Saturday, 24 September 2022 17:20

ጥላቻና መውደድ ቅርብና ሩቅ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 የማውቃቸውን ሰዎች እጠላለሁ፡፡ መልከ መልካም እናቴ ካልጠፋ ወንድ ፉንጋ አባቴን መርጣ አገባች፡፡ ስወለድ የአባቴን መልክ ይዤ ወጣሁ፡፡ ታናሽ ወንድሜ “ዮዮ” አሥር አመቱ ነው፡፡ የእናቴን ዓይን፤ አፍንጫ፤ ከንፈር፤ ጥርስ፤ መልክ ቀይነትን ይዟል፡፡ አንደበቱ ይጣፍጣል፡፡ አዕምሮው ብሩህ ነው፡፡ ጥሩ ውጤት ያመጣል። አስተማሪዎቹ ይወዱታል፡፡ ከግቢ ውጪ ያየው ሰፈርተኛ ጠርቶ ይስመዋል፡፡ ከትምህርት ቤት ሲመለስ ቤቱንና ግቢውን ያምሳል፡፡ ደጅ ከጓደኞቹ ጋር ወጥቶ ይጫወታል፡፡ እኔ እንደዚህ ዓይነት የልጅነት ጊዜ አልነበረኝም፡፡ ጉንጬን አልተሳምኩም፡፡ በዕቃቃ ጨዋታ ላይ ለሚስትነት አልታጨሁም፡፡ በዘመዶቼ ሰርግ ላይ አበባ በታኝ አልተደረግኩም፡፡ ኤለመንተሪና ሃይስኩል እየተማርኩ መልሱን የማውቀውን ጥያቄ እጄን አውጥቼ ለመመለስ እፈራ ነበር፡፡ ፕረዘንቴሽን ሲባል ክፍል አልገባም፡፡ “አመመኝ” ብዬ ቤት እቀራለሁ፡፡ አባቴ ምኔን እንዳመመኝ ይጠይቀኛል፡፡ “ሐኪም ቤት እንሂድ?” ይለኛል። ጥያቄው ያናድደኛል፡፡ እልህ በደም ሥሬ ይመላለሳል፡፡ የፈተና ውጤቴን በመድፈን ላካክሰው እሞክራለሁ፡፡ ውርደት ይሰማኛል። የማጠናው ለበቀል ነው፡፡ ክፍል ውስጥ አልሳተፍም፡፡ የምቀመጠው መጨረሻና ጥግ ላይ ነበር፡፡
የክፍል ሥራዎችን ከማንም ተማሪ ቀድሜ ሠርቼ እጨርሳለሁ፡፡ ዴስኬን ለቅቄ አስተማሪው ያለበት ፊት ድረስ ሄጄ ማሳረም ግን ይከብደኛል። እየዞረ የሚከታተል ከሆነ ሲመጣ ጠብቄ አሳያለሁ፡፡ የውጤት ቀን የፈተና ወረቀቶቼን ስቀበል መምህራኖቼ አያምኑኝም። የኮረጅኩ ይመስላቸዋል፡፡ ትምህርት ቤት በሌሊት ተነሥቼ እሄዳለሁ፡፡ ጥቁር ሰሌዳው ላይ በቤት ሥራነት የተሰጡ ጥያቄዎችን በወዳደቁ ቁርጥራጭ ጠመኔዎች ተደብቄ መስራት ያስደስተኛል፡፡ እንደ መምህር እየተንጎራደድኩ የምቀመጥበትን ዴስክ ከተለያዩ አንግሎች ከርቀት አየዋለሁ፡፡ አንገቴን ደብተሬ ላይ ደፍቼ እዚያ ወንበር ላይ ነበርኩ፡፡ ማንም አላየኝም፡፡ እግዜርም ከላይ ሆኖ የማያየው ሰው ይኖር ይሆን እንዴ? አጠገቤ የሚቀመጠው ትልልቅ ቢጋሮች ያሉት መነፅር የሚያደርግ ቀጭን ረዥም ልጅ ነው፡፡ አፉ ይሸታል፡፡ ጥርሶቹ ቢጫና የተወለጋገዱ ናቸው። የተያየነው ከእርሱ ጋር ነው፡፡ የጥያቄዎችን መልስ ከእኔ ደብተር ይገለብጣል፡፡ የመነፅሩ መስታወት ላይ የራሴን ነፀብራቅ አዘውትሬ አይ ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ በመነፅር መስታወት ውስጥ ያለች ትንሽዬ ሪፍሌክሽን ብቻ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር፡፡
