Tuesday, 08 February 2022 00:00

ረዳት ፕሮፌሰር ትንግርቱ ገ/ፃዲቅ በተለይ ለአዲስ አድማስ ክፍል 2

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   • ኢትዮጵያ ብዙ መከራ ያየች፤ የደከማትና የሰለቻት አገር ናት
                • ህዝባችን ህይወቱ ካልተቀየረ አሁንም ጦርነቶች ይቀጥላሉ

           ባለፈው  ሳምንት እትማችን ረዳት ፕሬፌሰር ትንግርቱ ገ/ጻዲቅ ጋር አዲስ አድማስ ጋዜጠኛ  ናፍቆት ዮሴፍ  ጋር ባደረጉት ቆይታ በሀገሪቷ አጠቃላይ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሰፊ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወቃል በዚህም ሳምንት በእነ ስብሃት ነጋ መፈታት “ተረኝነት” የሚባለው ነገር አለ የለም? ጦርነቱ ሲጠናቀቅ የአማራና የትግራይ ህዝብ ግንኙነት ምን መልክ ይኖረዋል በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውናል እንድታነቡት ጋብዘናል፡፡



               ዳያስፖራውን ጨምሮ ብዙዎችን ያስቆጣው ጉዳይ የእነ ስብሃት ነጋ ከእስር መለቀቅ ነው፡፡ የእነሱ ከእስር መፈታት በጦርነቱ የተከፈለውን አጠቃላይ መስዋዕትነት ዋጋ ቢስ የሚያደርግ ነው የሚል ቅሬታ ተሰምቷል፡፡ አንተስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አለህ?
መልካም እንግዲህ በነዚህ ሰዎች መፈታት ዲፕሎማሲያዊ ድል ተገኝቶበት ይሆናል። በዲፕሎማሲው ዘርፍ መንግስት ውጤት አግኝቶበት ይሆናል፡፡ ፖለቲካዊ ድል አይደለም፤ እነዚህን ሰዎች ከእስር መልቀቅ ፖለቲካዊ ድል ያስገኛል የሚል እምነት የለኝም፡፡ እንዳልኩሽ ግን በተወሰነው መልኩ የዲፕሎማሲ የበላይነት  ወይም የዲፕሎማሲ ድል ሆኖ ሊቆጠር  የሚችልበት ሁኔታ አለ፡፡ ለአጭር ጊዜ ማለቴ ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ ግን የወያኔን ባህሪ ለሚያውቅ ሰው ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡ ያኔ ስብሃት ሲያዝ “አርክቴክቱ ስብሃት ነጋ በቁጥጥር ስር ዋለ” ብለን ነበር የዘገብነው፡፡ በእርግጥ ውሳኔ ሰጪ ወይም አሁን ላይ ማስተር ማይንድ ናቸው እያልኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከባድ ሌጋሲ ነው ያላቸው ግለሰቡ፡፡ በህይወት መኖራቸው በራሱ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አለ፡፡ በጋብቻ በዝምድና የተሳሰሯቸው ሰዎች ናቸው የትግራይን ኢምፓየር የሚመሩት። የትግራይ ህዝብ በዚህ ሰውዬ ቁጥጥር ስር ነው ያለው፡፡ ስብሃት የትግራይ ህዝብ አድራጊ ፈጣሪ ነው፡፡ #ኧረ እሳቸው እኮ ይሄ ውሳኔ ሲወሰን የሉም” ልትይኝ ትችያለሽ፤ ነገር ግን ስብሃት ግለሰብ አይደለም፤ ተቋም ነው። ስብሃት ግለሰብ ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብ (አይዲዮሎጂም) ነው፡፡ ስለዚህ ትግራይ የእሱ brain child (የአዕምሮ ልጅ) ነች፡፡ አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ የምናየው ሁሉ የእርሱ የአዕምሮ ልጅ ነው፤ ምንም የሚደንቅ አይደለም ልልሽ ነው፡፡ እና እሱን መፍታት በፖለቲካው በኩል ድል አያመጣም፡፡  ነገር ግን ታውቂያለሽ፤ አሁን ያለው መንግስት አንድ ባህሪ አለው፡፡
ምን አይነት ባህሪ?
ያ ባህሪው ምንድነው መሰለሽ? ይህንን ስልሽ በጣም ቅንነት ባለው መንገድ ነው የምናገረው፡፡ ይሄ መንግስት አንድ ነገር ይፈጽምና ህዝብ  ኤክስፕሌይን እንዲያደርግ ይተወዋል፡፡ ራሱ ኤክስፕሌይን አያደርግም - አያብራራም፡፡ ልክ የማኪያቬሊ ዓይነት አካሄድ ይከተላል፡፡ እሱ የሆነ ነገር ይወስንና ህዝቡ ኤክስፕሌይን ያድርግ ይላል፡፡  እኔ እንደ አንድ ተራ የህዝብ አካልና ህዝብ ውስጥ እንደሚገኝ ልጅ ነው ኤክስፕሌይን ለማድረግ እየታገልኩ ያለሁት፡፡ ነገር ግን ይህንን እንዲያብራራ ጋዜጠኞች መጠየቅ ያለባችሁ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ነው፡፡ ለምን ስብሃትን ፈታኸው? ለመሆኑ እሱን በመፍታትህ ያገኘኸው ድል ምንድን ነው? ብላችሁ መጠየቅ አለባችሁ፡፡ የመንግስት ዋና ተግባሩ ተጠያቂነትና ግልጸኝነት ነው፡፡  ተጠያቂነትና ግልጸኝነት (ትራንስፓረንሲ) የዲሞክራሲ ዋና መገለጫዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እናንተ ለህዝብ ግልፅ መሆን አለባችሁ፤ ንገሩን ብለሽ አስገድደሽ መጠየቅ ያለብሽ የፈታውን አካል እንጂ እኔን አይደለም፡፡
ሌላው ጥያቄዬ፣ እስካሁን ለተፈጠረው ኪሳራ ሁሉ ጣታችንን እየቀሰርን ያለነው ህወኃት ላይ ነው፡፡ በእኛስ በኩል እንደ ፌደራል መንግስት ያሉብን ክፍተቶች  ምን ነበሩ? ይሄ ሁሉ ህይወት ሳይጠፋ፣ ይሄ ሁሉ መሰረተ ልማት ሳይወድምና ሊሽር የማይችል ጠባሳ ሳይፈጠር ጦርነቱን የምናሸንፍባቸው እድሎች አልነበሩንም? አንዳንድ ወገኖች፣ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይዘን፣ እንዴት እነሱ ጣርማ በር ድረስ አገር እያወደሙ መጡ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ አንተ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለህ?
