Saturday, 26 March 2016 11:12

‘ስድብ’ና ‘ጭብጫቦ’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…እኚህ ትረምፕ የሚሏቸው ሰውዬ እኛንም የአዛ ሰዉን ሁሉ ልክ ልኩን አጠጡት አይደል! ገንዘብና ስልጣን ምን የማይሠሩት ነገር አለ! እንደ ልብ ያናግራሉዋ! ይኸው…እኛ ዘንድ ወይ ‘ቦተሊከኛ’ ወይ ‘ዲታ’ ሆኖ ‘እንደ ልቡ የሚናገር’ መአት አይደል!
እናላችሁ… ጉልበተኛው ሰውዬ ነጩን ቤተመንግሥት የተቆጣጠሩ ጊዜ ዓለም ምን እንደምትሆን ጉድ አይተን፡፡ (ሀሳብ አለን…ቫለንታይን ዴይን እንደምናከብር፣ በታንክስ ጊቪንግ ዴይ በየሆቴሉ ዓለማችንን እንደምንቀጭ፣ ከእኛ ገና ይልቅ የእነሱን ‘ክሪስትማስ’ ከተማዋን በመብራት አንቆጥቁጠን እንደምናከብር ለሰውየው ይነገርልን፡፡ ድንገት ዙፋኑ ላይ የተቀመጡ እንደሆነ ሰዎቻችን ላይ እንዳይጨክኑ… ቂ…ቂ…ቂ…)
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የሚገርመው ነገር ደግሞ የደጋፊዎቻቸው ብዛት፡፡ ይቺ ስለእኩልነት ሲነሳ ስንት የሚደሰኮርላት አማሪካን፣ መብታችን ሲረገጥ ‘ትቆጣልናለች’ የምንላት አማሪካን እንዲህ አይነት ሰው ፖለቲካውን ሲቆጣጠሩት…አለ አይደል… ስለ ዓለም ያለንን አመለካከት ሁሉ ለመከለስ ይዳዳናል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…ብዙ ጊዜ ለጉልበተኞች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚጮሁትና የሚያጨበጭቡት ራሳቸው ስድባቸውን የጠጡትና ኩርኩም የቀመሱት ናቸው፡፡ ይኸው ቤን ካርሰን የሚሏቸው ሀብታምና የተከበሩ የህክምና ባለሙያ ስድባቸውን ሲጠጡ ከርመው በመጨረሻ ላይ “ትረምፕን ነው የምደግፈው!” አሉ አይደል! አፍሪካ አሜሪካውያንን “ወደ አፍሪካ ተመለሱ!” ያሉ ሰውዬ በእነዛው ተመለሱ በተባሉት ሰዎች ድጋፍ ሲያገኙ “አይ አማሪካን!” ያሰኛል፡፡
በቀደም ዕለት ‘ጥቁሩ’ የትረምፕ ደጋፊ ‘ነጩ’ን የትረምፕ ተቃዋሚ ሲደበድብ አያችሁልኝ አይደል! ምን ቤት መሆኑ ነው? ሰውየው ድንገት ስልጣን ከያዙ… በሁለተኛው ቀናቸው… “ይሄንን ሰውዬ በሉ በተገኘው መርከብ ላይ ጭናችሁ ወደ ሴራሊዮን መልሱልኝ…” ቢሉት ከመናደድ ይልቅ እንደምንስቅበት ይመዝገብልንማ፡፡ የምር… የሰውዬው ዘረኝነት በየንግግሮቻቸው እየታወቀ፣ ገና ስልጣን በር ላይ ሳይደርሱ “ወደመጣህበት ወደ አፍሪካ ተመለስ እየተባለ…” እንዲህ አይነት ማጨብጨብ ምንድነው!
 እናማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ለ‘ባለጊዜ’ የማጨበጨብ ነገር እዚህም በሽ ነው፡፡
ባለጊዜ ቦተሊከኛ አጃቢው መአት ነው፣
ባለጊዜ ሀብታም አጃቢው መአት ነው፣
ባለጊዜ ‘አርቲስት’ አጃቢው መአት ነው፣
ባለጊዜ ጋዜጠኛ…አጃቢው መአት ነው፣ (ልክ ነዋ…የጋዜጠኛ ባለጊዜ የለም ያለው ማን ነው!)
