Sunday, 21 August 2016 00:00

‘ያላየነው ጉድጓድ…’

Written by 
Rate this item
(13 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰዉ ክፉ ሆኗል…ምናምን ስንል…አለ አይደል… ‘ጨለምተኛ’ ምናምን የሚባልበት ዘመን ነበር፡፡
እዛ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ተጣራ
እዚህ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ወይ አለው
ጎበዝ ጠንቀቅ በል ይህ ነገር ለእኛ ነው
የሚሏት መአት ጊዜ የምንጠቅሳት ስንኝ ዘንድሮም…ድምጿን ጨምራ እያቃጨለች ነው፡፡
እኔ የምለው…ክፋት እንዲህ በእግረ ሙቅ ጠፍሮ የያዘን፣ የሆነ በጨረር ምናምን የላኩብን ነገር አለ እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ…የክፋታችን ልክ እኮ ወሰንም እያጣ ነው፡፡
የዚህ የእንጀራና ጄሶ ቅልቅል ነገር እኮ…አለ አይደል…‘ትልቁን ስዕል’ የሚያሳይ ነው፡፡ ይሄ አላግባብ ትርፍ የማግኘት ምናምን አይነት ነገር ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም…አለ አይደል… የክፋት፣ የሰብአዊነት ማጣት፡ የሞራል ዝቅጠት ምልክት ነው።
የምግብ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ… ሴትዮዋ ምግብ ቤት ገብታ አሳ ታዛለች፡፡ እናላችሁ…አሳው በደንብ ሳይበስል ይመጣላታል፡፡ በለብ ለብ ነው የተሠራው፡ ኃላፊው ይጠራልኝ ብላ ይጠራላታል፡፡ ሰውየውንም…
“ይሄ አሳ ሲያዩት አያምርም፣” ትለዋለች፡፡ ኃላፊው ምን ቢላት ጥሩ ነው…
“እመቤቴ፣ ለአሳው እዘኚለት እንጂ…አንቺም ሞተሽ እንዲህ ለብ ለብ ቢያደርጉሽ አታምሪም ነበር፣” ብሏት አረፈ፡፡
እግረ መንገዴን…ከተማ ውስጥ አንዳንድ ቦታ… ‘አንቺም ሞተሽ እንዲህ ለብ ለብ ቢያደርጉሽ አታምሪም’ አይነት ስሜት የሚያሳዩ አስተናጋጆች አሉ፡፡ ኮሚክ እኮ ነው…“ይሄ ምግብ በምን የሚሠራ ነው?” ስትሉ… “ቆይ ጠይቄ ልምጣ…” እያሉ ማድቤት የሚመላለሱ አስተናጋጆች ስታዩ አስቸጋሪ ነው፡፡
እናማ…‘ያላየነው ጉድጓድ እየዋጠን’ ተቸግረናል፡፡
መንገዱ ‘ወርቅ ነው፣ ጨርቅ ነው’ ምናምን ብለን ስንሄድ ያላየነው ጉድጓድ ውስጥ ዘው ማለት ዕጣ ፈንታችን አይነት ነገር ሆኗል፡፡
ጉዳይ ለማስፈጸም ከዚህ ቢሮ እዛኛው ቢሮ ስንንከራተት ‘ያላየነው ጉድጓድ’ ይደነቀርብናል፡፡
“አንተ እኮ ብትባበር…”
“ዝም ብለህ በባዶ ሜዳ ከምትሮጥ…”
ምናምን እየተባለ ‘ቋንቋው’ ከእኛ እየቀደመ አፍ መፍቻ ቋንቋችን እንኳን አልገባን እያለ አስተርጓሚ እያስፈለገን ነው፡፡ “ግዴታዬን ተወጥቻለሁ፣ መብቴ ይከበርልኝ…” ማለት የ‘ስታንድ አፕ ኮሜዲ’ ጸሁፍ ምናምን እየመሰለብን… አለ አይደል… “እውነቱን እኮ ነው…” ከመባል ይልቅ “ድንቄም…” እየተባልን መንገዳችን ጉድጓድ በጉድጓድ ሆኗል፡፡