ምን መሰለሽ--- መቶ ሚሊዮንና አምስት ወይም ስድስት ሚሊዮን የሚለው ንፅፅር ሁሌም ያስቀኛል፡፡ መቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ እየተዋጋ አይደለም። አምስትና ስድስት ሚሊዮኑን መቶ ሚሊዮኑ ወጥቶ አልገጠመም፡፡ እንደዚያ አይደለም የገጠምነው፡፡ እነሱ እንደ ህዝብ ነው የመጡት፤እኛ ደግሞ ባለን መደበኛ የፀጥታ መዋቅር ነው ለመከላከል የሞከርነው። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ የነበረችበትን ሁኔታ የማይረዳ ሰው፣ ወያኔ ለምን ይህን ያህል ተፅዕኖ ፈጠረ የሚለው ነገር በቀላሉ አይገባውም፡፡ አየሽ ላለፉት 27 ዓመታት ሙሉ የመንግስት መዋቅራችን የትግራይ መዋቅር ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የራሷ መከላከያ አልነበራትም፡፡ የነበረው የትግራይ መከላከያ ነው፡፡ አማርኛም ሆነ ኦሮምኛ የሚናገረው የትግራይ ስርዓት ጠባቂ ዘብ ነው እንጂ የመከላከያ ሰራዊት ሆኖ በነፃነት የሚያገለግል አልነበረም፡፡ በኢኮኖሚ ዘርፍ አገሪቱ ላይ ይሰሩ የነበሩ መሰረተ ልማቶች በዋናነት እንዲጠቅሙ ይደረግ የነበረው ያንኑ የትግራይ አንጃ፣ የስብሃትን ስብስብ ነው፡፡ ለ27 ዓመታት አገሪቱን ይገዛት የነበረው፣ ከላይ እስከ ታች ባሉ የጦሩ ክፍል ውስጥ ባለ አደረጃጀት ሙሉ መዋቅሩን በራሱ ቁጥጥር ስር ያደረገ፣ሰሜን ዕዝ ውስጥ እስከ 40 በመቶ የሚጠጋውን በትግርኛ ተናጋሪዎች የሞላ፣ የሀገሪቷን ወደ 80 በመቶ ያህል ተተኳሽ ወደ ትግራይ ያጓጓዘ፣ የሀገሪቷን በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት የዘረፈና ያሸሸ፣ ሀገሪቷን ለከፍተኛ ዕዳ የዳረገ፣ በጣም በርካታ ጥፋቶችን ያደረሰ ቡድን ነበር፡፡ እኔ ለዚህ መንግስት ለመከራከር አይደለም ይህን የምናገረው፤ ሀቅ ስለሆነ ነው፡፡ ይሄ መንግስትም ብዙ ደካማ ጎን ያለበት፣ አንዳንዴም በጣም ቀሽም የሆነ ስርዓት ሆኖ ታገኝዋለሽ፡፡  ነገር ግን ብዙ መከራዎችንና ውጣ ውረዶችን የተጋፈጠ መንግስት መሆኑም ደግሞ በግልጽ የሚታይና የሚታወቅ ነው፡፡ ይሄ መዘንጋት የለበትም፡፡ ወያኔ እዚህ አገር ላይ የፈጠረው ነገር ኢትዮጵያን አያስቀጥልም ነበር፤ በነገራችን ላይ ዕጣ ፈንታችን መፍረስ ብቻ ነበር፡፡ ወያኔዎችም “እኛ ከስልጣን ስንወርድ አገር ሆኖ የሚቀጥለው ትግራይ ብቻ ነው” ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ሌላው ሁሉ ይጠፋል ብለው ነበር የሚያምኑት፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያን ማስቀጠል በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ አሁን ያሉት ውጣ ውረዶች ቢኖሩም እንኳን ኢትዮጵያን ማስቀጠል ትልቅ ራስ ምታት ነው፡፡ ብዙዎች ይህንን ይዘነጋሉ። ምን አይነት አገር ነው የተቀበልነው? ፋይናንስ ነበረው? ብሔራዊ ባንክ ምን ያህል የዶላር ክምችት ነበረው? ሀገሪቷ በምን ያህል እዳ ነው እስከ እናቷ የሠጠመችው? የህዳሴው ግድብና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች በምን ደረጃ ላይ ነበሩ? የሀገሪቷ ግንኙነት፣ የፀጥታ ዘርፍ፣ መከላከያው፣ ከቀበሌ እስከ ላይ የነበረው ኔትወርክ፣ በክልሎች መካከል የነበረው ሁኔታ ሁሉ ምን ይመስል ነበር?
