Sunday, 09 October 2016 00:00

የህዝብ ጥያቄ፤ “የሞተር” እንጂ “የጎማ” ለውጥ አይደለም!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

    ኢትዮጵያ ውስጥ እንቅልፍ ከጠፋ ከራረመ። ከአድማስ ባሻገር የሚያይ አይን ጨላለመ፡፡  ልብም በስጋት አፈገፈገ፡፡ “ነገ” የሚለውን ቅርብ ቀን “እንዲህ ይሆናል!” ለማለት የተደረደሩ ጡቦች ረገፉ፤ ሁሉም ነገር ደቀቀ፤ላመ ፈሰሰ! ሀገር በምን ላይ ትቁም? ብንል ታሪክ ተንሸራትቷል፣ኪዳን ፈርሷል … ስለዚህ ቀጣዩ ቀን ምን ይመስላል? ምን ይሆናል? መንግስት የአንድ ሰውን ያህል እንኳ ኃላፊነት ያለበት አይመስልም፡፡ እንዴ? … መሪ‘ኮ ከተቃዋሚም ሆነ፣ ከህዝብ የራቀና የጠለቀ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከሌላው በተለየ ሁኔታ ህዝቡን የመጠበቅ ትልቅነት ኃላፊነት!! መንግስት ግን ያንን እየተወጣ አይደለም፡፡
 በደርግ ሙጣጭ ዘመን ተማሪ ሆኜ፣ብርጋዲየር ጀኔራል ፈለቀ እሸቴ፤ ብላቴ አየር ወለድ ማሰልጠኛ ጣቢያ መጥተው ንግግር ያደረጉ ዕለት፣የተማሪው የማያቋርጥ ረጅም ጭብጨባ፣ ዛሬም ድረስ በልቤ ገደል ውስጥ ያስተጋባል፡፡ እዚያ ድምፅ ውስጥ የተንጠለጠለ ሌላ ድምፅ ነበር … “ነገስ ምን ይሆናል?” የሚል፡፡ … ዛሬም የሚሰማኝ ያ ድምፅ ነው፡፡ ለዚህ ነው የገጣሚ መስፍን ወንድወሰን ግጥም ልቤን የጎተጎተው፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“እንቧ በይ … እንቧ በይ” ነበረ ዘፈኑ
ለፉከራ ሲመች ሲያስተማምን ቀኑ፡፡
ዛሬ ግን የኔ ዓለም
የሚጨበጥ የለም
ነገ አይገመትም ከርሞ አይተነበይ
እንዲያው ዝም ብለሽ እንጃ በይ … እንጃ በይ …
ግራ የመጋባት ዜማ፣ የራዕይ መፍረስ ድምጸት ነው የሚያስተጋባው፡፡ ከአድማስ ወዲያ የሚታይ ስዕል የለም፡፡ ነባሩ ስዕል እየፈረሰ ነው፡፡ “ምናልባት?” የሚለው ጉጉታችን እንኳን፣ አሁን ሙሉ ለሙሉ አፈር ቅሟል - በተለይ ሰሞኑን! …
ቀደም ሲል አንዳንድ የተስፋ ምልክቶች፣ የምኞት ካቦችም ነበሩ፡፡ በተለይ መሪዎቻችን ዕድሜያቸው ሲገፋ፣ በስሜታዊነትና ባለመብሰል የፈጸሟዋቸውን ስህተቶች እያቃኑ ይመጣሉ የሚል ጉጉት የነበረን ጥቂት አልነበርንም፡፡ … በተለይ እኔ ጥቂት ትዝታዎች ነበሩኝ፡፡ ተማሪ እያለሁ፣ ከብላቴናው ዘመቻ በኋላ አዲሶቹ የኢህአዴግ ሰዎች የጫሩብኝ … ተስፋ ነበር፡፡ በጊዜው የቀበሌ አመራሮች ጠርተውኝ፣ “ግጥም እንድትፅፍልን እንፈልጋለን” ሲሉኝ፣ ለኢህአዴግ እንደማልፅፍና ፍቃደኛ እንዳልሆንኩ ስነግራቸው፣በፍቅርና በነፃነት “ያንን አለማድረግ መብትህ ነው!” ብለው በፈገግታ ሲሸኙኝ፣ ወጣቷን ልቤን ክፉኛ አስፈንድቀዋት ነበር፡፡ … “እነዚህ ሰዎች ዴሞክራት ናቸው” በሚል ቀጣዩን ጊዜ እንድናፍቅ፣አንድ ጣፋጭ ተስፋ ጠብ አድርገውብኝ ነበር፡፡
