Tuesday, 12 April 2022 00:00

“ካህናቶች”

Written by  ሌሊሳ
Rate this item
(0 votes)

አዲስ ገቢ ካልሆኑ ነባር የትራፊክ ፖሊሶች በሙሉ ወፋፍራም ናቸው፡፡ አብዝተው ስለሚመገቡ ይሁን የተመገቡትን ያህል እስፖርት ስለማይሰሩ፣ ብቻ የሆነ ያልተወራረደ ነገር መሀል ወገባቸው ላይ  ተከፍሎ ይታያል።
አንዱን ባለፈው ጫንኩት፡፡ ህግ አስከባሪን በሊፍት መተባበር አልፈልግም፤ ስለማላምንበት ነው፡፡ ሊፍት ሊሰጣቸው ይገባል ብዬ አላምንም፤ ከተሰጣቸው መንግስት እንጂ እኔ ተራ ግለሰብ ልሆን አልችልም። ይሄ ነው እምነቴ፡፡
ስለ እምነቴ በዚህ ፅሁፍ ብዙ የምለው አለኝ። እና እንዳልኩት አንዱን በቀደም ጫንኩት፤  የምንተ እፍረቴን ነው። እጁን  ሲያመላክት ሊቆጣኝ መስሎኝ ሳቆም ዘሎ ተሳፈረ። “ውረድልኝ!” ማለት አለመቻሌ ነው፣ የምንተ እፍረቴን ነው ያልኳችሁ። እጁን ያመለከተው ባለ ቦርጩ ነው፤ የተሳፈሩት ግን ሶስት ሆነው ነው፡፡  ሴትም አለችበት፡፡ ባለ ቦርጩ ከፊት ገባ።
ውረድ ብለው የሚወርድ አይመስለኝም፤ እንዲያውም ምክንያት ፈልጎ ሊከሰኝ ይችላል። "ፖሊስ ጣቢያ ድረስ እንሂድ" ቢለኝ “ለምን” እለዋለሁ፡፡ "እዛ ስንደርስ እነግርሀለሁ" ቢለኝ ግን መልስ የለኝም። በራሴ መኪና እቤቱ መውሰድ ይሻላል፡፡ በራሱ አይሱዙ ያበደን ሰው ወደ አእምሮ ሆስፒታል  ሲወስዱ፣ የመኪናው ባለቤት አቅም ስለሌለው  መቃወም አይችልም። እኔም በተሳፈሩት ትራፊክ ፖሊሶች ፊት ብዙም አቅም የለኝም።
“ያለናንተ ማን አለን” እያልኩ ግን በሽንገላ አላሽቃብጥም፤ ፊቴን ቅጭም እንዳደረግሁ መንዳት ቀጠልኩኝ፡፡ የስራ መኪና ነው። እንደሆነም በተለይ ፊት የተቀመጠው ያውቃል፡፡ ትራፊክ ፖሊስ ግልፅ የራይድ ማስታወቂያ የለጠፈ መኪና ይቅርና ማንኛውንም ተሽከርካሪ ከእነ አገልግሎቱ፣ ውስጡን ወደ ውጭ ገልብጦ ያውቃል።
በእርግጥ ትራፊክ ፖሊሶች ላይ ያን ያህል ቂም  የለኝም፤ እንዲያውም ከፌደራል ፖሊስ ይሻሉኛል። ቢሆንም በሁለቱም ደስተኛ አይደለሁም፡፡ የኔን መብት ለማስከበር ይሁን የራሳቸውን የቆሙት አላውቅም። የመብት መከበር የሚረጋገጠው በኪሎ  መጠን አይደለም እንጂ ቢሆን የራሳቸውን መብት ለማስከበር ነው የቆሙት እል ነበር፡፡
ትራፊክ ፖሊስ ደጋግሞ ቀጥቶኛል፡፡ አንዱም ስህተቴ አሳምኖኝ አያውቅም፤ ግን ጥፋተኛ እንደዛ ነው፤ ባህሪው፡፡ ጥፋተኛ የባህሪ ልምድን የሚያዳብረው ስህተቱን ገግሞ ባለማመን ነው፡፡ ስለ እምነት ብዙ የምለው አለኝ፡፡ የእኔ ችግር አለማመን ሳይሆን አለመቀበል ነው።
