Sunday, 17 October 2021 18:25

ያለዕድሜ ጋብቻ በየቀኑ ከ60 በላይ ልጃገረዶችን ለሞት ይዳርጋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በለጋ ዕድሜ ወደ ትዳር በመግባት ከሚከሰት እርግዝናና ወሊድ ጋር በተያያዘ በአለማችን በየቀኑ ከ60 በላይ ልጃገረዶች ለሞት እንደሚዳረጉ እና በመጪዎቹ 9 አመታት ውስጥ ተጨማሪ 10 ሚሊዮን ያህል ልጃገረዶች ያለዕድሜያቸው ይዳራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
አለማቀፉ ግብረሰናይ ተቋም ሴቭ ዘ ችልድረን የአለም የልጃገረዶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳለው፣ በአለማችን በየአመቱ ከ22 ሺህ በላይ ያለዕድሜያቸው የተዳሩ ልጃገረዶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለሞት ይዳረጋሉ፡፡
በአለማችን በየአመቱ ካለዕድሜ ጋብቻ ጋር በተያያዘ በሚከሰት ወሊድ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ልጃገረዶች ለሞት የሚዳረጉት በምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ አካባቢ እንደሆነ የጠቆመው ጥናቱ፣ በአመት ከ9 ሺህ 600 በላይ የአካባቢው ልጃገረዶች በዚህ ሰበብ እንደሚሞቱም አመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ ምክንያት በደቡብ እስያ አገራት 2 ሺህ፣ በምስራቅ እስያና በፓሲፊክ አገራት ደግሞ 650 ያህል ልጃገረዶች ለሞት እንደሚዳረጉም ተቋሙ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
ወሊድ ልጃገረዶችን ለሞት በመዳረግ ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝ የተናገሩት የተቋሙ ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ጃንቲ ሶሪፕቶ፣ ምክንያቱም ልጃገረዶች ልጅ ለመውለድ ዝግጁና ብቁ የሆነ አካላዊ ብቃትና ዝግጁነት የሌላቸው መሆኑና ነው ብለዋል፡፡
መንግስታት የልጃገረዶችን መብቶች ለማስከበር፣ ያለዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ የሚያጋጥሟቸውን ጾታዊ ጥቃቶች ለመከላከልና መፍትሄ ለመስጠት በትኩረት እንዲሰሩም ተቋሙ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ባለፉት 25 አመታት በአለም ዙሪያ ሊፈጸሙ ይችሉ የነበሩ 80 ሚሊዮን ያህል ያለዕድሜ ጋብቻዎችን ማስቀረት ቢቻልም፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው የትምህርት ቤቶች መዘጋት፣ የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች መጓደል፣ የድህነት መባባስ ግን ያለዕድሜ ጋብቻን እንዳባበሰው ተነግሯል፡፡



Read 9769 times