Monday, 15 August 2016 09:32

በየአመቱ 66ሺህ ሴቶች በማህጸን በር ካንሰር ይያዛሉ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

   “አንዲት በእድሜዋ 26 አመት የሚሆናት ሴት ለምርመራ መጣች።የሶስት ልጆች እናት ናት። ሶስተኛውን ልጅ ከወለደች ገና ሁለት ወርዋ ነው። ምርመራ ለማድረግ ስንሞክር አስደጋጭ ነገር ነበር የገጠመን። የማህጸን በር የካንሰር ሴል ተስፋፍቶ ይታያል። ፈሳሽ ለመውሰድ አልቻልንም። ትደማለች። ልታስነካንም አልቻለችም። በጣም ተሰቃየች። ምን ማድረግ ይቻላል? እኛ ልናክማት አልቻልንም። ደረጃው በጣም አድጎአል። ከፍ ወዳለ ሆስፒታል ልከናታል። ግን ሕመሙን ለማጥፋት ወይንም ሙሉ ለሙሉ ለማዳን ሳይሆን ቢያንስ ሕይወቷ እስከአለ ድረስ ለማቆየት ይጥሩላታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በእርግጥ በወጣትነት እድሜያቸው ይህ ምልክት የታየባቸው ሌሎችም የነበሩ ሲሆን ይህ ግን በቅርብ ቀን ውስጥ ያጋጠመን በጣም የሚያሳዝን ነው።”
 ሲ/ር ዘውዴ አበበ በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ የአዲስ አበባ ሞዴል ክሊኒክ አስተባባሪ
በኢትዮጵያ ባለፈው ሰሞን ማለትም እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ጁላይ 25/2016 የተካሄደው የማህጸን በር፣ የጡትና የፕሮስነት ካንሰርን የመከላከል ጉባኤ እንደጠቆመው በአፍሪካ በየአመቱ 70.000/ሰባ ሺህ ያህል ሰዎች ከካንሰር ጋር በተያያዘ ሕመም ለሕልፈት ይዳረጋሉ። በኢትዮጵያ ደግሞ በየአመቱ ወደ 66.000/ያህል ሴቶች በማህጸን በር ካንሰር ይያዛሉ።ለዚህም እንደምክንያት ከሚቆጠሩት መካከል የመረጃ እጥረት ፣የመሰረተ ልማት አለመስፋፋትና የመድሀኒት አቅርቦት ችግር ሲሆን የግንዛቤ እጥረት መኖሩም በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት በማስከተል ላይ ነው። በህብረ ተሰቡ ዘንድ ቅድመ ምርመራና የመከላከል ስራዎች የሚሰራበት ልምዱና አመቺ ሁኔታው ባለመስፋፋቱ ለበሽታው መስፋፋትም ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ተጠቁሞአል። የማህጸን በር የጡት እና የፕሮስት ካንሰርን ለመከላከል አስፈላጊው ሁሉ እንደሚደረግም ጉባኤው መክሮአል።
የማህጸን በር ካንሰርን በመከላከል ረገድ በኢትዮጵያ ያለው አሰራር ምን ይመስላል ስንል ወደቤ ተሰብ መምሪያ አዲስ አበባ ሞዴል ክሊኒክ አምርተን ነበር ። በዚያም ያገኘናቸው ዶ/ር አሸናፊ ምትኩ በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ የአዲስ አበባ ሞዴል ክሊኒክ ሜዲካል ዳይሬክተር እና ሲ/ር ዘውዴ አበበ በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ የአዲስ አበባ ሞዴል ክሊኒክ አስተባባሪ ናቸው።
 “የማህጸን በር ካንሰር አይነቱ ብዙ ሲሆን አንዳንዱ መንስኤው የሚታወቅ አንዳንዱ ደግሞ መንስኤው የማይታወቅ ነው። በአገራችን ሴቶችን በብዛት የሚያጠቃውና ገዳይ የሆነው የማህጸን በር ካንሰር ግን CERVICAL CANCER (HPV) የተባለው ቫይረስ መንስኤው እንደሆነ በሳይንስ የተረጋገጠ ነው። ይህ ቫይረስ የማህጸን በር ካንሰር ብቻ ሳይሆን ከሌላ የብልት አካል ማለትም ከወንድ ብልትና ከሴት ብልት እንዲሁም ከሰገራ መውጫ አካባቢ ለሚነሱ የካንሰር አይነቶች መንስኤ መሆኑ ታውቆአል።”
ዶ/ር ካሳሁን ኪሮስ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት
በቅድሚያ የምናስነብባችሁ ሲ/ር ዘውዴ አበበ አስተባባሪ የሰጡትን ማብራሪያ ነው።
