Saturday, 30 July 2022 14:26

የኢትዮ ቴሌኮም የ2014 የሥራ አፈጻጸም በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  • 61.3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ አስመዝግቧል
         • በቴሌ ብር ከ21.8 ሚ በላይ ደንበኞች በማፍራት፣ 303.ቢ ብር ተንቀሳቅሷል
         • ከፍተኛ ግብር በመክፈል ለ3 ተከታታይ ዓመታት የፕላቲኒየም ደረጃ ተሸላሚ ሆኗል


           ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ 61.3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 87.6 በመቶ  ማሳካቱን ባለፈው ሐሙስ ባወጣው መግለጫ  አስታውቋል፡፡  
ይህ ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ገቢ ጋር ሲነጻጸር የ8.5 በመቶ  እድገት ያለው ሲሆን በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተለይም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት 3,473 የሞባይል ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው ከታቀደው የገቢ እቅድ አኳያ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል ያለው ኩባንያው፤ የጸጥታ ችግሩን በወቅቱ መቅረፍ ቢቻልና አገልግሎቱን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል መስጠት ቢቻል ኖሮ ግቡን ሙሉ በሙሉ ማሳካት የሚቻል እንደነበር ያሳያል ብሏል፡፡
ሆኖም ካሉት ተግዳሮቶች አንጻር የተመዘገበው የገቢ አፈጻጸም እጅግ አበረታች ሲሆን ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው የደንበኞች የቴሌኮም አጠቃቀምን ለማሳደግና ተሞክሯቸውን ለማሻሻል የሚያስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያ፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም የደንበኞችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ወቅታዊነትን የተላበሱ 67 አዳዲስ እና 77 ነባር የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን በማሻሻል ለደንበኞች ለማቅረብ በመንቀሳቀሱ ነው  ተብሏል፡፡
የተገኘው የገቢ ድርሻ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የድምጽ አገልግሎት 51% ድርሻ ሲኖረው፤ ዳታና ኢንተርኔት 27%፣ ዓለም አቀፍ ገቢ 10%፣ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች የ5.7%፣ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 6.6% ድርሻ አላቸው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 146.6 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን ይህም የእቅዱን 82.3% ያሳካ ነው ብሏል - ኢትዮ ቴሌኮም በመግለጫው፡፡
ኩባንያው በበጀት ዓመቱ የገቢ አማራጮችን ለማስፋፋት ከሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረት በተጨማሪ  ወጪን በአግባቡ የመጠቀም እንዲሁም አላስፈላጊ ወጪዎችን ለማስወገድና በአጠቃላይ ኩባንያውን ውጤታማና ምርታማ ለማድረግ የሚያስችል የወጪ መቆጠብ ስትራቴጂ (DO2SAVE & cost optimization strategy)  በመቅረጽና ተግባራዊ በማድረግ 5.4 ቢሊዮን ብር ወጪ በመቀነስ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ  ተችሏል፤ ተብሏል፡፡
“የአገልግሎታችን ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት 66.59 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን የበጀት አመቱ አፈፃፀም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ18.4% እድገት እንዲሁም ከእቅድ አንጻር የ104% አፈጻጸም አስመዝግቧል።” ያለው ኢትዮ ቴሌኮም፤ “በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 64.5 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ (Fixed Broadband) 506.8 ሺህ፣ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 885.3 ሺህ እንዲሁም የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 26.1 ሚሊዮን ናቸው።” ብሏል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም፤ የአገሪቱን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይን ዕውን ለማድረግ ባለው ቁርጠኝነት፣ የቴሌኮም አገልግሎቶችን የማዘመንና የማሻሻል ጥረቱ ቀጣይ እርምጃ የሆነውን የ5G የሞባይል ቴክኖሎጂ የሙከራ አገልግሎትን በአዲስ አበባ ከተማ በስድስት ጣቢያዎች ማስጀመሩን አውስቷል፡፡ በተጨማሪም የኩባንያውን መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋትና በማጠናከር የኔትወርክ ሽፋንና አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን በማከራየት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘትና የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አጠቃላይ 217 የፕሮጀክት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁሞ፤ የ4G/LTE እና 4G/LTE Advanced ማስፋፊያዎች፣ የሞባይል ጣቢያዎች ማስፋፊያ፣ ስማርት ፖሎች ተከላ፣ የሞባይል መኒ ሲሰተም ማስፋፊያ በዋናነት የሚጠቀሱና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ናቸው፤ ብሏል፡፡
ከዚህም ባሻገር የቀጣይ ትውልድ የቢዝነስ ሰፖርት ሲስተምን (Next Generation Business Support System (NGBSS)) የማዘመንና የማሳደግ ስራዎች በመስራት ከደንበኞች ምዝገባ ጀምሮ የቢሊንግና አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን ለደንበኞች በማቅረብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ ሲሆን ፕሮጀክቱ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፤ ብሏል ኩባንያው፡፡
የአገሪቱን  የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎት ፍላጎት ለማርካትና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ የሚያስችለው የቴሌብር አገልግሎት ከኢንዱስትሪው ልምድ በተለየ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ21.8 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን እንዳፈራ የጠቆመው መግለጫው፤ አጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ የግብይት መጠኑም (Transaction Value) 30.3 ቢሊዮን ብር መድረሱን አመልክቷል፡፡
 የቴሌብር አገልግሎትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግና የኩባንያውን አጋሮችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እስካሁን ድረስ 353 የኢትዮ ቴሌኮም ሽያጭ ማዕከሎች፣ 93 ማስተር ኤጀንቶች፣ ከ76 ሺህ በላይ ኤጀንቶችና ከ21 ሺህ 600 በላይ ነጋዴዎች /merchants/ ተሳታፊ ሆነዋል  ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ከ13 ባንኮች ጋር  የኢንተግሬሽን ሥራ ተጠናቆ ከባንክ ወደ ቴሌብር ገንዘብ ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን ከ11 ባንኮች ጋር ከቴሌብር ወደ ባንክ ዝውውር እንዲቻል ተደርጓል ያለው የኩባንያው መግለጫ፤ የቴሌብር ሃዋላ አገልግሎት በማስጀመርና ከዓለማቀፍ ገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት ጋር  በማገናኘት፣ በ37 ሀገራት የሚገኙ ዜጎች በቀላሉ ወደ ሀገር ቤት ገንዘብ ማስተላለፍ የሚችሉበት አማራጭ እንደተፈጠረላቸውና  ባለፉት 6 ወራት ውስጥ 974.3 ሺህ  ዶላር ለመቀበል እንደተቻለ አመልክቷል፡፡
የታለመ የነዳጅ ድጎማ ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ በቴሌ ብር እየተሰጠ ሲሆን ከበርካታ የመንግስትና የግል አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር የኢንተግሬሽን ሥራ በመስራት ሰፊ የኢኮሲስተም  የማስፋት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብሏል፤ኩባንያው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ለሁለንተናዊ ሀገራዊ እድገት ካለው አስተዋፅኦ በተጨማሪ ለመንግስት በተለያየ መልክ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገባ ተቋም እንደመሆኑ በበጀት ዓመቱ  18.8 ቢሊዮን  ብር ታክስና 500 ሚሊዮን ብር ዲቪደንድ ገቢ በማድረግ የሚጠበቅበትን ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ ለመወጣት መቻሉን በመግለጫው ጠቅሶ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከፍተኛ ግብር በመክፍል በተከታታይ የፕላቲኒየም ደረጃ ተሸላሚ ሊሆን መብቃቱን ጠቁሟል፡፡


Read 1678 times