Saturday, 15 January 2022 21:49

ዋልያዎቹና የ33 የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏቸው

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

  ከሳምንት በፊት የተጀመረው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሁለተኛ ዙር የምድብ ጨዋታዎች ቀጥሏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ምድቡን የመጀመሪያ ጨዋታ ያደረገው በመክፈቻው ወቅት ሲሆን በኬፕቨርዴ 1ለ0  የተሸነፈበት ነው። በዚህ ጨዋታ ዋልያዎቹ ተከላካዩ ያሬድ ባየህ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተሰናበተ በኋላ ከ70 ደቂቃዎች በላይ በ10 ተጨዋቾች ኬፕቨርዴን በኳስ ቁጥጥር የተወሰነ ብልጫ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የረባ ሙከራ ባለማድረጉ አስፈላጊውን ነጥብ ይዞ መጨረስ አልቻለም። ከጨዋታው በኋላ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ “የገጠምነው በአንጋፋ ተጨዋቾች ጥሩ ስብስብ ከነበረው የኬፕቨርዴ ቡድን ጋር ነው። የልምድ ማነስ ለሽንፈት ዳርጓል።” በማለት ለካፍ ኦንላይን አስተያየት ሰጥተዋል። ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ውይይት ደግሞ የአፍሪካ ዋንጫን መሳተፋችን ብቻ በቂ ነው ብለው የተናገሩ ሲሆን ከተጣለባቸው ሃላፊነት አንጻር መሳተፉ ብቻ እንደሚያረካ ቡድኑ ግን በሚያሳየው ብቃት ምርጥ 3ኛ ሆኖ የሚያልፍበት ዕድል መኖሩንም ጠቁመዋል። ከዚሁ ምድብ በመክፈቻው ጨዋታው ካሜሮን 2 ለ1 ቡርኪናፋሶን አሸንፋለች።
በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአዘጋጇ ካሜሮን ጋር ተገናኝቶ 4 ለ1 ተሸንፏል። በዚሁ ጨዋታ ላይ በ4ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሁጤሳ  ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመሪነት ጎሉን አስቆጥሮ ነበር። የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን አጥቂው ካርል ቶኮምቢ እና አምበሉ ቪንሰንት አቡበከር እያንዳንዳቸው ሁለት ጎሎችን አስቆጥረው 4ለ1 አሸንፏል። በምድቡ ሁለተኛ ዙር ጨዋታ ደግሞ ቡርኪናፋሶ  ኬፕቨርዴን 1ለ0 አሸንፋለች። ካሜሮን በ6 ነጥብና በ4 የግብ ክፍያ ወደ ጥሎ ማለፍ መሸጋገሯን ስታረጋግጥ ቡርኪናፋሶ እና ኬፕቨርዴ በእኩል 3 ነጥብ ሁለተኛ  ደረጃን ይዘዋል። የኢትዮጵያ ቡድን ያለምንም ነጥብ በ4 የግብ ዕዳ መጨረሻ ላይ ነው። ዋልያዎቹ በካሜሮን ከተሸነፉ በኋላ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለካፍ ኦንላይን በሰጡት አስተያየት “ከካሜሮን ጋር ባደረግነው ጨዋታ በጥሩ ብቃት የምንችለውን ሁሉ አድርገናል። የመሪነቱን ግብ በጨዋታው መጀመሪያ ላይ ብናስቆጥርም ውጤቱን አስጠብቀን ለመቆየት አልቻልንም። በትልቅ ውድድሮች ላይ ትምህርት እየወሰድን ነው። በእኛና በካሜሮን መካከል በልምድ ደረጃ ሰፊ ልዩነት አለ። እያንዳንዱ ጨዋታ ደግሞ የየራሱ ባህርያት አሉት። ግጥሚያዎች የተለያዩ ቢሆኑም ያሉንን ችሎታዎች በማሳየት ጥሩ ኳስ ተጫውተናል” ብለዋል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ከ473 ቀናት በላይ ያስቆጠሩት ውበቱ አባተ በ4 የወዳጅነት ጨዋታዎች፣ 4 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች፣ 4 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችና 2 የአፍሪካ ዋናጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን አድርገዋል። በእነዚህ ውድድሮች 13 ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ተገናኝተው በ6ቱ ሲያሸንፉ፤ በ3 አቻ ተለያይተው 7ጨዋታዎችን ተሸንፈዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ሰኞ ከቡርኪናፋሶ ጋር ያደርጋል። ሁለቱ ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታ ሲገናኙ ከ8 ዓመታት በኋላ ለ2ኛ ጊዜ በእግር ኳስ ታሪካቸው ደግሞ 4ኛ ጨዋታቸው ነው። በ2013 እ.ኤ.አ ላይ ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በተገናኙበት ወቅት ቡርኪናፋሶ 4ለ0 ማሸነፏ ይታወሳል።  በሌላ በኩልሁለቱ ቡድኖች በ2000 እ.ኤ.አ ላይ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በደርሶ መልስ ተገናኝተው ነበር። በመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ 2 ለ 1 ስትረታ በመልሱ ደግሞ ቡርኪናፋሶ 3 ለ 1 አሸንፋለች። በ2013 ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው ከምድ ማለፍ አልቻለም ነበር። በወቅቱ ዋልያዎቹ በመክፈቻው ጨዋታ ከዛምቢያ ጋር 1ለ1 አቻ ከተለያዩ በኋላ በቡርኪናፋሶ 4ለ0 እንዲሁም በናይጀሪያ 2ለ0 ተሸንፈው ከውድድሩ ውጭ በመሆን 14ኛ ደረጃ በመያዝ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏቸወን አጠናቅቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው በሁለቱ የምድብ ጨዋታዎች ኳስን  ተቆጣጥሮ ለመጫወት ችሏል። ከኬፕቨርዴ ጋር  44% እንዲሁም  ከካሜሮን ጋር 50%  የኳስ ቁጥጥር  ነበራቸው። ይሁንና በሁለቱም  ጨዋታዎች ላይ በቡድኑ ላይ የተስተዋለው ትኩረት ማጣት፣ የመከላከል ችግርና የልምድ ማነስ ከተፎካካሪነት አውጥቶታል። ከኬፕቨርዴ ጋር በተደረገው ጨዋታ የቡድኑ አጨዋወት ቅጥ የሌለውና  ወደ ግብ መድረስን ያላሰበ ነበር። ዋልያዎቹ የሚይዟቸውን ኳሶች ወደ ተቃራኒን ግብ ክልል ይዞ ከመግባት ወይም ወደ ግብ ከመሞከር ይልቅ በቅብብሎሽ ጊዜያቸውን ሲያባክኑ ነበር። በርካታ አጋጣሚዎች ላይም ኳሶቹን ያለአግባብ በመጠለዝም አበላሽተዋል። በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ደግሞ ዋልያዎቹ በማራኪ ኳስ አጨዋወት በ4ኛው  ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠራቸው የሚያስደንቅ ቢሆንም በቀጣይ ውጤታቸውን ለማስጠበቅ እንደ ቡድን የፈጸሙት ተግባር የሚያረካ አልነበረም። ከአዘጋጇ የካሜሮን  ቡድን ጋር 1ለ1 አቻ ሆነው ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል። ለ2ኛው ግማሽ ወደ ሜዳ ከተመለሱ በኋላ ግን የሚጠበቀውን መስዋእትነት ሊከፍሉ አልቻሉም።  በጨዋታው ላይ በተጋጣሚያቸው እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት አድርገው ባለመከላከላቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል። የማይበገሩት አንበሶች የኢትዮጵያን የተከላካይ መስመር ድክመት ባገናዘበ መልክ  ጎሎችን አከታትለው በማስቆጠር ድል አድርገዋል።
በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የኢትዮጵያ ቡድን ባደረጋቸው ሁለቱም የምድብ ጨዋታዎች ምርጥ ብቃቱን ያሳየው የግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ነው። ከኬፕቨርዲ ጋር  በተደረገው ጨዋታ ከ3 በላይ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን ያዳነው ተክለማርያም፣ ከካሜሮን ጋር በተደረገው ጨዋታውም በተመሳሳይ ማራኪ ትኩረትን በማሳየት ዋልያዎቹን ከከባድ ሽንፈት ታድጓቸዋል።
የካፍ ድረገጽ ባወጣው አሃዛዊ መረጃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአዘጋጅነት ከተሳተፈባቸው የአፍሪካ ዋንጫዎች ውጭ በሌሎች አገራት በተካሄዱ የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ በመሳተፍ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች በ15 ጨዋታዎቹ ተሸንፎ  በሁለቱ  ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። ከሜዳው ውጭ በአፍሪካ ዋንጫ በመሳተፍ ያሸነፈው ብቸኛ ግጥሚያ በ1963 እ.ኤ.አ ላይ ቱኒዚያን 4 ለ 2 የረታበት ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የውጤት ታሪክን 11VS11 የተባለ ድረገጽ እንደተነተነው ከ1943 እ.ኤ.አ  ወዲህ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ከ411 በላይ ጨዋታዎችን አድርጓል። 146 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ፣ በ84 አቻ ተለያይቶ በ171 ጨዋታዎች ተሸንፏል።
የአፍሪካ ዋንጫው ሲጀመር ከ130 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ትኩረታቸውን ወደ ብሄራዊ ቡድኑ ማድጋቸው ይታወቃል። ብዙዎቹ ደጋፊዎች ዋልያዎቹ ከምድባቸው ጥሩ ተፎካካሪ ሆነው በመገኘት ወደ ጥሎ ማለፍ ምዕራፍ መሸጋገራቸውን ጠብቀዋል። በብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የሚመዘገብ ውጤት የአገሪቱን አንድነት ያጠናክራል በሚልም ተስፋ ያደረጉ ጥቂት አልነበሩም። የዋልያዎቹ ስብስብ ከመላው አገሪቱ በተሰበሰቡ ተጨዋቾች እንደተገነባ ይታወቃል።
ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለዶቼቬሌ በሰጠው ልዩ ቃለ ምልልስ በጉዳዩ ላይ ሲናገር “አንዳንዶች የፖለቲካ ችግሮችን ከቡድኑ ጋር ለማያያዝ ቢሞክሩም፤ እኛ ግን እንደዚያ አናስብም። ጥንካሬ ይሰማናል፤ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን። እዚህ የተገኘነው ኢትዮጵያን ለመወከል ነው” ብሏል። “አብረን ስንሆን ሁሉም በጋራ ይዘምራሉ። ተጨዋቾቹ በጋራ መዘመራቸው የኢትዮጵያን  አንድነት ይወክላል” በማለትም ተጨማሪ አስተያየታቸውን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የገለጹ ሲሆን “አሁን በውድድር ላይ እንገኛለን። በብዙ ውጣውረዶች ውስጥ አልፈን ነው እዚህ የደረስነው። በአፍሪካ ዋንጫው ላይ መሳተፋችን በራሱ ትልቅ ድል ነው። በውድድሩ ላይ በመገኘታችን የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት ያስችለናል” በማለት ለጀመርመኑ የዜና አገልግሎት ዶቼቬሌ ተናግሯል።
የቀድሞውን የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝና በአሁኑ ወቅት በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን በተመሳሳይ አጀንዳ ላይ ለዶቼቬሌ አስተያየት ሰጥተዋል። “ተጨዋቾች ኢትዮጵያን ሲወክሉ፣ ብሔራቸው ምንም አስፈላጊነት የለውም። ተጨዋቾች ለብሔርተኝነት ፍላጎት የላቸውም። ሁሌም ንግግራቸው ስለአንድነትና ቡድናቸውን የተሻለ ደረጃ ስለማድረስ ነው” በማለት።

Read 8520 times