Sunday, 12 December 2021 00:00

መፅሐፈ ሚርዳድ እና ውብ ሀሳቦቹ

Written by  ሣራ አህመድ
Rate this item
(1 Vote)

  "ሁሉም መጻሕፍቶችህ ተቃጥለው አንዱ ይትረፍ ቢባል የምመርጠው መፅሐፈ ሚርዳድን ነው”
   
          የመፅሐፈ ሚርዳድ ደራሲ ሚካኤል ኔይሚ ከሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ወጣ ብሎ በሚገኘው የሳኒን ተራራ ግርጌ ባለችው መንደር እ.ኤ.አ ጥቅምት 17 ቀን 1889 ተወለደ። ሚካኤል ነይሚ በርካታ መፅሐፍት ቢፅፍም ድንቅ ሥራው የሚባለው ግን መፅሐፈ ሚርዳድ ነው። ኔይሚ መጀመሪያ መፅሐፉን ለንደን ውስጥ ለማሳተም ለአንድ አሳታሚ ሰጥቶ ነበር። የተራቀቀውን የመጽሐፍ ጭብጥ ፈፅሞ የሳተው ገምጋሚ፤ “አዲስ ቀኖና የያዘ ሀይማኖት ለማስፋፋት ያለመ ነው” በሚል አጣጥሎ መለሰው።
ኔይሚ መፅሐፉን ሀገሩ ሊባኖስ ውስጥ አሳተመው። ሚካኤል ኔይሚ እና ኻሊል ጂብራን በአረብ ስነ -ፅሁፍ ውስጥ የነበራቸው ሚና በቀላሉ የሚወሳ አይደለም። በተለይም ሁለቱም ኒውዮርክ በነበሩበት ዘመን በመሰረቱን ፔን ሊግ የተሰኘ የስነፅሁፍ ማህበር፣ የአረብ ስነ-ፅሁፍን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ስራዎችን አበርክተዋል። በማህበሩም ሚካኤል ኔይሚ ፀሀፊ የነበረ ሲሆን ፤ኻህሊል ጂብራን ደግሞ ሊቀ መንበር
ነበር። መፅሀፈ ሚርዳድ እና የኻህሊል ጂብራን “ዘ ፕሮፌት”ብዙ ተመሳስሎሽ ቢኖራቸውም፣ “ዘ ሮፔት” ለህዝብ የተነገረ ሲሆን መፅሐፈ ሚርዳድ ግን ለተመረጡ መነኩሴዎች የተነገረ ሙዚቃዊ ፍሰት ያለው፣ ጠንከር ያለ የቋንቋ አወቃቀር የያዘ መፅሐፍ ነው።
መፅሐፈ ሚርዳድ የታላቅነቱን ያህል ዝነኛ መፅሐፍ አልነበረም። አሁን ያለውን ተቀባይነት ያገኘው በኦሾ ምክንያት ነው። ኦሾ ስለ መፅሐፈ ሚርዳድ እንዲህ የሚል ሀሳብ ሰንዝሮ ነበር፡- “በዓለማችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ መጻሕፍት አሉ። መፅሐፈ ሚርዳድ ግን ከሁሉም ይልቃል። መፅሐፈ ሚርዳድ እንደ ሌሎች መፅሐፍት የተፃፈ ሳይሆን እንደ ህያው ፍጡር ተረግዞ የተወለደ ነው። እኔ ታውቃላችሁ በማንም አልቀናም። እንደው ልቅና ብል ግን የምቀናው በሚካኤል ኔይሚ ነው። ምክንያቱም መፅሐፈ ሚርዳድን እኔ ነበርኩ ልፅፈው የምፈልገው፤ ግን ቀድሞ ተፅፏል..”