እናማ…‘ያላየነው ጉድጓድ እየዋጠን’ ተቸግረናል፡፡
ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ‘ጥሬና ብስሉ’ እየተቀላቀለ የእኛንም ስሜቶች እያደበላለቀብን ግራ ገብቶናል፡፡ “መልካም ወዳጄ ነው፣ ለችግር ጊዜ ይደርስልኛል፣ ጉልበተኛ ቢያጠቃኝ የብረት አጥር ይሆነኛል፣ ቢከፋኝ ደገፍ ብዬ የማለቅስበት ትከሻ ይሆነኛል…” ያልነው ሰው ሳናስበው ‘አያ ጅቦ’ አይነት ነገር ይሆንብንና ከእሱ መሸሹ ሌላ ‘የህይወት ጥሪ’ ምናምን ይሆናል፡፡ በችግሩ ጊዜ ውለታ ውለንለታል፣ አይዞሀ ባይ ወዳጅ፣ ዘመድ ያጣ ጊዜ ከጎኑ ቆመናል…” ምናምን ያልነው ሰው ‘ዋናው ችግራችን’ ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡
እናማ…‘ያላየነው ጉድጓድ እየዋጠን’ ተቸግረናል፡፡
ስሙኝማ…አሜሪካኖቹ በፕሬዝዳንቶቻቸው፣ በፖለቲከኞቻቸው፣ በሙያተኞቻቸው ላይ ቀልደው የሚበቃቸው አይመስሉም፡፡…ይኸው ሰሞኑን በትረምፕ ላይ የሚጻፍባቸውን እናይ የለ! እናላችሁ… ሦስት የቀዶ ጥገና ሀኪሞች ስለ ችሎታቸው ራሳቸውን ከፍ እያደረጉ ይናገራሉ፡፡ አንደኛው የቀዶ ጥገና ሀኪም…
“አንድ ሰው ድንገት በባቡር ሀዲድ ላይ ወደቀና ባቡሩ በላዩ ላይ ሄዶበት ሁለት እግሮቹ ከጉልበቱ በታች ተቆረጡ፡፡ እነሱን በቀዶ ጥገና አስተካክዬለት የኦሎምፒክ ማራቶን አሸናፊ ሆነ…” አለ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ…
“አንዲት ሴትዮ ከመኪና መስታወት ጋር ትጋጭና ፊቷ ሙሉ ለሙሉ ይበላሻል፡፡ የተጎዳው ፊቷን በቀዶ ጥገና ካስተካከልኩላት በኋላ የሚስ አሜሪካን ውድድር አሸንፋለች…” ይላል፡፡ ሦስተኛው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“አንዱ ሰው በድንገት አውሮፕላን ሞተር ውስጥ ገብቶ ሰውነቱ እንዳለ ይበታተናል፡፡ ከዛም ከአእምሮው ምስር የምታክል ቁራጭ …አገኘሁና ወደ ላቦራቶር ወስጄ እንደገና ሙሉ ሰው አደረግሁት፡፡ አሁን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኗል…”   ቂ…ቂ…ቂ…  ትረምፕ የሚሏቸው ሰውዬ ይሄንን አልሰሙም እንዴ!  
እናማ…አገሩ ሰው የሌለበት ምድረ በዳ የሆነ ይመስል ፎካሪና ጉራ ቸርቻሪ በዝቷል፡፡
እናማ…‘ያላየነው ጉድጓድ እየዋጠን’ ተቸግረናል፡፡
አንድ የቴክሳስ ሰው እንግሊዛዊው ላይ ቴክሳስ በጣም ትልቅ ግዛት ስለመሆኗ እየተነሰነሰበት ነበር… “ሰኞ ጠዋት ምስራቅ ቴክሳስ ውስጥ ባቡር ትሳፈራለህ፣ በምዕራብ አቅጣጫ ሙሉ ቀን ትሄዳለህ፣ ሌሊቱንም ስትሄድ ታድራለህ፣ በማግስቱ ጠዋት ገና ከቴክሳስ አትወጣም…” ይለዋል፡ እንግሊዛዊው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“የእንግሊዝ ባቡሮችም እንዲህ ቀርፋፋ ናቸው…” አለውና አረፈው፡፡