እናቴን በመራጭነቷ አምርሬ እረግማታለሁ። በአባቴ ተመራጭነት አዝንበታለሁ፡፡ በወንድሜ ውበት እቀናበታለሁ፡፡ ለምን ቆንጆ ሆነ? …የሚመርጠኝ አላገኘሁም፡፡ የተለየሁ ብሆን፤ ነገሮችን መቆጣጠር ብችል፤ ሰዎች ልብ ቢሉኝ እወድ ነበር፡፡ የሚያምር ገላ እንዲኖረኝ እየተመኘሁ ነው ያደግኩት፡፡ የለየልኝ አኮፈንች ወጣኝ፡፡ ኮፍያ ያለው ሹራብ ለባሽ ሆኜ ቀረሁ። ኢንተርኔት ከዚህ ዓለም ያመለጥኩበት መስኮት ነበር፡፡ የማያውቁኝ ሰዎች አዲስ ሰው የመሆንን ዕድል አይሰጡኝም። ሶሻል ሚዲያ ላይ ለመሆን የወሰንኩትን ነኝ። ስሜን፤ ፆታዬን፤ የተወለድኩበትን ቦታና ጊዜ፤ የተማርኩበትን ትምህርት ቤት … ቀይሬ አካውንት መክፈት እችላለሁ፡፡ ከማላውቃቸው ሰዎች ጋር የተሰማኝን ሜሴንጀር ላይ በቴክስት አወራለሁ። ማንም አይዳኘኝም፡፡ በትላንቴ አይሰፍረኝም። ከሰዎች ጋር ለመግባባት በሥጋ መገለጥ አይጠበቅብኝም፡፡ ጊዜው ሰዎች በዓይን ካላዩት ሰው በፍቅር የሚወድቁበት ነው፡፡ ከማያውቀኝ ከማላውቀው ሰው ጋር ረዥም ርቀት አወራለሁ። በአካል ቢርቁም በመንፈስ ቅርብ የሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ ቴክኖሎጂ ድንበር አልባ ዓለም ፈጥሯል፡፡ እዚህ ሆኜ እዚያ ነኝ። “ያ” በሁሉ ቦታ የመገኘትን አምላካዊ ስሜት ያላብሰኛል፡፡ በየቀኑ ወደ ሕይወቴ አዳዲስ ሰዎች ይገባሉ፡፡ ቅርብ ያሉት ይርቃሉ፡፡ ሩቅ ያሉት ይቀርባሉ፡፡ ስሌቱ ምንድር ነው?
ኢንተርኔት እየተጠቀምኩ ባይሆንም አላወራም፡፡ ሳሎን ሶፋ ላይ ተቀምጬ የቴሌቪዥን ቻናሎችን እቀያይራለሁ። የማየው አርት ፖለቲሳይዝድ እንደሆነ ነው፡፡ ሾው፤ ሙዚቃዉ፤ ድራማው፤ ኢንተርቪው፤ዶክመንተሪው … ፕሮፓጋንዳ ነው። ብሰላችም ወደ ደጅ አልወጣም፡፡ “እሽሽሽ” የሚል ወይም ስርጭት ያልጀመረ ቀስተ ደመናማ ቀለሞችን የሚያሳይ ጣቢያ ላይ አድርጌው እቀመጣለሁ፡፡ ሲደክመኝ ቴሌቪዥኑን አጥፍቼ የተዘጋ ክፍሌ ውስጥ በዝምታ አሳልፋለሁ፡፡ ነጭ ኖራ የተቀባ ኮርኒሴ ላይ ዓይኖቼን እተክላለሁ። ተጋድሜ ስመለከተው ለስላሳ ኖራ ነው፡፡ ርቀቱ ግምቴን እንድጠራጠረው ያደርገኛል። ተነሥቼ አልጋዬ ላይ ቆሜ እንጠራራለሁ፡፡ እጆቼ አይደርሱልኝም፡፡ ትራሴን አመቻችቼ እቆምበታለሁ፡፡ ጣቶቼ የኮርኒሱን ገላ ይረማመዱበታል፡፡ ኮርኒሱ ከሩቅ እንዳየሁት ለስላሳ አይደለም፡፡ ችፍርግርግ ደቃቃ ዐተር መሳይ ፍንጥርጣሪዎቹ ይሸክካሉ፡፡
አንዳንዴ ለእኛ ከቀረቡት ሰዎች ይልቅ የራቁን ሰዎች አሳምረው ያውቁናል፡፡ ከአንድ እናት ተወልደው በአንድ ጣሪያ ሥር ከአደጉ ወንድምና እህት በላይ አራምባና ቆቦ ያሉ ሰዎች ይሳሳባሉ፡፡ ልብ ለልብ ይግባባሉ፡፡ እንጀራ ጠቅልለን የምናጎርሰውን ሆድ አናውቅም። አንዳችን የአንዳችንን ልብስ ለብሰን ስንሳሳቅ የምንተዋወቅ እንመስላለን፡፡ እንደ ወንድምና እህት የወረስናቸው ዓይኖችና ጆሮዎች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ እርስ በእርስ ግን አንተያይም፡፡ አንሰማማም፡፡ ዓይኖቻችን የሩቅ ሰው ያያሉ። ጆሮዎቻችን ባይተዋሩን ያደምጣሉ፡፡ በስጋ እንጂ በመንፈስ አልተዛመድንም፡፡
(ከእሱባለው አበራ ንጉሤ “ትዝታሽን፤ ለእኔ ትዝታዬ፤ ለአንቺ” መጽሐፍ የተወሰደ፤ ሐምሌ 2012 ዓ.ም)

Read 2301 times