ይህንን ሁሉ ለመፍታትና ለማስተካከል መሞከር አይደለም በዚህ ሁኔታ ውስጥ የነበረችን አገር ሀላፊነት ወስዶ መቀበል በራሱ ቀላል አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ አምስት ስድስት መሪዎችን ከሥልጣን እንዲለቁ ሊያስደርግ የሚችል ችግር ነው እዚህ አገር ያለው፡፡ ሱዳንን ተመልከቺ፤ ሀምዶክ አልበሽር ተክሎት የሄደውን ነገር አስወግዶ መቀጠል አቅቶት ስንት ጊዜ ነው ሪዛይን ያደረገው? ግሪክን ውሰጂ፤ በ2008 ዓ.ም የኢኮኖሚ ቀውስ በተፈጠረ ጊዜ ስንት ጠቅላይ ሚኒስትር ነው የተቀየረው። አንድ ሥርዓት ከአንዱ ወስዶ ማስቀጠል ቀላል አይደለም፡፡ ያውም ከሌባና ዘራፊ ላይ አገርን ተረክቦ!
ሙሉ በሙሉ የተዘረፈንና የወደመን አገር ማስቀጠል ከባድ ነው፡፡ ይህን የወደመና የተዘረፈ አገር ተረክቦ ለማስቀጠል በተደረገ ጥረትና ሂደት ውስጥ ማለትም ባለፉት ሶስት ዓመታት ብዙ ህይወት ጠፍቷል፡፡ ምክንያቱም አዲስ የምታመጪውም ቡድን ከቀደመ አስተሳሰቡ የፀዳ አይደለም፡፡ አዲስ ነው ብለሽ አምጥተሽ አሰልጥነሽ ስትሾሚው፣ በሀገር ወጪና ኪሳራ ሆዱንና ከርሱን መሙላት ነው የሚያስቀድመው፡፡ ከሀገር ክብር በላይ የራሱ ሆድ ይታየውና በፍጥነት ሌብነት ውስጥ ይገባል፡፡ ትቀይሪዋለሽ፤ የሚመጣውም ያው ተመሳሳይ ይሆናል፤ እንደገና ሌላ ገዳይ ስኳድ ይመጣል፡፡ ወያኔ’ኮ ትውልድ ነው ያጠፋብን፡፡ ለምሳሌ አሁን ላይ ሀገር አቀፍ ምክክር እናደርጋለን እያልን ነው፡፡ ማነው ሽማግሌያችን? ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካዎች ዴዝሞንድ ቱቱ ነበራቸው፡፡ የእኛ ዴዝሞንድ ቱቱ ማን ነው? ብሔር መርጠው የሚያለቅሱ የሀይማኖት አባቶች አይደሉም እንዴ ያሉን? ስለዚህም ማን ነው የሚያስታርቀን? የትኛው ተቋም ነው በብሔር ያልተበከለው? የትኛው ነው ንፁህ? የሆነ ቦታ ላይ ማንን እናስቀምጥ? ሁሉም ቀጣፊ፣ ሁሉም ገዳይ፣ ሁሉም ዘረኛና ወገንተኛ ሆነ፡፡ ምራ ብለሽ ከተማ  ስትሰጪው፣ ዘረኛና ጎጠኛ ሆኖ የሠፈሩን ልጆች ሊሰበስብ ይፈለጋል፡፡ በችሎታ መመራት ያለባቸውን ቦታዎች በደምና በጎሳ ሊመራ ይፈልጋል፡፡
ስለዚህ ቢሮክራሲው ወድቋል፤ ሀገሪቱ ውስጥ፡፤ ወያኔ ሙሉ ስትራክቸሩን ስልቅጥ አድርጎ ነው የበላው ትውልድን፣ትምህርቱን፣ተቋሞቻችንን….ሁሉንም ነው ያጠፋው፡፡ ስለዚህ የሀገር መከታ ማን ነው? አገርሽን ለአንድ ግለሰብ ሰጥተሸ ስታበቂ አፋጣኝ መፍትሄ እንዴት ትጠብቂያለሽ? ሀገሪቱኮ ተቋም የላትም!! እንደ ህዝብ ቆመን ነው ት/ቤቶቻችንን መስራት ያለብን፤መከላከያችንን መገንባት ያለብን፡፡ ሀገር አልነበረንምኮ፤ በግልጽ የወደቅን ሀገር ነበርንኮ፡፡
አሁን አገሪቱ ላይ ብዙ ነገሮች አያለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳንዴ የሚስቱት ነገር አለ፣የእርሳቸው ካቢኔዎች፣ ሚኒስትሮቻቸው የክልል አመራሮች ላይ ችግሮች አሉ፣ ዜጎች ይፈናቀላሉ፤ ነገር ግን እኔ አንድን ግለሰብ ብቻ አልወቅስም፤ ጣቴንም አልቀስተርም። እኛ ሀገራችንን ለዚህ አጥፊ ቡድን አሳልፈን ሰጥተን በባርነት ስንኖር የነበርን ህዝቦች ነን። በዚህ ሂደት  ውስጥ ብዙ ችግርና መከራ ተፈጥሯል። የኢትዮጵያ ህዝብ ያንን ስለተረዳ ለዶ/ር ዐቢይ አህመድ ድጋፍ አድርጎለታል። እስከ ሌሊቱ ስምንትና ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ተሰልፎ መርጦታል፡፡ ህዝቡ የኢኮኖሚ ቀውሱንም ተቋቁሟል፣ ለጦርነቱ ልጅህን ስጥም ሲባል ሰጥቷል፤ ህይወቱንም ሰጥቷል፤ በአጠቃላይ ህዝቡ ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ያ ዋጋ የተከፈለው ለኢትዮጵያ ነው እንጂ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አይደለም ሀገራችንን ለማሻገር የከፈልነው ዋጋ ነው። ይህንን ዋጋ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ልክ ዋጋ እንደሚሰጡት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጦርነትን፣ መዋረድን፣ መፈናቀልንና ችግርን ችለን አንዳንዴ አብረን እንድንኖር የሚያደርገን፣ የኢትዮጵያ የሀገራችን ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ መስዋዕትነት ሀገር እንድትቀጥል ካለን ፍላጎት እንጂ የተወሰኑ ሰዎችን ወደ ስልጣን አምጥቶ የእኛ ጊዜ ነው እያሉ እንዲፈነጩብን አይደለም ለማለት ነው፡፡
አንተ “ተረኛ ነን” ባዮች ህዝቡን እያማረሩ ነው ስለሚባለው ምን ትላለህ?
