Sunday, 10 July 2022 19:44

እኩል

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(1 Vote)

 እሷ እንደ አባቷ አይደለችም፡፡ እሷ አባቷን አትመስላቸውም፡፡ የሚመሳሰሉበት ነገር ቢኖር፣ የአያቷና የአባቷ አባት ስም አንድ መሆኑ ብቻ ነው፡፡
እሷ አባቷን መምሰል አትፈልግም፡፡ እሳቸው “እወድሻለሁ” ለሚሏቸው የልጆቻቸው እናት ክብር የላቸውም፡፡ አባቷ ከእናቷ ጋር ለጉዳይ ወጣ ሲሉ ፊት ፊት መቅደም ይቀናቸዋል፡፡ እናቷ ሳት ብሏቸው ባላቸውን ከቀደሙ፤ “ምንድን ነው ከፊት ከፊት መጠለፍ” ይላሉ አባቷ፣ እናቷን በቁጣ እየገረፉ፡፡ ጉዞአቸው ፊትና ኋላ ነው፡፡ “አባት መሪ- እናት ተከታይ”  የማይሻር የአባትየው የጉዞ ህግ ነው፡፡
አባቷ የሚደርቡት ጋቢ እንጂ የእናቷ ጠይም ኩታ መጽዳትን አልታደለም፡፡ የአባቷ ሸሚዝ እንጂ የእናቷ ውስጥ ልብስ ውሃ ይንካው አይባልም፡፡
ባርኔጣቸው ላይ የአመድ  ብናኝ ሲያዩ እንጂ በጥላሸት የጠየመ ቀሚስ የለበሱ ሚስታቸው ከኋላቸው ሲከተሏቸው ሲመለከቱ ቁጣ ቁጣ አይላቸውም፤ አባትየው፡፡
እሷ ግን አባቷን መሆን አትፈልግም፡፡ የሁለት ዓመት ፍቅረኛዋ ሁልጊዜ እንዲያምርላት ትፈልጋለች፡፡ አምሮና ተውቦ እንዲታይላት የማታደርገው ነገር የለም፡፡ እሷ የምትወደው ሰው እቅፏ ውስጥ ሆኖ እንዲሄድ እንጂ የሚከተላት ጥላዋ እንዲሆን አትሻም፡፡ ከጎኑ ተለጥፋ እንጂ ከኋላዋ አስከትላው አትጓዝም፡፡ ትወደዋለች፡፡ ማማር እንዳለበት ትመክረዋለች፡፡ የእሷ  ውበት የሚፈካው እሱ ሲያምር እንደሆነ ትነግረዋለች፡፡
“እስኪ ራስህን አትጣል…ራስህን ጠብቅ…” ትለዋለች
“ታዴ…. የሸሚዝክን ኮሌታ አይተኸዋል?”  ማጅራቱን እየደባበሰች ትጠይቀዋለች፡፡
“ጧት ቀያሬ እመጣለሁ” ብሎ ሊያመልጣት ይሞክራል፡፡ ቲያር ቤት ከመድረሳቸው በፊት ወደ አንድ ቡቲክ ይዛው ሄዳ አዲስ ሸሚዝ አስለብሳዋለች፡፡
“ፂምህ ሲያድግ አታምርም አላልኩኽም?” በሚያሳዝን ቅላፄ ሌላ ጥያቄ ትወረውራለች-ፂሙን እያሻሸች የቲያትር ቤቱ ደጃፍ ላይ ተሰልፈው ወረፋ ሲጠብቁ፡፡
“የጥርስ ቡርሽህ ጠፋ እንዴ ታድዬ?” ቲያትሩ ላይ የቤት ሰራተኛ ሆና በምትጫወተው ሴት ዳንስ እንባው እስኪፈስ እየሳቀ እያለ ጥርሶቹን በጨለማ ውስጥ እያየች ትጠይቀዋለች፡፡ ስለ ጥርሱም ስለ ልብሱም ትጨነቃለች፡፡ ያደጉ የጣት ጥፍሮቹን በጥርሶቿ ትከረክማቸዋለች፡፡ እንዲያምርላት ትፈልጋለች፡፡