እናማ…ለበጎ ብለን የተናገርነው ነገር፣ ለጨዋታ ብለን የቀለድነው ቀልድ፣ ለመተባበር ብለን ያቀረብነው ሀሳብ ጅራትና ቀንድ እየተተከለላቸው የምንለውን የሚሰማን ማግኘት የሰማይ ያህል ርቆናል፡፡ መንግሥተ ሰማያት የሚያደርስ ግንብ እየገነባን መቅሰፍት የወረደብን ይመስል አንዳችን የምንለው ለሌላኛችን ‘አልገባ’ እያለ… ሁሉም ተናጋሪ ሆኖ አንድም አድማጭ እየጠፋ ነው፡፡ አንዳንዴ ነገራችን የሞኝ ቢያስመስለንም ያን ያህል ሞኝነት እንኳን የለብንም፡ እናውቃለን፣ ግን ያላወቅን እንመስላለን…  ማወቅ ሁልጊዜም ያስከብራል ማለት አይደለምና፡፡
እሱስ ውሸቴን ነው
እኔም ብቻ አይደለሁ
በጣም እናውቃለን ሁላችን ሁላችን
አውቀን ባንፈጽምም
አውርተን ባንሠራም
ሰምተን ባናሰማም
በጣም እናውቃለን ሁላችን ሁላችን፣
የምትል የፈቃደ አዘዘ ግጥም አለች፡፡ እናማ… በባዶ ሜዳ ሲፎከርና፣ ጉራ ሲነዛ ዝም ብለን ስናዳምጥ ሞኝ መስለን ከታየን ‘ታሪካዊ’ ስህተት ነው፡፡
እናማ…እንዲህም ሆኖ ‘ያላየነው ጉድጓድ እየዋጠን’ ተቸግረናል፡፡
የሆነ ግንባታ ላይ የሚሠራ ሰው “የእኔን ያህል ጠንካራ ሰው የለም…” ምናምን እያለ የሥራ ባልደረቦቹ ላይ ይፎክራል፡፡ በተለይም አንድ በዕድሜ የገፉ ባልደረባውን ሁልጊዜ ይጨቀጭቃቸዋል፡፡ ሰውየውም ፉከራው እጅ፣ እጅ ይላቸውና…
“እሺ ከእኔ በላይ ጠንካራ ከሆንክ በገንዘብ እንወራረድ…” ይሉታል፡፡ ሰውየው ይስማማል፡፡ ሰውየውም…
“እኔ በዚህ ጋሪ ጭኜ እዛ ማዶ የማደርሰውን ማንኛውንም ነገር አንተ ጋሪው ላይ ጭነህ እየገፋህ መልሰህ ማምጣት አትችልም፣ ለዚህም የሳምንት ደሞዜን አስይዛለሁ ይላሉ…” ጉረኛውም…
“ሽሜው ትንሽ ነካ ሳያደርገው አይቀርም፡፡ እስማማለሁ…” ይላል፡፡
ከዛ ሰውዬው ጋሪውን ቀረብ አደረጉና ጉረኛውን ምን ቢሉት ጥሩ ነው… “በል ጋሪው ላይ ውጣ…” አሪፍ አይደል! ሰውየው ጋሪው ላይ ከሆነ እንዴት አድርጎ መልሶ እየገፋ ሊያመጣ ይችላል!
እናማ… ዝም ብሎ መፎከር፣ አገሩ ሰው የሌለበት ይመስል ጉራ መንዛት አሪፍ አይደለም፡፡ ብልጦቹ በሙሉ ተሰደው ሞኞች ብቻ ቀሩ ተብሎ ሹክ ተባለብን እንዴ!
እናማ…እንዲህም ሆኖ ‘ያላየነው ጉድጓድ እየዋጠን’ ተቸግረናል፡፡
ስሙኝማ…የሞኝነት ነገር ከተነሳ ይቺን ስሙኝማ…አንዱን ሰውዬ ማጅራት መቺዎች ከበው ሊዘርፉት ሲሉ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ልቡ እስኪጠፋ ይቧቀሳቸዋል፡፡ ከዛም ያሸነፉትና የገንዘብ ቦርሳውን ወስደውበት ሲከፍቱት ሁለት ዶላር ብቻ ያገኛሉ፡፡ ይሄኔ ተደንቀው…
“እንዲህ እስክትገጣጠብ የተቧቀስከው ለሁለት ዶላር ብለህ ነው!” ይሉታል፡፡ ሰውየው ምን አለ መሰላችሁ…
“እፎይ፣ ካልሲዬ ውስጥ የደበቅሁትን ሁለት መቶ ዶላር ታገኙብኛላችሁ ብዬ ፈርቼ ነበር…” ብሏቸው አረፈ፡፡  
‘ከማይታይ ጉድጓድ’ ይሰውራችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6508 times