Tuesday, 15 February 2022 17:43

ፍላጎታችን የወደፊቱ ታላላቅ ዳይሬክተሮችና ማኔጀሮች እንድትሆኑ ነው -ቢጂአይ ኢትዮጵያ-

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ማክሰኞ የካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡30 ጀምሮ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኤፍቢኢ አዳራሽ ውስጥ ከ500 በላይ የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታድመው ነበር - ከ5ቱ የዩኒቨርሲቲው ግቢዎች የመጡ፡፡ እኒህ ተማሪዎች  ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተያያዘ ጉዳይ አይደለም በአዳራሹ ውስጥ የተሰባሰቡት፡፡ ጉዳያቸው በቀጥታ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ጋር የተገናኘ ነው፡፡
ኩባንያው ባለፈው ዓመት የጀመረውንና እጅግ አመርቂና አስደሳች ውጤት አግኝቼበታለሁ ያለውን ቢጂአይ ኤክስፒ የተባለ ፕሮግራም፣ ለዘንድሮ የ2ኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለማስተዋወቅ ነበር፣ የማክሰኞውን  መርሃ ግብር በኤፍቢኢ አዳራሽ  ያዘጋጀው፡፡
የቢጂአይ ኤክስፒ ፕሮግራም፣ ተማሪዎች ከሁለተኛ ዓመት ጀምሮ፣ ከአካዳሚ ዕውቀት በተጨማሪ በሚፈልጉት ሙያ የሥራ ልምምድ እንዲያገኙና ሲመረቁ በሙያቸው የተሻለ አቅምና ችሎታ እንዲኖራቸው ለማገዝ ታልሞ የተቀረፀ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የዘንድሮን ኤክስፒ ፕሮግራም የምንጀምረው የአዲስ አበባው የቢራ ፋብሪካችን 100ኛ ዓመትን በምናከብርበት ወቅት ላይ ነው ያሉት የኩባንያው የሥራ ሃላፊዎች፤#እዚህ ለመድረስ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል፤ከአንድ ፋብሪካ ተነስተን ወደ ስድስት ፋብሪካዎች የደረስንበት የስኬታችን ምስጢር፣ በሥርዓትና በሥነምግባር የታነጹ ታታሪ ሠራተኞች ይዘን መጓዛችን ነው፡፡; ብለዋል፡፡
በቢጂአይ ኤክስፒ ፕሮግራም የሚታቀፉት የ2ኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች  ብቻ ሲሆኑ በአንደኛ ዓመት የትምህርት ዘመናቸው 3.5 እና ከዚያ በላይ አማካይ ውጤት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ባለፈው ዓመት በዚህ ፕሮግራም 25 ያህል ተማሪዎች  የታቀፉ ሲሆን ዘንድሮ ከ50-60 የሚደርሱ መመዘኛውን ያሟሉ ተማሪዎች ፕሮግራሙን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኩባንያው የሥራ ሃላፊዎች እንደተናገሩት፤ በዚህ ፕሮግራም የሚታቀፉ ተማሪዎች፣ በየዓመቱ ለ2 ወራት ትምህርታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ ደሞዝ እየተከፈላቸው፣ በቢጂአይ 5ቱም ፋብሪካዎች ውስጥ ሙያቸውን ለማዳበር የሥራ ልምምድ ያደርጋሉ።
 በሥራ ልምምድ ወቅት ተማሪዎች የኩባንያውን ሥርዓትና ደንብ ማክበር እንዳለባቸው የጠቆሙት ሃላፊዎቹ፤ #ሥነምግባርና ዲሲፕሊን የሌለው ተማሪ የትም አይደርስም; ሲሉ ተማሪዎቹን አስጠንቅቀዋል፡፡
#ይህ ያገኛችሁት ዕድል ትልቅ ዕድል ነው፤ በአግባቡ ልትጠቀሙበት ይገባል፡፡; በማለትም ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
በሥራ ልምምዱ ወቅት ከተማሪዎቹ ምን እንደሚጠበቅ በዝርዝር ያብራሩት የኩባንያው ሃላፊዎች፤ ባለፈው ዓመት ፕሮግራሙን የተቀላቀሉ ተማሪዎች ከቢጂአይ ጋር ያሳለፉትን ጊዜ በተመለከተም በምስል የተደገፈ ማብራሪያም ለዘንድሮዎቹ  እጩ ተማሪዎች ሰጥተዋል፡፡
#ከእናንተ የምንፈልገው በትምህርታችሁ የላቀ ውጤት አስመዝግባችሁ የኩባንያችን የወደፊት ታላላቅ ዳይሬክተሮች፣ ማኔጀሮች- ወዘተ እንድትሆኑ ነው; ያሉት የሥራ ሃላፊዎቹ፤ #በእኛ ኩባንያ ውስጥ የሥራ ልምምድ ካደረጋችሁ በየትኛውም ዓለማቀፍ ድርጅት ውስጥ ትቀጠራላችሁ፡፡; ሲሉ የሥራ ልምምዱ ያለውን ፋይዳ አጉልተውታል፡፡
ቢጂአይ ኢትዮጵያ ይህን ፕሮግራም የቀረጸው ምሳሌ ለመሆን ነው ያሉት ሃላፊዎቹ፤ ሌሎች ኩባንያዎችም ተመሳሳይ ፕሮግራም ቢቀርጹ ለራሳቸውም ሆነ ለአገሪቱ አቅምና ብቃት ያለው የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ አይተኬ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብለዋል፡፡
በኤፍቢኢ አዳራሽ ውስጥ ለታደሙት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቂ ማብራሪያና ገለጻ ከተሰጠ በኋላ ቢጂአይ ያዘጋጀውን የምዝገባ ቅጽ እንዲሞሉ የተሰጣቸው ሲሆን በመቀጠልም የጽሁፍ ፈተናና  ቃለመጠይቅ (ኢንተርቪው) ይጠብቃቸዋል፡፡ ለፕሮግራሙ ብቁ ሆነው የተገኙትም በአድራሻቸው እንዲያውቁት ይደረጋል ተብሏል፡፡

Read 8252 times