በኋላም የዓባይ ግድብ ሲጀመር የተሰማኝ ስሜት እንደዚሁ ቀና ነበር፡፡ “እነዚህ ሰዎች በዕድሜ ሲበስሉ፣ ለሀገርና ለታሪክ ማሰብ ጀመሩ” ጠላቶች አስቤ፣ ስነ ልቦናዊ ስብራታችን ፈውስ አገኘ፤ በሚል ልዩ ሀገራዊ ኩራት ተኮፍሼ ነበር፡፡ በማለት ልዩ ደስታ ተፈጥሮብኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። ልዩ ደስታ! በዚያ ላይ አቅም የላቸውም በሚል በተከታታይ እያሳደዱ ሀገራችን ለግድቡ መስሪያ ብድር እንዳታገኝ በር የሚዘጉባትን ታሪካዊ ጠላቶች አስቤ፣ስነልቦናዊ ሥብራታችን ፈውስ አገኘ በማለት፣በሀገራዊ ኩራት ተኮፍሼ ነበር፡፡
ያ ኩራት ዛሬ ፈርሷል፣ ያ - ተስፋ ዛሬ የለም፣ ያ - አበባ ያለ ፍሬ ጠውልጓል፣ ያ - የሳቅ ፏፏቴ ዛሬ የእንባ ኩሬ ሆኗል፡፡ አዎ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ስህተቶች ሰርቷል፡፡ ያሁኑ ግን አበባን በደም መንከር፣ የሰላም ዘንባባን ማቃጠል ነው፡፡ የዚህ ዋጋ ደግሞ ቀላል አይደለም፡፡ ደም ነው፡፡ ህይወት ነው። ወደ ከባድ ነውጥ የሚቀየር ምንዛሬ ነው፡፡ ይህንን በደል ፈፅሞ፣ ሰላምን መጠበቅ፣ ከእሳት ደመና፣ ውሃን መመኘት ነው፡፡ የጆን ኤፍ ኬኔዲ ምክትል የነበሩት ሊንደን ቢ. ጆንስን ያሉትን አስታወሰኝ፡፡ … ምክንያቱም እኛ ያለንበት ሁኔታ ነውና! … ዛሬን እንጂ ነገን ለመተንበይ እስኪያቅተን ድረስ፣ ፍንጭ አልባ ሆነናል ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡
“If one man can compel others unjustly and unlawfully, to do what he commands them to do, then a community is not a place of peace. If we have neither the will nor the way to settle disputes among neighbors without violence, then none of us can live in peace.”
(ሀገርና ሰፈር በግዳጅ ሰላም ሊያገኙ አይችሉም፤ ኢ-ፍትሀዊና  ኢ-ህጋዊ በሆነ አካሄድ ህዝብን በማስገደድ ማህበረሰቡን የሰላም አየር እንዲተነፍስ ማድረግ አይታሰብም፡፡)
… ብልህ ግን ከስህተቱ ይማራል፡፡ ያለመሳሳት ከሰው ልጅ አይጠበቅም፤ ስህተትን መድገም ነው ውድቀት!... ስህተት ፈፅሞ ስህተቱን ማረም ያልቻለ ሰው ደግሞ ወደባሰው አዘቅት ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው፡፡ አንድ ደራሲ እንዲህ እንዲል፡- ‹‹A person who makes a mistake and doesn’t correct it, commits a bigger one››
ግን ችግርን ለመፍታት መጀመሪያ መፈፀሙን ማመን ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ተመልሶ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ አለመዘፈቅ፤ መውጣት!... ከስህተት መማር፤ ስህተቱን ያለመድገም፤ ለስህተቱም ይቅርታ መጠየቅ!… ይህ የአንድ መሪ መርህ ሊሆን ይገባል፡፡