ኦሾ እንዲህ የቀናበትና እኔ ብፅፈው ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር ያለለት መፅሐፍ ደራሲም በአንድ ወቅት ተጠይቆ ሲመልስ፤ #ሁሉም መጻሕፍቶችህ ተቃጥለው አንዱ ይትረፍ ቢባል የምመርጠው መፅሐፈ ሚርዳድን ነው።” ብሏል። ብዙ ጊዜ ደራሲዎች የጥበብ ስራዎቻቸውን እንደ አብራክ ክፋያቸው የመሳሳት፣ ሁሉንም እኩል ባይባልም ተመሳሳይ በሆነ መጠን የመውደድ ስሜት ይታይባቸዋል። ኔይሚ መፅሐፈ ሚርዳድን  ከሁሉም ልጆቹ አስበልጦ  የሚወደው ለምንድነው ነው? እስቲ መጽሐፉን በወፍ በረር እንቃኘው፡፡
እነሆ መፅሐፈ ሚርዳድና ሀሳቦቹ፡-
“የአንድ ሰው ህይወት በሀሳቦቹ የተገነባ ነው” የሮማ ፈላስፋው ማርከስ ኦሬሊየስ
“የሰው ልጅ ቀኑን ሙሉ የሚያስበውን ነው” አሜሪካዊ ፈላስፋው ራልፍ ዋልዶ
ከ19ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ የሰው ልጅ የራሱ ህይወት ቀራጺና በህይወቱ የሚገጥሙት ነገሮች ሁሉ አስተሳሰቡ ላይ መሠረት ያደረጉ ናቸው የሚሉ ሀሳቦች በብዛት በፈላስፋዎች እንዲሁም በስነልቦና ጠበብትም ሲነሱ ተስተውሏል። በተለይ በስነልቦናው ሳይንስ ዘርፍ፣ አስተሳሰባችን በህይወታችን ላይ ያለው ተፅዕኖ ሳይንሳዊ በሆኑ ምርምሮች ተደግፈው ቀርበዋል።
አዕምሮን ንቁ የአዕምሮ ክፍል (conscious mind) እንዲሁም ድብቁ የአዕምሮ ክፍል (subconscious mind) በማለት ለሁለት ይከፍሉታል፤ የዘርፉ ጠቢባን። ንቁ የአዕምሮ ክፍል ከነባራዊ አለም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ሲሆን፤ የአስተውሎቱም መሳሪያዎች አምስቱ የስሜት ህዋሳት ናቸው። ይህ የአዕምሮአችን ክፍል ከአካባቢያችን ጋር ባለን ግንኙነት መሪያችንና ተቆጣጣሪያችን ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ የአዕምሮ ክፍል የስራ ድርሻዎች መካከል ማገናዘብ ፤ጥሩውን ከመጥፎ መለየት፤ምርጫና ውሳኔዎችን ማሳለፍ በዋነኝነት  የሚጠቀሱ ናቸው።
ድብቁ የአዕምሮ ክፍል ደግሞ በሰውነት ውስጥ የሚካሄዱ የተለያዩ ተግባራት - የልብ ምትን፣ የምግብ መፈጨት ስርአትን፣ የአተነፋፈስ፣ የደም ዝውውር ስርዓትን ይቆጣጠራል። በእኛ ምርጫና ፍላጎት የሚከናወኑ ሳይሆን ከእኛ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ስርአቶችን የሚቆጣጠረው ድብቁ የአዕምሮ ክፍል ነው። ድብቁ የአዕምሮ ክፍል በንቁ አዕምሮአችን የምናምነውን አሊያም ደግሞ እላዩ ላይ የታተመውን