Saturday, 05 February 2022 11:49

ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት 6 ወራት 28 ቢ.ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ኢትዮ-ቴሌኮም በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ውስጥ 28 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የዕቅዱን 86.4% ማሳካቱ የተገለጸ ሲሆን ይህም ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ6.7% ዕድገት ማሳየቱ ተጠቁሟል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፣ ባለፈው ሰኞ ጥር 23 ቀን 2014 ዓ.ም በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል የኩባንያቸውን የዓመቱን የመጀመሪያ 6 ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ኩባንያው በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ይህን ገቢ ማግኘት የቻለው የደንበኞች የቴሌኮም አጠቃቀምን ለማሳደግና ተሞክሯቸውን ለማሻሻል የሚያስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያዎችን፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም የደንበኞችን ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ ወቅታዊነትን የተላበሱ 23 አዳዲስና 19 ነባር የሃገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን አሻሽሎ ለደንበኞች በማቅረብ፣ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 74.8 ሚሊዮን ዶላር በማግኘትና የዕቅዱን 89.3% በማሳካት ነው ተብሏል።
የተመዘገበው ውጤት፣ በሃገሪቱ በወቅቱ ከነበረው እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር ሲታይ አመርቂ መሆኑ ተጠቁሟል።
ኩባንያው የገቢ አማራጮችን ከማስፋት በተጨማሪም የወጭ ቅነሳ ስትራቴጂ በመቅረጽና ተግባራዊ በማድረግም፣ በ6 ወራት ውስጥ ከ1.2 ቢ. ብር በላይ ወጪ መቀነስ  መቻሉ ተመልክቷል።
በኢትዮ ቴሌኮም የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት፤ በአገሪቱ ከተከሰተው ችግር ጋር በተገናኘ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ 3 ሺ 473 የሞባይል ጣቢያዎች ላይ የአገልግሎት መስተጓጎል የተፈጠረ ሲሆን በዚህም ሳቢያ 3.67 ቢሊዮን ብር አጥቷል፡፡ በጦርነቱ በተጎዱና እስካሁን መድረስ በተቻለባቸው አካባቢዎች ላይ የወደሙ ንብረቶችን ለመተካትና አገልግሎቱን ለማስጀመር 328.9 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉ ተጠቁሟል።
አሁንም በጸጥታ ችግር ምክንያት ትግራይ ክልልን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት መስጠት ያልተቻለባቸው ወረዳዎች እንደሚገኙ ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አልተቻለም ብሏል።
በቅርቡ የተጀመረውን የቴሌብር አገልግሎት በተመለከተ፣ ከኢንዱስትሪው ልምድ በተለየ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ13 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት አጠቃላይ የግብይት መጠኑ 5.1 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተጠቁሟል። የቴሌብር አገልግሎትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግና የኩባንያው አጋሮችንም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እስካሁን ድረስ ከ46 ሺ በላይ ኤጀንቶችና ከ11 ሺ በላይ ነጋዴዎች ተሳታፊ ሆነዋል ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪም ከ11 ባንኮች ጋር የኢንተግሬሽን ስራ ተጠናቆ ከባንክ ወደ ቴሌብር ገንዘብ ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን ከ8 ባንኮች ጋር ከቴሌብር ወደ ባንክ ዝውውር ማድረግ እንደተቻለ ተነግሯል፡፡
ኩባንያው ባወጣው ሪፖርት መሰረት፤ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት 60.8 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከዕቅድ አንጻር የ100% አፈጻጸም ተመዝግቧል ተብሏል። አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የ20% ዕድገት አሳይቷል። በአገልግሎት ዓይነት ሲታይ የሞባይል ድምጽ ደንበኞች ብዛት 58.7 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንክ ደንበኞች 433 ሺህ፣ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 923 ሺህ እንዲሁም የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 23.8 ሚሊዮን  መሆናቸው ታውቋል።
በተጨማሪም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው የኩባንያውን መሰረተ ልማቶች በማስፋፋትና በማጠናከር የኔትወርክ ሽፋንና አቅም እንዲሁም የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አጠቃላይ ሰፊ የፕሮጀክት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በዚህ ግማሽ ዓመት የ4G/LTE የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ በድምሩ 136 ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ተደርገዋል ብሏል። “ደንበኞቻችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል 4G/LTE Advanced በተጀመረባቸው የክልል ዋና ከተሞች የ4G ቀፎ በቅናሽ የማቅረብና አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ የማስተዋወቅ ስራ ተከናውኗል።” ብሏል- ኩባንያው።
 የቢዝነስ ሰፖርት ሲስተም (Next Generation Business Support System (NGBSS)) የማዘመንና የማሳደግ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን ይህም ከደንበኞች ምዝገባ ጀምሮ የቢሊንግና አዳዲስ ምርትና አገልግሎት ለደንበኞች በማቅረብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ ነው ተብሏል፡፡ ፕሮጀክቱ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን ይህን አዲስ ሲስተም በመጠቀም በርካታ ምርትና አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ገበያ ማቅረብ እንደተቻለም ታውቋል፡፡

Read 5673 times