊበራሊዝም” ምሶሶዎች ጋር ካላጣመርነው፤ ዲሞክራሲን በቁንፅል ካንጠለጠልነው፤ ውሎ አድሮ፣ መፍረክረክ፣ መጋጨት፣ መተራመስና ወደ አምባገነንነት መመለስ የግድ ይሆናል። በየአገሩ እያየን ያለነውም ይህንኑን ነው - በአፍሪካ፣ በአረብ አገራት፣ ከዚያም አልፎ፣ ከቬኒዝዌላና ከብራዚል፣ እስከ ራሺያና ቱርክ፣ ከሃንጋሪና ፖላንድ እስከ ታይላንድና ኢንዶኔዢያ ወዘተ...።
እንዲህ አይነቱ አደጋ፣ ወደ ምዕራብ አውሮፓና ወደ አሜሪካ ዘልቆ ይሆን?
የአውሮፓና የአሜሪካ ቀውስ
ፍራንሲስ ፉክያማ እንደሚሉት፣ በአውሮፓ አገራት፣ በአሜሪካም ጭምር፣ በስልጣኔ አቅጣጫ ሲጓዝ የነበረው የፖለቲካ ስርዓት፣ ባለፉት 30 ዓመታት እየተሸረሸረና እየተዳከመ መጥቷል።
ፋሪድ ዘካሪያም እንዲሁ፣... በእርግጥም፣ የአሜሪካና የአውሮፓ አገራት አዝማሚያ ያሳስባል ይላሉ። ቢሆንም፣... ቢሆንም፣... “ከስጋት አልፎ፣ ለክፉ ይሰጣል? ከመብረክረክ አልፎ ይፍረከረካል?”
አሜሪካና አውሮፓ፣ ቀስ በቀስ የኢኮኖሚ እድገት እየራቃቸው፣ የድንዛዜና የቀውስ ፈተና እየደጋገመ ይጎበኛቸው ጀምሯል። የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ ልንለው እንችላለን። የቢዝነስ እንቅስቃሴን፣ በአላስፈላጊ የቁጥጥር መመሪያና ደንብ እየተበተቡ የኢኮኖሚ እድገትን እያዳካሙ ናቸው - የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት። ምርታማ ሰዎችን፣ በታክስ ጫና ደፍጥጠው፣ መፈናፈኛ አሳጥተዋል። የድጎማ መዓት እየፈለፈሉ፤ የመንግስትን የወጪ በጀት አለቅጥ ያሳብጣሉ። በታክስ የሚሰበሰበው ገንዘብ፣ የድጎማ ወጪዎችን መሸፈን ሲያቅታቸው፣ በየአመቱ በብድር ላይ ብድር እየጨመሩ፣ የእዳ ቁልል ተጭኗቸዋል። ለዚህ የድንዛዜና የቀውስ ጉዞ ለማስቆም፣ የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብና ተግባራዊ ለማድረግ የሚሞክር ባይጠፋም፤ ዳር ዳሩን ከመነካካት ያለፈ ሁነኛ ሃሳብ ይዞ ተግባራዊ የሚያደርግ ፓርቲ አልተገኘም።
ለዚህም ይመስላል፣ በአውሮፓና በአሜሪካ፣ የነባሮቹ ፓርቲዎች ተቀባይነት እየቀነሰ የመጣው። በነባሮቹ ምትክ፣ ወደ ዘረኝነት ያዘነበሉ ወይም ሶሻሊዝምን የሚሰብኩ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፣ ተደማጭነት እያገኙ ነው።
በቅርቡ በአውሮፓ የተካሄዱ ምርጫዎችን መመልከት ይቻላል። ከሁለት ሳምንት በፊት፣ በጀርመን በተካሄደ የክልል ምርጫ፣ ሁለቱ ነባር ፓርቲዎች እንደወትሮ፣ የለመዱትን ያህል ደምፅ አላገኙም። የዛሬ ሦስት ዓመት የተመሰረተ አዲስ ፓርቲ ግን፤ ከነባሮቹ ጋር ለመፎካከር የሚያስችል ድምፅ አግኝቷል። በፈረንሳይም፣ ከጥቂት ወራት በፊት የተካሄደው የክልል ምርጫ ላይ፣ የዘረኝነትና የሶሻሊዝምን ዝንባሌዎች አቀላቅሎ የያዘ ፓርቲ፣ ከሁለቱ ነባር ፓርቲዎች የማይተናነስ የድጋፍ ድምፅ አግኝቷል።
በአየርላንድ የተካሄደው ምርጫም፣ ከቀድሞው የተለየ ነው። ስልጣን ላይ የሚፈራረቁት ሁለቱ ነባር ፓርቲዎች፣ መንግስት ለመመስረት የሚያበቃ ድምፅ ሳያገኙ ቀርተዋል። በስፔንም እንዲሁ፣ ሁለት አዳዲስ ፓርቲዎች፣ የመራጮችን ድምፅ በመሻማታቸው የተነሳ፣ ነባሮቹ ሁለት ፓርቲዎች፣ አልቀናቸውም።
የአሜሪካ የምርጫ ዘመቻ ላይም፣ በትንሹም ቢሆን ተመሳሳይ አዝማሚያ እየታየ ነው። በእርግጥ፣ ነባሮቹን ፓርቲዎች የሚፈታተን፣ ሌላ ፓርቲ ጎልቶ አልወጣም። ነገር ግን፣ በአንድ በኩል ዶናልድ ትራምፕ፣ በሌላ በኩል ሶሻሊዝምን የሚሰብኩ በርኒ ሳንደርስ፣ ለሁለቱ ፓርቲዎች የጎን ውጋት ሆነዋል።
የእነዚህ ሁሉ ትርጉም ምንድነው? የአውሮፓና የአሜሪካ መንግስታዊ ስርዓቶች፣ ቀስ በቀስ እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን ያመለክታል ይላሉ ፉክያማ።
ዘካሪያ በበኩላቸው፤... አዎ፣ የአውሮፓና የአሜሪካ አዝማሚያ አሳሳቢ ነው። ነገር ግን፣ በቀላሉ መፍትሄ ሊበጅለት ይችላል፤ ከስጋት አልፎ፣ ለክፉ አይሰጥም፤ ከመብረክረክ አልፎ አይፈረካከስም ይላሉ።
መፍትሄ ቢያበጁለት ነው የሚሻለው። ለነሱ ብቻ ሳይሆን፤ ለኛም። አውሮፓና አሜሪካ ሲደናቀፉ፤ ሌሎቹ አገራት ይብስባቸዋል።

Read 5711 times