Saturday, 28 August 2021 14:54

ውዳሴ ባለ 21 ህንፃ የመልቲ የስፔሻሊቲ ማዕከል ሊገነባ ነው

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(3 votes)

     በዘንድሮ “ጳጉሜን ለጤና” ዘመቻ ከ3ሺህ በላይ ሰዎች ነፃ ምርመራ ያገኛሉ
                         
           የዛሬ 13 ዓመት ባለሁለት ስላይስ ሲቲ ስካን በብድር ገዝቶ ስራ የጀመረውና አሁን  128  ስላይስ ሲቲ ስካንን ጨምሮ በዓለም ላይ አሉ የሚባሉ የምርመራ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀመው ውዳሴ ዲግኖስቲክ ማዕከል፤ሀገራችን በጤና  ምርመራ ዘርፍ ያለባትን ክፍተት እየሞላ መሆኑን ይገለጻል፡፡
ማዕከሉ ከዚህ ጎን ለጎን ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት በማሰብ ከተመሰረተበት 1ኛ ዓመት አንስቶ  “ጳጉሜን ለጤና” በሚል በጀመረው ዘመቻ  እስካሁን በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ ምርመራው እያስፈልጋቸው ነገር ግን ከፍለው ለመመርመር አቅም ላጡ ወገኖች ነፃ ምርመራ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡  ባለፈው ዓመት በ”ጳጉሜን ለጤና” ዘመቻው ከ1 ሺህ 600 በላይ ለሆኑ ወገኖች የምርመራ አገልግሎቱን እስከ ታህሳስ መጨረሻ ባሉት ጊዜያት ሰጥቶ ሲያጠናቅቅ፣ የዚህ ዘመቻ የተጀመረበት 11ኛ ዓመት ሥለነበረ ከምርመራው ጎን ለጎን 11 ዓይነት በጎ ተግባራትን አከናውኖ ነበር።
ዘንድሮም 12ኛ ዓመት ዘመቻውን ምክንያት በማድረግ 12 የበጎ አድራጎት ስራዎችን ከነሐሴ 24 ቀን ጀምሮ ለ12 ቀናት እንደሚያከናውን ከትላንት በስቲያ በተለምዶ አሮጌው ቄራ ተብሎ ቢጠራው የማእከሉ ቢሮ ማዕከሉ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን በዚሁ ዕለት “ውዳሴ መልቲ ስፔሻሊቲ ሴንተር” በሚል ለሚገነባው ባለ 21 ወለል ህንፃ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡
የዘንድሮውን የ”ጳጉሜን ለጤና” ነፃ የምርመራ አገልግሎት ከዓምናው ዓመት በእጥፍ በማሳደግ 3 ሺህ  ተገልጋዮችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ መሆኑን የጠቆመው ማዕከሉ፤ ቅርንጫፎቹን ከ3 ወደ ስድስት ማሳደጉ ዕቅዱን ዕውን ለማድረግ ያግዘዋል ተብሏል፡፡
ማዕከሉ የሚሰጣቸውን ማንኛውንም አይነት የምርመራ አገልግሎት (ስቲ ስካን፣ ኤክስሬ ኤምአርአይና፣ አልትራ ሳውንድ፣ አድቫንስድ ላብራቶሪ፣ የኮቪድ 19 ምርመራና ሌሎችንም)  ለመጠቀም የወጣውን መስፈርት (ከመንግስት የጤና ተቋም ምርመራው የታዘዘላቸውና ከፍለው መታከም የማይችሉ መሆናቸውን የሚገልጽ ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ) የሚያሟሉት ይስተናገዳሉ ተብሏል፡፡ ምዝገባው ከጳጉሜ 1 ጀምሮ እስከ ጳጉሜ አምስት እንደሚዘልቅ የተጠቆመ ሲሆን ለመመዝገብም በስልክ ቁጥር 0940-05 05 05/0940-04 04 04 እና በ9888 የጥሪ ማዕከል መጠቀም እንደሚቻል ተገልጿል።
የጳጉሜን ለጤና 12ኛ ዓመት ዘመቻን አስመልክቶ ለ12 ቀናት የሚካሄዱት የበጎ አድራጎት ተግባራት ደግሞ ነሀሴ 24 እንደሚጀምሩ የተገለጸ ሲሆን ነሀሴ 24 ከኢትዮጵያ አየር  መንገድ ሰራተኞች ጋር በመተባበር የደም ልገሳ፣ ነሀሴ 25 ለተቸገሩ ወገኖች የአስቤዛ ልገሳ፣ ነሀሴ 26 ወደ 400 ለሚጠጉ የጎዳና ልጆች ብርድ ልብስ ልገሳ፣ ነሀሴ 27 ወደ 1 ሺህ ለሚጠጉ የጎዳና ልጆች የምሳ ምገባ፣ ነሐሴ 28 ቀን የፅዳት ዘመቻ፣ ነሀሴ 29 ቀን 700 የሚሆኑ የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማእከልና የእህት ኩባንያዎች ሰራተኞች በትብብር የሚያካሂዱት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርና ነሀሴ 30 ቀን ደግሞ ፈርሰው እንደ አዲስ የተሰሩ የአቅመ ደካሞች ቤቶች የማስረከቢያ ቀን ይሆናል ተብሏል፡፡ ከጳጉሜ 1-5 ቀን 2013 ዓ.ም ሶስት ሺህ የሚሆኑ ምርመራ  የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን የመመዝገቢያ ቀን መሆኑን የማዕከሉ ባለቤትና ዋና ስራ  አስፈፃሚ አቶ ዳዊት ሀይሉ ገልጸው፤ ማዕከሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ ፈተና የሆነውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመዋጋት በሚደረገው ትግል በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የኮቪድ ምርመራ ማእከል ከፍቶ ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ምርመራ እየሰጠ እንደሆነም አመልክተዋል።
ባለፉት ዓመታት በተካሄደው የጳጉሜን ለጤና ዘመቻ ከክፍለ ሀገራት የሚመጡ ምርመራው የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቅድሚያ እየተሰጣቸው አገልግሎቱን ማግኘታቸው የተነገረ ሲሆን ዘንድሮም በመጡ ሰዓት ቀጠሮ በያዙበት የማዕከሉ የትኛውም  ቅርንጫፍ ለማደሪያና ለቀለብ ገንዘብ ሳያወጡ በቅድሚያ እንዲስተናገዱና እንዲመለሱ ይደረጋል ተብሏል።