ምን መሰለሽ ….ተረኝነት የሚለውን ቃል ማን እንደፈጠረውና እንዴት ሌብል እንደተደረገ አላውቅም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ ሀገሩን፣አንድነቱንና ፍቅሩን የተነጠቀ ህዝብ ስለሆነ ቶሎ ይደነግጣል፤ ቶሎ ይከፋዋል፤ ቶሎ ይደነብራል፤ እና ነገሮችን አያምንም፡፡ በዚህ ጉዳይ በነገራችን ላይ መንግስት በጣም መጠንቀቅ አለበት፡፡ ምክንያቱም በህዝብ ላይ አመኔታን መፍጠር ቀላል ነገር አይደለምና፡፡ ተቋማዊ እምነት ከሌለ አገር አይቀጥልም፣ሰው በሚሰራበት ተቋም ላይ እምነት ከሌለው፣ሰው አብሮት ከሚሰራው ጋር እምነት ከሌለው፣በጋራ እንደ ሀገርና እንደተቋም መተማመን ከሌለ ከባድ ነው፡፡ ያንን አመኔታ ማምጣት ደግሞ የመንግስት ቀዳሚ ሚና መሆን አለበት፡፡ መንግስት ማድረግ ያለበት ድጋሚ እንደ ወያኔ እንደማይሰርቀንና እንደማይዘርፈን በተግባር ማሳየት ነው እንጂ “ከወያኔ ተቀብለናል፤ ምንም አታመጡም” የሚል አይነት መበሻሸቅ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡
ሌላው ምን መሰለሽ የተፈጠረ ናሬቲቭ (ተረክ) አለ-የተረኝነት ናሬቲቭ የሚል፡፡ ይህን ናሬቲቭ በትክክል መሬት ላይ ያለው እንደዛ ነው ወይ ብሎ በማስረጃ መሞገት ተገቢ ነው፡፡ በፋክት መሞገት አስፈላጊ ነው፡፡ እንደዛ አይነት ለውጦች አሉ፣ “የኦሮሞ የበላይነትን ለማምጣት የሚድረጉ ነገሮች አሉ” እያሉ አቤቱታ የሚያነሱ አሉ፡፡ እነዚህ ትንንሽ  ቅያሜዎች አይደሉም። በህዝቡ መካከል የሚኖረውን መተማመን ይጎዳሉ፡፡ ስለዚህ መንግስት እነዚህን ነገሮች መፈተሽና በትክክልም እየሆኑ ከሆነ፣ ነገ ውጤቱ ተመሳሳይ ስለሚሆንና ዞሮ ዞሮ እዛው ጦርነት ውስጥ ስለሚከተን ከነዚህ አይነት መጠለፎች ህዝቡንም አገርንም መታደግ አለበት፡፡ ቀደም ብዬ ነግሬሻለሁ፤ ከየትኛውም ቦታ ሰው አምጥተሽ አንድ ቦታ ላይ ብትሾሚ ከወያኔ አስተሳሰብ የፀዳ አይደለም። ሌብነትን፣ ወገንተኝነትንና አድሎአዊነትን ሲለማመድ የኖረ ነው፡፡ ወያኔ‘ኮ ሆን ብሎ ሌብነትን የኢትዮጵያ እሴትና መገለጫ አድርጎታል። ዘረኝነትም የእሴታችን አካል ሆኗል እኮ። በየቢሯችን‘ኮ የምናመጣቸው የአማራም፣ የኦሮሞም፣የትግሬም፣ የሶማሌም የጋምቤላም፣ የአፋርም የሁሉም ልጆች ናቸው። ነገር ግን ወያኔ ነው ያሳደጋቸው፡፡ በወያኔ ተቋማት ውስጥ በአንድም በሌላም ስንሰራ የነበርን ነን እኮ! ስለዚህ እንዴት ሆነን እንዴትስ አድርገን ዜጎችን በእኩልነት እናገልግል? ያ ልምምድስ ገና መች መጣ? ገና በጣም ብዙ ትግል ይጠይቃልኮ! ሚዲያዎቻችንን ማጠናከር ይጠይቃል! ገና ብዙ የምናጠናክራቸው ነገሮች አሉብን፡፡
ኦሮሞ ስለሆነ ብቻ ተረኛ ነው፣ ትግሬ ስለሆነ ብቻ ጁንታ ምናምን ነው እየተባባሉ በመፈራረጅ የሚገነባ ሀገር የለም፡፡ ይልቅ  ስህተቶችን በፋክት አስደግፎ የመንግስት ተቋማት ታማኝ እንዲሆኑ፣ለህዝብ ተጠያቂ እንደሆኑ ማድረግ ነው የሚያስፈልገው። በዋናነት የተረኝነት አዝማሚያ የሚያሳዩና እንደዚህ የሚያደርጉ ሰዎች፣ የኦሮሞን ህዝብ አይጠቅሙትም፤ የኦሮሞ ህዝብ አቅም የሌለው ህዝብ አይደለም፡፡ ልጆቹን አስተምሮ አርሶና ነግዶ እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ “ግባ ያንተ ተራ ነው” የምትይው ሳይሆን እንደሌላው ህዝብ ተወዳዳሪ የሆነ ህዝብ ነው፤ በተፈጥሮው ማለቴ ነው፡፡ ተወዳዳሪ የሆነ ህዝብ እንዲጦር አይፈልግም። አንጡርህ ካሉት እየገደሉት ነው፡፡ ነገ ጦርነት ነው የሚያስቀምጡለት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ያንን ያደርጋሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡
ነገር ግን አሁን በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ባንዲራ ያዛችሁ ተብሎ የሚደረግ ነገርና ማዋከብ፣አንዳንዴም በሀይማኖት በኩል ሀላፊነት የጎደለው የፖለቲካ ንግግር ተገቢ አይደለም፡፡ በአርአያነት ህዝብን መምራት ትልቅ ነገር ነው፡፡ የፖለቲከኞች ሚናም መሆን ያለበት ይሄ ነው፡፡ እኔን የሚደግፉኝን ሰዎች ብቻ እያስደሰትኩ  መቀጠል ፖለቲካ ሳይሆን ድንቁርና ነው፡፡ ፖለቲካ ማለት በሀሳብ የማይመስሉኝን ማሳመን መቻል ነው፡፡ የፖለቲካ ሀሳቤን መሸጥ መቻሌና ሌሎች የኔን ሀሳብ ከደሜና ከብሔሬ ወይም ከሀይማኖቴ በላይ አስበው “የተሻለ የፖለቲካ ሀሳብ አለው፤ ስለዚህ እኔም የዚህ ሀሳብ አካል ነኝ እንዲሉ ማድረግ ነው -ፖለቲከኛነት፡፡                                                                                                                                                 ከዚያ ውጪ ያለው ትራይባሊዝም (የጎሳ ስርዓት) እንጂ ፖለቲካ አይደለም፡፡ ስለሆነም ፖለቲካ ለመገንባት ራሳችንን ከእንደነዚህ አይነት የጎሳዊ አስተሳሰብ ነፃ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ተቋሞቻችንንም ብሔርን ሳይሆን የሰው ልጅን እንዲያገለግሉ አድርገን መገንባት አለብን፡፡ አንቺና አንድ ቻይናዊ አንድ መሥሪያ ቤት ብትሄዱ እኩል የምትገለገሉበት ሀገር እንዲሆን ነው መስራት  ያለብን፡፡ ከዚያ ውጪ ግን “የእንትን ብሔረሰቦች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል” የሚል አስቂኝ የሆነ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመጣ አንፈልግም። ከእንደነዚህ አይነት ነውሮች መንግስት ብዙ የተማረ በመሆኑ እነዛን ነውሮች ስርዓት አድርጌ እቀጥላለሁ ይላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አየሽ ወያኔ ስርዓት ስላልነበረው፤ ነውር ስርዓት አድርጎ ቆይቷል፡፡ አሁን ያንን ማስቀጠል አይቻልም፡፡
መንግስት እንዴት ነው ራሱን ከሌቦችና ዘረኞች የሚያጸዳው?
ዞሮ ዞሮ የውስጥ ትግል ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን መፈራረጅ አሁንም ተገቢ አይደለም፡፡ በጣም ጄኒዩን የሆኑ ኢትዮጵያዊያን አሉ ሀገራቸውን የሚወዱ፡፡ ከተባበርን ብዙ ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ ይሄ ለውጥና ሥርዓት የመጣው በኢትዮጵያዊያን መስዋዕትነት ነው፡፡ ማነው ተራን የሰጠው? ማን ነውስ ተረኛ? የተከፈለው መስዋዕትነትና የተደረገው  ትግል አንድ ብሔር ነቅሎ ሌላ ብሔር ለመትከል የተደረገ አይደለም፡፡ ትግሉን በዚያ መልኩ ናሬት የሚያደርጉት ሰዎች እንዲመጣ የሚፈልጉት ያንን ስለሆነ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ይሄንን ሌብሊንግ (ፍረጃ) ወያኔ ጋር አገኘዋለሁ፡፡ ነገር ግን አንቺ እንዳልሽው ለሁሉም ፍረጃ ተጠያቂ ወያኔ ነው ማለትም መኖር የለበትም፡፡ እኔ የወያኔን ባህሪ እረዳለሁ፡፡ በሁለት ህጻናት ፀብ መካከል እንኳን ወያኔ ሊኖር የሚችልበት እድል ከፍተኛ ይሆናል፤ አትጠራጠሪ፤ ነገር ግን የመንግስት መዋቅሮች ሊጠለፉ ይችላሉ፤  ስለዚህ መንግስት ከእነዚህ አስነዋሪ ተግባራት ራሱን ማቀብ አለበት፡፡ ሪፎርም ማድረግ አለበት። ጠንካራ አደረጃጀቶችን መፍጠር አለበት። በተለይ ህዝቡ ተቋሞቹን እንዲገመግም እድል መስጠት አለበት፡፡ በየአካባቢው አካታች የሆነ ታማኝ የአስተዳደር ሥርዓት መኖር አለበት፡፡ በየመስተዳደሩና በየከተሞቹ የህዝብ ተሳትፎን ማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡ ህዝብ ዘረኛውን፣ሌባውን ቀጣፊውን እያሳለፈ እንዲሰጥ መድረኩን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡
ህዝባዊ ትግል ካላደረግሽ መንግስት በራሱ “ቼክ ኤንድ ባላንስ” የራሱን ዘረኞች፣ሌቦችና ተረኞችን ነቅሎ ማውጣት አይችልም፡፡ “Give the power to the people” ህዝብ በየሰፈሩ ይሰበስብ፣የደረሰበትን በደል፣ የመጣውን ልማት፣ ያልመጣውን ልማት ኦዲት የሚያደርግ ይሁን፡፡ ህዝብ ላይ የሚያርፍ ነገር ግልፀኝነትንና ተጠያቂነትን ስለሚያመጣ ማለቴ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉንም እገመግማለሁ ቢሉ የማይሆን ነገር ነው፤ አይችሉትም፡፡ ህዝቡን በማብቃት፣ ሚዲያውን በማጠናከር፣ በማንቃት አጓጉል አሰራሮች ካሉ መዋጋት ይቻላል፡፡ እንዳልሽው የተረኝነት ነገር እናምጣ ቢባል፣ ያንን ታግሰን የምናስቀጥልበት እድል አሁን የለም። ኢትዮጵያ ብዙ መከራ ያየች የደከማትና የሰለቻት አገር ናት፡፡ በጣም የሚገርመኝን ልንገርሽ፡፡ ይሄ አገር ከድሆች ላይ የሚዘረፍበት አገር ነው፡፡ እናም ህዝባችን በአስነዋሪ ድህነት ውስጥ እንዲኖር አድርገን ነው እኛ ስለ ተረኝነት የምናወራው፡፡ ስለ ሀብትና ስልጣን መቀራመት የምናወራው! ያለንበት የድህነት ደረጃ በጣም  አስነዋሪ ነው። ይሔ በደንብ መታወቅ አለበት፡፡ እንኳን እንደዚህ ተባልተን አይደለም ሌት ተቀን ሰርተንም ይህንን ህዝብ ከድህነት ለማውጣት እንቸገራለን፡፡ እናም ባለስልጣኖቹ ቢያስቡበት መልካም ነው። ያለበለዚያ ግን መንግስት የሚባለው ፅንሰ ሀሳብ ኢትዮጵያ ውስጥ አደጋ ላይ ይወድቃል። ሶማሌ ላንድ ላይ እንደዛ ነው የሆነው፡፡ መንግስታቸው ደካማ ነው። ለምን ደካማ እንዳደረጉት ታውቂያለሽ? ጠንካራ መንግስት ከሆነ ሁሉም ለመዝረፍ እርስ በእርስ ይዋጋል፤ ወደ ስልጣን እኔ ነኝ የምመጣው” እያለ፡፡ ከዚያ መንግስታቸውን ደካማ አደረጉትና ተውት፡፡ እንደዚያ አይነት መንግሰት ቢሆን ኖሮ ወያኔ አይወጋንም ነበር፡፡ መንግስት ሀብታም ስለሆነ ነው ወያኔ የሚወጋን፡፡ መንግስት መሆን ምን ማለት እንደሆነ ስለሚያውቀው ነው የሚወጋን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ የደኸየ ህዝብና በጣም ሀብታም ባለጸጋ መንግስት ነው ያለው፡፡ ይሄ ለትልቅ ጦርነት ምክንያ ነው፡፡ ህዝባችን ህይወቱ ካልተቀየረ አሁንም ጦርነቶች ይቀጥላሉ፡፡
የማህበረሰብ አንቂ ነን የምንል ሰዎች ደግሞ ለህዝቡ የምንቆረቆር ከሆነ ህዝቡ ያለበትን ሁኔታ መረዳት አለብን። ህዝባችን ዳቦ ይፈልጋል፣ ለውጥ ይፈልጋል፣ ኑሮውና አኗኗሩ እንዲሻሻል ይፈልጋል፣ በሰላም ወጥቶ መግባት ይፈልጋል፣ ሰላምና ክብሩን ማስጠበቅ ይፈልጋል። እየተዋረደ፣ እየተገደለና በድህነት እየተሳደደ መኖር አይፈልግም። ይሄ ነገር በጣም ታክቶታል። ስለዚህ እላይ ያለን ሰዎች ታች ያለውን ህዝብ ለመቀየር ካልሆነ የምንሰራው በአደጋ ውስጥ  ነን ማለት ነው።
ሌላው የብሄር ግጭት ኢንተርፕረነሮች አሉ፤ በሁሉም ቦታ ላይ ማለት ነው። አክቲቪስት ነን ይላሉ። ለምሳሌ የአማራ አክቲቪስት ነን የሚሉት የኦሮሞን ህዝብ መሳደብ ነው ስራቸው። ለአማራ ህዝብ ኦሮሞ እንደዚህ አደረገ ብሎ በመሳደብ የአማራን ህዝብ የፖለቲካ ጥያቄ የፈቱ ይመስላቸዋል። የኦሮሞ ጠበቃ ነኝ የሚለውም አማራን በመስደብ ነው ኦሮሞን ነጻ የሚያወጣ የሚመስለው። ነገር ግን የአማራም የኦሮሞም የጋራ ጠላት አስከፊ ድህነት ነው። የሰው ልጅ በምድር ላይ እንዲህ ሆኖ ይኖራል ተብሎ ሊገመት በማይችል ደረጃ ነው የድህነታችን ደረጃ። ሀብት ላይ ተቀምጠን ሀብት ይዘን ማለት ነው። ምክንያቱም በጋራ ሰርቶ በጋራ ለምቶ ለመኖር የሚያበቃ ማህበራዊ አንድነትና ስምምነት ላይ መድረስ ስላልቻልን!!