…መንግሥታችን ግን ይህንን አላደረገም፡፡ ደርግን በጠመንጃ ተዋግቶ ጣለ፤… የፓርቲዎችን ትግል በጠመንጃ አከሸፈ፡፡ ዛሬም ሲቪሉን ሕዝብ በጠመንጃ ለማሸነፍ እየሞከረ ነው፡፡ ያልገባው ነገር ግን ያሁኑ እንደ ቀድሞ ቀላል አይደለም…. ከፓርቲ ጋር አይደለም የገጠመው፡፡ ከህዝብ ጋር ነው፡፡ ሕዝብ በጥይት አያልቅም!... ብዙ ሀገራት ውስጥ ተመሳሳይ ነገሮች አይተናል፡፡ ታሪክም ብዙ ያስተምረናል - የራሳችንን ታሪክ ጨምሮ፡፡ ከታሪክ የማይማር ግን ሰነፍ ነው፡፡ ‹‹People who doesn’t learn lessons from history is doomed›› እንዲል ሺቭ ኬራ፡፡
የሀገራችን ጉዳይ - ጣጣውና ጥፋቱ፣ ወደማይታረምበት ደረጃ የደረሰ ይመስለኛል፡፡…በተለያዩ ጊዜያት ሕዝብ ጥያቄ ሲጠይቅ የሚሰማው አልነበረም፡፡ ‹‹ራበኝ›› ያለውን ሕዝብ ጠግቧል ብሎ ካድሬው ሪፖርት ሲያቀርብ፣ ልማታዊ ጋዜጠኛ፤ አረንጓዴ ቀዬ ቀርፆ ‹‹የእነገሌ ሰፈር በዕድገት ጎዳና!›› ብሎ ከበሮ ሲደልቅ ሕዝቡ እያለቀሰ፤ መንግስት ፌሽታ እየረገጠ ኖረ፡፡… ሀገሪቱም በሪፖርት ሠማይ ነካች፡፡… ሰዎች እየፈረሱ… ፎቆች ተገነቡ፡፡ ፎቆቹ የማናቸው? ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ግን ሕዝቡ ውስጥ ውስጡን ተከፋ፡፡ በታችኞቹ ተማርሮ የበላይ ዘንድ ሲሄድ፤ ‹‹እዚያው ይጨርሱልህ!›› እያሉ እንደ ቅሪላ ከወዲያ ወዲህ ጠለዙት፡፡ ምሬቱ ሲገነፍል ብድግ አለ፡፡ ያን ጊዜ ‹‹የነ እንትና ተላላኪ!›› ተባለ። የከፋውን ሰው፣ ብሦት የጫረውን ሕዝብ ማን ሊልከው ይችላል? እራሱ እኮ ነው የነደደው!...  ይሄኔ ነበር ብልህ መሪ የሚያስፈልገው፡፡
በተለመደውና በእንጭጩ ዘመን እንደለመደው ታርጋ መለጠፉን ትቶ፣ ብልሃት የተሞላበትና  በፍቅር የታጀበ ሥራ ቢሠራ፤… ማን ለማን ተልኮ ሞት ይፈልጋል?..መንግስት እንደሚለው፤ ሕዝቡ ደልቶት ቢሆን፤… ከምቾቱና ከፌሽታው ውስጥ ሆኖ የማንን ፕሮፓጋንዳ ይሠማ ነበር?... ይልቅስ ለመንግስቱ እልልታውን እያቀለጠ ነበር የሚኖረው፡፡ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የጠገበ፣ በገሀድ የተራበና አንጀቱ ያረረ ሕዝብ ሆ! ብሎ ቢወጣ ምን ይገርማል!…
የገጣሚ በለው ገበየሁ ግጥም፤ ያልተቃና ነገር ቆይቶ ይሰበራል የሚል መልዕክት ይፈነጥቃል፡፡   “የዘገየ እርማት” ነው - ርዕሱ፡፡
የተከልኩት ቀርካ ረዝሞ
ከግቢዬ መሀል ቆሞ፣
ለከርሞ ጌጥ ያኔ ባጨው
አልሆነ ላይ ጎኑ ጠሞ፣
በእንጭጭነት ላዩ ቃግሞ፣
በለጋነት ጦዞ፣ ዘሞ
ወይ የብክር ሳላቀናው - ያኔውኑ አስቀድሜ
ጊዜ ስቸር ስመፀውት - በመታከት ከራርሜ
ለጋነቱ ነጥፎ ኑሮ - ላቃናው ብል ድንገት ዛሬ
ለካ ደረቅ አይታጠፍ - አረፍኩታ ሰባብሬ፡፡
በተገቢው ጊዜ ያልታረመ ነገር መጨረሻው መፈራረስ ነው፡፡ የፈራረሰ ነገር ከመጠገን ደግሞ አዲስ መግዛት፣ መለወጥ የተሻለ ነው፡፡ “አሮጌ መኪና ባለቤቱን አቃጥሎ ይገድላል!” እንደሚባለው ዐይነት!