በህክምናው ተስፋ የተጣለበት “ውዳሴ መልቲ ስፔሻሊቲ ሴንተር”
ይህ ማዕከል በተለምዶ አሮጌው ቄራ እየተባለ በሚጠራውና የመጀመሪያው የውዳሴ ዲያግኖቲክ ማዕከል  ውስጥ የሚገነባ ሲሆን በ2 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍና ባለ 11 እና ባለ 21 ወለል መንታ ህንፃዎችን የሚይዝ እንደሆነ ተገልጿል።
ባለ 21 ወለሉ ህንፃ ከ1-7ኛ ፎቅ  ሙሉ ለሙሉ ለህክምና አገልግሎት የሚውል ሲሆን፣ ከ8ኛ እስከ  20ኛ ያለው ደግሞ በአንድ ወለል አራት አባወራዎችን የሚይዝ የመኖሪያ ቤት ይሆናል ተብሏል። በስተምስራቅ የሚገኘው ባለ 11 ወለሉ ህንፃ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ለህክምና አገልግሎት  የሚውል ሲሆን አድቫንስድ ኦንኮሎጂ ማዕከል፣ አድቫንስድ ኒዩሮ ስፓይናል ማዕከል፣ የመሃንነትና ተያያዥ ምርመራና ህክምና ማዕከል
የቆዳ ህክምናና የፕላስቲክ ሰርጀሪ ማዕከል፣ አድቫንስድ የምርመራና የላብራቶሪ ማዕከል፣ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ንቅለ ተከላን ጨምሮ በርካታ የላቁ የህክምና ማዕከሎችን ይይዛል ተብሏል። ለግንባታው ከ2-3 ዓመት የጊዜ መጠን የተያዘት ሲሆን 943  ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለታል
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ደረጃ ድጉማ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት ሥነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ለጤናው ዘርፍ መንግስትን በማገዝ እያደረገ ላለው አገልግሎት  ከፍተኛ ምስጋና አቅርበው፤ አዲስ የሚገነባው ግዙፍ የህክምና ማእከልም የውዳሴ ብቻ ሳይሆን የእኛም ነው ብለዋል፡፡ በግንባታ ሂደቱም ሆነ በማንኛውም ጉዳይ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚፈልጉትን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ራዲዮሎጂስትና አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ከበደ በበኩላቸው፣ ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማእከል በኮቪድ ምርመራ አገልግሎት ከሌሎች አቻ ተቋማት በመላቅ አርአያ ለመሆን እንደቻለ በዕለቱ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

Read 2333 times