Sunday, 26 June 2022 10:12

በሰሜን ኮሪያ ብቻ!!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ሟቹ የቀድሞው መሪ ኪም ኢሉ-ሱንግ፣ አሁንም አገሪቱን በመንፈስ እንደሚመሯት በሚታመንባት ሰሜን ኮሪያ፤ አያሌ ቅጥ አምባራቸው የጠፋ ህጎችና ደንቦችና ይስተዋላሉ። አገሪቱን በጨረፍታ ለማስቃኘት ያህል ጥቂቶቹን እነሆ፡-


           አንድ እጩ ብቻ የሚቀርብበት ምርጫ
ሰሜን ኮሪያ እ.ኤ.አ ከ1948 ዓ.ም አንስቶ በአንድ ቤተሰብና ፈላጭ ቆራጭ በሆነ አገዛዝ እየተዳደረች  እንደምትገኝ ዓለም ሁሉ የሚያውቀው ሃቅ ነው፡፡ አስቂኙ ነገር ታዲያ አገሪቱ ምርጫ በየዓመቱ ማካሄዷ ነው፡፡ መራጩ ህዝብ ደግሞ እንዲመርጥ የሚቀርብለት አንድ አማራጭ ብቻ ነው። ለከንቲባም ይሁን ለክልል ገዢዎች አሊያም ለወረዳ ም/ቤቶች ምርጫ በየግዛቱ የሚቀርበው አንድ እጩ ብቻ ነው፡፡ መራጩም ለብቸኛው እጩ ድምፁን ሰጥቶ (መርጦ) ወደ የቤቱ ይመለሳል፡፡

ወላጆች የት/ቤት ዴስኮችን ማቅረብ አለባቸው  
ልጆቻቸውን ወደ ት/ቤት የሚልኩ ወላጆች፣ የራሳቸውን ዴስኮችና ወንበሮች ማቅረብ ግዴታቸው ነው፤ እንደ ደብተርና የጽህፈት መሣሪያዎች፡፡ ት/ቤቶች ለተማሪዎች መቀመጫ ዴስኮችንና ወንበሮችን አያዘጋጁም፡፡ በዚህ ዓይነት አሰራር ሰሜን ኮሪያ በዓለማችን ብቸኛዋ አገር ሳትሆን  አትቀርም። ይሄም ሳያንስ አንዳንድ ተማሪዎች ለመንግስት የጉልበት ሥራ እንዲሰሩም ይገደዳሉ። ለምሳሌ የተጣሉ ቁሳቁሶችን እንዲሰበስቡ ይታዘዛሉ- በነጻ!
የሦስት ትውልድ ቅጣት ህግ
የሦስት ትውልድ ቅጣት ህግ፣ የሰሜን ኮሪያ ሰቅጣጭ እውነታ ነው- ከዜጎች ምንም ዓይነት ትችትም ሆነ ይግባኝ የማይቀርብበት!! አንድ ሰው ወንጀል ከፈፀመ ከእነዘር ማንዘሩ (አያቶቹን፣ ወላጆቹንና ልጆቹን ጨምሮ ማለት ነው) ተለቃቅሞ ከርቸሌ የሚወርድበት አሰራር ነው- የ3 ትውልድ ቅጣት ህግ።

ኮምፒውተር ለመግዛት የመንግስት ፈቃድ
በሰሜን ኮሪያ ዜጎች 28 ድረገፆችን ብቻ ነው መጎብኘት የሚፈቅድላቸው። የአገሪቱ ኢንተርኔት “ክዋንግምዮንግ” ወይም “ብራይት” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን  ኮምፒውተር ያላቸው ዜጎች በነጻ መጠቀም ይችላሉ። ክፋቱ ግን ኮምፒውተሮች በአገሪቱ እጅጉን ውድ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ ኮምፒውተር ለመግዛት በቅድሚያ የመንግስት ይሁንታ ያስፈልጋል። መንግስት ሳይፈቅድ መግዛት አይቻልም።

ሰማያዊ ጂንስና ኢምፔሪያሊዝም   
ሰሜን ኮሪያ ሰማያዊ ጂንስን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ተምሳሌት አድርጋ ነው የምታየው፡፡ በዚህም የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ እገዳ ተጥሎበታል፤ አይመረትምም አይለበስምም!!

የፀጉር አቆራረጥ ለእስር ይዳርጋል
በሰሜን ኮሪያ መንግስት የማይቆጣጠረው ነገር አለ ለማለት ያዳግታል። በአገሪቱ ወንዶች ፀጉራቸውን እንዳሻቸው መቆረጥ (መስተካከል) አይችሉም፡፡ በመንግስት ይሁንታ ያገኙ 28 የፀጉር አቆራረጥ ስታይሎች አሉ፡፡  በመንግስት ከተፈቀደው የፀጉር ስታይል ውጭ መስተካከል ለእስር ሊዳርግ ይችላል፡፡ ያላገቡ ሴቶች ፀጉራቸውን ማሳጠር ያለባቸው ሲሆን፤ ያገቡ ሴቶች  በአንጻሩ የተሻሉ አማራጮች አላቸው፡፡

የሰው ሰገራ ለማዳበሪያነት
እ.ኤ.አ በ2008 ደቡብ ኮሪያ ለሰሜን ኮሪያ ትልከው የነበረውን ማዳበሪያ ማቆሟን  ተከትሎ፣ አገሪቱ ከፍተኛ የማዳበሪያ እጥረት ገጥሟት ነበር፡፡ ይሄን ጊዜ እንደሌላው ነገር ሁሉ አዲስ ህግ የተደነገገ ሲሆን ዜጎች ሰገራቸውን እየሰበሰቡ ለባለስልጣናት እንዲያስረክቡ ትዕዛዝ ተሰጣቸው - ለማዳበሪያነት እንዲያገለግል፡፡

Read 3289 times