ሀሳብ ይቀበላል። እንደ ንቁ የአዕምሮ ክፍል የማገናዘብ ችሎታ የለውም። የተሰጠውን ማንኛውንም ሀሳብ መጥፎም ሆነ ጥሩ ያለማንገራገር ይቀበላል። በኑረታችንም የተቀበለውን ሀሳብ ይገልጠዋል። ይህንን ሀሳብ በሰመመን ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ በተደረገው ጥናት ላስደግፈው፡፡ በሰመመን ውስጥ ያለ ሰው የሰመመን ባለሙያው፤ “አንተ ድመት ነህ/ውሻ ነህ; ቢለው፣ ይህ ግለሰብ እንደተባለው ለጊዜው ማንነቱን በመርሳት፣ ባለሙያው ነህ ያለውን የእንስሳት ባህሪ ማሳየት ይጀምራል።
ድብቁ የአዕምሮ ክፍላችን የምንሰጠውን ሀሳብ ይህን ያህል ከተቀበለና ከተገበረ፣ ራሳችን ስለ ለራሳችን ምን እንላለን? እኔ ማነኝ እንላለን? ሚርዳድ “እኔ” የሚለውን ሀሳብ ፈጣሪ ቃል ይለዋል። አለማለቱ ላይ የተፈጠሩ የሆኑ ሁነቶች ሁሉ በዚህ ቃል መነሻ ነው እኔ በሚለው እና እሱን ተከትሎ የሚነሱ ሀሳቦች ሰናይ አለምን እንዲሁም እኩይ አለምን የመፍጠር አቅም አላቸው።
ገፅ 48 ላይ ከሰፈረው ሀሳብ እንጨልፍ፡-
“እኔ” መነኩሴዎች ሆይ ፈጣሪ ቃል ነውና።….የዚህን ቃል ምትሀታዊ ሀይል በእጃችሁ ካላስገባችሁ፣ ገዢ ሀይሉም ካልሆናችሁ፣ መዝፈን ሲገባችሁ የምታቃስቱ፣ ሰላም መሆን ሲገባችሁ የምትፋጁ፣ በብርሀን ከፍ ከፍ ማለት ስትችሉ በወህኒ ጨለማ የምትማቅቁ ነው የምትሆኑት፤ይላል፡፡
እኔያችን በፍቅር የታጀለ ነው ወይስ በጥላቻ?
ፍቅርስ ምንድነው?
አንድ የተለመደ ገለፃ አለ፡- ፍቅርን በተመለከተ #ፍቅር ዕውር ነው” የሚል፡፡ ይህ ገለፃ ፍቅር ከአመንክዮ ጋር ስምምነት እንደሌለው፣ አፍቃሪም በስሜት ከመመራት ጋር ተያይዞ መንገድ እንደሚስት ለማሳየት ብዙ ጊዜ ሰዎች ይጠቀሙበታል። ሚርዳድ ግን ይህን ሀሳብ እንከን ማየት አለመቻልን፣ ከዳኝነት መንፃት ፤የሌሎችን ስህተት ከማየት መቆጠብ፤ በፍቅር ዓይኖች መራራት፤ ሁሉን የማየት ከፍታ፤ ደግሞም መታወር ይለዋል።
ፍቅር ምንድነው?
ሚርዳድ ፍቅር ልክ እንደ ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ መሠረታዊ ፍላጎት ነው ይላል። ሁሉም የሰው ዘር የሚያስፈልገው ከጎደለ በእጅጉ የሚያቃውሰው መሠረታዊ ፍላጎት፡፡ ገፅ 86 እንዲህ ይላል፡-
#ፍቅር የህይወት ወለላ ነው። ጥላቻ ደሞ የሞት መግል። ፍቅር ልክ እንደ ደም ሳይታጎልና ሳይገደብ በህይወት ስሮች ውስጥ ሊፈስ ይገባዋል።;
 ሚርዳድ ስለ ፍቅር መነሻ መፀነሻ ሲናገር፤ የመውደድ አብራኩ ራስን
ማፍቀር ነው ይለናል። ፍቅርን በገንዘብ መግዛት ይቻላል? ገንዘብ ምንድነው?