እና ሦስት ሆነው በስራ መሥሪያ መሳሪያዬ ውስጥ ተቀመጡ፡፡ ሁለቱ ከኋላ፣ ባለ ቦርጩ  ከፊት፡፡ ወደ ኋላ በሚያሳየው መስታወት ፊታቸው እንጂ ቦርጫቸው ስለማይታይ እንጂ ኋላ ያሉትም ይኖራቸዋል፡፡ የሴቶች ትራፊኮች ቦርጭ መቀመጫቸው ላይ ነው የሚወጣው፡፡ መኪናውን ማንቀሳቅስ ጀመርኩ፡፡  ከመኪና ብር የማይፈልግ የለም። መንግስት የከተማውን ስራ ፈት ወጣትና የገጠሩን ቦዘኔ አደራጅቶ የከተማ ፓርኪንግ ቲኬት ቆራጭ አድርጓቸዋል። ስራ መፍጠር ጥሩ ነው፤ ግን ስራ የሚፈጠረው በመኪና ባለቤት ጫንቃ ላይ መሆኑ  ያበግነኛል፡፡ ይሄ እስከ መቼ እንደሚዘልቅ አላውቅም፡፡ መኪናውን ለማቆያ እለታዊ ወጪው ሀያስ እና ከዛ በላይ የሆነበት ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ህጉ ህገ-ወጥነት ስለተደባለቀበት አያሳምነኝም። ትራፊክ የሚቀጣኝ በማያስቀጣ ጥፋቴ ነው። በቀደም ለለማኝ ሰጠህ ብሎ እየበረረ መጥቶ መብራት ሳይለቀኝ በፊት መንጃ ፈቃዴን ነጠቀኝ፡፡ ሰው ጭኜ ነበር፡፡ ገና የክስ ወረቀት አልቆረጠልኝም፡፡ የክስ ወረቀቱን በተወሰደብኝ መንጃ ፈቃድ ፈንታ ካልያዝኩ አደገኛ ነው፡፡ ሌላ ትራፊክ ሲያስቆመኝ  ውስጠን --- ነው ሚለው፡፡ ያሳፈርኩትን ሰው አውርጄ ተመልሼ ስመጣ፣ እንደ እድል፣ ነጣቂውን እዛው ቦታ አገኘሁት። ትንሽ ዲስኩር ቢጤ አደረገ፡፡ “ቅጣቱ እኔን ለማስተማርና ለማነፅ ስለማስፈለጉ”…. ስለማላምንበት ጎንበስ ብዬ ምክሩን አልተቀበልኩትም፡፡ ከምክሩ በኋላ ቅጣቱ ይደገሳል፤ በምክር ብቻ አይለቀኝም፡፡ እኔም ምህረት አልጠብቅም፡፡ መንግስት ራሱ ካሰረ በኋላ ነው የተንገላታውን በምህረት የሚለቀው፡፡ እና ብቻ አያሳምነኝም። አሳመነኝም አላሳመነኝም መቀጫው ይቀጥላል። ህግ በማስከበር ስም አድርገሃል የተባልነውን እየተቀበልን እንቀጣለን፤ ገንዘብ ደመወዝ ተብሎ ስለሚጠራ የገንዘብ ቅጣቱም የደም ተመን ነው ያለው፡፡ በተለይ ለራይድ አሽከርካሪ፣ ከተሳፋሪ የሚቀበለው እያንዳንዱ ብር፣ የደም ዋጋ ነው ያለው።
እና ለማን ብቀጣ ነበር የሚሻለው? ስል ራሴን ጠይቄአለሁኝ፡፡ ለለማኙዋ ብከፍል እመርጣለሁ፡፡ ከመንግስት ይልቅ ለለማኙዋ ብቀጣ ለማህበረሰብ እዳዬን የመክፈል ተልዕኮዬን የተወጣሁ ይመስለኛል።
“ለምን ለማኞቹን ከትራፊክ መብራት አካባቢ አያባርሩም?; ብዬ ያንን ባለዘርፋፋ ቦርጭ ትራፊክ  ጠይቄዋለሁ፡፡ የክሱን ወረቀት ያለአክብሮት ነጥቄው ከመሄዴ በፊት የማይመስል መልስ ሲሰጠኝ የመስማት ፍላጎት አልነበረኝም።
“የሥራ ዘርፌ ህግ አስከባሪ እንጂ ደንብ አስከባሪ አይደለም” ነው ያለኝ፡፡ መኪና የሌላቸው ሰዎች፣ በመንደር መንገድ ላይ ለፍጥነት ማብረጃ “speed breaker” በሚል ስም እንደሚቆልሉት አርማታ ነው። ፍጥነት ቀንሰው እንዲነዱ አሽከርካሪዋን በማድረግ ስም፣ የመኪናውን አካል መስበር ነው ግቡ። “ያማል ቅኔው” የተባለው የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ በማነጽ ስም መበቀል ነው ግቡ። ህግ በማስከበር ስም ህግን እንዲያምን ማድረግ፡፡ ስለ እምነት ነው ይሄ ፅሁፍ፡፡ ወዲያው እምነት በሰው ህግ ላይ ስለማጣቴ።