 “በክሊኒኩ የሚሰራው በስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ዙሪያ ያሉ ምርመራዎችና ሕክምና ነው። ይህም ማለት የወሊድ መከላከያ ዘዴዎችን ፣የአጭር ጊዜ ፣የረጅም ጊዜና ቋሚ የእርግዝና መከላከያዎችን ፣የአባላዘር በሽታ ምርመራና ሕክምና ፣የማህጸን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራና ሕክምና እንሰጣለን። እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን ምርመራ በማድረግ ሕክምና ከመስጠት ባሻገርም በሕግ ስንጠየቅ ምስክርነት እንሰጣለን።” ብለዋል።
በተለይም ከማህጸን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ ጋር በተያያዘ የሚከተለውን ብለዋል ሲ/ር ዘውዴ ፡-
 “የማህጸን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ ወሲባዊ ግንኙነት የጀመሩ ሴቶች ማህጸን ጫፍ ላይ የካንሰር ሴል አለ ወይንስ የለም የሚለውን የምንመለከትበት የምርመራ ሂደት ነው። ማንኛዋም ሴት የወሲብ ግንኙነት ማድረግ ከጀመረች በሁዋላ ምርመራውን ማድረግ ትመከራለች። በእኛ አገር በነበረው ልምድ ግን ይህንን ማድረግ ብዙም የሚሞክር ሰው የለም። ወደሐኪም ቤት የሚኬደው የህመም ምልክት ሲታያ ወይንም ደግሞ ፈሳሽ ሲበዛ የመሳሰሉ ችግሮች ካልተከሰቱ በስተቀር ወደሕክምና የሚሔድ ብዙም የለም። ነገር ግን ያልታወቀው ነገር የህመም ምልክት የሚያሳየው ካንሰሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ እንጂ አስቀድሞ ምንም የህመም ስሜት አይኖረውም። ስለዚህ ያ ሳይሆን በፊት ማንኛዋም ወሲባዊ ግንኙነት የጀመረች ሴት ከ4-5 አመት ጊዜ ውስጥ በሐኪም መታየት እጅግ ጠቃሚ ነው። ከዚህም በታች በየሁለት እና ሶስት አመት ጊዜ ውስጥ መመርመር ቢቻል ጥሩ ይሆናል። ካንሰር እየተሰራጨ ወደ ማህጸን የሚሄደው ከማህጸን በር ካንሰር በመነሳት ነው።ስለዚህም ምርመራው የሚያግዘው የካንሰር ሴል ምልክት ካለ ወደማህጸን ውስጥ ሳይስፋፋ በጊዜ ለመቅጨት እና ሴትየዋን ከአደጋ ለመጠበቅ እንዲቻል ነው።”
ዶ/ር አሸናፊ ምትኩ ሜዲካል ዳይሬክተር ስለታካሚዎች ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጸዋል።
“ለምርመራ የሚመጡ ሰዎች በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። አንዳንዶች የተለያየ ህመም ስሜት ተሰምቶኝ መጣሁ ይላሉ። ይህ እንግዲህ ከማህጸን ወይንም ከመውለድ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ነው። ሌሎች ደግሞ ...አ.አ.አይ ...ምንም ሕመም አይሰማኝም። ግን ለመታየት መጣሁ ይላሉ። በአይነታቸውም በተለያየ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እድሜ ያቸውም እንዲሁ ከወጣት እስከ ትልልቅ እድሜ የደረሱ ሲሆኑ እኛም እንደየአመጣ ጣቸው ምርመራ እና ሕክምና በማድረግ እንሸኛቸዋለን። ከእኛም በላይ ከሆነ ወደሆስ ፒታል እናስተላልፋቸዋለን። በእርግጥ ምንም የህመም ስሜት ሳያስገድዳቸው ለቅድመ ካንሰር ምርመራ የሚመጡት ሰዎች ውጤት ሁል ጊዜ እንደጠበቁት አይሆንም። አንዳንድ ጊዜ ሲመረመሩ የካንሰር ምልክቱ ይገኝና ያስደነግጣቸዋል። እኛ ግን መደንገጥ አይገባቸውም ነው የምንለው። ምክንቱም አስቀድመው በመምጣታቸው ሁኔታው ከሕክምና በላይ ሳይሆን ስለደረሱ በተገቢው መንገድ ታክመው ስለሚድኑ ጥሩ እርምጃ እንደወሰዱ እንነግራቸዋለን።” ነበር ያሉት።