እናቷ በአባቷ ተፅዕኖ፣ ፍቅረኛዋ በቸልተኝነት አምረው ተውበው መታየትን አልታደሉም። የአባቷን ተፅዕኖ ማሸነፍ ባትችልም፣ የፍቅረኛዋን ቸልተኝነት የሚያሸንፍ አቅም እንደማታጣ ይሰማታል፡፡ ለዚህ ነው ሳትሰለች የምትንከባከበው፡፡ ለቀናት ተለያይተው ሲገናኙ እየተፍለቀለቀች ትጠመጠምበታለች። እየተስገበገበች ደረቱ ሥር ስትለጠፍ ግን ፈገግታዋ ይከስማል፡፡ ብብቱ ሥር ስትሸጎጥ ገዝታ የሠጠችውን  ዲኦደራንት አሁንም እንዳልከፈተው ይገባታል፡፡ ሲከፋት ያይና ሊያጽናናት ይሞክራል፡፡ ከበብቱ ወደፊቱ ትዞራለች፡፡ ጉንዳን የወረረው ብስል ማንጎ ወደመሰለ ጉንጩ፡፡
“አያምርብህም አላልኩህም ታዴ? ፂምህ ሲያድግ ታስጠላለህ አላልኩህም?” ትጠይቀዋለች፡፡
“ብለሽኛል ፈትሊ…” ከአይኖቿ ለመሸሽ እየሞከረ፡፡
“ታዲያ ለምን  አትሰማኝም?” አገጩን ይዛ ትመልሰዋለች፡፡
“እሰማሻለሁ! ዛሬውኑ እላጫለሁ” የለመደውን ቃል ይገባላታል፡፡ በሾሃማ ፂም በታጠሩ ከንፈሮቹ ሲስማት መለስ ትላለች፡፡
“I promise ፈትለ…. ዛሬውኑ እላጫለሁ” ይላታል፤ ፊቱን የወረረውን ፂም እያሻሸ። ታሳዝነዋለች፡፡ ከቸልተኝነቱ ጋር ተፋጦ ሊያስደስታት ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው አንድ ማለዳ ከመስሪያ ቤቱ አጠገብ ወዳለች አነስተኛ ፀጉር ቤት ያመራው፡፡
ነጭ ጋዋን የለበሰች ጠይም ሴት መቀስና ማበጠሪያ እያፀዳች አገኘ፡፡ ዓይኖቿ ያምራሉ፡፡ የሆነ የተለየ ያልተለመደ አይነት ቀለም አላቸው።
“ብዙ ይቆያል?” ጠየቃት በግድግዳው መስታወት አሻግሮ እያያት።
“ማን?” በዚያው መስታወት ውስጥ  መልሳ ጠየቀችው፡፡
“ፀጉር አስተካካዩ” ወደ ባዶው ተሽከርካሪ ወንበር እየጠቆመ፡፡
እየሳቀች ነገረችው፡፡ ብዙ ደምበኞች በእሷ ልዩ ችሎታ ውበታቸውን ተጎናጽፈው፣ ፀጉራቸውን አራግፈው እንደወጡ ነገረችው።
እየሰማት ተሽከርካሪ ወንበሩ ላይ ተቀመጠ። ከፊት ለፊቱ በተዘረጋው መስተዋት  ውስጥ ፂማሙን ታደሰ ተመለከተ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እንደዚህ አይሆንም፡፡ ያምራል፡፡ ፍቅረኛውን ያስደስታል፡፡
ፈትለወርቅ ስትፍለቀለቅ ታየው፣ ስትጠመጠምበት፡፡
ፀጉር አስተካካይዋ ሥራዋን ቀጥላለች፡፡ ማጅራቱን ለብ ባለው ግራ እጇ ደግፋ፣ በቀኙ የጉንጩን ዳዋ ታጭዳለች፡፡ ግራ ቀኝ እያዟዟረች አንገት ሥሩን ታስሳለች፡፡ አገጩን ወደ ኮርኒሱ ቀስሮ አይኖቹን ጨፈነ፡፡ ማንቁርቱ ከላይ እታች ምራቅ እያቀባበለ ይንገራገጫል፡፡ እጇ ለስላሳ ነው- ትንፋሿ ሙቅ፡፡ ካንጋጠጠበት መልሳ ብናኝ ፀጉሮቹን በቡርሽ ስታራግፍለት፣ እንደምንም ብሎ ዓይኑን ወደ መስታወቷ ውስጥ ፀጉር አስተካካይ ላከ፡፡ ለደንበኞቿ የምትሰጠው ውበት  ከእሷ  የተረፈውን ሳይሆን አይቀርም ሲል አሰበ፡፡ በመስታወቱ ውስጥ ደግሞ አያት። ዓይናቸው መስታወቱ ውስጥ ተጋጩ፡፡ ፈገግ ብላለች፡፡ ደማቅ ፈገግታ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ፍቅረኛው ፈትለ ጉንጮቹን እያሻሸች የምትለግሰውን ዓይነት ሙቅ ፈገግታ ጠይም  ፊቷ ላይ ይንተከተካል፡፡