ልክ ነዋ…ዘንድሮ ‘ማጀብ’ እኮ የእምነት ምናምን ጉዳይ ሳይሆን የ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ ጉዳይ ነው፡፡
እናላችሁ…ይቺ ከባለጊዜ ጋር ‘ሰልፍ ማስተካከል’ የሚሏት ነገር አለች አይደል…ትረምፕ ለሚሏቸው ሰውዬ ከሚያጨብጭቡት መሀል…አለ አይደል… ይሄኔ “ጊዜው የእሱ ስለሆነ ሰልፍን ማስተካከል ነው…” የሚሉ መአት ይኖራሉ፡፡
በየቦታው ለጉልበተኞች የምናጨበጭብ፣ “በእርሶ መጀን” የምንል ሰዎች… አለ አይደል…ወይ እስከ ዶቃ ማሰሪያችን ድረስ የተነገረን፣ ወይ ኩርኩሙ ጭንቅላታችንን የዘይት ጉድጓድ ያስመሰለው መሆናችን የሚገርም ነው፡፡
እናላችሁ…እዚህም አገር የብዙዎቻችን ችግር ይኸው ነው፡፡ አለ አይደል…ነፋሱ እኛን አይነካን ይመስል፣ ጫፋችንን የሚነካን የሌለ እየመሰለን…ጊዜ እንደሚገለበጥ አለማወቅ ቅሽምና ነው፡፡
እኔ የምለው… ያ አዲስ አበባ ሰዉ ሁሉ ሲሰዳደብ ሰምቶ…“አዲስ አበባ ገዳይ ጠፋ እንጂ ሟችስ ብዙ ነበር…” ያለው ገጠሬ ትረምፕን ቢሰማ ምን ይል ነበር! “አይ ነዶ!…አይ ነዶ! ምን አለ ያለበት ቢያደርሱኝና በተወለወለ የወይራ ሽመል አንቆራጥጬ፣ አንቆራጥጬ…” ምናምን ባይል ነው! የምር እኮ እዚቹ ከተማችን ውስጥ “በወይራ ሽመል አንቆራጥጬ፣ አንቆራጥጬ…” የሚያሰኙ መአት አሉ፡፡ በዛ ሰሞን አንድ የሚኒባስ ሾፌር የሆነች ሴትዮን ይሰድባት የነበረው ስድብ… አለ አይደል…ለዕለታዊ ግጭት ሳይሆን፡ ለስር ነቀል ሪቮሊሲዮን የሚያስነሳ ነበር፡፡
እግረ መንገዴን…የታክሲ ሾፌርን ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ፡፡ መቼም የአንዳንድ ታክሲ ነጂዎች ነገር ግርም ይላል፡፡ ለምን እንደዛ እንደሚንቀዠቀዡ አንድዬ ይወቀው፡፡ እናላችሁ…በየቀኑ “ኧረ እባከህ ቀስ በል…” የሚለው የታክሲ ጭቅጭቅ የተለመደ ነው፡፡
አንድ ቄስ ይሞቱና መንግሥተ ሰማያት ይሄዳሉ። መንግሥተ ሰማያት ለመግባትም ይሰለፋሉ፡፡ ከፊት ለፊታቸው ትልቅ መነጽር ያደረገ፣ ቆዳ ጃኬትና ጂንስ የለበሰ ሰው ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ለሰውየው ጥያቄ ያቀርብለታል፡፡ “መንግሥተ ሰማያት ትገባ አትገባ እንደሆነ ለመወሰን ስለ ራስህ ንገረኝ፣” ይለዋል፡፡ ሰውየውም…
“ጆ እባላለሁ፣ የታክሲ ሾፌር ነኝ፣” ይላል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ሊስቱን ይመለከታል፡፡ ከዛም “ይህንን የሀር ካባና ይህን የወርቅ ዘንግ ያዝና መንግሥተ ሰማያት መግባት ትችላለህ፣” ይለዋል፡፡ የታክሲ ሾፌሩም እንደተባለው እየተንጎማለለ መንግሥተ ሰማያት ይገባል፡፡
