ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ የተቋቋመው ሻሎም ሲኒማ በመጪው አርብ ሥራ ሊጀምር ነው፡፡ በቲዋይ ሻሎም ፕሮሞሽን የተቋቋመው ሲኒማ ቤት 400 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን የፒያሳ፣ የጐላ ሚካኤልና የቸርችል ጐዳና አካባቢ ፊልም አፍቃሪዎችን በቅርበት እንደሚያገለግልና ለዕይታ ወረፋ የሚጠባበቁ ፊልሞችን ችግር በከፊል እንደሚፈታ ተገልጿል፡፡ በብዙ የውጭ ሀገራት ተዘዋውረው ደረጃቸውን የጠበቁ ሲኒማ ቤቶች ማየታቸውን የተናገሩት የሲኒማ ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ወልደሰንበት፤ ውጭ ሀገር እንዳሉትም ባይሆን ለወደፊት ይበልጥ ደረጃውን የጠበቀ ሲኒማ ቤት እንሰራለን ብለዋል፡፡ ለአካል ጉዳተኞች የተስማማ ሲኒማ ቤት እንዲሆን አስበንበታል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ “ቤቱ ለትንፋሽ በሽታ እንዳያጋልጥ ዘወትር ክፍት የሚሆን በር አለ፤ ጣራው በዝናብ ምክንያት ተመልካች እንዳይረብሽም ሳር ይለብሳል” ብለዋል፡፡