የፈትለን ፈገግታ ለማየት፣ ከፀጉር አስተካካይዋ ዓይኖች ለመሸሽ ዓይኖቹን ጨፈነ።
ፊቱን በለስላሳ ጣቶቿ ላላ አድርጋ እያሸችው ነው፡፡ ለብ ባለ ፎጣ እየወለወለችው…. በቅባት እያወዛችው፡፡ ከፍቅረኛው እንጂ ከፀጉር አስተካካይ ሴት አግኝቶ የማያውቀውን ነገር እያደረገችው፡፡
“የሚስተካከል ነገር ይኖራል?” ችሎታዋን ይመሰክርላት፣ መርካቱን ይነግራት ዘንድ ዓይኖቹን አስገለጠችው፣ አፉን አስከፈተችው፡፡
“በጣም ሀሪፍ ነው፡፡ ደስ ይላል፡፡” ተጣድፎ መለሰላት፡፡ አፉ እንዳመጣለት መለሰላት እንጂ ደስ ያለው መዋቡ ይሁን የጣቶቿ ልስላሴ፣የፈትለ ይሁን የእሷ ፈገግታ በውል አያውቅም፡፡
ሰዓቱን ተመለከተ፡፡ ከፈትለ ጋር ለመገናኘት የያዘው ቀጠሮ ሰላሳ ደቂቃ ያህል አልፏል። ከዚህ በፊት ከቀጠሮው ሰዓት ሰላሳ ደቂቃ ቀድሞ ነበር ፍቅረኛውን ከቀጠረበት ቦታ የሚደርሰው። በቀጠሮ አይታማም፡፡ ዛሬ ግን ዘገየ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘገየ፡፡ ፍቅረኛውን ፈትለን ለማስደሰት ዘገየ፡፡ ሂሳቡን ከፈለ፡፡ ምስጋናና ፈገግታ ተቀበለ፡፡ ሌላ ፈገግታ ፍለጋ ወደ ፈትለ ሲጓዝ እየተጣደፈ ነበር፡፡
መዘግየቱ የፈጠረባትን ንዴት በውበቱ ሻረችው፡፡ ቃሉን በማክበሩ ተደሰተች፡፡ አንገት ሥሩን እያሻሸች (መቀስና ምላጭ ባልያዘ ጣት) በፈገግታ ተመለከተችው፡፡
ከዚያች ቀን ጀምሮ ፂሙን አሳድጎ አያውቅም፡፡ አምሮ ይመጣላታል፡፡ ፂሙን አራግፎ..ተሻሽቶ… ተወልውሎ፡፡ ስትቀጥረው አምሮ እንደሚመጣ አርግጠኛ ሆናለች፡፡ ባይሆን አሁን አሁን የጀመረው የቀጠሮ ሰዓት ያለማክበር አባዜ ያናድዳታል እንጂ እንደ ሚያምርላት ታውቃለች፡፡
ትዕዛዟን ያከብራል፡፡ ቶሎ ቶሎ ፂሙን ይላጫል፡፡ እሷን ከማግኘቱ በፊት ወደ ፀጉር ቤቷ ያመራል፡፡ ከፍቅረኛዋ ፈገግታ እኩል የፀጉር አስተካካይዋ ፈገግታ ይናፍቀዋል፡፡
 ጉንጮቹን ሌጣ ለማድረግ ነጋ ጠባ ወደ ፀጉር ቤቷ መመላለሱን ቀጥሏል፡፡ የፀጉር ቤቷ ተሽከርካሪ ወንበርና የፍቅረኛው ጭን ሁለቱም እኩል ምቾት ይሰጡት ጀምረዋል፡፡
የፍቅረኛውም፣ የፀጉር አስተካካይዋም… የሁለቱም ጣቶች እኩል ይለሰልሱታል፡፡
ጺሙ አደገም አላደገም … ወደ ፀጉር ቤቷ መመላለሱን  ተያይዞታል፡፡
(ከደራሲ አንተነህ ይግዛው “መልስ አዳኝ እና ሌሎች አጫጭር ልብወለዶች”፤2002፤ መድበል የተወሰደ)

Read 1041 times