ለአሮጌ መኪና በየጊዜው መለዋወጫ መግዛት አድካሚና አሰልቺ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ዕድሜ ያሳጥራል፡፡… ጎማ መቀየርም ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ሞተሩ አዲስ ከሆነ ብቻ ነው ጎማው መለወጥ ያለበት፡፡ … ለዚያውም መንገዱ አስፋልትና የተመቸ ከሆነ ነው፡፡ አሁን ኢህአዴግና ህዝቡ እንዲህ የሆኑ ይመስለኛል፡፡ ህዝቡ ለሃያ ዓመታት ያህል አስፋልት ነበር፣ አሁን ግን ተቦርቡሮ አልቆ ኮረኮንች ሆኖዋል፡፡ ለመንግስት አይመችም፣ ያንገጫግጫል፣ አንዳንድ ቦታ ገደል ሰርቷል፡፡ … ስለዚህ አሮጌው መኪና በዚህ ኮረኮንች ላይ እንዴት ይዘልቃል? ጎማ ቀይሮ? … አይመስለኝም፡፡ መቀየር ያለበት ሞተሩ ነው፡፡ ሞተሩ አርጅቷል፡፡
ኢህአዴግ አሁን ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣት ያለበት አርቆ በማሰብ ነው፡፡ በትጥቅ ትግል ከፍያለሁ የሚለውን መስዋዕትነት፣ ከዚያም በኋላ የሰራቸው መሰረተ ልማቶች ወዘተ ዋጋ እንዳያጡና በታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን ካሰበ፣ እንዲሁም የባንዲራ ስር ቁማርተኞች ህዝቡን ሸቀጥ አድርገው እንዳያፈርሱት የሚጨነቅ ከሆነ፣ በተረጋጋ ሁኔታ የሽግግር መንግስት አቋቁሞ፣ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ቢያሸጋግራት ለዝንተ ዓለም ይወደሳል፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ግን፣እልቂት ቢፈጠርና ወሮበሎች አጋጣሚውን በመጠቀም፤ ስልጣን ላይ ቢፈናጠጡ ውድቀቱ ለልጅ ልጅ ይተርፋል፡፡ አሁን ኢህአዴግ ያለው “ጥልቅ ተሃድሶ”፣ ለዚህ ለተንገሸገሸና ለመረረው ህዝብ ውጤት አያመጣም፡፡ በጣም የዘገየ ይመስላል፡፡   
በ1966 ዓ.ም አብዮቱ ባስገመገመበት ወቅት፣ የሀገሪቱንና የህዝቦችዋን ጥያቄ መልስ ለመስጠት፣ለስድስት ወራት የቀጠረውን መንግስት አስመልክቶ አንድ የቆየ “ፀደይ” መጽሔት ላይ የተፃፈው እንዲህ ይላል፡-    
“የኢትዮጵያ ህዝብ የጠየቃቸው መሰረታዊ መሻሻልና ለውጦች እንኳንስ ስድስት ወርና ስድስት ሰዓት የሚጠይቁና የሚያስፈልጋቸው አይደሉም። ይህን ያህል ዘመን ፍሬ ቢስ ተስፋ ብቻ ሲመገብ የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ አሁን በቆራጥነት ታጥቆ ተነስቶ፣ መብቴን አሁኑኑ በእጄ አስረክቡኝ” በሚልበት ወቅት፣ “ወኔህ እንዲቀዘቅዝ፣ ኃይልህ እንዲኮስስ፣ ዓላማህ እንዲጨነግፍ ስድስት ወር ስጠንና ከዚያ በኋላ የፈለግነውን እናደርግልሃለን” ቢሉት፣ በባዶ ተስፋና በአጉል ሽንገላ መታለሉ ሰልችቶታል፣ አሜን ብሎ ተቀብሎ ወደ ኋላ ለመመለስ አይችልም፣ አይቃጣውም፡፡”
አሁንም የተፈጠረው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይመስለኝም፡፡ ህዝብ ሰልችቶታል፤ተስፋ ቆርጧል፡፡ እንደ እኔ፣የባሰ መዘዝ ውስጥ ከመግባት ውጭ የተለየ ነገር አይመጣም፡፡ እልቂትና ጥፋት ከተፈፀመና ሁኔታዎች መልካቸውን ከቀየሩ በኋላ፣ ከመፀፀት አሁኑኑ መፍትሄ መፈለግ የግድ ነው፡፡ ጎማውን ሳይሆን ሞተሩን መቀየር!    

Read 2366 times