የማህጸን በር ካንሰር የሚከሰተው Human papillomavirus (HPV) በሚባለው የቫይረስ አይነት ነው። ይህ ቫይረስ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታይና ከብዙዎቹ ቫይረስ አይነቶች አንዱ ነው። ይህ ቫይረስ ምናልባትም ከመቶ በላይ የሚቆጠሩ አይነቶች ሲኖሩት ከእነዚህም ወደ 13 የሚደርሱት ካንሰርን ለማምጣት ምክንያት ሆናሉ። የሚተላለፈው በአብዛኛው በወሲባዊ ግንኙነት ምክንያት ነው። የማህጸን በር ካንሰር በአለም ላይ ሁለተኛው በሴቶች ላይ በስፋት የሚታይ ሲሆን በአለም በግምት በአመት ወደ 445.000/አዳዲስ ህሙማን እንደሚታዩ የ2012/የአለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያሳያል። በ2012 በተጨማሪ እንደተገለጸው 270.000 ሴቶች በማህጸን በር ካንሰር ምክንያት የሞቱ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ 85 ኀ የሚሆኑት በታዳጊ ሀገራት የሚኖሩ ናቸው። የማህጸን በር ካንሰር የሚያመጡት የ HPV ቫይረስ አይነቶች ቁጥር 16 እና 18 ናቸው። ሴቶች እስከተወሰነ እድሜ ክልል በተለይም የወሲብ ግንኙነት ከመጀመራቸው በፊት ቫይረሱ ለወደፊቱ እንዳይከሰትባቸው ክትባት መስጠት በአለም ላይ ተጀምሮአል።
ሴቶችን ይጎዳሉ ተብለው የሚታወቁ የካንሰር አይነቶች የማህጸን በር ካንሰር ፣ከሴት ዘር ፍሬ ማፍለቂያ እንዲሁም ከማህጸን ግድግዳ የሚነሳ ካንሰር ነው።
 “የተገኙት የካንሰር ክትባቶች ለሁለቱም ጾታዎች ወንድና ሴት ሊሰጡ የሚችሉ ናቸው። ክትባቶቹ ሰዎች ለቫይረሱ ከመጋለጣቸው ማለትም የግብረስጋ ግንኙነት መፈጸም ከመጀመራቸው በፊት ቢሰጥ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ምክንያቱም ቫይረሱ በግብረስጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚተላለፍ የአባላዘር በሽታ በመሆኑ ነው። ወንዶች ክትባቱን ካገኙ ቫይረሱን ወደ ሴቶች ማስተላለፍ አይችሉም ማለት ነው። እስከአሁን ባለው አሰራር ግን በብዙ አገሮች ክትባቱ ለወንዶች የማይሰጥ ሲሆን ሴቶች ግን በእድሜያቸው ከ9-26 አመት ባለው የእድሜ ክልል እንዲወስዱ የሚደረግበት ሁኔታ አለ።...”
 ዶ/ር ካሳሁን ኪሮስ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት
ወደ ሲ/ር ዘውዴ ስንመለስ የታካሚዎችን ልምድ ይገልጹልናል።
“ እስከቅርብ አመት ድረስ ማለትም የዛሬ 3/አመት ገደማ ያሉን ታካሚዎችን ስንመለከት በእድሜያቸው ትልልቅ የሚባሉ ምናልባትም ከ45 አመት እድሜ በላይ ያሉ ታካሚዎችን ነበር የምናስተናግደው። የዚህም ምክንያቱ ካንሰር ተብሎ ሲታሰብ የትልልቅ ሰው በሽታ ተደርጎ ይገመት ስለነበር ነው። አሁን ግን ዘመኑ እየተለወጠ ነው። በመገናኛ ብዙሀን የሚነገሩ መረጃዎችን በማድመጥ እንዲሁም በኢንተርኔት እየገቡ በማንበብ ህብረተሰቡ የተለያዩ መረጃዎችን ስለሚያገኝ የተመርማሪውን ቁጥር ከፍ ከማድረጉማ በላይ ወጣቶችም ወደምርመራው እንዲመጡ አስችሎአቸዋል። በእርግጥ አሁንም በቂ ቁጥር ነው አንልም። ምናልባት በወጣት እድሜ ክልል ያሉት ተመርማሪዎች ብዛት እስከ 20 ኀ ሊደርስ ይችላል። ነገር ግን አሁንም ወደሕክምና መምጣት ተለምዶአል የሚያሰኝ ደረጃ ደርሰናል ልንል አንችልም። መታወቅ ያለበት ካንሰር የትልቅ ሰው በሽታ ተደርጎ መታየት የለበትም። በተለይም የማህጸን በር ካንሰርን ስንመለከት ወጣቶች ተጋላጭ የሚሆኑባቸው ምክንያቶች አሉ። ለምሳ ሌም ከተለያዩ ወንዶች ጋር ወሲብ ግንኙነት መፈጸም... እንዲሁም የወንድ ጉዋደኞችም እንደዚሁ ከተለያዩ ሴቶች ጋር የወሲብ ግንኙነት የሚፈጽሙ ከሆነ ለአባላዘር በሽታ የመጋለጥና ለቫይረሱ መዛመት ምክንያት ሊሆን ይችላል። Human papillomavirus (HPV) ልክ እንደ ኤችአይቪ ቫይረስ በወሲብ ጊዜ ስለሚተላለፍ ለማህጸን በር ካንሰር ተጋላጭነትን ይጨምራል። ስለዚህ ማንኛዋም የወሲብ ግንኙነት የጀመረች ሴት እድሜ ሳይወስናት በተወሰኑ አመታት ልዩነት ቅድመ ካንሰር ምርመራ ብታደርግ ይመከራል።

Read 4940 times