እንደኔ እንደኔ ኦሮሞን በመስደብ የሚገኝ የአማራ ክብርም ሆነ የፖለቲካ ከፍታም የለም። አማራን በመውጋትና በመግደል ትግራይ ነጻ አይወጣም። ብልህ የኦሮሞ ፖለቲከኛ የአማራን ህዝብ ድጋፍ መሻት ነው ያለበት። ብልህ የአማራ ፖለቲከኛ አብዛኛውን የኦሮሞን ህዝብ ማስተባበር የሚችል ሀሳብ ነው ማፍለቅ ያለበት። የትግራይንም ህዝብ እንደዛው። ይህ ካልሆነ አሁንም በድንቁርና መቀጠል ነው። ምርጫው የእኛ ነው።
ይሄ ጦርነት በምን መልኩ እንደሚጠናቀቅ መተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን ደግሞ አንድ ቀን መቋጨቱ አይቀርም፡፡ ታዲያ በዚህ መልኩ ደም የተቃባው አማራና የትግራይ ህዝብ የወደፊት ግንኙነት አያሳስብም? የአፋርም ህዝብም ተመሳሳይ ነው…
ጥሩ ጥያቄ ነው። እውነት ነው ያስጨንቃል። በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ ከደረሰው በደል አንጻር እንዴት አድርጎ ዳግም ከትግራይ ህዝብ ጋር ይኖራል የሚለው ያስጨንቃል። ወያኔ ለትግራይ ህዝብ የሚፈጥርለት ጠላት እንጂ ቴክኖሎጂ አይደለም። በየቦታው ከላይም ከታችም ከጎንም ያናክሰዋል። ከሰማይ ከፈጣሪም ያጣላው ይመስለኛል። ምክንያቱም ጥምቀትን አትወጣም፤ አታከብርም እያለ ይከለክላል። በእውነቱ እነዚህ እነዚህን ነግሮች ሳስብ፣ በጣም  ቁርጠኛ የሆኑ ልጆች ያስፈልጋሉ። ለምሳሌ እኔ በበኩሌ የአማራና የትግራይ ሀዝብ እንደ ህዝብ መሰረታዊ ቅራኔ አለበት የሚል እምነት የለኝም። የቅራኔው መሰረት ግን አመራሮቹ ናቸው። ወያኔ በአማራ ላይ የፈጸመው በደል በዓለም በገሃድ የታየ ነው። ይህን ሪኮግናይዝ ማድረግ ያስፈልጋል።
በነገራችን ላይ እኔ ከጦርነቱ በፊት ይመስለኝ የነበረውን ነገር ልንገርሽ፡፡ ወያኔ “ኢትዮጵያን ልውጋት” ሲል የትግራይ ህዝብ “የለም አትወጋም” ብሎ ይቃወመዋል ብዬ ነበር። እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙ ሰዎች እንደዛ እንጠብቅ ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ እንደዛ አልሆነም። የትግራይ ህዝብ ራሱ የጦርነቱ አካል እንዲሆን “ለጦርነቱ ልጅህን የማትሰጥ ባንዳ ነህ” ተብሎ ተፈርጆ፣ ህዝቡን በዚህ ውስጥ እንዲሳተፍ አድርጎታል። ለዚህ ነው ቀደም ሲል መቶ ሚሊዮን ህዝብ ከ6 ሚሊዮን ህዝብ ጋር አልተዋጋም ያልኩሽ።
እኛ ኢትዮጵያዊያን የትግራይን ህዝብ አይደለም እየተዋጋን ያለነው። ያኛው ነው (ህወሃት) ያገኘሁትን ሁሉ እወጋለሁ የሚለው። ስለዚህ እኛ ባንድ የጸጥታ መዋቅር በጣም በሰለጠነ መንገድ፣ ወንድማማችነትን በሚያሳይ መልኩ ነው ራሳችንን እየተከላከልን ያለነው፡፡ የምንማርካቸውን ልጆች ለመንከባከብ ጥረት እያደረግን ነው ያለነው። አንቺ እንዳልሽው ችግሩ ጦርነቱ እንደሚጠናቀቅ ደንቆሮዎች አያምኑም። አምስት መቶና አንድ ሺህ ዓመትም እንዋጋለን ብለው  ነው የሚያስቡት የእነሱ ሀሳብና ልምምድ ከንቱ እንደሆነና እንደሚያልፍ አይረዱም ፤በዚህ ምክንያት ጦርነቱ እንደሚጠናቀቅ አያምኑም።
የሆነ ሆኖ ሁለት ምርጫ ነው ያለው። አንደኛ ወያኔ ሙሉ ለሙሉ እጅ መስጠትና መሸነፍ፤ ሽንፈቱንም አምኖ ራሱን አሳልፎ መስጠት ነው ያለበት። ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ ወያኔ ለኢትዮጵያ ሊውል የሚችለው ውለታና ሀገሪቱን እዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ከከተታት በኋላ ሊያደርጋት የሚችለው አንዲት በጎ ነገር አለች። ራሱን አሳፎ መስጠት ነው የሚሆነው፡፡ አንደኛው ይሄ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የትግራይ ህዝብ ራሱን ከዚህ ቡድን ነጻ ማውጣት አለበት፣ መታገል አለበት፣ የታጠቀውን መሳሪያ ወደ ወያኔ ማዞር አለበት። ይሄ በጣም ጠቃሚ ነው። ከዚያ በኋላ ከአማራ ህዝብ ጋር ለሚኖረው ግንኙነት የትግራይና የአማራ ህዝብ ይወስናሉ። ልሂቃኑና አክቲቪስቱ አይደሉም የሚወስኑላቸው። ህዝብ ተቋማቱን አስተባብሮ መገናኘት አለበት። ይሄ ወደፊት ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ይሄ ሁሉ በአማራ ህዝብ ላይ የደረሰውን ጥፋና በደል የትግራይ ህዝብ መጥቶ እንዲያይ ማድረግ ያስፈልጋል። ለምንድነው የትግራይ ህዝብ መሪ ጠላት ብሎ የፈረጀን ብሎ የአማራ ህዝብ የሚነጋርበት ጊዜ ይመጣል ብዬ አስባለሁ።
ሶስተኛ አማራጭና ዋነኛው አማራጭ ሊሆን የሚችለው ግን ይህንን ቡድን በሃይል ማንበርከክ መቻል ነው። ለዚህ ደግሞ መንግስት በቂ ዝግጅት እንዳደረገ በቅርቡ ጀነራሉ የተናገሩትን ሰምተናል። በሀይል ወያኔ  ትጥቅ እንዲፈታ ማድረግና ህዝቦቹን ነጻ አውጥቶ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እርቅ፣ ውይይት፣ መካስ ያለበት እንዲካስ ማድረግ፣ ለፍትህ መቅረብ ያለበት ቀርቦ በፍትህ እንዲዳኝ ማድረግ ይኖርብናል። እና እኔ ተስፋ የማደርገው፤ ወያኔ የሚባል ቡድን ለእርቅ ዝግጁ ይሆናል እጁን ይሰጣል ተብሎ አይታመንምና፣ የመጨረሻው ፍጻሜ የሚሆነው በጦርነት ማንበርከክ ነው። “You can’t stop war unless you use war” ይባላልኮ። ከዚህ በኋላ ወያኔ ለትግራይ ህዝብ የሚውልለት ውለታ፣ እጁን ሰጥቶ የሚመጣውን ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ መቀነስ ቢሆንም፣ ወያኔ ይህንን ያደርጋል ብዬ አላምንም።
አንዱ ወገን ለጦርነት ራሱን እያዘጋጀና ጦር እየሰበቀ፣ አንቺ የሰላም ዘንባባ ይዘሽ ስትሄጂ፣ አንዲት እናት ሄደው ደብረጽዮን እግር ላይ ሲወድቁ እንዳስነሳቸው ነው የሚያስነሳሽ። አምባ ገነን ስለሆነ እንድታለቅሺ አይፈቅድልሽም፤ ራሱም ሟች አይመስለውም፤ የሚያልቀው የደሀው ልጅ ስለሆነ። ወያኔ ከተፈጠረ 45 ዓመቱ ነው፡፡ ስንትና ስንት ጦርነት እንዳደረገ ያውቃል የትግራይ ህዝብ። ሌላ ሀገር በ45 ዓመት ውስጥ ይህን ያህል ጦርነት ያደረገ ታውቂያለሽ? ወያኔ ብቻ  ነው። ከደርግ፣ ከሻዕቢያ፣ ከኤርትራ ጋር ተዋጋ፡፡ ከሶማሊያ ጋር  ገብቼ ልዋጋ ብሎ ተዋጋ ከጦርነት ሱሱና ናፍቆቱ የተነሳ፡፡ እንደገና አሁንም የራሱን ወገን ተዋጋ! መቼ ከጦርነት እፎይ ብለን እናውቃለን ወያኔ ከተፈጠረ። መለስ ዜናዊ እንኳን በቃለ ምልልሱ ምናለ? “መዋጋት የሚፈልግ ሄዶ ይዋጋ፤ እኛ ግን አንገፍግፎናል፤ ጦርነትን በወሬ ሳይሆን በተግባር አይተነዋል” ብሏል። እነዚህ ደንቆሮዎች ቢያንስ የራሳቸውን ማስተር እንኳን አያከብሩም። ጦርነት መዘዙ ምን እንደሆነ እንኳን አይረዱም። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ በነዚህ ደንቆሮዎች ተይዞ፣ መሳሪያ ሆኖ ነው ያለው። ወያኔዎች ህዝቡን አስጨርሰው 15 እና 16 ቢቀሩ እንኳን ችግር የለባቸውም። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ እጣ ፈንታውን መወሰን፤ ወያኔን በቃኸኝ ማለት አለበት። ከዚያ በኋላ ከአማራና ከአፋር ህዝብ ገር ስለሚኖረው የወደፊት ግንኙነት ከህዝቦቹ ጋር ራሱ ይወስናል። ብቻ እነዚህ ደንቆሮዎች ይልቀቁት፡፡ እኔ እንደዚህ ነው የማስበው። ይሄም የእኛ መንግስት ከዚህ ሂደት ብዙ መማር አለበት እንጂ ሁሉንም ሃጢያት በወያኔ ማሳበብ የለበትም ባይ ነኝ፡፡ ስለነበረን ሰፊ ቆይታና ውይይት አመሰግንሻለሁ፡፡

Read 2882 times