ቀጥሎ የቄሱ ተራ ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም… “መንግሥተ ሰማያት መግባት አለመግባትህን ለመወሰን ስለማንነትህ ንገረኝ፣” ይላቸዋል፡፡ እሳቸውም…
“እኔ ቄስ ነኝ፣” ይሉትና ይመሩት የነበረውን የጸሎት ቤት ስም ይነገሩታል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም መዝገቡን ያገላብጥና…“ይህንን የጥጥ ካባና የእንጨት ዘንግ ያዝና መንግሥተ ሰማያት መግባት ትችላለህ፣” ይላቸዋል፡፡ ይሄን ጊዜ ቄሱ ይናደዳሉ፡፡
“ከእኔ በፊት የነበረው ሰው የታክሲ ሾፌር ሆኖ የሀር ካባና የወርቅ ዘንግ ሰጠኸው፡ እኔ ቄስ ሆኜ እንዴት የጥጥ ካባና የእንጨት ዘንግ ትሰጠኛለህ!” ይለዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ምን ብሎ ቢመለስለት ጥሩ ነው…
“አንተ እየተጎተትክ ስትሰብክ ሰዉ ሁሉ እንቅልፍ ይወስደዋል፡፡ እሱ ግን እየፈጠነ ሲያሽከረክር ሰው ሁሉ ይጸልያል፡፡” አሪፍ አይደል፡፡
እናላችሁ…የስድብ ነገር ካነሳን አይቀር…አለ አይደል… እዚሀ አገር ስድብ ማናደዱ ቀረ ልበል! ይሄ የወረዳ በጀት የሚያወጡ መኪኖች የሚያሽከረክሩት ሰዎች ሁሉ ሲሳደቡ ስትሰሙ “ገዳይ ጠፋ እንጂ…” እንዳለው ገጠሬ የሚቆረቁረው ጠፋ ነገር ያሰኛችኋል። ከጾሙ ብዛት “ኧረ ይሄን ሰው በልክ አድርግ በሉት!” የሚባለው ሰውዬ በጾሙ መሀል ሙልጭ አድርጎ ሲሳደብ ትሰሙታላችሁ፡፡ አንድ ጊዜ የሆነ የኃይማኖት አባት “እሱንስ አናቱን ማለት ነበር!” ሲሉ ይሄ ጸሀፊ ሰምቷል፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…“ሰምቻለሁ” ከማለት ይልቅ “ይሄ ጸሀፊ ሰምቷል” ሲባል የሆነ ከበድ ያለ ነገር አይመስልም! አሀ…ጸሀፊዎችም ራሳችን ትከሻ ላይ ኮከብ የምንጭንባቸው ዘዴዎች አሉና!)
እናላችሁ…የስድብ ሌላው መንገድ እኮ ማጣጣል ነው፡ ፊት ለፊት ሳይሳደቡ የተሠራውን ሥራ በማሳነስ በተዘዋዋሪ ስድብ የሚሰነዝር መአት ነው፡፡ ትረምፕ የሚሏቸውን ሰውየው አይታችሁ እንደሆነ የሁሉንም መልካም ሥራ ሲያጣጥሉ ነው የከረሙት፡፡ ማኬይን የሚባሉትን ሰውዬ እንኳ…“እና በጠላት ቢታሰር ፈሪ ስለሆነ ነው…” ምናምን ብለዋቸው የለ! የኦባማን የልደት ሰርተፊኬት “የውሸት መሆኑን ከታማኝ ምንጭ ሰምቻለሁ…” ምናምን ብለዋል፡፡
እናላችሁ…እንደ ትረምፕ የሌላውን ጥሩ ተግባር ማጣጣልና መልካም ስምን ማበላሸት የለመድናት ነገር ናት፡፡ አይደለም አሁን ያለነው ከስንት መቶ ዓመታት በፊት የነበሩት ወገኖቻችን ሁሉ አንዱ ወገን ሲያወድሳቸው ሌላኛው ወገን ሲያጣጥላቸው ትሰማላችሁ፡፡
ከትረምፕ አይነት ተሳዳቢና “ወደመጣችሁበት ተመለሱልን” ተብለውም ከሚደግፏቸው ሰዎች አይነት ‘አጨብጫቢዎች’ ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 4451 times