የጥላሁንን ገሠሠ አንድ ዘፈን አለ፡- “እያለ ካልሆነ ከሌለህ የለህም” የሚል የዘመናችንን መንፈስ የሚያሳይ ስራ ነው። በዘመነ ካፒታሊዝም ገንዘብ ጥልቁ ሀይል ነው። ጥላሁን እንዳለው፤ ከሌለህ የለህም ነው ጨዋታው፤ መኖርህን ለማረጋገጥ ራሱ ገንዘብ ያስፈልጋል።
በሚርዳድ ገንዘብና ሀብት እንዲህ ተገልፀዋል፡
ገንዘብ "ሰውን አስሮ ማስገበሪያ፣ ብልጣብልጡ ከሰው ላቦት ደም ያበጀው ቁራጭ ብረት ወረቀት ነው።”
ሀብት #ብዙ ያልደሙ ብዙ ያላባቸው፣ ብዙ የደሙ ብዙ ያላባቸው መመዝበሪያ፣ ከሰዎች ያለቡበት ላብ እና ደም ነው”
ማንን ልዋጋ?
ብዙ ግጭቶች፣ ውጊያዎች መነሻዎቻቸውን ብንፈትሽ፤ የግጭቱን እርሾ ውስጣችን እናገኘዋለን። ሚርዳድ ስለ ውጊያ ሊጠይቀው የመጣውን ልዑልም ያለው ይኸንኑ ነው። ልዑሉ፤ #ከጎረቤቴ ጋር በሰላም ለመኖር እሻለሁ፤ እሱ ግን ከወጋኝ ምን ላድርግ?;
ሚርዳድም፤ "ተዋጋ! ጎረቤትህን አይደለም። አንተንና ጎረቤትህን እንድትዋጉ የሚያደርጉ ነገሮችን ሁሉ ተዋጋ!;
ብዙ ልንዋጋቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፤ እንደ ማህበረሰብ ጥላቻ፣ ክፋት፣ ስንፍና፣ ምቀኝነት ሁሉ ልንዋጋቸው የሚገቡን ነገሮች ናቸው። ሚርዳድ ከመነኩሴዎቹ ጋር ስለ ፍትህ፣ ስለ ጊዜ፣ ስለ ወዳጅነት፣ ስለ ፍርድ ቀን፣ ስለ ፀሎት ሀሳቦችን አንስቷል። ሀሳቦቹ ከሰው መንጋ ገንጥለው ለብቻ የማንሳፈፍ አቅም አላቸው።
ሜካኤል ኔይሚ ከመፅሀፈ ሚርዳድ በኋላ በርካታ መጻሕፍት የፃፈ ቢሆንም፣ እንደ መፅሐፈ ሚርዳድ የተዋጣለት ግን አልነበረም። መፅሐፉ ካነሳቸው ሀሳቦች በተጨማሪ ሙዚቃዊ ቃና ያለው ፍሰቱና ግጥሞቹ ለነፍስ ቅርብ ያደርጉታል። እንደ መሰናበቻ አንድ ግጥም እንመልከት፡- (ገፅ- 77)
ስታስብ ይህን አስብ፣
ሁሉ እንዲፈርድ አይቶ
ሀሳብህ ቢታተም ሰማይ ላይ ወጥቶ
እውነቱ እንዲያ ነው እኮ
ስትናገር
ስታወራ ቃልህን ለመቅለብ
ዓለም ጆሮ ሆኖ እንዳቆበቆበ
ያህል ሆነህ አውራ!
በእርግጥ እንዲያ ነው እኮ
ስታደርግ -ስትሰራ
ለሌላው የከወንከው በጎ ስራ ሁሉ ላንተ እንደሚያፈራ
በሰፈርከው ቁና እንደምትሰፈር
በማስከው ጉድጓድ እንደምትቀበር
በዘራኸው እሾህ እግር እንዳይነደል
አስበህ ተጋደል
በእርግጥ እንዲያ ነው እኮ
ደግሞስ እያንዳንዳቹ
“ህይወቴን ኑሩልኝ"
ልክ ያላችሁ ያህል ራሱ እግዜሩ
ህይወታችሁን ኑሩ!!
በእርግጥ ብሏል ጌታ
ተናግሯል ፈጣሪ
ኖራችሁ አሳዩታ…

Read 3497 times