አስተማሪ ከባድና ከሚያስተምረው ትምህርት ጋር መሰረታዊ ቅርርብ የሌለው ፈተና አክብቦ የሚያወጣው ለማሳለፍ ሳይሆን ለመጣል ነው፤ ለማሳወቅ ሳይሆን ለማደንቆር፡፡ ሁሉም አስተማሪ ተልዕኮው ይሄ ነው ብዬ  መዝጋት አልፈልግም፡፡ ይሄማ “ሁሉም ከንቱ ከንቱ ነው” ብዬ በጨለማ እንደ መቀመጥ ይሆናል፡፡ ወይንም ተስፋ መቁረጥን ተስፋ ማድረግ፡፡
አዝኖ የሚቀጣ ትራፊክ ፖሊስ አይቼ አላውቅም፡፡ የቢንጎ ሎተሪ እንደአጋጣሚ የደፈነ ሰው የሚሰማው ድል አድራጊነት ነው ቀጪው ላይ የሚንፀባረቀው፡፡ ባይታረም ደስ ይለዋል።
“ጋሽ ትራፊክ፤ በቀደም በቀጣኸኝ ጥፋት ላይ መሻሻል አሳይቻለሁ፤ በቅጣቱ ታንጼአለሁ” የሚል አሽከርካሪ እንደሌለው ሁሉ፣እንደዚህ ሲባል ደስ የሚለው ትራፊክ የለም፡፡ "ታላግጥብኛለህ" ብሎ ሊደግመው ይችላል፡፡ የትራፊኩ ስራ ስህተትን ማጥፋት አይደለም፤ ከጠፋማ ገቢ ለመንግስት አይኖርም፡፡ ምናልባት የትራፊኩም የወር ደመወዝ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ በስህተት ላይ የሚከፈት የስራ ዘርፍ ቅኔው ይሄ ነው፡፡ ደንብ በማስከበር ስም ጥሰት ሁሌ እንዳይደርቅ የሚመኝ ነው፡፡ #ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም; የሚለው፣ የሰው ድካም ላይ ተቋምን አደራጅቶ፣ ዝንተ ዓለም መቀጠል ይቻላል።
ከፊት  የተሳፈረው ትራፊክ የተመቸው እንደሆነ ያስታውቃል፤ በቀላሉ ይስቃል፤ ይሳሳቃሉ፡፡ እነሱ እየቀጡኝ የተማርኩት አንድ የማልረሳው ትምህርት አለ፤ እሱም የአሽከርካሪ ቀበቶ ማሰር ነው፡፡ የራስን ብቻ ሳይሆን ከጎን የተቀመጠው ሰውም ማሰሩን አረጋግጣለሁ፡፡ ይሄም የራይድ ሹፌርነቴም አንዱ የስራ ልምድ ሆኖ ተዋህዶኛል። ካልታሰረ ይታወቀኛል፤ በልምድ ብዛት እምነቴ ሆኗል፡፡
ከፊት የተቀመጠው ትራፊክ ቀበቶ አለማሰሩ ታወቀኝ፡፡ ከነከነኝ፡፡ ዝም ማለት ነበረብኝ፤ ግን አላስቻለኝም፡፡ አላስቻለኝም ሳይሆን አሰጋኝ፡፡ እራሱ ባላሰረው ቀበቶ መልሶ እኔን እንደሚቀጣኝ አሰጋኝ። የድመትና የአይጥ ጨዋታ ህግ በሚል ስም እንደሚጠራ አውቃለሁ፡፡ ደንብ አስከባሪው ዩኒፎርሙን ሲለብስ ድመት ሆኗል ማለት ነው፡፡ እኔ “ተበላሁ” ስል እውላለሁ። የማውቃቸው ወጥመዶች አሉ። የማላውቃቸውም እንደዚሁ፡፡ ለምሳሌ ለለማኝ መስጠት እንደሚያስቀጣ አላውቅም ነበር፡፡ አላውቅም ወይም ዘንግቼዋለሁ። የእውነት አውቅ  የነበረው  ግን መንጃ ፈቃድ የሌለውን ሰው --- ማለማመድ ሆነ አሽከርካሪ ወንበር ላይ ማስቀመጥ የማይቻል መሆኑን ነው፡፡ በዚህ የእውቀት ማነስ የገጠመኝን በቀጣዩ ምዕራፍ እገልጻለሁ። አሁን ቦርጫሙ ትራፊክ ቀበቶ ሳያስር ከጎኔ ተቀምጦ እየሳቀ በመጓዝ ላይ መሆኑን የነቃሁበት ቅፅበት ላይ ነኝ።
“ትራፊክ ነው” ብዬ ልተወው አልፈለኩም፡፡ የማላውቀው ቅጣት ከማውቀው ውስጥ ሊሰጠኝ ይችላል። ጉሮሮዬን አጥርቼ፤ “እባክህ የተሽከርካሪ ቀበቶውን እሰር” አልኩት፤ በተቻለኝ መጠን ድምጼን በትህትና አለስልሼ ነው ይሄንን ያልኩት፡፡ (ይቀጥላል)Read 2131 times